«አንዱ ልማቱ፣ ሌላው ደግሞ ጥፋቱ ብቻ እንዲነሳላቸው የሚፈልጉበት ሁኔታ አለ»- አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአጋር ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ

29

እንደ አገር በሁሉም መልኩ አዲስ ክስተትን እያመላከተ ያለ ለውጥ መጥቷል፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ በህዝብ ተጠንስሶ ለዚህ የደረሰ ብቻ ሳይሆን በቀጣይም የህዝብን ጠበቃነት የሚፈልግ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ሆኖም ህዝብ እንደ ህዝብ ከፊት ቀድሞ የሚመራው አካል ይፈልጋልና ኢህአዴግ ይሄን ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ታዲያ ለውጡን የሚመጥን ቁመና ከመያዝ አኳያ ኢህአዴግ እንዴት እየሰራ ይሆን? በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአጋር ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ ከሆኑት አቶ ፍቃዱ ተሰማ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር በመጣው ለውጥ ውስጥ የኢህአዴግ ሚና ምን ነበር ብለው ያምናሉ?

አቶ ፍቃዱ፡- ኢህአዴግ ሚና ከሁለት ነገር አንጻር ማየት ይቻላል፡፡ በዚህም ላለፉት 27 ዓመታት የሚታይና ማንም ሊክደው በማይችል መልኩ በተለይም በጤና፣ በትምህርት፣ ብሎም ግብርናውን ለማዘመን፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ለማድረግ፣ አጠቃላይ ሁለንተናዊ ለውጦች በአገር ደረጃ እንዲመጡ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል፡፡ አጠቃላይ እድገትም የተመዘገበበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ የተማረ ወጣት ማፍራት በመቻሉም እድገቱ ቁሳዊ እድገት ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ እድገትንም የያዘ ነበር፡፡ በዚህም የዓለም ሁኔታ የሚረዳና መብቱን የሚጠይቅ፣ የሚከራከር፣ የሚቃወምና የሚደግፍ ህብረተሰብ በስፋት የተፈጠረበት ነው፡፡ ከቁሳዊ እድገቱ ባለፈ ጠያቂና ለመብቱ የሚታገል ህብረተሰብ በአገር ደረጃ መፈጠሩ በራሱ አንድ ውጤት ነው፡፡

ሁለተኛ፣ ባለፉት ተከታታይ ሦስትና አራት ዓመታት በአገራችን ከጫፍ እስከጫፍ ሊባል በሚችል መልኩ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ በ2009 ዓ.ም የጥልቅ ተሃድሶ ገምግሞ የወሰደው እርምጃ ህዝቡን ሊያረካና ውጤት ሊያመጣ ባለመቻሉ፤ ይልቁንም ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዳረገ፣ ህዝቡም በኢህአዴግ ላይ እምነት እንዲያጣ ያደረገ ሆነ፡፡ እናም መሰረታዊ ለውጥ ከውስጥ መምጣት አለበት በሚል በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ላይ ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ ማድረጉ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይሄ እርምጃ ደግሞ አገሪቱን ከመበታተን አድኗል ብለን እናስባለን፡፡

ከእነዚህ ሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ኢህአዴግ ለውጡ እንዲቀሰቀስ በሁለት መንገድ ምክንያት ሆኗል፡፡ አንዱ፣ በ27 ዓመት በሰራቸው ስራዎች ተጨማሪ ነገር የሚፈልግ ጠያቂ ህብረተሰብ ከመፍጠር አኳያ ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ የተነሱ ጥያቄዎችን በወቅቱ ባለመመለሳቸው ምክንያት የተነሱ ህዝባዊ የለውጥ ጥያቄዎችን ተገንዝቦ በራሱ ውስጥ ለውጥ በማድረግ ለውጡን በመምራት ሚናው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢህአዴግ ለውጡን በሚገባ መርቶታል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ተከትሎ በመንግስት እየተከናወነ ካለው ለውጥ በተጓዳኝ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ከለውጡ ጋር ከመራመድ ረገድ ምን እየሰራ ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ኢህአዴግ የሪፎርሙ ባለቤት ነው ስንል፤ ሪፎርሙም ብቃት ያለው ወጣትና የአመራር ልዩ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች በማምጣት በተደረገው የአመራር ለውጥ ቀጥሏል፡፡ ከዚህ አኳያ በኢህአዴግ የተካሄደው የአመራር ለውጥ «ከእኔ በላይ ለአገር» በሚል እሳቤ «ከእኔ የተሻለ ሰው ይምጣ» በማለት  የቀድሞው የግንባሩ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁት፡፡ ይሄን ተከትሎም አዲስ የግንባሩን ሊቀመንበርና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ተመርጧል፡፡

