የቀደሙትን ስናከብር እኛም እንከብራለን!

11

ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው።

በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካና አፍሪካውያን በብዙ መልኩ ትገለጻለች፡፡ ቀደምት የስልጣኔ ባለቤት እንደመሆኗ የራሷ ፊደል ቀርጻ ታሪኳን የምትሰንድ፣ በራሷ ቁጥር ሂሳብ የምታሰላ፤በራሷ የቀን ቀመር ዘመኗን የምትቀይር፤ ወዘተ… አገር መሆኗ እና ነፃነቷን አስከብሮ በመቆየት የጀግንነት አኩሪ ታሪክ ባለቤትነቷ የዚህ ጥቂት ማሳያዋ ነው፡፡ አንድነት ኃይል ሲሆን፣ መበታተት ግን ኃይልን አዳክሞ ለችግር አጋልጦ እንደሚሰጥ አበክራ በመምከር አፍሪካውያን የጋራ ህብረት ፈጥረው ሁለንተናዊ ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ የአንበሳውን ድርሻ ወስዳ የሠራችም ናት፡፡

ይህ ሁሉ የአገር ታሪክ መገለጫ ይሁን እንጂ በታሪክ ሁነት ውስጥ መነሳት የሚገባቸው የአገር መሪዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያም «አንቱ» የተባሉ መሪዎችን በየዘመኗ አሳልፋለች፤ በእ ነርሱ እየተመራች አኩሪ ታሪክን ከትባለች፡፡ ይሁን እንጂ እኛው በእኛው ተነቃቅፈንና የውስጥ ገመናችንን ወደ ውጪ አውጥተን የራሳችንን ታሪክ ስናኮስስ፤ የራሳችንን መሪዎች ስናናንቅ ራሳችንን በአደባባይ አሳየን፡፡ ለራሳችን የነፈግነውን ክብር ሌላው አይሰጠንምና በነፃነቷ ብቻ ሳይሆን ገዢ ሃሳብ በማቅረብ ለመመስረቱ ትልቅ ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያ የህብረ ቱን መቀመጫ ከማግኘት ባለፈ አንድም የመሪዎቿን ሚና የሚያሳይ አሻራ ማስቀመጥ ሳትችል ቆይታለች፡፡

ለምሳሌ ያህል፣ የዓድዋ ድል ሲነሳ፣ ምኒልክ አብረው እንደሚታወሱ ሁሉ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ምስረታ ሲታወስ ቀድመው ከአዕምሮ የሚመ ጡት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ቢሆኑም፤ እኛው በነሳናቸው ክብር ምክንያት በህብረቱ አዳራሽ ግድግዳ እንደ ማንኛውም የአባል አገር መስራች መሪ ከተንጠለጠለች አንዲት ፎቶ ግራፍ የዘለለ መታሰቢያ ማግኘት አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ ስናከብር እንደምን ከበር፤ ስናዋርድ ግን እንደምንዋረድ ካለማወቅ፤ ይልቁንም እርሳቸው እንዲከብሩ በማድረጋችን ለእርሳቸው የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰው ነገር ያለመኖሩንና በእርሳቸው ክብር ውስጥ የአገ ርና ህዝብ ክብር መኖሩን ካለመረዳት ይመስለ ኛል፡፡

ንጉሡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት የተናገሩት ሃሳብ ምን ያክል ለአፍሪካ ልዕልና፣ ለአፍሪካውያንም አንድነት ይቆረቆሩ እንደነበር ያስረዳል፡፡  የምስረታውን ቀን «ይህ ቀን ለአፍሪካውያን በሙሉ ታላቅና ታሪካዊ ቀን ነው» ሲሉ ከመግለጽ አልፈው፤ የህብረቱ እውን መሆንን መናፈቃቸውን «ሕዝቦቻችን ከእኛ የሚጠብቁትን ተግባር ለመፈፀምና ክፍለ ዓለማችን በዓለም አቀፍ ጉባዔ የሚገባትን ትክክለኛ ስፍራ እንድትይዝ ለማድረግ ተሰብስበናል» በማለት ነበር በዕለቱ መላው ዓለም አተኩሮ እነርሱን እየተመለከተ መሆኑን ጭምር በመግለጽ ለመሪዎቹ ማሳሰቢያ አዘል ንግግር ያቀረቡት፡፡ «አፍሪካውያን እርስ በእርሳቸው በመጣላት የተከፋፈሉ ናቸው የሚሉ አካላት አሉ፤ እውነትም አንዳንድ አሉ፤ ቢሆንም ይህ መጥፎ አስተያየት ያላቸው ሁሉ የተሳሳተና ሃሳባቸው ሁሉ ከንቱ መሆኑን በሥራችን እናሳያቸው!» ሲሉም መሪዎቹ ወደ ቁርጥ ውሳኔ እንዲደርሱ ተማጽነዋል፡፡

ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ በወቅቱ አፍሪካ ከሞላ ጎደል ነፃ ብትሆንም፤ ከትናንትናዋ አፍሪካ ወደነገዋ አፍሪካ በመሸጋገር ላይ ያለችን አህጉር ዳግም ውልደቷን ማወጅ ነበር፡፡ ሕይወት ያለ ነፃነት ዋጋ እንደሌለው የሚያው ቁት እኝህ ብልህ ንጉሥም «ትግሉ ያለቀ መስሎን ሳናመነታ ወደፊት እንግፋበት! ትግላ ችንን ለማጠንከር ጊዜው አሁን ነው! …አንድነት ኃይል እንደሆነ መለያየት ደግሞ ደካማነት እንደሆነ እናውቃለን! …በመካከላችን ሊኖሩ የሚችሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች ወደጎን ትተን ሁላችንንም ለሚያስተባብረን ለአፍሪካ አንድነት መድከም አለብን! …እርስ በእርሳችን መነታረክ ትርፉ የሌላ ሲሳይ መሆን ነው! …አፍሪካ የበለጠ እንድትነቃ ማድረግ አለብን! …የእያንዳንዱ አፍሪካዊ ታማኝነት ለጎሳውና ለመንግሥቱ ሳይሆን ለአንድ አፍሪካ ሊሆን ይገባል!» የሚል ነበር ለተሰብሳቢው ያስተላ ለፉት መልዕክት፡፡

በጎሳ መለያየት የአህጉርን ብቻ ሳይሆን የአገርን አንድነት የሚያፈርስ መሆኑም በዚያን ወቅት ተረድተው ያስረዱም ሲሆን፤ «በእጃችን የጨበጥነው የፖለቲካ ነፃነት በኢኮኖሚና በሶሻል ዕድገት ካልተደገፈ ከፍ ያለ አደጋ ላይ ሊጥለን ይችላል» በሚለው ንግግራቸውም አፍሪካውያን ለነፃነት ብቻ ሳይሆን ይሄን አጽንቶ ለማቆየት የሚያስችል የኢኮኖሚ መሰረት ሊኖራቸው እንደሚገባም ነግረው ነበር፡፡

ከውቂያኖሱ ሃሳባቸው በባልዲ እንደመጭለፍ ተቀንጭቦ በቀረበው መልኩ ንጉሡ ለህብረቱ መመስረት የሃሳብ ትግል በማድረግ ካበረከቱት ሚና ባለፈ፤ የአፍሪካን ጉዳይ በዓለም መድረክ በማስተጋባትም ይታወቃሉ፡፡ በተለይ ነፃነት፣ የሰው ልጅ እኩልነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የኒኩሌር ጦር መሳሪያ ጉዳይ በትኩረት ከሚያነሷቸውና የዓለም መንግሥታትን ከሚሞግቱባቸው ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ንግግራቸው ደግሞ የዚህ አንድ ማሳያ ሲሆን፤ ንግግሩም ንጉሡ ኒውዮርክ ተገኝተው እአአ በ1963 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከተናገሩት የተወሰደ ነው፡፡

