የኮንትሮባንድ ንግድን ያጋለጡ ተሸለሙ

11

አዲስ አበባ፤  የቶጎ ጫሌና ጅግጅጋ ጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፍ ሠራተኞች የኮንትሮባንድ ንግድን በመቆጣጠር ላበረከቱት አስተዋፅኦ የገቢዎች ሚኒስቴር የተለያዩ ሽልማቶችን አበረከተ። በክልሉ የእቃ መጫኛ መመልከቻ  (ካርጎ ስካኒንግ)  እና በሙከራ ደረጃ  የሚገኘው ከስተም ማኔጅመንት ተመረቀ፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቶጎ ጫሌ በተካሄደ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት፤  ሽልማቱ ሠራተኞች በሥራቸው ላስመዘገቡት ስኬት የተበረከተ ሲሆን፣ ለሀገርና ለወገን በጥቅማ ጥቅም ሳይንበረከክ ለሚሠራ ሁሉ ሽልማት ይገባዋል።

ህገ ወጥ ንግድን መከላከልና መቆጣጠር ሀገርና ሕዝብን ከውድቀት ማዳን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ በጥቅም ሳይታለሉ ህገ ወጥ ንግድን በሚገባ ለተፋለሙ በሁሉም የሥራ መደብ ለሚገኙ ሠራተኞች የማበረታቻ ሽልማት  እንደሚገባቸውም አስታው ቀዋል።

ሀገራችንን ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች  ለማውጣት  በጋራ እና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በኮንትሮባንድ የሚገቡ የጦር መሳሪያዎች፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችና መሰል ሸቀጦች ዜጎችን ለዘርፍ ብዙ ችግሮች እየዳረጉ እንዲሁም የሀገርና የህዝብን ራዕይ የሚያጨልሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ልንዋጋቸው ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

 የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የጉምሩክ ሠራተኞችና አጠቃላይ ህብረተሰቡ እንዲሁም  የፀጥታ አካላት ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሠሩት ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ከቴክኖሎጂውም በላይ በህዝባችን እንተማመናለን ያሉት  ወይዘሮ ኣዳነች፣ መልኩንና የማታለል ስልቱን በየወቅቱ እየቀያየረ ያለውን  ኮንትሮባንድ ለመከ ላከልና ለመቆጣጠር ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ  አቅማችን በፈቀደ መጠን ጥቅም ላይ እንዲውል እናደርጋለን  ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም በክልሉ የእቃ መጫኛ መመልከቻ  (ካርጎ ስካኒንግ)  እና በሙከራ ደረጃ  የሚገኘው ከስተም ማኔጅመንት ተመርቋል፡፡ የከስተም ማኔጅመንቱም ግዙፍ ዘመናዊ አሰራር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

አንድ ቦታ (ጣቢያ)  ላይ የሚከወን የታክስ፤ የጉምሩክና ሌሌች ተያያዥ ሥራዎችን በሁሉም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዘርፎች ( ዋናውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጨምሮ) የሚያሳውቅና የመረጃ ፍሰቱ ወጥ የሆነ ሐሰተኛ መረጃዎች በቀላሉ  እንዲጋለጡ የሚየስችል መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ህዝባችንም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ጥረት በመደገፍ ኮንትሮባንድና ኮንትሮባንዲስቶችን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሽልማቶችም ዘመናዊ ሳምሰንግ ሞባይል S9 (+) ቀፎዎች፣ ዘመናዊ ላፐ ቶፕ፣ አንድ ኤፍ.ኤስ.አር እና ፒክ አፕ መኪናዎች መሆናቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ድረ-ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011

በጋዜጣው ሪፖርተር