ከዚህ ምርጫም በኋላ ከባድ ሪፎርም ነው የተካሄደው፡፡ ምናልባትም ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚና ምክር ቤት ከተቀመጠው አቅጣጫ በላይ የራሳቸውን ክህሎትና ጥበብ በመጨመር የመደመር ፍልስፍናን በማምጣት ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነቃነቀና እንደ ኢትዮ-ኤርትራ አይነት የማይደፈሩ አይነት ውሳኔዎችን ጭምር በመወሰን ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል፡፡ በውጭ አገር የነበሩ ወገኖችን የማሰባሰብ፣ በሁለቱ ትልልቅ ሃይማኖቶች መካከል የነበረውን ክፍፍል ለማርገብ በግላቸው የተጫወቱት ሚና ከአቅጣጫውም በላይ የነበራቸው ሚና ነው፡፡ በትልቅ የአገር ፍቅር ስሜት፣ ብቃትና ችሎታ፣የመፍጠር ክህሎት ታግዞ በዚህች በአጭር ጊዜ ይሆናሉ ተብሎ የማይታሰብ ከፍተኛ የሆነ ሪፎርም በአገራችን ታይቷል፡፡ በዚህ መልኩ የአመራር ክህሎቱ ያላቸውና ሪፎርሚስት የሆኑ አመራሮችን ማምጣት መቻሉ አንድ ከለውጡ ጋር የመራመዱ አመላካች ነው፡፡

ሁለተኛም፣ መጠኑ ሊለያይ ይችል ይሆናል እንጂ በየጉባኤዎቻችን በሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶቻችን ወጣቶችንና አዲስ ትኩስ ሃይልን፣ የተማሩና በህብረተሰቡ ዘንድም ተቀባይነት ያላቸውን፣ ለውጡን በተሻለ ደረጃ ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ወጣቶችን ወደ አመራር አምጥተናል፡፡ ለአብነት፣ ጅማ ላይ የተካሄደው የኦዴፓ ጉባኤ የተማሩ፣ ጠናካራና ለውጡን ተሸክመው ብዙ ርቀት ሊሄዱ የሚችሉ ከ95 በመቶ በላይ አዳዲስ አመራሮችን ነው ያመጣው፡፡ አዴፓም ሆነ ደኢህዴን እንዲሁም ህወሃት መጠኑ ይለያይ እንጂ በዚሁ ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ ሪፎርም የሚጀምረው ወረቀት ላይ ሳይሆን ጭንቅላት ላይ ነው፡፡ ያንን ጭንቅላት ለማሰባሰብም ነው ጥረት የተደረገው፡፡

ይሄ ደግሞ አዲስ ሃይል ይዞ ለመሄድ ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይም ኦዴፓና አዴፓ ከስምና አርማ ለውጥ ጀምሮ አባሉንም ሆነ ህብረተሰቡን በሚያቅፍ መልኩ እንዲሆን ለማድረግ  ሰፊ ስራ ሰርተዋል፡፡ እንደ ኢህአዴግም ከቢሮ ጀምሮ አደረጃጀቱን እያስተካከለ ሲሆን፤ ጊዜ ያለፈባቸውንና አሁን ላለው ለውጥ የማይመጥኑትን በመለወጥና ወደፊት ሊያስፈነጥሩ የሚችሉትን በማከል አደረጃጀቱን መልሰን እየፈተሽን ነው፡፡

