ሕብረቱ ሰላምና ወንድማማችነትን በጋራ ተጠቃሚነት ማጽናት ይጠበቅበታል

10

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን በአንድ ቆሞ ነፃነት መጎናጸፍ ፋና ወጊ ሆና ሠርታለች፡፡ የአፍሪካን ድምፅም በዓለም መድረክ ስታሰማ፤ ለአፍሪካውያን ሰላምና ልማትም የድርሻዋን ስትወጣ ቆይታለች፡፡ አሁንም ይሄንኑ የፋና ወጊነት ተግባሯን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ ኢትዮጵያ ከውስጥ ወደ ውጭ በሚመለከተው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ተመርታ በርካታ ውጤት ማስመዝገብ የቻለች፤ በቀጣይም ይህንኑ ውጤት ለማስቀጠል አቅጣጫ ነድፋ እየሠራች ያለች አገር ናት፡፡ ከአንድነት ጥንካሬ እንደሚወጣ ሁሉ፤ ከጋራ ተጠቃሚነትም መተሳሰብ ይወለዳል፡፡ ይህ መተሳሰብ ደግሞ ወንድማማችነትን ይፈጥራል፤ በዚህ መልኩ የሚፈጠር ወንድማማችነት ደግሞ ፍቅርን የሚያነግሥ እንጂ ለጸብ ቦታ የሌለው ስለሚሆን ሰላም ተዘርታ ለፍሬ ትበቃለች፡፡

ኢትዮጵያም ይሄንኑ የአንድነት፣ የመተሳሰብና የመተሳሰር መስመር ይዛ፤ ህዝቦቿን በአንድ መስመር ለማሰለፍ ብቻ ሳይሆን፤ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጎልበት ተግታ እየሠራች ትገኛለች፡፡ በዚህም የቀጣናው አገራት የሰላም አየር እንዲተነፍሱ ከማስቻል አልፋ፤ ወንድማማችነታቸውን ለማጽናት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመርኩዛ ለፍሬ የበቃ ተግባር አከናውናለች፡፡

ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀው መቃቃር በሰላም ተተክቶና የህዝቦች ወንድማማችነት ወደ ጽኑ መሰረቱ ሲመለስ የታየበት ሀቅ አብይ ምሳሌ ሲሆን፤ ይህ የወንድማማችነትና የሰላም ጉዞው ያማረ መቋጫ እንዲኖረው ለማድረግም አገራቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የንግድና መሰረተ ልማት ትስስር ሥራዎችን ጀምረዋል፡፡ የጦርነትና ስደት ማዕከል ብቻ ሆና ትታይ የነበረው ምሥራቅ አፍሪካም ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ በመግባቷ ዛሬ ላይ የብዙዎችን ዓይንና ጆሮ መያዝ ችላለች፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና መለወጥ ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ ብቻ ሳይሆን ተኪ የሌለው ነበር፡፡ ይህ ተግባሯ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ አገር፤ መንግሥቷንም እንደ መንግሥት፤ ህዝቧንም እንደ ህዝብ የሚያስመሰግን ሲሆን፤ በቀጣይ በአፍሪካ እንዲመጣ ለሚፈለገው ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት እንደ ምሳሌ ሆኖ የሚታይ ሥራም ነው፡፡ እናም የአፍሪካ መሪዎችም በየአገራቸው ከሚያከናውኑት ተግባር፤ በየትብብር ቀጣናቸው ከሚወጡት ሚና ባለፈ፤ የበለጸገች፣ ሰላም የሰፈነባትና ለህዝቦቿ ምቹ የሆነች አፍሪካን በመፍጠር ሂደት ውስጥ የአፍሪካ ህብረት በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ላይ ቁርጠኛ ደጋፊና ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ምክንያቱም አፍሪካ ዛሬም የጥይት ድምፅ የሚሰማባት ብቻ ሳይሆን ሴቶችና ሕፃናት በጥይት አረር የሚሞቱባት፤ ሚሊዮኖችም በግጭትና ጦርነት የሚሰደዱባት ሰላምን አብዝታ የምትሻ አህጉር ናት፡፡ አፍሪካ ዛሬም፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶቿ ሥራ አጥተው ያሉባት ብቻ ሳትሆን፤ በልቶ ለማደር ሲሉ ባህር አቋርጠው የሚሰደዱባት፣ በሺ የሚቆጠሩትም በበረሃ አሸዋና በባህር ዓሣ ተውጠው የሚቀሩባት ምድር ናት፡፡ አፍሪካ ዛሬም ሚሊየኖች ከድህነት ወለል በታች ያሉባት፤ በረሃብና ድርቅ የሚጎሳቆሉባት፤ በርካቶችም ለምጽዋት እጆቻቸውን የሚዘረጉባት አህጉር ናት፡፡ እናም ይህች አህጉር ከመሪዎቿ ብዙ ትጠብቃለች፤ ከህብረቱም የችግር ካባዋን የሚገፍፍላት ሰፊ ሥራ ትሻለች፡፡

