የግብር ጉዳይ- ማሳ ገልብጦ እስከ መዝራት

20

በሀገራችን የግብር ጉዳይ አነጋጋሪ እንደሆነ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡ በግብር አሰባሰብ ላይ ሀገሪቱ ሌላ ታምር ማድረግ አይደለም የሚጠበቅባት፤ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ግብር መሰብሰብ ብቻ ነው መሥራት ያለባት፡፡ ይሁንና በሀገሪቱ ከግብር እየተገኘ ያለው ገቢ ዝቅተኛነት ይህን ማድረግ እንዳልተቻለ ያመለክታል፡፡

ግብር መሰወር፣ ማጭበርበር፣ የአየር በአየር ንግድ፣ ኮንትሮባንድ፣ ከግብር ሰብሳቢ ሠራተኞች ጋር ተመሳጥሮ ዝቅተኛ ግብር ማስተመን፣ ኪራይ ሰብሳቢነት በአጠቃላይ የጨለማ ኢኮኖሚ ዛሬም እንዳለፉት ጊዜያት የግብር ሥርዓቱ ቁልፍ ተግዳሮቶች ሆነው ቀጥለዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች መፍታትን ታሳቢ በማድረግ መልኩ ብዙ ለመሥራት ተሞክሯል፡፡ የግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችን አሰራር ለመቀየር ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም፤ አዳዲስ አሰራሮች ተዘርግተዋል፤ አዋጅ ደንብ እና መመሪያ ተሻሽሏል፡፡ አዳዲስ ህጎች ወጥተዋል፡፡ የግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት ሠራተኛን ሙሉ ለሙሉ በሚያስኝ መልኩ ለዚያም በጥሩ ነጥብ በተመረቀ የተማረ የሰው ኃይል ለመቀየርም ብዙ ተለፍቷል ፡፡

ዘርፉ በርካታ የሰው ኃይል የሚፈልግ መሆኑ እንዳለ ሆኖ  በግብር ሰብሳቢ ሠራተኞች ላይ የሚስተዋለው የኪራይ ሰብሳቢነት በሽታ ወደ አዳዲሶቹ ሠራተኞች እንዳይተላለፍ በሚልም ይመስላል አዳዲስ ሠራተኞች እስከመቅጠር  የተደረሰው፡፡ ለነባሩም ሆነ ለአዳዲሶቹ ሠራተኞች የሚሰጠው ሥልጠናም የዚያኑ ያህል ሰፊ ነበር፡፡  ምን አለፋችሁ ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ ተገልብጦ የታረሰ እስከ ሚመስል ነው እነዚህ ሥራዎች ሲከናወኑ የቆዩት፡፡

በተለይ ኮንትሮባንድ አዘዋዋሪዎችን ልክ ያስገባል፤ አደብ ያስገዛል የተባለው ኮንትሮባንድን ሲያዘዋውር የተገኘ ተሽከርካሪ እንደሚወረስ አሽከርካሪውም አይቀጡ ቅጣት እንደሚጣልበት የሚደገነግገው ህግ የወጣ ጊዜ በዚህ ወንጀል ተጠርጥሮ የሚያዘውን እኔን አያድርገኝ ያላለ አልነበረም፡፡የኮንትሮባንድ ንግድ አበቃለት አሰኝቶም ነበር፡፡

ይህ ሁሉ ርብርብ ግን ይህ ሁሉ የግብር አሰባሰቡን ለማሻሻል እየተባለ የተከናወነ ተግባር በሀገሪቱ የግብር አሰባሰብ ላይ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን አላስቀረም፤ ሀገሪቱም ከግብር የምትጠብቀውን ያህል እንድታገኝ አላደረገም፡፡

ይልቁንም ሀገሪቱ የኮንትሮባንድ ማራገፊያ ሆናለች፤ የሀገሪቱ በሮች ኮንትሮባንድን ይጠየፋሉ ሲባል ቀይ ምንጣፍ ዘርግተው  እንዲቀበሉ ተደርገዋል፤ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች መርካቶ ውስጥ በጠራራ ፀሐይ ሲራገፉ ማየት ምንም የሚያም ሊሆን አልቻለም፤ በከተማዋ ጎዳናዎች እና አደባባዮች ለእግረኛና ለተሸከርካሪ መንቀሳቀሻ እስከሚቸግር ድረስ በኮንትሮባንድ የገቡ ሸቀጦች እየተቸበቸቡ ናቸው፡፡

