“ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ይወርዳሉ!”

1065

“እ…አብይ ይወርዳል? የትኛው ነብይ ወይም ሟርተኛ ነህ አንተ ደግሞ!” እንዳትሉኝ። ቸኩላችሁ እንዳትበይኑ፤ ጥሎብን ችኩል ፈራጆች ሆነናል። ነገሩን በጥሞና ተመልክቶ መዳኘትና ሚዛናዊ ፍርድ መስጠት ብርቃችን ሆኗል አይደል!? የምናስበውን እንጂ እውነታውን ቀርበን መመርምር ሰልችተናል። አቤት ስንቶችን ባልተገኙበት አውለን ያለተግባራቸው ስም ሰጥተን፣ ያላሰቡትን አስበንና ያላዩትን ቀለም ቀብተን በችኩልነታችን ችካል ሆነንባቸው ይሆን? ዛሬ ዛሬማ እንደልማድ በስሚ ስሚ “ተደረገ” እና “ተባለ”ን ተከትልን የምንነጉድ በመሆናችን ተወራ ብለን መበየን ተክነንበታል። እንዴት ከኛ አርቀን ማስተዋልን ጭራሽ ዘንግተን እርግጠኛ ባልሆንበት ጉዳይ የመንጋ ብያኔ መስጠት ቀልሎናል። ለዛሬ ችኮላችንን የሚያሳይ አንድ ገጠመኜን ላካፍላችሁ ወደድኩ።

 ጠዋት የመጽሀፍ መደርደሪያዬን ተጠግቼ አንድ መጽሀፍ ስፈልግ ጊዜ ወሰደብኝ። ተራ በተራ ከተደረደሩት መካከል ማግኘት አልቻልኩም። ደግሜ ከላይ እስከታች ፈለግሁ፤ የለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጽሀፍ ማዋስ መተው እንዳለብኝ እየተሰማኝ ነው። አንዳንድ ሰው መጽሀፍ ለማንበብ ተውሶ መመለስ አይወድም። አሊያም ደግሞ መዋሱን ይረሳዋል መሰለኝ መልስ ካላሉት በራሱ እንደ ጨዋ አመስግኖ የሚመልስ እየጠፋ ነው። እኔ ደግሞ የፈለኩትን/የነበረኝን መጽሀፍ ከመደርደሪያዬ ላይ ሳጣ ያናድደኛል። ዛሬም የፈለኩት መጽሀፍ የለም። ማን እንደወሰደው ማስታወስ አልቻኩም። በወሰደው ሰው ሳላወቀው አኮረፍኩ። ለስራ በጣም ስለፈለኩት በመጨረሻ አማራጭነት መግዛት እንዳለብኝ ከራሴ ጋር ተስማማሁ። ቁርሴን እንደ ነገሩ ቀመስ አድርጌ ከቤቴ ወጣሁ። መጽሀፉ ቆየት ያለ ስለሆነ ይገኛል ብዬ ወዳሰብኩበት ለገሀር አካባቢ ወዳለ መጻሕፍት ቤት ለማምራት የሜክሲኮን ታክሲ ያዝኩ።

 ቡልጋሪያ ማዞሪያ ስደርስ አንዲት በዕድሜ ገፋ ያሉ እናት የተሳፈርኩበት ታክሲ  አስቁመው፤ ባለ 25 ሊትር ቢጫ ጀሪካን በረዳቱ አጋዥነት ወደ ታክሲው አስገቡ።  በእጆቻቸው በሩንና ወንበር በመያዝና ዕድሜ የተጫናቸውን እግሮቻቸውን እየጎተቱ፤ በከፊል ተደግፈው ገብተው ከጎኔ አረፍ አሉ። እንደገቡ ሹፌሩ ያውቃቸዋል መሰል “እማማ እንዴት አደሩ ሰላም ነዎት? ከየት ነው?” አላቸው። እሳቸውም ቀና ብለው ወደ ሹፌሩ ተመልክተው በፈገግታ፡- “አብደላ አንተ ነህ እንዴ? ደህና ነህ አለህ ለመሆኑ …እሰይ! እሰይ! ልጄ በርትተሀላ እቺን ገዛህ፤ ላዳዋን ትተህ፤ ጎበዝ ልጄ እግዛብሄር ይባርክልህ” ምርቃቱን አከታተሉለት።  እኔም በውስጤ ምርቃቱ ቅቡልነት እንዲኖረው ተመኘሁ። ከትላልቅ ሰዎች የሚገኝ ምርቃት የመንፈስ ምግብ አይደል! ደስ ሲል፤

ቀጠሉ እማማ፡ “ከየት አልከኝ ልጄ ውሀ ልቀዳ ሄጄ። ይሄው አስራ አምስት ቀናችን ውሀ ከጠፋ እነዚህ ሙሰኞች በየቀበሌና በየወረዳው የተሰበሰቡ የመንግሥት ሹመኞች አስቸገሩን። ቆይ መስሎዋቸዋል ገና ዶ/ር አብይ ይወርዳል። ሹመት ላይ ዘላለም የሚቀመጡ መስሎዋቸው እኮ ነው ሰውን የሚያንገላቱት…” ሰትዬዋ በሚናገሩት ተሳፋሪው ሁሉ ጆሮ ሰጥቶ ያደምጣቸዋል። በአብዛኛው ተሳፋሪ ትኩረት የተሰጠው አንድ አረፍተ ነገር በተለይ ደጋገሙት “ዶ/ር አብይ ይወርዳል።”