ከዚህ አንጻር ህብረቱ አጀንዳ 2063ትን ነድፎ ለተግባራዊነቱም እየሠራ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህ ተግባር ፍሬ እንዲያፈራም አፍሪካ እንደ አህጉር፣ አፍሪካውያንም እንደ ህዝብ አንድ ሆነው የሚሠሩበትን፣ አንድ ሆነው የሚለሙበትን፣ አንድ ሆነው ለመብታቸው የሚታገሉበትን፣ አንድ ሆነው ስለ አህጉራቸው አፍሪካ የሚዘምሩበትን ዕድል መፍጠር ይገባል፡፡ አፍሪካውያን ወጣቶች በአህጉራቸው ጉዳይ ተሳትፎ የሚያደርጉበት፤ ከልማቱም የሚጠቀሙበት ዕድል ሊፈጠርላቸው ያስፈልጋል፡፡ አፍሪካውያን ሴቶች የአፍሪካ ሁለንተናዊ መሰረት መሆናቸውም በተግባር መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

ለዚህ መሆን ደግሞ የአፍሪካ አገራትና መሪዎች አንድም በሁለትዮሽ ትብብራቸው፤ አንድም በቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስራቸው ላይ የትኩረት አጀንዳቸው ሊያደርጉት ያስፈልጋል፡፡ አፍሪካውያን ከሌሎች አህጉራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ፋይዳ ባለው መልኩ ማጠናከር ላይም ማተኮርም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሲሆን በትብብር ውስጥ የሚመጣ ጥቅምን በማስገኘት የአፍሪካውያንን መብት ለማስጠበቅ ይረዳል፤ አፍሪካውያንም አንድ ሆነው ለጋራ ሰላምና ልማታቸው የሚሠሩበትን ዕድልም ያመጣል፡፡

የሰላም፣ የደህንነትና የጸጥታ መደፍረስ የአፍሪካና አፍሪካውያን ስጋት የማይሆንበትን ዘመን እውን ለማድረግ፤ በልማትና ኢኮኖሚ የተሳሰረች አህጉር ለመፍጠር፤ የህዝቦችን ወንድማማችነት ለማጽናት እና የዜጎችን ሞትና ስደት ለመግታት የህብረቱ የቀጣይ አቅጣጫዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ ስለሆንም ህብረቱ ትናንት በጀመረውና ዛሬም ቀጥሎ በሚውለው 32ኛ ጉባኤው በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊመክርና አቅጣጫም ሊያስቀምጥ ይገባዋል፡፡ ዛሬን በድል ተሻግራ ነገን ለህዝቦቿ ምቹ አፍሪካን ለመፍጠርም ሰላምና ወንድማማችነትን እውን ማድረግ በሚያስችለው የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሥራት በሚቻልበት ሂደት ላይም አጽንዖት ሊሰጥ ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 4/2011