ስምምነትን የማፍረስና የማደስ ትንቅንቅ

11

አውዳሚው የኒውክለር የጦር መሳሪያ ምርት ለልዕለ ኃያል አገራት የባላንጣነት ፍጥጫ ዋነኛ መንስኤ መሆን የጀመረው ከሰባት አስርት ዓመታት በፊት ነው። በመሳሪያው ስጋት በአይነ ቁራኛ ለመተያየት፥ በስጋትና ባለመተማማን ለመታጃብ የተገደዱ አገራት በተለይ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ አውዳሚውን መሳሪያ ይበልጡኑ ታጥቀዋል። ማብለያን ተከለዋል።

አገራት በቀጠና በአህጉር ብሎም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን የሚጠቀሙት አይነኬነት፣ እድገትና የብልጽግናቸውን የሚያስመሰክሩትና ጡንቻቸውም የሚያሳዩብት ኒውክለር ጦር መሳሪያቸው ከሆነም ዋል አደር ብሏል።

ይህ ሲሆን ታዲያ ስርጭቱ ገደብ ከተበጀለት ብዙ አገራት የኒውክለር ባለቤት ከሆኑ መሳሪው ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበት እድል የዚያኑ ያህል ይጨምራል በሚል ስጋቱን የሚያስወግዱ የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦች ቀርበዋል። ከኒውክለር የጸዳ ዓለም እንዲፈጠር የተለያዩ ስምምነቶ ተፈርመዋል።

ኒውክለርን ለሃይላኑ ኢኮኖሚ ፍላጎት ጥቅም ላይ ከማዋል በስተቀር አውዳሚነቱን ተጠቅመው እርስ በእርስ ላለመጨራረስ፤ ብሎም  የሚያመርቷቸው ኒውክለሮች ገደብ እንዲኖራቸው ስምምነት ፈርመዋል። አሜሪካና የያኔዋ የሶቭየት ህብረት የአሁኗ ሩሲያ እ.ኤ.አ 1987 ዓ.ም የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ የኒውክለር ጦር መሳሪያን የተመለከተ የመካከለኛ እርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል  ስምምነት መፈረማቸው ይታወቃል።

በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጌንና በሶቭየቱ አቻቸው ሚካኤል ጎርቫቾቭ መካከል በዋሽንግተን የተፈረመ ይህ ስምምነት ሁለቱ ሃያልን አገራት የሚያመርቷቸው የባለስቲክና ክሩዝ ሚሳኤሎች የመወንጨፍ አቅም ከአምስት መቶ እስከ አምስት ሺህ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር እንዳይበልጥ ገደብ አስቀምጧል።

ይሁንና ምንም እንኳን ሁለቱ ሃያላን አገራት የገቡትን ስምምነት በአደባባይ ማፍረሳቸውን በይፋ ባያሳውቁም አንዳቸው አንዳቸውን መውቀስ ግን አላቆሙም። በተለይ ዋሽንግተን ሞስኮ ስምምነቱን አልጠበቀችም በሚል ከአንድም ሁለት ጊዜ ክስ አቅርባለች።

የቅርቡን እንኳን ብንመለከት ከአምስት ዓመታት በፊት የቀድሞው የአሜሪካ ፐሬዚዳንት ባራክ አባማ  ሞስኮ ቃሏን ማጠፋን በሚመለከት ወቀሳ በማቅረብ ምርምራ እንዳካሄድ ጥያቄ እስከማቅረብ ደርሰው ነበር። ባራክ ኦባማን ተክተው ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ይህን ጥያቄ ደጋግመው አንስተዋል።

«ሞስኮ ውስጥ ውስጡን ራሷን በተከለከሉ የኒውክለር መሳሪያዎች እያደራጀች ነው፤ ለበርካታ ዓመታትም ስምምነቱን ስትጠስ ቆይታለች» ሲሉ ከሰዋል። ከዚህ ተሻግረውም ጉዳዩ እልባት እስካላገኘ አገራቸው ከስምምነቱ ራሷን ለማውጣት እንደምትገደድ ሲያስጠነቅቁም ቆይተዋል።

ይህ የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ  ሩሲያ ከእኩይ ተግባሯ እንድትታቀብ ያግዛል ቢባልም፤ ሞስኮ በአንፃሩ አሻፈረኝ ብላለች። ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ከተፈረመው ስምምነት«አንድም ያፈረስኩት ቃል የለም፤ ይህም መረጋጋጥ የሚችል ሃቅ ነው»በማለት የዋሽንግተንን ወቀሳ ደጋግማ አስተባብላለች።