በዚህ አደረጃጀት ደግሞ ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ እስከመምጣት ድረስም እየሰራን ነው፡፡ ለዚህም ሰፋፊ ጥናቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም አጋር ድርጅቶችም ጭምር በዚህ ውስጥ እንዲካተቱና ሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ፣ ሁሉንም አካባቢ የሚያቅፍ አገራዊ ፓርቲ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ጥናቱም ከሞላ ጎደል እየተጠናቀቀ ሲሆን፤ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ውሳኔ ለሚሰጠው አካል በማድረስ የሚኬድበት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ በዚህ ደረጃ የሪፎርሙ አካል ሆኖ ሪፎርሙን ለመምራት እንደተዘጋጀ ሃይል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ ቀደም ሲል ከሚታማባቸው ጉዳዮች አንዱ በእህት ድርጅቶቹ መካከል ያለ መጠራጠርና የስልጣን ሽኩቻ ይጠቀሳል፡፡ በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት ይሄ ችግር ተፈትቷል ቢባልም ለውጡን ተከትሎ ማገርሸቱን በተለይም በኦዴፓ፣ አዴፓና ሕወሃት መካለል ያለውን አሰላለፍ በማንሳት የሚናገሩ አካላት አሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ እርሶ ምን ይላሉ?

አቶ ፍቃዱ፡- ኢህአዴግ ውስጥ ክርክሮች ይካሄዳሉ፡፡ የሀሳብ ፍጭት ይደረጋል፡፡ ይሄ ክርክርና የሀሳብ ፍጭት ያን ያክል የፕሮግራምና ሕገ ደንብ ለወጥ፣ አጠቃላይ የመርህ ለውጥና አንድ ሆነው የማይቆይበት አይነት አይደለም፡፡ ክርክሮችና የሀሳብ ልዩነቶች መኖር ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ትግል ከሌለ ጠንካራ ነገር ሊወጣ አይችልም፡፡ ዋናው ነገር ግን በመጨረሻ ላይ በምን ተስማምተን ወጣን የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡

ለምሳሌ ሐዋሳ ላይ የተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጭምር የተሳተፉበት ብቻ ሳይሆን እንደ ድርጅት ሰፊ ክርክር የነበረው፤ ሊበታተኑ ነው የሚል ስጋት የተፈጠረበት ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ግን በአቅጣጫዎቹም ሆነ በመረጥነው ሊቀመንበር ላይ ምንም አይነት ልዩነት ያልነበረበት፤ መቶ በመቶ ተስማምተው የወጡበት ነበር፡፡ እናም እንደ ስራ አስፈጻሚም ይሁን እንደ ምክር ቤት በሚወሰኑ ውሳኔዎች የሃሳብ ፍጭቶች ይኖራሉ፡፡ መጨረሻው ግን ሁሉም በዚሁ አግባብ በጋራ ስምምነት ወስኖ ነው የሚወጣው፡፡ ስለዚህ ይሄ እንደመከፋፈል ተደርጎ ሊታይ አይገባውም፡፡

ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ ግን የለውጥ ባህሪ ስለሆነ ሁሉም በአንድ ጊዜ ይሰለፋል ማለት አይደለም፡፡ ይህ የለውጥ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው፡፡ ኢህአዴግም ከየትኛውም ፕላኔት የመጣ ስላልሆነና የሰዎች ስብስብ ስለሆነ እንዲህ አይነት ነገሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ለውጥ እንደስጋት የሚያዩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ደግሞ ያንን ሀሳብ እዚህ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ መከራከር አለ፤ የሀሳብ ልዩነቶች ይደረጋሉ፤ ግን ደግሞ መጨረሻው ለአንድነት የሚያሰጋ ነገር አይደለም፡፡

