የኢትዮጵያ ያልተማከለ ፊስካል ሥርዓት ገጽታ

17

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኢኮኖሚያቸውን በፍጥነት የማሳደግ ጉዞን በጀመሩ እና የፌዴራል ስርዓትን በሚከተሉ አገራት፣ እውን እንዲሆን የሚጠበቀው ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት እንዲረጋገጥ በአገራቱ የሚኖረው ሀብት የማመንጨት፣ በሀብቱ የመወሰንና ሀብቱን ወጪ የማድረግ ሂደቶች እጅጉን ወሳኝ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ አንድም፣ ኢኮኖሚዋ በፍጥነት አዳጊ በመሆኑ፤ አንድም የፌዴራል ሥርዓትን የምትከተል መሆኑ የፋይናንስ አስተዳደር ሂደቷ በልማቷ ብቻ ሳይሆን በህዝቦች መካከል ለሚኖረው እኩል የመልማት መብት መረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው፡፡

ይህ ደግሞ ገንዘብን ከማመንጨት ጀምሮ እስከመጠቀም ያለውን ሂደት የሚመለከት ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ያልተማከለ የፊስካል ሥርዓቱ (ፊስካል ፌዴራሊዝሙ) ለዚህ ያለው አመቺነት በተለይም በፌዴራልና በክልሎች ፋይናንስን ከማመንጨት እስከ መጠቀም ያለውን ሂደት ይወስናል፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ፊስካል ፌዴራሊዝም ከሕግ አኳያ ያለው ገጽታ ምን ይመስላል፤ በሚለው ዙሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግና አስተዳደር ትምህርቶች ኮሌጅ መምህር የሆኑት ዶክተር ሰሎሞን ንጉሴ፣  «የፊስካል ፌዴራሊዝም አተገባበር በኢትዮጵያ – ስኬቱና ክፍተቱ» በሚል ርዕስ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሳይነስ አካዳሚ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ያቀረቡት ጽሑፍ ላይ መሰረት በማድረግ ለንባብ በሚመች መልኩ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡

ያልተማከለ ፊስካል ሥርዓት በኢትዮጵያ

ያልተማከለ ፊስካል ስርዓት፣ በአንድ አገር የሚኖርን የወጪ ፍላጎት፤ ገቢ የመሰብሰብ ዓቅም፣ የገቢና ወጪ ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የፊስካል ሽግግር ስርዓትና ብድርን፣ ተቋማዊ አደረጃጀትን የሚመለከት ሲሆን፤ ባልተማከለ ስርዓት ውስጥ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ በመሆኑም ያልተማከለ ፊስካል ሥርዓት የፌዴራል ሥርዓትን ዓላማዎች ለማሳካት፣ በተለይም የመንግሥትን የመፈፀም አቅምና የአገልግሎት አቅርቦትን ለማሳደግ፤ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን፤ ከሀብት ክፍፍል ጋር የሚነሱ ግጭቶችን በአግባቡ ለመፍታት፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማረጋገጥም ያስችላል፡፡

ኢትዮጵያም ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ የመንግሥት ሥርዓት እንዲሁም ለዘመናት የዘለቀ የቀረጥና ግብር አስተዳደር ቢኖራትም፤ ያልተማከለ ፊስካል ሥርዓትን እውን ያደረገችው ግን ከ1983 ዓ.ም በኋላ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአብዛኛው ስልጣንን ወደ ታችኞቹ እርከኖች ማውረድ ጠቃሚ እንደሆነ ከሚነሱ ነጥቦች ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ በተለይም ወጪ የማድረግ ኃላፊነትንና ገቢ የመሰብሰብ ሥልጣንን ለፌዴራልና ክልሎች በማከፋፈል ኃላፊነትን ወደታች ማውረድን ይመለከታል፡፡

ገቢ የማመንጨት፣ የመወሰንና ወጪ የማድረግ ሥልጣን

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ባልተማከለ ፊስካል ሥርዓት የፌዴራሉና የክልል መንግሥታት የራሳቸው የሆነ ገቢ የማመንጨትና ገቢያቸውን የመወሰን አሠራር ሥልጣን አላቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል የታክስና የገቢ ምንጮች አመዳደብና አስተዳደር አንዱ ሲሆን፤ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥቱ የራስ የታክስና ገቢ ምንጭ እና የጋራ የታክስ ስልጣን አላቸው፡፡ በዚህም መሰረት በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 98 የፌዴራሉና የክልሎች የጋራ የታክስና የግብር ሥልጣንን በሚመለከት ተደንግጓል፡፡

