በሱዳን በባህር ዳርቻማ አካባቢዎች የተጀመረው አመፅና ለውጡ

7

ሱዳን በታሪኳ ሁለት የተሳኩ ለውጦችን አድርጋለች፡፡ እአአ 1964 እና 1985 ላይ፤ አገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረውን ወታደራዊ መንግሥት ለመፈንቀል በተደረጉ ህዝባዊ አመፆች አንባገነኑን መንግሥት ጥለዋል፡፡ በሁለቱም ጊዜያት በተደረጉ አመፆች በዋና ከተማዋ ካርቱም ምሁራን የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ዓይነተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡  በአሁን ወቅት ደግሞ አገሪቱ በቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ሰዎች በአገሪቱ ለውጥ ለማምጣት እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ አድርገው ቆጥረውታል፡፡ የአሁኑ የለውጥ እንቅስቃሴ በዋና ከተማዋ ካርቱም ላይ መሰረት ያደረገ አይደለም፡፡ ይልቁንም እንቅስቃሴው ከባህር ዳርቻማ አካባቢዎች ጀምሮ በሁሉም ከተሞች እየተስፋፋ ይገኛል፡፡

የመጀመሪያው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የጀመረው በሰሜን ምሥራቅ ናይል ወንዝ አካባቢ በምትገኘው አትባራ ላይ ነው፡፡ እኤአ 2018 ታኅሣሥ 19 በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በዋጋ ጭማሪንና መሰረታዊ ሸቀጦች እጥረትን መሰረት በማድረግ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን ገለጹ፡፡ ወደ አደባባይ የወጡት ዜጎች ከዳቦና ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጥያቄ ወደ መንግሥት ይውረድ ተቃውሞ ተሻገሩ፡፡

በዚህም በአትባራ የሚገኘው የመንግሥት ሕንፃ ተቃጠለ፡፡ በሰሜን ምሥራቅ ናይል ወንዝ ዳርቻ የሚገኙት ባርባርና ኢል ዳመር ከተሞች በፍጥነት ወደ ተቃውሞው ተቀላቀሉ፡፡ በቀጣይ ቀናት ተቃውሞው እንደ ሰደድ እሳት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በመሻገር በምሥራቅ በምትገኘው ጋዳሪፍ ከተማ ደረሰ፡፡ በአገሪቱ የመጀመሪያ ያስባለ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ፡፡ እንደ ኢንዲፔንደት አክቲቪስት ቡድን ሙስታግሎን ገለጻ፤ ተቃውሞ በተጀመረበት ቀን ብቻ 22 ሰዎች በመንግሥት ታጠቂዎች ተገድለዋል፡፡

በደቡብ ብሉ ናይል አካባቢ የምትገኘው ራባክ ከተማ ታቃውሞውን በመቀላቀል በከተማው የሚገኘውን የገዥውን ፓርቲ ቢሮ አቃጥለዋል፡፡ በሰሜን አካባቢ በምትገኘው ኮርዶፋን ከተማ ኢል ኦቢድ ደግሞ ተቃውሞ በሚያሰሙ ሰዎችና በፀጥታ አስከባሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት ሆስፒታል ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በሆስፒታሉ  የሚሠሩ ዶክተሮች  በከተማዋ ላይ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ አድርገዋል በሚል የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለድብደባና ለእስር ተዳርገዋል፡፡

በምራብ ዳርፉር አካባቢ ኢል ፋሸር እና ኒያላ ተቃውሞው ከተስፋፋባቸው ቦታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በአገሪቱ የተነሳው ተቃውሞ በከተሞች ብቻ ሳይሆን በገጠራማ አካባቢዎችም ተዛምቷል፡፡ በካርቱም አቅራቢያ በምትገኘው ኢል ጀዚራ መንደር ተቃውሞውን ተቀላቅላለች፡፡ እኤአ 2019 ጥር ወር አጋማሽ በሱዳን ውስጥ ከሚገኙ 18 ክልሎች 15ቱ ተቃውሞ አስተናግደዋል፡፡

