እቅጩን እንኑር!

6

ኢትዮጵያዊያን ስንባል ከሌላው ዓለም የተለየ ባህሪ አለን። ይህንን ስላችሁ በባህላችንና በምንኩራበት ግን ደግሞ መድገም ባልቻልነው ታሪካችን የተገኘ እንዳይመስላችሁ። ለነገሩ ዛሬ ላይ መቆማችንን ዘንግተን ያለፈውን በመተረክ ብቻ የምንኖር የተለየን ህዝቦች ሳንሆን አንቀርም (የ«ነበር» ህዝቦች ተብለን ብንጠራ ያስከፋን ይሆን?)

ይህ የተነጠለ ባህሪያችን ከተቀረው ዓለም እንዳንደርስ የቆመ ግንብ ይመስል መናድ አቅቶን ዘመናትን ኖረናል። አብዛኛው ነገራችን የተንተራሰውም እያደር በሚናዱ እውነቶች ላይ ነው። የሚናድ እውነት ታውቃላችሁ? ለመናድ የተለመደው መሬት ስለሆነ በዚህ ላስረዳችሁ። ስትመለከቱት የተለየ ያልነበረው መሬት መናድ የሚጀምረው ስትረግጡት ነው። ከናዳው የተረፈው መሬትም ደህና መስሏችሁ ስትቆሙበት ባህሪው ነውና እርሱም ደግሞ ይከዳችኋል።

እኛም እንዲህ ዓይነት ባህሪ ተጠናውቶናል፤ በቀላሉ መናበብም አቅቶናል (ትንሿን ፍሬ ለማግኘት ብዙ ልጣጭ እንደማንሳት ዓይነት)። ነገሬን በአጭርና ግልጽ መንገድ ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ላቅርብ። አንድ ዕቃ ለመግዛት ወደ ገበያ ወጥታችሁ ከፍለጋ በኋላ አገኛችሁት፤ ነጋዴውንም ዋጋውን ጠይቁት።

«100 ብቻ ነው» ይላችኋል እየተቅለሰለሰ፤ «ኧረ ተወደደ» በሉት፤ ከአፋችሁ ቀበል አድርጎ «እሺ በቃ 90 ውሰዱት» ይላል። «ኧረ አስተያየት አድርግበት» ስትሉት ደግሞ ስለመጣበት ሁኔታ፣ ዕቃው ከገበያ ላይ እየጠፋ ስለመሆኑ እንዲሁም ስለ ጥራቱ ጥቂት ካስረዳችሁ በኋላ፤ በ85 ብር እንድትገዙት ያስማማችኋል።

 ኮስተር ብላችሁ «የመጨረሻ መሸጫ ዋጋ» ከጠየቃችሁትማ አንገቱን ደፍቶ «የእኔ ትርፍ ይቅርና በ75 ውሰዱት» ይላችኋል። እመኑኝ አሁንም መወደዱን ነግራችሁ አማራጭ ፍለጋ ሌላ ቦታ እንደምትሄዱ ብትነግሩት፤ እግራችሁን ከማንሳታችሁ አስቀድሞ ከተማጽኖ ጋር በ50 እና ከዚያ ባነሰ ዋጋ ይሸጥላችኋል(ልፋ ቢለው እኮ ነው)

 ወገን እቅጩን ተናግሮ እንደመሸጥ ክርክሩ ጉንጭን ከማልፋት የተሻገረ ምን ጥቅም ይሰጣል? ለነገሩ ዝም ብሎ የሚገዛው ካገኘ በእጥፎች ከማትረፍ ወደኋላ ስለማይል ነው። ጥሩው ነገር ደግሞ ገዢውም ይህንኑ ስለሚያውቅ ሳይከራከር አይገዛም(ስንተዋወቅ አንተላለቅ ይመስላል ነገሩ)   

እናማ አብዛኛዎቻችን በትርኪ ምርኪ እንደተሞላ መጽሐፍ ፍሬ ነገሩን(ለእኛ ደግሞ ማንነታችንን) ለማግኘት ብዙ መገለጥ ያለብን ወደ መሆኑ አዘንብለናል። ይህ ባህሪያችንም ከአንዳችን ወደ ሌላችን እየተጋባ እንደ ህዝብ የምንጋራው በሽታ ሆኗል ብል ማጋነን አይሆንም (ህዝብ እንዴት በአንዴ ሊታመም ይችላል ግን?)

 ኑሯችንም እንደ ነጋዴው ከመጨረሻው መድረስ አቅቶታል፤ እያደር የሚናደው እውነትም ይህ ነው። ዛሬ ስለ አንድ ሰው ያወቅነው ነገ ተንዶ ደግሞ ሌላ እውነት ብቅ ይላል፤ በሌላኛው ቀን ደግሞ ሌላ እውነት መሳይ እውነት። በመንገድም ሆነ ከአንድ ስፍራ በትውልዱ ተማሮ የሚናገር ሰው ገጥሟችሁ ይሆን?

