ኃይሉ የደከመ የላፕቶፕ ባትሪን ወደ ቀድሞ ጉልበቱ የሚመልስ የፈጠራ ስራ

15

መምህር አቦሀይ ውብሸት ይባላሉ። መምህሩ ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ከጐንደር ከተማ በ210 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ በምትገኝው ጃን አሞራ ከተማ ነው። ከ1ኛ ደረጃ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዛው በጃን አሞራ ከተማ በሚገኝው መካነ ብርሃን አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን፤ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ በኬሚስትሪ ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ2009 ዓ.ም አግኝተዋል።

 በአሁኑ ጊዜ ትምህርታቸውን በተከታተሉበት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተቀጥረው በመምህርነትና በጥናትና ምርምር ዘርፍ ላይ እየሰሩ ይገኛሉ። መምህሩ የፈጠራ ሥራና ምርምሮችን የጀመሩት በልጅነታቸው ነው፡፡ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆነው ከተለያዩ ጥራጥሬና የበቆሎ አይነቶች ነዳጅ በማበልጸግ ውጤታማ ሆነዋል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በመከታተል ላይ እያሉም በተመሳሳይ የሀድሮጅንና የካርቦን ይዘታቸው በጣም ከፍተኛ ከሆኑ ከተለያዩ የአፈር አይነቶች ነዳጅን ማበልጸግም ችለዋል።

 ከልጅነታቸው ጀምሮ በምርምርና ፈጠራ ለሀገራቸው አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኙት መምህር አቦሀይ የተለያዩ ችግር ፈች የፈጠራ ሥራዎች ለማበርከት ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ይዘንላችሁ የቀረብነው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እየተማሩ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሆነው የሰሩትን ፈጠራ ነው፡፡ ስለባትሪና ኤሌክትሮን በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተማሩትን ሥራ ላይ ያዋሉ ሲሆን፣ውጤታማም ሆነዋል። እርሳቸው እንዳሉት ትምህርቱን ሲከታተሉ ወደ አዕምሮአቸው የመጣላቸው ጽንስ ሀሳቡን ወደ ተግባር መቀየር ነበር፡፡ በባትሪ ኃይል የሚሰሩ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች የባትሪ ጉልበታቸው ሲደክም ሰዎች ሲቸገሩ ስለሚያዩ የባትሪ ጉልበቱ እንዳይደክም የሚያስችል አይነተኛ መፍትሄ ለመስጠት የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ የፈጠራ ስራውን ለመስራት እንደተነሳሱ ይናገራሉ። በተለይም ጉልበቱ የደከመና ያለቀ የላፕቶፕ ባጠትሪን ወደ ነበረበት ጉልበቱን የመመለስ እና ከዚያ በላይ ኃይል እንዲሰጥ የሚያስችል ችግር ፈች የፈጠራ ስራ ለመስራት በቅተዋል። መምህር አቦሀይ የፈጠራ ስራውን ከሰሩ በኋላም ቢሆን የተሻለ ለማድረግ በተለይ የባትሪ ኃይሉ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ለስድስት ስዓት ኃይል እንዲሰጥ ተደርጎ የተሰራውን የላፕቶፕ ባትሪ ወደ ስምንት ስዓትና ከዚያም በላይ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ነው ጥረታቸው። በዚህም የላፕቶፕ ባትሪውን ከስድስት ስዓት በላይ ሰላሳ ደቂቃ ተጨማሪ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ የቻሉ መሆኑን ገልጸው፤ ተጨማሪ ደቂቃዎች መጨመሩ በላፕቶፑ ላይ የሚያሳድረው ተጽኖ አለ የለም የሚለውን ጥናትና ምርምር እያካሄዱ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የፈጠራ ስራቸው ውጤታማ እንዲሆን በየጊዜው የማሻሻያ ስራዎችን በመስራት ላይ ናቸው፡፡

የተለያዮ የጎንዮሽ ጉዳቶችን በላፕቶፕ ላይ ባያስከትልም፤ የላፕቶፑን ደህንነት ለመጠበቅ በላፕቶፑ ላይ ምን ምን ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል? የተዘጋጀው ኬሚካል መቸ ላይ ኃይሉን ሊጨርስ ይችላል? የፈጠራ ስራው ምን አይነት ቅርጽና ይዘት ይኑረው? የሚጠቀሙት የኬሚካል ግብአት ለረጅም ጊዜ ሲቆይ በላፕቶፑና በሰው ላይ የሚያሳድረው ተጽኖ አለ ወይ? የሚሉ የቅድመ መከላከል ስራዎችን ጥናትና ምርምር በማድረግ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ቀድሞ ለመከላከል በማሰብ እየሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል። የፈጠራ ሥራቸው በተለይ ሰፊ ሥራ ያላቸው ትላልቅ ተቋማት እንደሚጠቅማቸው ይገልጻሉ፡፡