…ልንደክምበት የሚገባ ዓላማና ግብ ጸጥታችንና ሰላማዊ ኑሯችን በዚህ ታላቅ ድርጅት ሊጠበቅልን የሚችልበትን ሁኔታ ማስገኘት እና ለመላው ዓለም የሰው ልጅ ደህንነት ሲባል ለግልና ለብሔራዊ ጥቅም ብቻ መገዛትን ማስወገድ ነው፡፡ ይህን ግብ እስክንደርስበት ድረስ ፍጹም ሰላም የማያገኝና የሰው ልጅም የወደፊት ኑሮው አስጊ በሆነ ሁኔታ ላይ ያለ መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ የዓለም ጸጥታ አዋኪና ለሰላም ጉዳይም መሰናክል የሆኑትን ሁሉ ዓይነተኛ ችግሮች እዚህ ላይ ልንጠቅሳቸው እንፈቅዳለን፡፡ እነዚህም የጦር መሳሪያዎች ቅነሳና በሰዎች መካከል የእኩልነት መብት እንዲኖር ማድረግ ናቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜያችን ለዓለም ዋናው አስቸኳይና አስገዳጅ ጉዳይ የጦር መሳሪያዎች ቅነሳ ነው፡፡ የጦር መሳሪያዎችን መቀነስ ወይም የኒኩለር መሳሪያዎችን ሁሉ ማጥፋት ወዲያውኑ ሰላምን የሚመሰርትና በመንግሥታት መካከልም የሚኖረውን ማናቸውንም የሃሳብ ልዩነትና ክርክር ወዲውኑ የሚያስወግድ ይሆናል በማለት ሳይሆን፤ ዛሬ በሰው እጅ የሚገኘውን የጥፋት ኃይል የቱን ያህል እንደሆነ ሲገመት የጦር መሳሪያዎችን ከማጥፋት የበለጠ ለዓለም ሌላ አስቸኳይና አስገዳጅ ጉዳይ አለበት ለማለት አያስደፍርም፡፡ መሳሪያ ከድንጋይ ጊዜ ጀምሮ ለሰው ዘር መግቻ በመሆን ቆይቷል፡፡ አጣርቶም ለመሰብሰብና ለመጠበቂያ አስፈላጊውን ለማደራጀት ጊዜ ቢወስድም፤ መመስረቱ የሰው ልጅን ሕሊና ያሳውካል፡፡

የኒኩለር መሳሪያዎችን አየር ላይ መሞከሩ እንዲታገድ የተፈረመውን ውል ኢትዮጵያም የደገፈችው፤ የጦር መሳሪያዎችን ጨርሶ ለማስወገድ ወደሚያስችለው ግብ በከፊል እንኳን ቢሆን ያደርሳል በማለት ነው፡፡ ፍሬ ነገሩ፣ ከኒኩሌር ጦርነት ፍጹም ጥፋት ማንም ሊያመልጥ የማይችለው መሆኑን በመገንዘብ፤ ይህንን ለመፈረም በተስማሙት የኒኩሌር ባለቤቶች በሆኑት አገሮች መካከል አሁን ያለው ሁኔታ እየባሰ እንዳይሄድ ለማድረግ እና የተባበ ሩት መንግሥታት ድርጅትና እኛም አባሎቹ ለዓለማችን የሚበጀንን አንድ ነገር አስበን እንድናደርግ የትንፋሽ ማውጫ ጊዜ እንኳ ሊያስገኝልን ይችል ይሆናል በማለት ነው፡፡

የሰውን ልጅ የእኩልነት መብት ለማስ ገኘት የሚደረገው ትግል በታሪክ ገጾች ተጽፈው እንደሚገኙት፤ በተለይ በአፍሪካና በእስያ አህጉሮች ላይ ባለፉት ብዙ ዓመታት ደርሶ የነበረውን ግፍ ለማስወገድ ለሚደረገው ጥረት ነው፡፡

እአአ በግንቦት ወር 1963 በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎች ከፍ ያለ ጉባኤ አድርገው እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በሦስት ቀናት የስብሰባ ጊዜ ውስጥ የ32 መንግሥታት መሪዎች በፈጸሙት ተግባር፤ መልካም ፈቃድና ቆራጥነት ካለ ልዩ ልዩ ባህልና እምነት በአስተዳደር ያላቸው ህዝቦችም ሆኑ መንግሥታት የጋራ ጥቅም ከሚያስገኘው ግብ ለመድረስ እና ሁላችንም የምንመኘውን እኩልነትና ወንድማማችነት ለማስገኘት መቻሉን በጉልህ አሳይተዋል፡፡

እንዲሁም የዘር ልዩነትን በሚመለከት ረገድ አንዱ ዘር ከሌላው ዘር ይበልጣል፣ ይሻላል፣ የሚባለው እምነት ዋጋ እንዲያጣ ሆኖ ካልተወገደ፤ በአንድ አገር ውስጥ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ካልተሰረዘ፤ አንድ ሰው በቆዳው ቀለም ብቻ የመብቱ መጓደል ካልቀረ፤ ለሁሉም ሰው የዘር ልዩነት ሳይታሰብ እኩል የኢኮኖሚክና ተመሳሳይ ሰብዓዊ መብት ካልተሰጠው፤ እነዚህ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ሁሉ እስከተፈጸሙበት ቀን ድረስ ሁላችንም የምንደክምለትና የምንመኘው የዓለም በሕግና በደንብ መተዳደር ሊደረስበት የማይቻል እና እንደዚሁም በዓለም ላይ ሰላም ጸንቶ እንዲኖር የምናደርገው ሙከራ ሁሉ ባዶ ምኞትና ወና ሆኖ የሚቀር ግብ እንዳይሆን የሚያሰጋ መሆኑን አስተምሮናል፡፡

