ኮሌጁ የመካንነትና የሥነ ተዋልዶ ህክምና ማዕከል አስመረቀ

5

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ትናንት ማዕከሉን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የማዕከሉ መቋቋም በዘርፉ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ከመቅረፍ አኳያ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በተለይ የማዕከሉ ዕውን መሆን ከዚህ ቀደም በዘርፉ በቂ ህክምና ባለመኖሩ ሲንገላቱ የነበሩትን የአገልግሎቱን ፈላጊዎች ችግር ለማቃለል ያግዛል፡፡ ከፍትሐዊነት አኳያም የሴቶችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡

 ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት፤ የመካንነትና የሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳይ ምንም እንኳን ሁለቱንም ፆታ የሚመለከት ቢሆንም፣ ችግሩ ይበልጥ ጎልቶ የሚስተዋለው ሴቶች ላይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የአገልግሎቱ መጀመር በጤና ሥርዓቱ ውስጥ ሴቶችን ፍትሐዊ ተጠቃሚ ለማድረግና ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው፤ በሃገሪቱ የሥነ ተዋልዶ ጤና ፖሊሲ የተቀመጠው የቤተሰብ ዕቅድ እንጅ የቤተሰብ ምጣኔ አለመሆኑን በመጠቆም፤ ፖሊሲውንም በተግባር መሬት ላይ አውርዶ በመጠቀም ረገድ ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ የቤተሰብ ዕቅድ ማለት ማንኛውም ቤተሰብ መውለድ በሚፈልግበት ጊዜ እንዲወልድና መውለድ በማይፈልግበት ጊዜ ደግሞ የፈለገውን እንዲያደርግ ምርጫ መስጠት መሆኑንም በመግለጽ፤ ከዚህ አኳያ የማዕከሉ ተመርቆ ወደሥራ መግባት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን አመላክተዋል፡፡

     መውለድ ከማይፍልጉትና መዘግየት ከሚፈልጉት የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች አኳያ መውለድ ፈልገው መውለድ ያልቻሉት ሲያገኙ የነበረው የህክምና አገልግሎት ጥቂት የሚባል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የህክምና ማዕከሉ በተለይ መውለድ እየፈለጉ መውለድ ላልቻሉ ቤተሰቦች ከፍተኛ ፋይዳ የሚኖረው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

«ዕድሜያቸው ለመውለድ ከደረሱ አጠቃላይ የሃገራችን ጥንዶች መካከል አስራ አምስት በመቶ የሚሆኑት መውለድ የማይችሉ ናቸው» ያሉት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ፕሮቮስት ዶክተር ወንድማገኝ ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ ይህን ችግር በመቅረፍ ረገድ የማዕከሉ መቋቋም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ይህን ያህል መውለድ የማይችል የህብረተሰብ ክፍል ይኖራል የሚል ግምት ባለመኖሩ ዘርፉ ትኩረት ሳይሰጠው ተዘንግቶ መቆየቱን በማውሳት፤ በአንድ አገር ውስጥ አንድ ሰው መውለድ ፈልጎ መውለድ አለመቻል ትልቅ ህመም እንደመሆኑም ማዕከሉ በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ  እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

በዚህ ረገድ ሃሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ የመካንነትና የሥነ ተዋልዶ ህክምና ማዕከሉን በማቋቋሙ ሂደት ለረጅም ጊዜ ሲደክሙ ለቆዩትና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱት የሥነ ተዋልዶ መብቶች ጠበቃ፣ ሃኪምና አሰልጣኝ ለሆኑት ፕሮፌሰር ሰናይት ፍስሃ ታላቅ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሰናይት በበኩላቸው፤ የመካንነትና የሥነ ተዋልዶ ህክምና ማዕከል የማቋቋም ሃሳብ እአአ ከ2012 አንስቶ የማህጸንና ፅንስ ሃኪሞችን በማሰልጠን የተጀመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከስምንት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ጥረት በኋላ ተመርቆ መከፈቱን በመጠቆምም፤ «በኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶችን ህይወት መቀየር ከፈለግን ማድረግ የሚገባን ለሴቶች የሥነ ተዋልዶ ነፃነት መስጠት ነው» ብለዋል፡፡ ማዕከሉም የችግሩ ዋነኛ ተጋላጭ የሆኑትን ሴቶች ማዕከል በማድረግ አጠቃላይ የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ትልቅ ጅምር መሆኑን አመላክተዋል፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 4

ይበል ካሳ