ይህን ያጤነችው ዋሽንግተንም ከቀናት በፊት ዓለምን ያስደነገጠ ውሳኔዋን ይፋ አድርጋለች። ሩሲያና ሌሎችም አገራት ተወንጫፊ ሚሳኤልን በሚመለከት ለታሰረው ስምምነት ተገዥ እስካልሆኑ ድረስ እኔም በስምምነቱ ለመቆየት አልገደድም ስትል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማይክ ፖንፒዮ በኩል አሳውቃለች። ይህ ፍላጎቷ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት እውን ካልሆነም ራሷን ክስምምነቱ በይፋ እንደምትነጥል  አስረግጣለች።

 ይህን የሰሙት የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ዋሽንግተን ያለችውን ካደረገች እኛም ቃላችንን እናጥፋለን ሲሉ ተደምጠዋል። የአገሪቱ ወታደራዊ ሃይልና ባለሙያዎችም አዲስ ተወንጫፊ ሚሳኤል ለመፍጠር እንዲዘጋጁ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

 ይህን የሁለቱ አገራት የአውዳሚ ጦር መሳሪያ ትንቅንቅ ተከትሎም፤ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ተንታኞችም፤ ውሳኔያቸው ምን አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ማስነባባቸውን ተያይዘውታል። የአገራቱ ከስምምነቱ የመውጣት ውሳኔም ሁለቱ አገራት ይፋዊ የኒውክለር ጦር መሳሪያ ፍልሚያ ፉክክር ውስጥ ከመግባት  ባሻገር ዓለምን ለዘግናኝ አደጋ ሊዳርጓት አስበዋል በሚል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

በጉዳዩ ላይ የባለሙያዎችን አስተያየት በማካታት ሰፊ ትንታኔን ያስነበበችው የአልጀዚራዋ  ዛሂና ራሺድ በበኩላ፤ በአገራት መካከል ያለው ከስምምነቱ የመፋታት ብርቱ ጥረት ዓለማችንን ከኒውክለር ጦር መሳሪያ ጦርነት ጋር ይበልጥ ያቅራርባታል ብላለች።

 የሁለቱ ሀገሮች ውሳኔ ለአውሮፓ ከባድ እንደሚሆንም ነው እየተገለጸ ያለው፡፡ በስታንፎርድ  ዪኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ደህንነትና ትብብር በተለይ በኒውክለር ጦር መሳሪያ ቁጥጥር ላይ ተመራማሪ የሆኑት ስቴቬን ፒፈር ስምምነቱ እስካልፀና ሞስኮ  ከ3ሺህ እስከ 5ሺህ 500ኪሎ ሜትር የሚወነጨፉ የኒውክለር መሳሪያዎችን እንደምትስድርና ለእዚህ እርምጃዋም ዋሽንግተንን ምክንያት እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

በተለይ የትራምፕ ውሳኔ ሩሲያ በአውሮፓ ምድር ወታደራዊ ምጥጥን እንድትቀምር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላትና ከኔቶና ከአውሮፓዊያኑ አገራት ጋር መልከ ምድራዊ ቀረቤታዋን በመጠቀም አሉኝ የምትላቸውን ሚሳኤሎች በቀጠናው ራዳር ስር ልትስድር እንድምትችል ሰፊ ግምት አግኝቷል።

ዋሽንግተን በአንፃሩ ሚሳኤሎቹን ለመሰደር እየዞሽ፤ በእኔ ግዛት ውስጥ ይህን ማድረግ ትችያለች የሚል አገር  ስለሚያስፍልጋት ከውሳኔዋ የምታገኘው ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ግልፅ ያልሆነና መጠነኛ ብሎም እጅጉን እድገኛ መሆኑም ተመላክቷል። ይልቅስ እ.ኤ.አ  በ1980ዎቹ እንደተከሰተው አይነት ሚሳኤሎቿን በቀጠናቸው ላይ ለመሰደር አጋሮችን ፍለጋ ብዙ እንድታማትር አስገድዷቷል ተብሏል።

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአንፃሩ አገራችን ሚሳኤሎችን በቀጠናው ራዳር ስር የምትሰድረው አንዳች እርምጃ ከዋሽንግተን በኩል የተሞከረ እንደሆነ ነው»ሲሉ ተደምጠዋል።