 የሀገራችን ኮንትሮባንዲስቶች የኮንትሮባንድ ሸቀጦችን ወደ ሀገራችን በማስገባት ላይ ብቻ አልቆሙም፤ የግብርና ምርቶቻችንን ወደ ጎረቤት ሀገሮች በመላክ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ገቢም አሳጥተዋል፡፡የችግሩ እየሰፋ መምጣት በመንግሥት ድጎማ የገቡና የድሃው የእለት ጉርስ የሆኑ ምርቶችን ጭምር ሊምር አልቻለም። ሲሆን የታየው ግን ይህን ሀብት ከየት አመጣችሁ ተብለው የማይጠየቁ የፓርቲ የንግድ ድርጅቶችና ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ባለጸጋ ሲሆኑ ነው፡፡

በአዳዲስ አሰራሮች በሀገሪቱ ትንሽም ቢሆን የመጣው ለውጥ እኔ እስከ ሚገባኝ ድረስ ተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰብ መጀመሩ እንዲሁም የሽያጭ መሳሪያ ተግባራዊ መደረግ በጀመረበት ወቅት የታየ ነው፡፡እነዚህ አሰራሮች በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለውጥ ያመጡና እንደ አሰራር ችግር የሌለባቸው ቢሆኑም እየተገለጸ ያለው ግን ተግዳሮት በተግዳሮት መሆናቸው ነው፡፡

 እነዚህ አሰራሮች ተተግብረውና ህገወጦቹ እየተቀጡም ከህገወጥ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ያልቻሉበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ለመሰብሰብ በርካታ ነጋዴዎች ቢመዘገቡም ገንዘቡን እየሰበሰቡ በወቅቱ ገቢ የሚያደርጉት ጥቂት ናቸው ሲባል ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስበው የሚሸጡ እንዳሉ ሁሉ ይህን ታክስ የማይሰበስቡ መኖራቸውም ሌላው ችግር ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ተጨማሪ እሴት ታክስ የማይሰበስበው  በዝቅተኛ  ዋጋ የሚሸጥበትን ሰብሰቢው ደግሞ 15 በመቶ እየጨመረ የሚሸጥበት ሁኔታ በመፈጠሩ ህብረተሰቡ ዋጋ የሚቀንስለትን እንዲመርጥ አድርጎታል፡፡ ይህ በመሆኑም በነጋዴዎቹ መካከል የተፈጠረው ልዩነት ነጋዴው የተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብስብ ውስጥ ላለመግባት እንዲያንገራግር አድርጎታል። ይህም ጉዳይ የተጨማሪ እሴት ታክስ አሰራርን የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳይገኝበት አድርጓል፡፡

የሂሳብ መሰብሰቢያ ማሽኑም ቢሆን ተመሳሳይ ችግር ገጥሞታል፡፡ነጋዴዎች ማሽን አስቀምጠው ወይም ደረሰኝ እያላቸው ያለደረሰኝ የሚሸጡበት ሁኔታ በስፋት ታይቷል፡፡ በየንግድ ቤቱ ግድግዳ ላይ ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሂሳብ አይክፍሉ የሚል የይስሙላ ማሳሰቢያ ቢቀመጥም ትእዛዙ የግልብጥ ሆኖ ደረሰኝ ሳይቆረጥ የሚደረገው ሽያጭ የግብር አሰባሰቡን አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡

በዚህ ሁሉ የተነሳም በሀገሪቱ እየተሰበሰበ ያለው የግብር መጠን ከእቅዱ ጋር ሊቀራረብ አልቻለም፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት ሊሰበሰብ ከታቀደው ግብር የተሰበሰበው       ብሎ ያቀረበውም መረጃ ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡

በአጠቃላይ ሀገሪቱ አዳዲስ አስራሮች ብትተገብርም፣ አዋጆች ብታሻሻልም፣ የግብር ሠራተኛውን ያልተነካካ በሚል በአዲስ ብትቀይርም የመጣ ትርጉም ያለው ለውጥ የለም፡፡ ዛሬም እንደበፊቱ ምንአልባትም ከበፊቱም በላይ የግብር አሰባሰቡን መለወጥ በሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ የግብር አሰባሰቡ ይህን ያህል ርቀት መጥቶም እንደአዲስ ጥሬ ሆኖ ንቅናቄ ውስጥ እንድንገባ እያደረገን ነው፡፡

