በ2010 ዓ.ም. ግምታዊ ዋጋ 900 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃ ተይዟል

24

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2010 ዓ.ም. 776 ሚሊየን 865ሺህ 292 የገቢ ኮንትሮባንድ እና 177 ሚሊየን 909ሺህ 149 የወጪ ኮንትሮባንድ መያዙን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህግ ማስከበር ሥራዎች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ ገለጹ፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ኅዳር 16/2011 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባደረገው የኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥ ንግድ ጉዳትና የመከላከል ቀጣይ አቅጣጫዎች የውይይት መድረክ ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፤ በ2010 ዓ.ም. ከተያዙ የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ ሚኔ 169 ሚሊየን 455ሺህ (21.81 በመቶ)፣ ሞያሌ 101 ሚሊየን 277ሺህ 156 (13.04 በመቶ)፣ ሃዋሳ 99 ሚሊየን 403ሺህ (12.80 በመቶ)፣ ድሬዳዋ 95 ሚሊየን 629ሺህ 552 (12.39 በመቶ) እንዲሁም ጅግጅጋ 94 ሚሊየን 755ሺህ (12.37 በመቶ) ድርሻ የያዙ ሲሆን 27.6 በመቶ የሚሆኑት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቀሩት ስምንት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ከተያዙት ወጪ ኮንትሮባንድ ግምታዊ ዋጋቸው ጅግጅጋ 63 ሚሊየን 507ሺህ 442 (29.62 በመቶ)፣ አዲስ አበባ ኤርፖርት 57 ሚሊየን 680 ሺህ 109 (26.90 በመቶ) አዲስ አበባ ቃሊቲ 29 ሚሊየን 402ሺህ 849 (13.71 በመቶ)፣ መቀሌ 6 ሚሊየን 706ሺህ፣ ጅማ 6 ሚሊየን 372ሺህ (2.97 በመቶ) ሲሆን ቀሪው 23.67 በመቶ የሚሆነው በሞያሌ፣ ድሬዳዋ፣ ጋላፊና ባህር ዳር ቅ/ጽ/ቤቶች መያዙን አቶ ዘመዴ አሳውቀዋል ሲል መረጃውን ያደረሰን የገቢዎች ሚኒስቴር ነው፡፡