ነገር ግን መስተካከል ያለበት አተያይ አለ፡፡ ባለፈው 27 አመት ጉዟችን በልማት ጥሩ ስራ ሰርተናል፡፡ ይህ የኢህአዴግ የጋራ ስራ ውጤት ነው፡፡ ሆኖም ይሄን ብቻ በማጉላት የተሰሩ ስህተቶችን ደግሞ መደበቅ አንችልም፡፡ የተሰራውን ብቻ እንዲነሳ፣ ያጠፋነው ግን እንዳይነሳ የሚፈልግ ግለሰብና ቡድን ይኖራል፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ የተሰራው ስራ ተሰራ ተብሎ መቀመጥ አለበት፡፡ ሁለተኛም እኛ በምንመራት አገር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል፡፡ የተሰራው ስራ በሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ሊሸፍን፤ አንዱም አንዱን ሊበላ አይችልም፡፡ ስለዚህ ሁለቱም በሚዛናቸው ነው መቀመጥ ያለባቸው፡፡

በኢህአዴግ ፍላጎትና ኢህአዴግ አመራር ሰጥቶበት እንዲህ አድርግ ባይባልም፤ እንደ ድርጅት ተወስኖበት የተኬደበት ነገር ባይሆንም፤ በተቋማት የበላይ አመራሮችና በግለሰቦች የግል ብሎም የቡድን ጥቅምና ፍላጎትን ለማሳካት ሲባል የተሰሩ ግፎች አሉ፡፡ ይሄንን ኢህአዴግ በሊቀመንበሩ አማካኝነት ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ስለዚህ ይሄም እኩል መነሳት አለበት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የልማቱን ያህል የተጎዳ ህዝብና ዜጋ አለ፤ ኢትዮጵያዊ ነውና ሊያመን ይገባል፡፡ የተሰለፍነውም፣ የታገልነውም ለህዝቦች ነጻነትና ዴሞክራሲ ነውና ይሄንኑ ማስከበር አለብን፡፡

ከማያስማሙ ብዙ ነገሮች መካከል የተደራጀ ሌብነትና ዘረፋም አለ፡፡ ለዚህም ሃላፊነት መውሰድ አለብን፡፡ ልማት አለ ብለን እንደምናነሳው ሁሉ በተፈጸሙ በሰብዓዊ ጥሰቶች ላይም እኩል ማንሳት አለብን፡፡ በዚህ ላይ አንዱ ልማቱ ብቻ እንዲነሳ፤ ሌላው ደግሞ ጥፋቱ ብቻ እንዲነሳ የመፈለግ ነገሮች አሉ፡፡ ይሄ በልካቸው መታየት አለበት፡፡ ጥፋቱም፣ ልማቱም ለአንድ ድርጅት ወይም ለሆነ አካል የሚሰጥ ሳይሆን የጋራ ነው፡፡ በግለሰብ ረገድ የተወሰኑ ችግሮች ሊኖሩ ቢችሉም፤ በዚህ ደረጃ መታየት ግን አለበት፡፡ ምክንያቱም ለውጡ አንደኛ፣ ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ አድርጎ አገር ሳትበተን እንድትቀ ጥል ያስቻለበትና የሪፎርሙን አቅጣጫ ያስቀመጠ በመሆኑ፤ ሁለተኛ፣ ለውጡ ሕገ መንግስታዊና ሕጋዊ መሰረትን (ሊቀመንበር ሲመረጥ የግንባሩን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሾምም የፓርላማውን አሰራር) ተከትሎ የተከናወነ በመሆኑ፤ ሦስተኛም፣ ለውጡ በህዝቡ የተጠነሰሰ፣ አክቲቪስቱ፣ አትሌቱ፣ አርቲስቱ፣ ሚዲያው፣ በተለይም ወጣቱ ደረቱን የሰጠበት የህዝብ ለውጥ በመሆኑ ነው፡፡ እናም አሁን የሚነሱ ስጋቶችም በሂደት እየጠሩና እየተስተካከሉ ይሄዳሉ፡፡ አሁንም አንዳንድ ነገሮች እየተሻሻሉ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ማየቱም ተገቢ ነው፡፡ በቀጣይም በዚህ አግባብ እየታየ ችግሩን መፍታት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ የአራት ድርጅቶች ግንባር እንደመሆኑ አገራዊ ገጽታን ለመያዝ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ለመሆኑ በምን መልኩ አብሮ ሲሰራ ቆየ? ከለውጡ በኋላስ በምን መልኩ እየደገፋቸው ይገኛል? በቀጣይስ ከአጋርነት ወጥተው በኢህአዴግ ማዕቀፍ ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ያለው ስራ ከምን ደረሰ?