እስከ አሁን ሥራ ላይ እንዲውሉ የተደረጉት አዳዲስ አሰራሮች ሠርተው ቢሆን ኖሮ ዛሬም ስለተመሳሳይ ነገር ማውራት ባልነበረብን ነበር፡፡ ማውራት ካለብን የግብር መሰረቱን ስለሚያሰፉ እና አዳዲስ ተግባሮች ነበር፡፡ ይህ ግን ሊሆን አልቻለም፡፡ አሁንም እየተነጋገርን ያለነው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ግብር መሰብሰብ ስላለመቻላችን፣ ስለኮንትሮባንድ ንግድ መንሰራፋት፣ ስለዘርፉ ኪራይ ሰብሳቢነትና ዛሬም ከሰሀራ በታች ከሚገኙ ሀገሮች ዝቅተኛ ግብር የምንሰበስብ ስለመሆኑ ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ የግብር አሰባሰቡን ለማሻሻል  የተከናወኑ ተግባሮች በሀገሪቱ ግብር አሰባሰብ ላይ ለውጥ ካላመጡ ለውጡ በምን ላይ ነው የመጣው የሚል ጥያቄ እንዲሰነዘር ያደርጋሉ፡፡እርግጥ ነው አንዳንድ የፓርቲ ድርጅቶችና ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር ስውር ግንኙነት ያላቸው ነጋዴዎች በሚገርም የሀብት ማማ ላይ የተገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አሰራሩ የንግዱን ማህበረሰብ በመቆጣጠር አዳዲስ የንግድ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ አልተደረገም ማለትም አይቻልም፡፡ ሀብት በአስማት አይገኝም፤ እየሆነ ያለው ግን ሌላ ነው፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች በኮንትሮባንድ ንግድ፣ ያለቁጥጥር እንዳሻቸው ይሠሩ የነበሩ በመሆናቸው ዛሬ ቢጠሯቸው የማይሰሙ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

ታዲያ ይህ ሁሉ ችግር  የሀገሪቱን ገቢ እያመነመነ ቋቷን አስደንግጦታል፡፡ አሁንም ግብር መሰብሰብ ላይ እንድትዘምት አስገድደዋታል፡፡ አሁንም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ግብር መሰብሰብ እንዳልተቻለ እንዲሁም ሀገሪቱ ከሰሀራ በታች ግብር በመሰብሰብ ደካማ ከሚባሉ ሀገሮች ተርታ ናት እየተባለ ስለግብር መሰብሰብ ፋይዳ ግብር መክፈል ሀገራዊ ኃላፊነት ስለ መሆኑ ወደ ማስተማር ሥራ እንድትመለስ ተገዳለች፡፡

መንግሥትም  ሀገሪቱ በቀጣይ ማከናወን ለምትፈልጋቸው ሥራዎች አንዱ የፋይናንስ ምንጭ ከዜጎች የሚሰበሰበው ግብር መሆኑን በመጥቀስ በግብር አሰባሰብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቋል። ለዚህም እንዲረዳ የግብር ሰብሳቢውን መሥሪያ ቤት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ሰጥቶታል፡፡

ይህ የመንግሥት እርምጃ ትክክለኛ እርምጃ ነው፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴርም ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣት ሰፋፊ ሥራዎችን ማከናወን ውስጥ ገብቷል፡፡ በግንዛቤ ማስረጽ፣ በህግ ማስከበር፣ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ እያስታወቀ ነው፡፡ በቅርቡም ሰፊ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የግብር ሩጫ እና የጽዳት ዘመቻ እንደሚያካሂድ ይፋ አድርጓል፡፡

በእርግጥም የግብር ከፋዩን ህዝብ ግንዛቤ ማሳደግ ይኖርበታል፡፡ግብር መክፈል የሚጠበቅበት ህብረተሰብ በተንጣለለው አስፋልት መንገድ፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃው ፣ በመብራቱ ይገለገላል፤ ይሁንና እንዴት እና በምን እንደተሠራ አያውቅም፡፡ ወይም እያወቀም አላዋቂ ለመሆን ይፈልጋል፡፡  ሰላምና ደህንነቱ ተጠብቆ በሰላም ሲወጣና ሲገባ  ሀገሪቱ ከሰበሰበችው ግብር የተወሰነው ለዚህ ሰላምና ደህንነት ኢንቨስት የተደረገበት መሆኑን የሚያውቅ አይመስልም፤ ወይም እያወቀ ያልፋል፡፡ የማያውቀውንም እያወቀ ያደፈጠውንም ግንዛቤ ማሳደግ የግድ ይሆናል ፡፡