ካርቱም የተቃውሞው ሰልፍ የተካሄደባት ቢሆንም የመሪነት ቦታውን ግን አልያዘችም፡፡ ተቃውሞ ከመቀስቀሱ በፊት የሱዳን የሠራተኞች ማህበር ዝቅተኛ ደመወዝ ለሚከፈላቸው ሠራተኞች እንዲጨመር በመጪው በፈረንጆቹ መጋቢት ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን በከተሞች አካባቢ የተነሳው ድንገተኛ ተቃውሞ ማህበሩ መጋቢት ሊያካሂደው ያሰበውን ሰልፍ ሊያስቀረው እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የሱዳን ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል የጀመረው እኤአ 2011 ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ነበር፡፡ ደቡብ ሱዳን እራሷን ስትችል ሱዳን 80 በመቶ ገቢዋ ቀንሷል፡፡ ሱዳን እራሷን ምትችልበት ኢንዱስትሪዎች ማጣትና ሙስና መንሰራፋት ከቻይና እና ከባህረ ሰላጤ አገራት የሚሰጣት ብድር ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ አላስቻላትም፡፡ በዚህም እኤአ 2018 በአገሪቱ ያለው ኢኮኖሚ ደካማ ነበር፡፡ ሱዳን 50 ቢሊዮን ዶላር እዳ ያለባት ሲሆን፤ አበዳሪ አገራትም ተጨማሪ ብድር ከልክለዋታል፡፡ እኤአ 2019 የመጀመሪያው ወር ቤንዚንና ናፍጣ ሙሉ ለሙሉ ከገበያ ጠፍተዋል፡፡ ነዋሪውም ያስቀመጠውን ገንዘብ ከባንክም ሆነ ከኤ.ቲ.ኤም ማሽን ማግኘት አልቻለም፡፡ በተጨማሪም ዳቦ ከገበያ መጥፋት በአገሪቱ ተቃውሞ እንዲነሳ አድርጓል፡፡

በአገሪቱ ያለው የተቃውሞ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን፤ መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በካርቱም እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለውጥ አላመጣም፡፡ በካርቱም ነዳጅና ዱቄት ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት ሌሎች ክልሎችን እያስቆጣ ይገኛል፡፡ በምሥራቅ አካባቢ በምትገኘው ካሳላ የነዳጅ ሰልፉ በጣም ረጅም በመሆኑ ነዳጅ ለማግኘት ሦስት እና ከዚያ በላይ ቀናት ይፈጃል። ነዳጅ በካርቱም አቅራቢያ በምትገኘው መዳኒ ከተማ እጥረት ያለ ሲሆን፤ በጋዳሪፍ ግን ከነጭራሹ ነዳጅ የለም።

በሱዳን የተፈጠረው ሁኔታ የመጀመሪያ አመሆኑን ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ህዝቡም በተለያዩ ምክንያቶች እየተገፋ ወደ ተቃውሞ መግባት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን እየታየ ያለው ተቃውሞ በአስተዳደር ችግርና የመንግሥት ባለስልጣናት ትዕቢት የፈጠረ መሆኑን ነው የሚነገረው፡፡ በአገሪቱ የተከሰተው ተቃውሞ ከረጅም ጊዜ በኋላ በድንገት የተከሰተ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳኖች ሁለተኛ ዜጋ ተደርገናል ብለው ለ21 ዓመታት ታግለው ነፃነታቸውን ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ እኤአ 2003 ላይ ደግሞ የዳርፉር ነዋሪዎች በኢኮኖሚ ተጎድተናል፣ የፍትህ እጦትና ማግለል ደርሶብናል ብለው ተቃውሞ አንስተው ነበር። በብሉ ናይል እና በደቡብ ኮርዶፋን ከተማ ተቃውሞዎች እየቀጠሉ ሲሆን፤ ማዕከላዊ መንግሥቱ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የወሰደው ዕርምጃ ውጤት አላመጣም። ለአስርት ዓመታት ስልጣንና ሀብት ተይዞ የነበረው በአንድ ጎሳ ሲሆን፤ መቀመጫቸውን ዋና ከተማው ላይ በማድረጋቸው በካርቱም መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ደረጃ እንድትደርስ አድርጓታል፡፡