በተመሳሳይ አንቀጽ 96 ስር የተዘረዘሩት የፌዴራል መንግሥቱ የገቢ ምንጮች ሲሆኑ፤ አንቀጽ 97 ስር የተዘረዘሩት የክልል መስተዳድሮች የገቢ ምንጮች በመሆናቸው በእነዚህ የገቢ ምንጮች ላይ የታክስ ህግ የማውጣት፣ የመጣልና የመሰብሰብ ስልጣን የክልሎች ነው፡፡ ሆኖም እስከአሁን የፌዴራሉን ህጎች መሠረት ባደረገ መልኩ የተደነገጉ ናቸው፡፡

የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና ታክስ ስርዓትም ሌላው ገቢ የማመንጨና የመወሰን ሥልጣን ድርሻቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ ከዚህ አኳያም በአንቀጽ 40/3፣6 በተቀመጠው መሰረት አስተዳደሩና አፈጻጸሙ አሁን ከተፈጥሮ ሀብት የሚገኝ ገቢ የሚከፋፈልበት ቀመር፤ እንዲሁም በአንቀጽ 100 መሰረት የታክስ ምንጮችና ክፍፍል ይወሰናል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 98 መሠረት ለፌዴራሉ መንግሥትና ለክልሎች በጋራ የተሰጠው የታክስ ሥልጣን አለ፡፡ ሆኖም ቀመሩ ከሃያ ዓመት በላይ በሥራ ላይ የቆየ፤ የጋራ ታክስና ግብር የመሰብሰብና የማከፋፈል ሥራ ግልጽነት የጎደለው፤ ከተፈጥሮ ሀብት ላይና ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ባለው ክፍተትም በቀጣይ በፖለቲካው ላይ ጫና ሊፈጥር የሚችል ነው፡፡

የክልሎች ገቢ የመሰብሰብ አቅም በተመለከተም የሚጠቀሱ ውሱንነቶች ያሉባቸው ቢሆንም፤ በሚሰበስቡትና በጥቅል ድጎማ በሚያገኙት ላይ የመወሰን ስልጣን አላቸው፡፡ ሆኖም የክልሎች በድጎማ ላይ ጥገኛ መሆን በራሱ በክልሎች የመወሰን ሥልጣን ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ በሁኔታ የተገደበ ድጎማ ግን የክልሎችን የመወሰን ሥልጣን የሚገድብበት ሁኔታ አለው፡፡

ወጪ ማድረግን በሚመለከትም በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ተለይተው የሚሰጡ ኃላፊነቶችን ለመደልደል የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ መርሆዎች አሉ፡፡ እነዚህ መርሆዎች ለድልድሉ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና አስተዳደራዊ የሆኑና አንድ ኃላፊነት በፌዴራል ወይም በክልል መንግሥት ስልጣን ስር በመሆኑ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም የሚተነትኑ ናቸው፡፡ በኢፌዴሪ ሕገመንግሥትም ወጪ የማድረግ ኃላፊነት በአንቀጽ 51 እና በአንቀጽ 52/2 መሰረት የሚከናወን ነው፡፡

አንቀጽ 51 ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ልማታዊ ጉዳዮች ላይ ፖሊሲና ስትራቴጂ ዕቅድ የማውጣትና የማስፈጸም ስልጣን አለው፡፡ በተመሳሳይ በአንቀጽ 52(2መ) መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን በሚመለከት የፌዴራሉ መንግሥት ህግ የማውጣት ሥልጣን ሲኖረው፤ ክልሎች ግን የማስተዳደር ስልጣን አላቸው፡፡ ከእነዚህ አንቀጾች መረዳት የሚቻለው ደግሞ በፌዴራል እና ክልሎች ያለውን ግንኙነት ወደ ማዕከል ያጋደለ እንዲሆን ማድረጉ ነው፡፡

ለምሳሌ፣ ከፍተኛ የእርሻ ኢንቨስትመንት ሂደትን ማየት ቢቻላል፤ የፌዴራሉ መንግሥት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ልማታዊ ጉዳዮች ላይ ፖሊሲና ስትራቴጂ የማውጣትና የማስፈጸም፤ ክልሎች ደግሞ እነዚህን ፖሊሲዎች የመፈጸም ስልጣን አላቸው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት የክልሎች ከ90 በመቶ በላይ በጀታቸው የሚውለው ለጠቅላላ አስተዳደርና ጸጥታ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትና የሙያ ስልጠና፣ ጤና፣ ግብርናና ገጠር ልማት፣ አካባቢ ጥበቃ፣ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት፣ የገጠር መንገድ ግንባታና ጥገና፣ የከተሞች እድገት፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ እድገት ዘርፎች ላይ ነው፡፡