አቶ ፍቃዱ፡- ኢህአዴግና አጋሮቹ በመሰረታዊነት የአደረጃጀት፣ የፖለቲካ ፍልስፍናና የውግንና ልዩነት የላቸውም፡፡ እንደሚታወቀው ኢህአዴግ የአርሶአደር ፓርቲ ነው፡፡ ውግንናውም በአብዛኛው ለአርሶአደሩ ነው፡፡ የአርሶአደሩ ማህበራዊ መሰረት ባለበት ነው ኢህአዴግ የሚኖረው የሚል ነው የነበረው አስተሳሰብ፡፡ በእነዚህ ክልሎች ግን ለአርሶ አደር የሚመች ማህበራዊ መሰረት የለም፡፡ አብዛኛው አርብቶ አደር ነው፡፡ እንደ ሐረሪ ያሉት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ንግድ ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ስለዚህ ማህበራዊ መሰረቱ እስኪሟላ ወይም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር እስከሚደረግ ድረስ በአጋርነት ይቆያሉ፤ በአገራዊ ጉዳይ ግን አብረን ነው የምናየው፣ አብረን ነው የምንመካከረው የሚል ነበር፡፡

ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢህአዴግ አራቱን ክልሎች ብቻ ይዞ መምራት ስለማይችልና እነዚህ ድርጅቶችም አምስትና ስድስት የሚሆኑ ክልሎችን የሚመሩ እንደመሆናቸው፤ ድርጅቶቹ ነጻነታቸውን ጠብቀው ኢህአዴግም መደገፍ የሚገባውን እንዲደግፍ የሚያስችል በኢህአዴግና በአጋር ድርጅቶች መካከል የህብረት ስምምነት አለ፡፡ ምክንያቱም የሚወጡ የመንግስት ፖሊሲዎች በተቻለ መጠን ተፈጻሚ ሆነው ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ፤ ህዝቡም የዚህ ተጠቃሚ እንዲሆን እነዚህን አጋር ድርጅቶች መደገፍ፣ የአቅም ግንባታ ስራ በመስራት የማስፈጸምና የፖለቲካ አመራር ሰጪነት ሚናቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት ቀላል የማይባሉ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ ድጋፍም ተደርጓል፡፡ አሁንም በኢህአዴግ ምክር ቤትም ሆነ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ይሳተፋሉ፡፡ በተሳትፏቸውም ከውሳኔ ውጪ የሚቀር ምንም ነገር የለም፤ ሀሳብ የመስጠትና የመታገል ሙሉ መብት አላቸው፡፡

እነዚህ ድርጅቶች ለውጡን ተከትሎ በአብዛኛው ቦታ የአመራር ለውጥ አድርገዋል፡፡ ሆኖም የአመራር ለውጡ በሚደረግበት ጊዜ ለውጡን ለማሻገርና ቶሎ ወደ እኛ ክልል መጥቶ ተግባራዊ መሆን አለበት ብሎ በሚፈልጉ እና ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈልጉ ሃይሎች መካከል ትግል ነበረ፡፡ በመካከላቸውም በቡድን የመከፋፈል፤ በተለይ በጎሳና በብሔር የመከፋፈል እና ለስልጣን ሽኩቻ የመቧደን አይነት ነገሮች በከፍተኛ ሁኔታ ነበሩ፡፡ ከዚህ አኳያ ኢህአዴግ በታዛቢነትና በአጋርነት ከእኛ ጋር ሆኖ ግምገማችንን ማካሄድ አለብን የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው አብዛኞቹ እዚህ አዲስ አበባ እየመጡ አካሂደዋል፡፡