በካርቱም አቅራቢያና ራቅ ያሉ ከተሞች አካባቢ ተቃውሞች ቀደም ብለው በመቀስቀሳቸው መንግሥት ለመቆጣጠር እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ለሁኔታውም መንግሥት ትኩረት ባለመስጠቱ የጸጥታ አስከባሪዎች በካርቱም ስልጣን፣ ሀብትና የባለስልጣናትን ቤተሰብ በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱት ተቃውሞዎች የመንግሥት ባለስልጣናትን ያስደነገጠ በመሆኑ የፀጥታ አካላት ጥብቅ ቁጥጥርና ዕርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ በየአካባቢው የተነሳውን ተቃውሞ ለማብረድም ወታደሮች የተሰማሩ ሲሆን፤ በጠረፍ አካባቢ በሚገኙ ከተሞች ፈጣን ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዕርምጃ በዳርፉር ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ ጥቅም ላይ ውሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የሱዳን መንግሥት ውድቀት የገጠመው በተነሳው ተቃውሞ ብቻ አይደለም፤ ተቃውሞ እንዲቆም ለህዝቡ የሰጠው መግለጫም ውጤት አላመጣም፡፡ ከካርቱም ውጪ የሆኑ ከተሞች በማህበራዊ ሚድያ ድምፃቸውን በማሰማት ተቃውሟቸውን ቀጥለውበታል፡፡ በመጀመሪያው የተቃውሞ ሳምንት የአገሪቱና የየአካባቢው ባለስልጣናት ዕርምጃ ለመውሰድ የተንቀሳቀሱ ሲሆን፤ በዚህም ብዙ ተማሪዎችን የአማፂ ቡድን አባል ናችሁ ብለው አስረዋል፡፡

ይህ የእስር ሁኔታ ግን ተቃውሞ ከማስቆም ይልቅ የበለጠ ውጤታማ ተቃውሞ እንዲያካሂዱ ገፋፍቷል፡፡ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰዎች ‹‹ትዕቢተኞችና ዘረኞች›› የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡ መፈክሩን በአሁን ወቅት ከዳርፉር ተነስቶ ከጋዳሪፍ እስከ ካርቱም ከተሞች በተቃውሞ ወቅት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በዳርፉር ለ15 ዓመታት የዘለቀው ተቃውሞ ነዋሪው በስደተኞች መጠለያ እና በሰላም አስከባሪ እጅ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡

በአሁን ወቅት የተነሳው ተቃውሞ ግን አገር አቀፍ በመሆኑ ውጤት ያመጣል ተብሎ ተጠብቋል፡፡ ትክክለኛ የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣበት ሰዓት ይመስላል፡፡ አሁን ያለው የአንድ ጎሳ የፖለቲካ ስልጣን የበላይነት አክትሞ እኩል ፍትህ የሚመጣበት አዝማሚያዎች እየታዩ ነው፡፡ እየተደረጉ ያሉት ንቅናቄዎች በትክክለኛ መንገድ መመራት አለባቸው፡፡ ለውጥ ሲመጣ ስልጣን በምን ዓይነት መንገድ መከፋፈል እንደሚገባና የአገሪቱን ሀብት እኩል እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡  በተቃውሞ ወቅት ለተጎዱ ሰዎች  በተለይ በዳርፉር፣ በብሉ ናይልና በደቡብ ኮርዶፋን እንዲሁም በብሉ ናይል፣ ካሳላ፣ ጋዳሪፍ እና በሰሜን ከተሞች ከቦታቸው ለተፈናቀሉ ፍትህ አስፈላጊ ነው፡፡ በአገሪቱ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማሟላት የተሠሩ ግድቦች እኩል አገልግሎት እንዲሰጡ መደረግ ይኖርበታል፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 4/2011

በመርድ ክፍሉ