በደቡብ አፍሪካ፣ በአንጎላ፣ በሞዛምቢክ የሚገኙት ወንድሞቻችን ካሉበት የባርነት ቀንበር ነፃ እስኪወጡ ድረስ፤ መላው አፍሪካዊና እስያኖች በዓለም ሸንጎ በእኩልነት ደረጃ ድምፃቸው እስኪደመጥ ድረስ፤ የአፍሪካና የእስያ ክፍለ ዓለም ሙሉ ሰላም አላቸው ለማለት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ እኛ አፍሪካውያን ትግላችንን አናቋርጥም፡፡ በመጨረሻም መልካም መጥፎን ድል እንደሚነሳና እኛም እንደምናሸንፍ ጥርጥር የለውም፡፡ …

…በዛሬው ጊዜ ታላላቅ መንግሥታት እንኳን ዕድላቸውን የመወሰን ስልጣን በእነርሱ እጅ ብቻ እንዳልሆነ ማስታወስ ይገባቸዋል፡፡ ሰላም እንዲኖር የሁላችንም ተባብሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ የመጀመሪያውን እሳት የሚጭ ረው ማን እንደሆነ ይታወቃልን? የሁላችንም ዕድል አንድ ነው፡፡ ወይ መጥፋት፤ ወይ መዳን፡፡ ሁላችንም ጥፋትን አንፈልግም፡፡ ሁላ ችንም ከዝህች ዓለማችን ላይ ድንቁርናና ድህነት፤ ችጋርና በሽታ እንዲወገዱ እንፈል ጋለን፡፡ ሁላችንም የሰው ዘር የኒውክለር ጦርነት እንዳይደርስበት እንፈልጋለን፡፡

ዛሬ ዓለምን የገጠማት ችግር ከዛሬ በፊት ከደረሰባት ችግር እጅግ የከበደ ነው፡፡ የሰው ልጅ ካለበት ችግር ለመውጣት የታሪክን ገጽ ያገላብጣል፡፡ ግን መፍትሔውን አላገኘም፡፡ ይህ ነው ታላቁ ፈተና፡፡ ከጥፋት እንድንድን ከተፈለገ የእግዚአብሔርን ሕግ ተከትለን አብረን ተባብረን የተቻለንን ተሻሽለን መኖር አለብን፡፡ ለመኖር ከፈለግን በጊዜያችን ከገጠመን ከባድ ችግር ለመዳን ቁልፉን የት ነው የምናገኘው? ከሁሉ አስቀድሞ የሰውን ልጅ ከእንስሳ አስበልጦ የማሰብ ኃይል ወደሰጠው ፈጣሪያችን መዞርና መመልከት አለብን፡፡ በአምሳሉ የፈጠረው ሰው ራሱን እንዲያጠፋ እንደማይተወው ማመን አለብን፡፡ ከዚያም ወደራሳችን መመልከትና ራሳችንን መመርመር አለብን፡፡ ከአሁን ቀደም ያልነበረውን መሆን አለብን፡፡ ካሁን ቀደም ከነበረው ይልቅ ደፋር፣ ብርቱ፣ መንፈሰ ጠንካራ፣ ልበ ሰፊ፣ አርቆ አስተዋይ ሆኖ መገኘት አለብን፡፡ ጥቃትን፣ ጥቅምን የተወ ለአንድ መንግሥት ሳይሆን ታማኝነቱ ለመላው ለሰው ልጅ ያደረገ አዲስ ዘር መሆን አለብን፡፡…

እናም የእኚህ «የአፍሪካ አባት» ለአፍሪካና አፍሪካውያን ልሳን ሆነው የሠሩ መሪ፤ በመሰረቱት ቤት በዚህ ልክ ክብር ተነስቷቸው መቆየቱ የሚያሳዝን ተግባር ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ ታሪካቸው ሊታወስ፣ ስማቸ ውም ሊነሳ የሚችልበት መታሰቢያ ሀውልት ሊቆምላቸው መቻሉ ይበል የሚያስብል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሌሎችን እያከበርን እኛም እንድከብር የሚደርግ ነውና ለራሳችን ክብር መስጠት የመጀመራችን አንድ ውጤት እንደ መሆኑ አርአያነቱ ሊቀጥል ይገባል እላለሁ፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ! ሠላም!

አዲስ ዘመን የካቲት 4/2011

በወንድወሰን ሽመልስ