ይህ ደግሞ ችግሮቹ እየተባባሱ ከሄዱ የሰላም፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያስከትሉና ወደ ጥፋት የሚያመሩ በመሆናቸው የህብረተሰብ ቀውስ ስለሚያስከትሉ በጊዜ መፍትሄ ማግኘት ይገባቸዋል በሚል የተካሄደ ነው፡፡ ኢህአዴግም በዚህ ላይ በመመስረት ውይይትና ግምገማቸውን የመደገፍ፣ በነጻነት እንዲገማገሙና ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዙ የማድረግ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በግምገማቸው በመስማማት፣ የአመራር ለውጥ በማድረግ ሪፎርም እያካሄዱ ነው፡፡

አሁንም ድጋፉ ለሁሉም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በቀጣይም ሰፋፊ የአመራርና ካድሬ ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችል ካሪኩለም እየተዘጋጀ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ አግባብ በጥብቅ ቁርኝት ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሰራን እንገኛለን፡፡ ለውጡን የጀመሩትና ሪፎርም ያካሄዱበት ስለሆነ ጥሩ ውጤት የታየበት ነው፡፡

ድርጅቶቹን ከአጋርነት ወደ አባልነት እንዲመጡ ከማድረግ አኳያም በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ለዚህ ደግሞ አንደኛ፣ ኢህአዴግ ራሱ ከግንባር ወደ ወጥ ፓርቲነት ለመሄድ የሚያስችለው ጥናት አልቆ መወሰን በሚችለው አካል ቀርቦ እንዲወሰን የማድረግ ስራ ይከናወናል፡፡ አጋር ድርጅቶቹንም እንዴት ወደ ኢህአዴግ ማምጣት ይቻላል የሚለው ጥናት ወደመጠናቀቁ ስለሆነ፤ ልክ ጥናቱ እንደተጠናቀቀ መጀመሪያ ኢህአዴግን ማዋሀድ፤ ከዚያ በኋላ አጋር ድርጅቶቹን የማዋሀድ ሁኔታ ይኖራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከፊት ለፊት ምርጫ እንደመኖሩ አሁን ካለው የለውጥና የህዝብ ፍላጎት አንጻር ኢህአዴግ እህትና አጋር ከሚል ጉዞ ወጥቶ ጠንካራ ተወዳዳሪ ከመሆን፤ ተፎካካሪዎችም ለዚህ የሚሆን ብርቱ ፉክክር እንዲያደርጉ ከማስቻል እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከማድረግ  አኳያ ኢህአዴግ እንደ መሪ ድርጅት ምን እየሰራ ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- የኢህአዴግ የፓርቲነት ጉዳይ ምርጫን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን ጥናቱ ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ የቆየ፤ በምክር ቤትም ሆነ በጉባኤ አቅጣጫ የተሰጠበት ነው፡፡ እናም ጥናቱ ሲጠቃለልና የሚመለከታቸው ካዩት በኋላ ወደሚወስነው አካል ሄዶ የሚተገበር ይሆናል፡፡ ይህ ጉዞ አጠቃላይ አገራዊ ለውጡን ለመምራት የሚያስችል ሁኔታን በውስጡ የያዘ፤ ጥንካሬን ሊያመጣለት የሚችል፤ የነገውን ኢህአዴግ በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም የሚደረግ ተግባርና እንቅስቃሴ ነው፡፡

