ዓይናችንና ለቀማ

14

 መቼም የነገር ሁሉ መጀመሪያ «በዛሬ ጊዜ…በአሁን ጊዜ…በዚህ ጊዜ» ሆኗል። በእውቀቱ ስዩም «…ቀኑ ደመናማ ነበር…» ብሎ ስለሚጀምር ድርሰት የጻፈው ወግ ቢጤ ትዝ ሲለኝ፤ በዛሬ ጊዜ እንደዛ ያለ የነገር መጀመሪያ እንዴት እንደናፈቀን ባወቀልን ያሰኘኛል። ዛሬ «ቀኑ ደመናማ ነበር» አልያም «ከዕለታት በአንዱ ቀን» ብሎ ነገር መጀመር ቀርቷል።

እና እኔም እላችኋለሁ፤ በዛሬ ጊዜ ርዕሰ ጉዳይ የማይሆን ነገር የለም። ለምሳሌ ጥቀሽ ብትሉኝ፤ የአንድ ሰው የቤት ኪራይ ዋጋ ለአንድ ሳምንት ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሲያያዝበት፣ ሲጣድበት፣ ሲራገብና ሲለኮስበት ይቆያል። ከዛ ይኸው ነገር መቋጫው ሳይታወቅ፤ ሌላው ይነሳና «…እገሌ ግን ለምን እንትናን አደንቀዋለሁ አለ? ከዚህ በፊትም ብሎ ነበር» በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሀሜታና ውይይት፤ ብሎም ስድድብ ይካሄዳል። አይሰለችም!?

ይሄ የምን ምልክት ነው? «የእድገት»፤ እመኑኝ አድገናል¡ አውሮፓውያን ስለዝነኞቻቸው የቁርስ ዓይነትና የምሳ ማወራረጃቸው ይዘት የሚያወሩት፤ ታዋቂ ሰዎች የለበሱትን ልብስና ያደረጉትን ጫማ መነጋገሪያ የሚያደርጉት ለምን ይመስለናል? ሥራ ፈትተው ነው። ዋና ዋናውን ሥራ ስለጨረሱና እድገት ደረጃ ላይ ስለደረሱ ምን ይሥሩ? በቃ! እኛም አድገን ጨርሰን ሥራ ስለፈታን፤ ሁሉም ጉዳይ ርዕስ ይሆናል።

ይህቺ ጠጋ ጠጋ! አትሉም? እና እኔስ ምን አለበት ስለ ለቀማ እና ስለ ዓይናችን ባነሳ? የምን ለቀማ? በእርግጥ ምስር ለቀማ ቀርቷል መሰለኝ። ነፍስ ካወቅሁ በኋላ፤ ስንዴና ምስር መልቀምም ሙያ መሆኑን እናቴ ስትነግረኝ ድንቅ ብሎኝ ነበር። አልሰሜን ግባ በለው! በዚህ ጊዜ ሁሉም አልቆለት ገበያ እየተገኘ ሙያ ቢስ ሊያሰኘን ሆነ፤ መልቀምም ሙያ ሆኖ?

ምን ትዝ ይለኛል? አንድ ከቤታችን የማትጠፋ ልጅ ነበረችና፤ እንደው አንዳች ድግስ ኖሮ እግር ጥሏት ከመጣች ሁሌም የምትደርሰው ለቀማ ላይ ነው። እድልኮ! «ጎሽ እንኳን መጣሽ! ይህቺን ምስር ለቀም አድርጊያት!» ይሏታል፤ ሰብሰብ የድግስ ቤቱን ሥራ ለማቃለል ተፍ ተፍ የሚሉ፤ ጎመን የሚከትፉና ወጥ የሚያማስሉ ደጋግ ጎረቤቶች። እርሷም አሻፈረኝ አትልም፤ ትለቅማለች።

ታድያ እናቴን ላለማስቀየም ነው መሰለኝ ጥርት አድርጋ ለመልቀም ስትል ገለባቸውን ጠርጋ ልታቆያቸው የምትችላቸውን የምስር ፍሬዎች ትጥላለች። «ልጄ! ይሄምኮ ያው ምስር ነው። አየሽው!?» ትልና አንዷ አጋዥ ጎረቤት፤ የምስሩ ልቃሚ ከወዳደቀበት መካከል አንዷን አንስታ፤ ፍሬዋን የጋረደውን ገለባ ልጣ ታሳያታለች። ቀጥላም «አይ! የምስሩን ቆሻሻ እንጂ መች ምስሩን ልቀሚ ተባልሽ…እውነትም ምስር ለቀማ!» ትላለች፤ ከንፈሯንና ዓይኗን ጠመም አድርጋ።

‘ዓይናችን ቆሻሻ ለማንሳትና ለመልቀም ከመፈለጉ የተነሳ፤ በእጃችን ካገኘነው ምስር መካከል ለቅመን የምንጥለውን አናውቅም ማለት ነው’ ስል አሰብኩ። ጠቢብት አይደለሁ? በእርግጥ የተፈጥሮም ደንቡ ሆኖ ጎልቶ የሚታየው ለየት ብሎ የወጣ ነገር ነው። ልክ ሁሌም በምሳሌነት እንደሚጠቀሰውና በልሙጥ ነጭ ሉክ ላይ እንዳለው ጥቁር ነጥብ ወይም ይዘት ማለት ነው።