እርሳቸው እንዳሉት፣ ካለባቸው የስራ ብዛት ላፕቶፖችን በገዙ ማግስት የላፕቶፕ ባጠትሪው ጉልበቱ ይደክምና ሥራቸው ይጓተትባቸዋል፡፡ በሚያግጥም የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች በባትሪ ይጠቀማሉ፡፡ በመሆኑም ለባትሪ ወጪ ከፍተኛ በጀት ይመድባሉ፡፡የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትም ይቸገራሉ፡፡ፈጠራው የላፕቶፕ ባትሪ ኃይል ወደ ነበረበት በመመለስና መጀመሪያ ከነበረው ኃይል በላይ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል በመሆኑ ለችግሩ አይነተኛ መፍትሄ የሚሰጥና ወጭንም የሚቀንስ ነው ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አሉ፣ የፈጠራ ባለቤቱ መምህር አቦሀይ ከተማሩት ትምህርት ጽንስ ሀሳብ ተነስቶ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት የተለያዮ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻልና ከዚህም አልፎ የስራ እድል ፈጥሮ ትልቅ ገቢ ለራስና ለሀገር ማስገኝት መቻሉ የፈጠራ ስራው ዘርፈ ቡዙ ፋይዳና ጥቅም ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

 መምህሩ እንደገለጹት የፈጠራ ስራውን ከፍተኛ ወጪ በማይጠይቁና በቀላሉ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ እንደ ውሃና በውስጡ በማእድን የበለጸገ የአለት ድንጋይን በመጠቀም ነው የሰሩት። የፈጠራ ስራቸው ገበያ ውስጥ ገብቶ ዋጋ ወጥቶለት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ቤተ ሙከራ ውስጥ ባትሪውን የመሙላት አገልግሎት በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ዋጋው እንደ ላፕቶፑ የባትሪ የኃይል መጠን የሚለያይ ሲሆን፣ከ800 መቶ ብር እስከ 1ሺህ 800 መቶ ብር ዋጋ አገልግሎቱ እየተሰጠ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙና የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠቀሙባቸው ኃይላቸው የደከመ የላፕቶፕ ባትሪዎችን በትብብር በመሙላት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል። የፈጠራ ስራቸው እውን እንዲሆንና አገልግሎቱም ተደራሽ እንዲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ ድጋፍ ከጎናቸው እንደነበር እና በተለይም እንደነ ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ፣ ኢንጂነር ሶሎሞን ምስፍን የመሳሰሉ የዩኒቨርስቲው መምህራኖች በማማከርና እውቀታቸውን በማካፈል እገዛቸው ከፍተኛ እንደነበር ይናገራሉ፡ ፡

የጃን አሞራ ወረዳ የትምህርት ጽፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ሀይሉ ለፈጠራ ስራ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁሶች በግላቸው ገዝተው በመስጠት እና አሁን ለደረሱበት ደረጃ እንዲበቁ ድጋፋቸው ያልተለያቸው ሰው እንደሆኑም ይገልጻሉ፡፡ለሁሉም ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል፡፡ መምህር አቦሀይ የፈጠራ ሥራ ሲሰሩ ይህ ነው የሚባል ችግር ባይገጥማቸውም ቀላል እንዳልነበር ግን ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ለፈጠራ ስራው ግባቶችን ለማግኝት ያደርጉ የነበረው ጥረት አድካሚ ነበር።ለፈጠራ ስራው የሚውሉ የተለያዩ ግባቶችን ለማግኝት ለጥናትና ምርምር ከከተማ ወጣ ብለው በሄዱባቸው አካባቢዎች ህጋዊነታቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ እንኳን ይዘው አንዳንድ ተቋማት ለመተባበር ፈቃደኛ ያለመሆን ችግር የጥናት ስራቸውን ለማከናወን እንቅፋት ሆኖባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

መምህር አቦሀይ ከተሞክሮአቸው በመነሳትም ለሌሎች ምክር ሰጥተዋል፡፡‹‹ጥናትና ምርምር ማድረግ በጣም ትግስት የሚጠይቅና እልህ አስጨራሽ ሂደት ነው፡፡ተማሪዎችም ሆኑ የፈጠራ ስራ የሚሰሩ ሰዎች ይህን እውነት በመረዳት የሚሰሩት የፈጠራና ምርምር ውጤቱን እስኪያዩ ድረስ ተስፋ ሳይቆርጡ በትዕግስትና በጽናት ማለፍ አለባቸው››ብለዋል። እውቀት ይዞ የሚወለድ የለም የሚሉት አቶ አቦሀይ የፈጠራ ባለሙያው በአካባቢው፣ በትምህርት ቤት፣ በስልጠና ከማህበረሰቡ ያገኝውን እውቀትና ጽንስ ሀሳብ ወደ ተግባር ቀይሮ ለችግር መፍቻ ሊያውለው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ችግሮቻችን በመቅረፍ ለራሳችንም ስራ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ አለብን›› ብለዋል። የፈጠራ ስራዎችና ምርምሮች ችግር ፈች ብቻ ሳይሆኑ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ዘርፈብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው ግንዛቤ ሊያዝ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የፈጠራ ባለሙያዎች በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ማማ ላይ የደረሱ ሀገሮችን ልምድ የሚያገኙበት በተለይም ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ሀገሮች ድረስ የመሄድ ዕድል በመንግሥት በኩል ቢመቻች የተሻለ የፈጠራ ሥራ ለመስራት እንደሚያስችል በመጠቆም መንግሥት በዚህ በኩል እንዲያስብበት ጠይቀዋል፡፡ መምህር አቦሀይ በሌላ የፈጠራ ሥራቸው ጥቅም ላይ ውለው የተጣሉ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብ በሳይንሳዊ ዘዴ ወደ ምርት በመቀየር ለብረት፣ለመኪና ለቤት ቀለም አገልግሎት እንዲውል ማድረጋቸውንና ውጤት እንዳገኙበትም ገልጸዋል፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011

ሰለሞን በየነ