ምርጫን በሚመለከት ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መጥተዋል፤ ኢህአዴግን ለመሞገትና ለመከራከር የተጀመሩ ስራዎች አሉ፡፡ ተቋማት እየተገነቡ ነው፤ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ሌሎችም ነጻ ሆነው ህዝቡ የሚያምንበት ምርጫ እንዲካሄድ እየተሰራ ነው፡፡ ኢህአዴግም እንደ ዋና ግብ አድርጎ የሚያየው ማን ተመረጠ ሳይሆን፤ በዚህች አገር ዴሞክራሲያዊ፣ እውነተኛና ትክክለኛ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ ሊቀበለው የሚችለው ምርጫ ተካሂዷል ወይስ አልተካሄደም የሚለውን ነው፡፡ ይሄ ከተሳካ ኢህአዴግ አሸንፏል ማለት ነው፡፡

ሌላው የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር፣ ተቋሞቹ ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ለማድረግ፤ የተጀማመሩ ነገሮች አሉ፡፡ ፍርድ ቤቶችና የደህንነት አካላት ነጻ የሚሆኑበት፤ የምርጫ ቦርድም ገለልተኛነት እንዲረጋገጥ እየተሰራ ነው፡፡ ይሄው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በኢህአዴግ በኩልም ለምርጫ በሚዘጋጅበት ጊዜ ሪፎርም በማምጣት የሪፎርሙ ዋነኛ ማዕከል በአገር ደረጃ ዴሞክራሲ፣ የሀሳብ ነጻነትና ማንም የማይሸማቀቅበት ብሎም ተቋማቱ ዋስትና የሚሰጡበት ሁኔታን የመፍጠር ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በምርጫ ሂደት ርዕዮተ ዓለም ወሳኙ ጉዳይ ቢሆንም፤ ለውጡን ተከትሎ በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች መካከል የጠራ የርዕዮተ ዓለም ምልከታ የለም ይባላል፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ?

አቶ ፍቃዱ፡- ሲጀመር ከርዕዮተ ዓለም አንጻር አሁን ያለው ርዕዮት የካፒታሊስት ርዕዮት ነው፡፡ ኢህአዴግም ይሄንኑ የነጻ ገበያ ርዕዮት ነው የሚቀበለው፡፡ ኢትዮጵያም የዳበረ የነጻ ኢኮኖሚ ሥርዓት የምትገነባ አገር ናት፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የሚባል ርዕዮተ ዓለም የለም፡፡ ይሄ ፕሮግራም ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም የዳበረ የነጻ ገበያ ሁኔታ ስላልተፈጠረ ይሄን ዕውን ለማድረግና ሽግግሩን ለማሳለጥ የምናራምደው ፕሮግራም፤ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡  በዚህ ዙሪያ ብዥታ ያለው ብሔራዊ ድርጅት አለ ብዬ አላስብም፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታም መሆን የሚችለው ይሄው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ ኢህአዴግ ለውጥ ፈላጊውን ህዝብና በለውጥ ላይ ያለችን አገር ወደላቀ የለውጥ መስመር ለማስገባት በምን መልኩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል? በዚህ ሂደትስ የባለድርሻዎች ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?