 መሰረተ ልማትን መጠየቅ፣ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያስፈልገውን ግብር ግን መደበቅ ካለ በእርግጥም ከግብር ከፋዩ ጋር በቅድሚያ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በህግ መሰረት ግብር እንዲከፍል ማድረግም ይጠበቃል፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡

ሀገራችን በርካታ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የሚገነቡባት ሀገር ናት፡፡ የውሃው፣ የትምህርቱ፣ የጤናው፣ የስኳሩ፣ የኃይል ማመንጫው፣ ወዘተ እየተገነባ ያለው በታምር በተገኘና በሚገኝ ሀብት አይደለም ከህዝብ በሚሰበሰብ ግብር አማካይነት እንጂ፡፡ ከሀገሮችና ከአበዳሪ ተቋማት በብድር የተገኘ ገንዘብ እንኳ ቢሆን ዞሮ ዞሮ ተከፋይ ነውና ግብር መሰብሰብን የግድ ያደርገዋል፡፡

በመንግሥት ውስጥ ስውር አጀንዳ ያላቸው አካላትን መለየትም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ችግር መደገም የለበትም፡፡ በስውር እጆች የሚነግድና በኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ የተዘፈቀ ወይም ባለሥልጣን ሲገኝ ቆርጦ መጣል ያስፈልጋል፡፡ ይህ መከናወን ያለበት ለውጥ የገፋው ወገን ሲለው በነበረ መልኩ አይደለም። ይህን አይነቱን ባለሥልጣን ወይም ቡድን ቆርጦ ስለመጣል ማውራት የሚያስፈልገው፡፡ የምር መሆን አለበት፡፡

የሚሠራው ለሀገር መሆን አለበት፡፡ ባለሥልጣናትና ሠራተኞች እጃቸው ካልጸዳ በተለይ የግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ከኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ካልጸዱ የቱንም ያህል ጥረት ቢደረግ የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ ያለፉት 27 ዓመታት ታሪካችን አስተምሮን አልፏል፡፡

በግብር መሰብሰብ ሥራ ላይ የተሰማራው አመራር እና ሠራተኛ  እዚያ የተቀመጡት ለሀገር ብልጽግና እንጂ የግል ኑሯቸውን ሊያደላድሉ አይደለም፡፡ ከፍተኛና ቁልፍ የኃላፊነት ቦታ ላይ ነውና ያሉት በእነዚህ ወገኖች ላይ አጥብቆ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ገቢ በአስማት የሚሰበሰብ አይደለም፡፡ በአስማት ከእጅ ውስጥ የሚወጣም አይደለም፡፡ ተሠርቶ ከሚገኝ ሀብት የሚከፈል ዜግነታዊ ግዴታ ነው፤ ለመሥራት ሰላምና ደህንነት ሊኖሩ ይገባል፤ የሚያሠራ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ወዘተ ያስፈልጋል፤ ከሙስና የጸዳ አመራር ሠራተኛ እና ግብር ከፋይም ያስፈልጋል፡፡

ከሁሉም የግብርን ፋይዳ ተረድቶ ግብር የሚከፍለው ለመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ለጤና ለትምህርት ለጸጥታና ደህንነት መጠበቅ ወዘተ ነው፤ ልማትን ለማሳለጥ ለሚያስችሉ ተግባሮች ነው ብሎ መሥራትን የሚያስብ ግብር ከፋይ ሊኖር ይገባል፡፡

ይህን እውን ለማድረግ አሁንም ማሳ ገልብጦ መዝራትን የሚጠይቅ ተግባር ማከናወን ይገባል፡፡ በግብር አሰባሰብ ወቅት ይታዩ የነበሩ ተግባሮች እንዲሁም እየተሰበሰበ ያለው የግብር መጠን የሚያስገነዝበውም ይህንኑ ነው፡፡ እነዚህን የሥራ ደንቃራዎች ነቅሶ ማስወገድ ይገባል፡፡ ለእዚህ ደግሞ ማሳ ገልብጦ እስከ መዝራት የሚደርስ የገቢ ግብርን የማሳደግ ተግባር ማከናወን ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011 በኃይሉ ሣህለድንግል