 የሌላውን ልጅ አኳዃን ሲወቅስና አሳዳጊውን ሲኮንን እኮ፤ አንዳች እንከን የሚገኝበት አይመስልም። ኧረ  የእርሱን ልጆች ስነ-ምግባር አዋቂነት እስክትመለከቱ ልትጓጉም ትችላላችሁ። ታዲያ አንድ አጋጣሚ ብታገኙ፤ እንዲያ ያደነቃችሁት ሰው በልጆቹ ሲንጓጠጥ እና ከፍና ዝቅ ሲደረግ ታዩት ይሆናል። 

 ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለትውልዱ መበላሸትና በመጤ ባህሎች መጠመድ የሚያወግዝም አለ። ታዲያ ለዚህ ምክንያት አድርጎ የሚያነሳው የመገናኛ ብዙሃን እና ትምህርት ቤቶች የሚሰጡት ትምህርት ግብረ ገብነት የጎደለው መሆኑን ነው። ነገር ግን እግር ጥሏችሁ ቤቱ ብትገኙ ከእነ ልጆቹ ለ24 ሰዓታት የውጭ ፊልም የሚመለከት ሆኖ ታገኙታላችሁ።

 እዚህ የሌላውን ልጅ እየኮነነ ስለ ስነ-ምግባር የሚሰብከው እዚያ የራሱን ልጅ እያበላሸ መሆኑ አይገርምም? የየትኛውም ነገር መነሻ ቤቱ ሆኖ ሳለ ሙገሳን ለራስ ወቀሳን ደግሞ ለሌሎች መተው ምን ይባላል? መጣመሙን ገና ከችግኙ በቁጥጥር ስር ያላዋለውን አናጺው እንዴት ስርዓት ሊያስይዘው ይቻለዋል?   

 ደግሞ አሉ በየመድረኩ የሃገር ባህል ልብስ ለብሶ፤ ስለ ባህል መበረዝ የሚያብራራ። ጥንተ ባህሉ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ጥረት ማድረጉን እየደሰኮረ፤ ቤቱን ከአውሮፓ በመጡ ዕቃዎች የሚያደረጅ (በልጆቹም «ማሚ እና ዳዲ» የሚባለው)። 

ስለ ሃገር ፍቅር የሚያስተምረውን ሰውም አርዓያ ይሆናል ብላችሁ ታሪኩን ብትጠይቁት በኩራት «አንዷ ልጄ አሜሪካ ነዋሪ ናት፣ ሌላኛው ልጄ ጣሊያን፣…» የሚል ዝርዝር ውስጥ ይገባል(ኩራት በሃገር መሆኑን እየተናገረ የሚኩራራው ግን አውሮፓ ባሉት ልጆቹ ነው)።

ስለ ስደት መጥፎነት የሚዘምረውስ ቢሆን፤ አስከፊነቱን የሚያሳየው ከተዋቡ ሕንፃዎች መካከል፣ ባማረ መንገድ ላይ ምቾት የሚጎላበት ሰውነቱን በዘመናዊ ልብሶች አንቆጥቁጦ አይደለም እንዴ? (በሌላ አነጋገር ተሰደዱ የሚሉ እኮ ነው የሚመስለው) ወገኑ የመሰደድ አስከፊነቱን ተመክቶ ሃሳቡን እንዲቀይር የማድረግ አቅም ያላቸው ዘፈኖችን ብቻም ሳይሆን ትዕይንቶችን ማሳየትም እኮ አስፈላጊ ነው።

 ስለ ዘረኝነት እና አሁን ስለሚታየው ሁኔታ ያሉትን አስታራቂ ሃሳቦች በየመገናኛ ብዙሃኑ ተገኝቶ ሲደሰኩር እና ትንታኔ ሲሰጥ ቆይቶ ፌስቡክ ላይ «እዚያ እንዲህ አደረጉ፤ እዚህም እንዲህ ተፈጠረ» እያለ ሚሊዮኖችን የሚያጭበረብር ምሁር ነኝ ባይም በዝቷል። እዚህ ጥሩ ሲናገር አድንቀነው እዚያ አድናቆታችንን በቅሬታ መሸፈን አዋቂነት ይሆን? (ዲግሪያቸውን በማጭበርበር የያዙ እኮ ነው የሚመስለው)።

ይህ ባህሪ በግለሰቦች ብቻም ሳይሆን በተቋማት ላይም እኮ ይንጸባረቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ በቅጡ ተደራሽ ያልሆነ እንዲያውም ከዓመታዊ ዕቅዱ ግማሹን እንኳን ለመፈጸም የሚያቅተው ተቋም በሁለትና ሦስት ዓመታት በምሥራቅ አፍሪካ እዚህ ደረጃ ለመድረስ አስቤ እየሠራሁ ነው ይላል(ምጸት እኮ ነው)። 

ወዳጆቼ ሆይ ምድሪቷ አንድ ናት፤ ሁለት እግር ቢኖረንም በአንዱ እዚህ በሌላኛው እዚያ መርገጥ አይሆንልንም። ስብዕናም እንዲሁ ነው፤ ሁለትና ከዚያ በላይ ሊሆን አይችልም፤ እንዲያ ሳይሆን ማስመሰልን ብቻ ሥራችን ካደረግን ግን እየኖርን አይደለም ማለት ነው። በየዕለቱ የሚለዋወጥና እንደ አዲስ የሚገለጥ ማንነት መያዝስ ለምን ይጠቅማል። እንደነጋዴው ቢሆንልኝ እጥፍ አተርፋለሁ ካልሆነም በተገኘው እሸጣለሁ ብሎ ዙሪያ ጥምጥምና አታካች ክርክር ከመግጠምስ፤ እቅጩን መኖር አያዋጣም ትላላችሁ?  

አዲስ ዘመን የካቲት 4/2011

በብርሃን ፈይሳ