የሰው ልጅ ድክመቱ ያ ይመስለኛል፤ ከብዙ መልካም ነገሮች ይልቅ ጥቂት ጉድለትን የሚያሳየው መመልከቻው፤ ከብዙ መልካም ዜናዎች ይልቅ ክፉውን የሚስበው ማዳመጫው። እሱን እንዳለ ትተን ደግሞ፤ ያልኳችሁ የምስር ለቀማ ነገር፤ ነገሩን ያብሰዋል። ከልሙጥ ነጭ ወረቀት ላይ ነጥብን ማየት አንድ ነገር ሆኖ፤ ከምስር መካከል ገለባ የሸፈናትን ምስር አውጥቶ መጣል ደግሞ ሌላ አንድ ነገር ነው።

ልብ በሉ! በዚህ ጊዜ ቆሻሻ እያልን እየናቅንና እየጣልን ያለነው ምስሩን ነው። ለምን? በለቀማችን ጊዜ በገለባ የተሸፈነችውን የምስር ፍሬ ገላልጦ ለማየት ጊዜ ስለሌለን። ከዛስ? ከዛ ደግሞ ለአንዲት ምስር ፍሬ ደንታም ስለማይሰጠንና ስናጎድላት ታጎድላለች ብለን ስለማናስብ። በመጨረሻ ግን ታጎድለናለች።

እንበልና፤ አንዲት የምስር ፍሬ ብቻዋን በምድረ በዳ ብትገኝ፤ ሰው ምን ይላል? «ውይ! ይህቺን የምስር ፍሬ እዚህ ማን ጣላት?» ይላል። ያቺ ምስር ፍሬ ከሌሎች መንጋዎቿ ብትነጠልም ምስርነቷ አይቀየርማ። ደግሞስ!ገለባውን ጠርጎ ምስሯን መጠቀም ሲቻል፤ ከቆሻሻ ቆጥሮ ምስሩን የጣለ፤ መልሶ ከቆሻሻ መካከል ምስር ለቀማ መግባቱ መች ይቀራል?

አሁን ተመልከቱ! እንዲህ ነገር ለማመሳጠር ስሞክር አልገርማችሁም?! ግልጹ ነገር ይህ ነው፤ ነገሩን የማኅበራዊና ፖለቲካ መልክ አስይዛችሁ ተመልከቱት። መቼም ዞረን ዞረን እዛው አይደለምን? እና ምን ለማለት ነው፤ በዚህ ጊዜ ዓይናችን የሚለቅመውን አላወቀም፤ ጆሯችንና አንደበታችንም እንደዛው።

አንድ ደህና የለበሰና መነጽር ያጠለቀ ግለሰብ የወደቀን ሰው ከመሬት ሲያነሳ ስናይ፤ «ምን አለበት መነጽሩን እንኳ ቢያወልቅ፤ ንቀት መሆኑ ነው?» የምንል ሆነናል። አለመተማመንና መጠራጠር ይሁን እንጃ! ግን ከምስር ውስጥ ምስር ለቅመን እየጣልን ነው። መልቀምም ሙያ ሆኖ!? ከንጹህ ስንዴ መካከል እንክርዳድ መለየት ሙያ ሆኖ፤ ስንዴውን ለቅሞ መጣል ምን የሚሉት ነው?

እንዲህ ያለው ለቃሚ ዕጣ ፈንታው ምንድን ነው? በዚህ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ የተሠራ አይመስለኝም። ከምስር መካከል ምስሩን የጣለ፣ ከስንዴው መካከል ስንዴውን ልቃሚ ያደረገ፤ በእጁ ላይ የሚተርፈው ቆሻሻው፣ እንክርዳዱ፣ ገለባው ወይም ልቃሚው ነው። እንዲህ ያለው ለቃሚ ጭራሽ ያለቤቱ ላግዝ ብሎ መጥቶ ሲሆን ደግሞ አስቡት! ለእንግዳ ምን ልታቀርቡ ነው?

እና ዓይናችን እና ለቀማ ላይ ያለን ነገር፤ እንደዛች ምስር ለቃሚ ሴት የላይ የላዩን ነው። ዓይናችን ምንም እንኳ ቀያይ ከመሰሉ የምስር ፍሬዎች መካከል ጥቁር የለበሰውን ለይቶና አጉልቶ ቢያሳየንም፤ ከውስጡ ፍሬውን እናገኝ እንደሆነ ማየት ነው። አሸት አሸት በማድረግ፣ በማብላላትና ደጋግሞ በማሰብ። ፍሬዋ እንቢኝ ብላ ከገለባው የሙጥኝ ካለች ግን፤ ያው ልቃሚ ናት ብሎ መወርወር ነው። ልቃሚ ለማንም አይጠቅምማ! ሰላም!

አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011

ሊድያ ተስፋዬ