አቶ ፍቃዱ፡- ኢህአዴግ በጉባኤው ግልጽ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ እስከሚቀጥሉት የጉባኤ ጊዜያትም እነዚህ አቅጣጫዎች ናቸው እየተሸራረፉ ተግባራዊ የሚሆኑት፡፡ ከእነዚህ አቅጣጫዎች አንዱ ለውጡን ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ማድረስና ተቋማዊ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ዴሞክራሲን ማስፋት ሲሆን፤ ዴሞክራሲ ደግሞ ስለፈለግን ብቻ ስለማይመጣ በዚህ ላይ የማንደራደርበት ቁርጠኛ አቋም ይዘናል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የዴሞክራሲ ተቋማት ሊገነቡ ይገባል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚደራደሩበት አሰራርና የቃልኪዳን ሰነድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ምክንያቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከማስተማርና የህብረተሰቡን አስተሳሰብ ከመቅረጽ አኳያ ትልቅ ሚና ስላላቸው፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከንትርክ፣ ከቂም በቀልና ጥላቻ ወጥቶ የኢትዮጵያን ህዝብ ስሜትና ፍላጎት የሚያንጸባርቅና የሚወክል ማድረግ ይገባል፡፡ እንዴት የበሰለ የፖለቲካ አስተሳሰብን እናምጣ የሚለውም መታየት ያለበት፡፡ በዚህ ዙሪያ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ሚዲያውም ሚዛናዊነት የጋዜጠኝነት ሙያውና ነጻ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እንዲሁም ህዝባዊ ውግንና ኖራቸው የህብረተሰብ አስተሳሰብን መቅረጽ አለባቸው፡፡ ተቃዋሚውንም ሆነ ኢህአዴግን በማንኳሰስ ወይም በማሞካሸት ላይ መጠመድ የላቸውም፡፡ ሀሳብ ላይ መስራት አለባቸው፡፡ ዴሞካራሲን የሚያቀጭጩ፣ ጥላቻን የሚነዙ፣ ቂምና በቀልን የሚያሰርጹ፣ በብሔሮች መካከል ግጭትን የሚፈጥሩ ሳይሆኑ፤ የሃሳብ ፍጭት ተደርጎባቸው የተሻለ አገር የሚገነባበትንና ዴሞክራሲያችን የሚበስልበትን ሁኔታ መፍጠር አለባቸው፡፡

የዴሞክራሲ ተቋማትም ነጻና ገለልተኛ መሆን አለባቸው፡፡ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ መከላከያና ደህነነት ተቋማት ለአንድ ወገን ወይም ቡድን የሚሰሩ ሳይሆን ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ አገርን ማዕከል አድርገው መሆን ይገባዋል፡፡ ምርጫ ቦርድና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የመሳሰሉ ተቋማትም በተመሳሳይ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሲቪክ ማህበራትም ብዙ ድምጾችን የሚይዙ እንደመሆናቸው የተሻሻለውን አዋጅ መሰረት በማድረግ በሚገባቸው ልክ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡

ሌላው የልማት ስራ ነው፡፡ ግብርናው ሊዘምን፤ ልማታችን መፋጠን አለበት፡፡ ሆኖም ልማት ያለዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲም ያለሰላም አይሆንም፡፡ በየቦታው ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እየተሰራ ሲሆን፤ የተለያዩ ስህተቶች የተፈጸሙበት ስለሆነ እርቅ ያስፈልጋል፡፡ ከቤተሰብና ጎረቤቱ ጀምሮ ሰው ከበደለው ጋር ይቅር መባባል ይኖርበታል፡፡ የተበደሉ የሚካሱበት፤ የበደለው አካል ይቅርታ የሚጠይቅበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ በመንግስት የተከናወኑ ስህተቶች ካሉም መንግስት ይቅርታ መጠየቅ፤ በህዝቦች መካከል የተፈጠረ ነገር ካለም መፈታት አለበት፡፡ ከማንነትም ሆነ ከወሰን ጋር የተለያዩ ሰላማችንን የሚያናጉ ነገሮችን ለመፍታትም የድንበር ኮሚሽንና የተለያዩ ነገሮች እየተሰሩ ነው፡፡ አዋጁም ጸድቆ ሰዎችም የተመደቡበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

በአጠቃላይ በሰላም ላይ፣ በልማት ላይ፣ በዴሞክራሲ ላይ፤ በእነዚህ በሦስቱ ላይ አቅጣጫ ስለተቀመጠ ይሄን አቅጣጫ አጠንክረን የምንሄድ ይሆናል፡፡ አገር የኢህአዴግ ብቻ አይደለም፤ የሁላችን ናትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት፤ የፖለቲከኛውም፣ የነጋዴውም፣ የጎዳና ተዳዳሪውም፣… ናት፡፡ ስለዚህ መረጋጋትን፣ ሰላምን፣ መቻቻልንና መፋቀርን በሚያመጡ ነገሮች ላይ በኃላፊነት ስሜት ሁሉም አካላት መስራት አለባቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ፍቃዱ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011

በወንድወሰን ሽመልስ