አውሮፓዊያን በበኩላቸው ገና ከወዲሁ ሃያላኑ አገራት በእርስ በአርስ ሹኩቻ በቀጠናችን በሺዎች የሚቆጠሩ ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን በመትከል ይበልጡኑ ሊያጨናንቁን ይችላሉ በሚል ስጋት ተወጥረዋል። በርካታ የምዕራብ አውሮፓና የኔቶ አባል አገራትም የሁለቱን አገራት በስምምነቱ መፅናትን ፋይዳ በማስረዳት እስከመለመን የደረሰ መማጸን ሲያደርጉ ተጠምደዋል።

አውሮፓዊያኑ ሚሳኤሎችን በቀጠናቸው የመሰደር ፍላጎት እንደሌላቸው ሁሉ በእሲያ ምድርም ቢሆን የዋሽንግተን ወዳጅ የሆኑት ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ከዚህ ተቃርኖ በመወሰን መሬታቸውን ለዋሽንግተን የሚቸሩ ከሆነ ግን መጪውን የኒውክለር  ፍልሚያ ይበልጥ እንደሚያጋግለው ተሰምሮበታል።

በተለይ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ምንም አይነት ዓለም ዓቀፍ የኒውክለር ስምምነት ላይ ፊርማዋን ያላኖረችው ቤጂንግ ሯሷን ወደ ትንቅንቁ ለመጨመር እንደምትገደድና በፓስፊክ አካባቢ ለአሜሪካ ከባድ ፈተና እንደምትሆን እየተገለጸ ነው፡፡

ቀጣይ ምን መፍትሄ ይኖረዋል ለሚለውም በርካታ ወገኖች አስተያየታቸውን  አስፍረዋል። የስታንፎርድ ዪኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ደህንነትና ትብብር ተመራማሪ ስቴቬን ፒፈር ዋሽንግተን ሩሲያ 9ኤም729. እንድታስውግድ ፀኑ ፍላጎት መያዟ፤ ሞስኮ ባንፃሩ ይህን የማድረግ ፍላጎት እንዳላት የሚያሳዩ ምልክቶች አለማሳየቷ ስምምነቱን ለማፅናት የሚያስችሉ አማራጮች መሟጠጣቸውን አስምረውብታል።

ይህም ሆኖ ምን አይነት አማራጮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተጠይቀውም፤ሞስኮም ሆነ ዋሽንግተን የኒውክለር ጦር መሳሪያን እስካ ፍንጫቸው መታጠቅ የሚሰጣቸውን ደስታ በመርሳት ሰላማዊነትን ምርጫቸው ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጠቁመው፤ ይህ ደግሞ በቅርብ ጊዜያት ይሆናል ብለው እንደማያስቡም አመላክተዋል።

ይህን እሳቤ የሚጋሩት የካሊፎርኒያ ዪኒቨርሲቲው ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ምርምር ተባባሪ ፕሮፌሰር፤ ጄፍሪ ፊልድስም«ስምምነቱ አሁንም ቢሆን አላበቃለትም፤ ስድስት ወራት ይቅሩታል፤ ይህም ሰላማዊ መንገድን ለመምረጥም በቂ ጊዜ ነው፤ ይሁንና አገራቱ ሰላማዊ መንገድን ያራምዳሉ ብዬ አላስበም» ብለዋል።

እንደ ሮይተርሱ ብሬት ሳሙኤልስ ከሆነ ግን አሁንም ቢሆን የሰላም መንገዶች ዝግ አልሆኑም። ዘገባው የሩሲያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋቢ በማድረግ፤ ምንም እንኳን ዋሽንግተን አዲስ የስምምነት እቅድን ይዛ ባትመጣም ሩሲያ ሌሎች አገራትን ባካተተ መልኩ አዲስ ስምምነትን ለመደራደር በሬ ክፍት ነው ስትል ማሳወቋን አስነብቧል።

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ሰፊ ትንታኔ ያሰፈሩት በአውስትራሊያም የዩኒቨርሲቲ የዓለም ዓቀፍ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰርራሜሽ ታኩር እንዳሉት፤ በዚህ የሰላም መንገድ ሁለቱ አገራት ካልተጓዙና ስምምነቱ ከፈረሰ እንዲሁም ሌሎችም የመሳሪያ ቁጥጥር ስምምነቶች ይፋ እስካልሆኑ ድረስ ዓለም እ.ኤ.አ ከ1972 ዓ.ም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአውዳሚው ጦር መሳሪያ ማዕቀብ ውጪ በመሆን ከአውዳሚው ጦር መሳሪያ ጋር ፊት ለፊት ትፋጠጣለች። ከሁሉም በላይ የስምምነቱ መፈረስ  ጦስ ለሶስተኛው የዓለም ጦርነት ሁነኛ ምክንያት መሆኑ አይቀሬ ነው።

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011

በታምራት ተስፋዬ