የክልሎች የሀብትና ገቢ ክፍፍል

በፌዴራል መንግሥትና  በክልሎች መካከል ስለሚኖር ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሲነሳ አንድም፣ የፌዴራል ድጎማ (ጥቅል እና በሁኔታ ላይ የተገደበ)፤ አንድም፣ የጋራ ገቢ ክፍፍልን የሚመለከት ይሆናል፡፡ የፌዴራል በጀት ለመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት የሚያደርገው ወጪ አመዳደብንም መሰረት ያደርጋል፡፡ ከዚህ አኳያ የፌዴራሉ ድጎማ ጥቅል ድጎማ በቀመር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ እስከ 35 በመቶ ድረስ የፌዴራል መንግሥት በጀት በድጎማ ይከፋፈላል፡፡ ወደ ኋላ የቀሩ አካባቢዎችም ትኩረት አግኝተው በሥርዓቱ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

ይሁን እንጂ በፍትሐዊነቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም፣ የጋራ ገቢዎች አሠራር ድክመትና ግልጽነት አለመኖር፤ በሁኔታዎች የተገደበ ድጎማ አሠራር ግልጽ አለመሆኑና የሚሠራበት መርህ አለመኖር፤ የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ግንኙነት በመርህና በእኩልነት ላይ የተመራ አለመሆኑ እና የፖለቲካው አካሄድ በማዕከላዊነት መመራቱ ሂደቱን ተዓማኒነት እንዲጎለው ማድረጉ፤ የፌዴራል መንግሥት በኢኮኖሚው ባለው ሚና ራሱ ኢንቨስተርና ራሱ ተቆጣጣሪ መሆኑ ወገንተኝነቱ እና የቁጥጥር መላላት መፍጠሩ፤ የፌዴራል ወጪ አመዳደብ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች መኖር ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ሂደቶች የማረም ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የተዋረድም ሆነ የጎንዮሽ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች

ያልተማከለ ፊስካል ሥርዓት የሚጠበቀውን የኢኮኖሚ ውጤት እንዲያስመዘግብና በክልሎች መካከልም ተመጣጣኝ የገቢና ወጪ ስርጭት እንዲሰፍን ከማድረግ አኳያ በቀጣይ ሊከናወኑ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል፤ የፌዴራልና ክልሎች ግንኙነት በመርህና ተቋማዊ አሠራር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ አንዱ ሲሆን፤ ለዚህም ተቋማዊ አደረጃጀትን፣ አቅም ግንባታን፣ በጠቅላላው እና በተለይ የፊስካል ተቋማት ግንባታን ማጠናከር ይገባል፡፡ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ተአማኒነት እንዲኖረው ማድረግ፤ የጋራ ገቢዎች አሠራርን እንደገና መፈተሽ፤በሁኔታ ላይ የተመሠረተ ድጎማ አሠራርን በመርህ እንዲመራ ማድረግ፤ የታክስ መሠረትን ማስፋት፤ የመሬት አስተዳደር ጉዳይ ግልጽነት እንዲኖረው ማድረግም ተገቢ ነው፡፡

በተመሳሳይ ከኢንቨስትመንትና ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምም ሆነ ከታክስና ገቢ ምንጭት ጋር በተያያዘ መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች አሉ፡፡ ለአብነት ያክል፣ የድጎማ ቋት በህግ እንዲመራ ማድረግ፤ የድጎማ ቀመር ላይ የሚሠራው የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ገለልተኛና ነፃ በሆነ ኮሚሽን እንዲደገፍ ማድረግ፤ የአካባቢ አስተዳደሮች ከተፈጥሮ ሀብት ከሚሰበሰብ ገቢ ላይ ድርሻ የሚያገኙበትን ሥርዓት መዘርጋት፤ የፊስካል ፌዴራሊዝም ውጤታማነት ከዴሞክራሲና የፖለቲካ ብዝሃነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆን ማድረግም አስፈላጊ ነው፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 4/2011

በወንድወሰን ሽመልስ