ተሳፋሪው ድምጽ በማውጣት ጭምር አጉረመረመ “…እ..እ..”  በጥያቄ መልክ መሆኑ ነው። ሰው መሪውን ሲወድድ ደስ ይላል። ጠቅላይ ሚኒስትራችን በህዝቡ ዘንድ፤ በሰው ዘንድ ያስወደዳቸው ሁሉም ባንድነት የተቀበላቸው የዘመኑ ምርጥ መሪ ስለመሆናቸው ማሳያ የሴትየዋን “ዶ/ር አብይ ይወርዳል” የሚለውን ዓረፍተ ነገር መሰማት ተከትሎ በተቀየረው የተሳፋሪዎች የፊት ገጽታ ይበልጥ ተደመምኩ።

ሴትዬዋ ቀጠሉ፡ “የወረዳው ሰራተኞች ስራ አይሰሩም። በማይረባ ወሬ ነው ቀናቸውን የሚጨርሱት፤ ቧንቧ ተበላሸ እባካችሁ ስሩልን ብለን መመላለስ ከጀመርን 10 ቀን አለፈ። አልሰራ ብለውን በስተርጅና ጀሪካን ተሸክመን እንዞራለን። እንቢ አሉ። የተነገራቸውን መስማት አቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አብይ ይወርዳል! አብያችን ቀበሌ ድረስ ወርዶ ሁሉንም ያስተካክላል። እስከዚያ እንዳሻቸው ያድርጉን፤ ጉዳቸው ማሾፋቸው እስኪታወቅ ነው አብያችን መቶላቸዋል፤

ለካስ ይወርዳል፤ እስከ ቀበሌ ድረስ፤ የሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩን አዲስ አሰራር ነው። ተሳፋሪው ከስልጣን ይወርዳል ብለው እሱን እየዘለፉ መስሎት ጆሮውን አቁሞ በቅሬታ እየገላመጣቸው እንዳላዳመጠ ነገሩ ሲገባው በፈገግታ እርስ በእርሱ ይተያይ ጀመር። ሴትዮዋ ቀጠሉ፤ ሁሉም ተሳፋሪ በፈገግታ እሳቸውን ነው የሚሰማው፤ “ የሚናገረውን አልሰማህም ልጄ? ህዝብን አገልግሉ፤ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን ኢትዮጵያዊ አደራችሁን ተወጡ ሲል፤ እሱ የተባረከ ነው! ቃሉም ተግባሩም የሚያጠገብ፤” እሳቸው የሚያወሩት ሹፌሩን እየተመለከቱ ነው ሌላውን ተሳፋሪ ቁብ ሰጥተው አላዩትም።

“አይ እኛን በነገር ካስረጁን ዕድሜያችን ከገፋ በኋላ ለእናንተ ምርጥ መሪ መጣ። እኛማ ጃጀን። በዚህ ዕድሜያችንም ቢሆን ይሄን ሀገር ወዳድ መሪ ስለሰጠን አምላክን እናመሰግነዋለን።” የሴትዮዋ የሰላ ንግግር ጆሮ ያስጥዳል። በመሀል ሹፌሩ ረዳቱን “እንዳትቀበላቸው የሳቸው ተከፍሏል” አለው። ረዳቱ የተቃውሞ ምላሽ ሠጠ፡-“ኧ ዴች ነው። አብዲ ተቀብያለሁ። ብዙ ነው እስከነ ጀሪካናቸው” አለ። አስር ብር ማለቱ ነበር። ሴትዮዋ፡- “የምን ቋንቋ መቀየር ነው ግብዣ ከፍ ሲል ነው የሚጥመው፤ መልስላት ተባልክ መልስ!” ሲሉ በታክሲው ውስጥ የነበርነው ሁላችንም ተሳፋሪዎች በሳቅ ተንከተከትን።

በነገራችን ላይ የቋንቋ አጠቃቀማችን ብዙ ያስተዛዝባል አይደል፤ በእርግጥ የረዳቱ ከሹፌር ወይም መሰል የሙያ ባልደረቦቹ ጋር መግባባት የሚችሉበት ቋንቋ መፍጠራቸው ችግር ባይኖረውም፤ ከማንና እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው አለመረዳታቸው ተግባቦትን ያፋልሳል። “አራዶች” የኛ የሚሉት ካራዶቹ ጋር ካልሆኑ ከኔ ቢጤው ጋር ሊያግባባቸው አይደለም በወጉ ሊያጋጫቸውም ይከብዳል። በየሆቴሉ መዝናኛና አቅጣጫ አመላካች የሆኑ ቦታዎች ላይ የሚለጠፉ ማህበራሰቡን ወይም ነዋሪውን የዘነጉ የቋንቋ አጠቃቀሞች አብዛኞቹ በእኛ አገር እና ለኛ የተዘጋጁ እኛን ግን የማያግባቡ መሆናቸው ወደፊት የምናየው ይሆናል።

የረዳቱ ከሹፌሩ ጋር የተነጋገረበት የራሱ ቋንቋ እናታችን በሰጡት የመልስ ምት ድል ሆነና ሹፌሩ በድጋሚ እንዲመልስላቸው ነግሮት መለሰላቸው። በመጨረሻ ሜክሲኮ ኬኬር ህንጻ አጠገብ ሲደርሱ ለሹፌሩ እንዲያቆምላቸው ነግረው የምርቃት መዓት አዥጎድጉደውለት ወረዱ። የምን አስር ብር ነው ይህን ምርቃት ለማግኘት ምንስ ቢሰጥ፤ እናም ወረዳ ምናምን ላይ ያላችሁ አስፈጻሚዎች፤ እባካችሁ በእናንተ አቅም የሚፈታውን የህዝቡን ጥያቄ  እየለያችሁ ፍቱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እናንተ ዘንድ ከመድረሱ በፊት እባካችሁ እናንተ ወደ ህዝቡ ዘንድ ውረዱና አድምጡት፤ ብለዋችኋል እናታችን፤

አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011