የ1999 ዓ.ም የህዝብና ቤት ቆጠራ ስህተት እንዳይደገም አ.ብ.ን አሳሰበ

120

አዲስ አበባ፤ በ1999 ዓ.ም የተከናወነው ሦስተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የአማራ ህዝብን ቁጥር ዝቅ በማድረግ የታየው ችግር ሳይደገም ሂደቱ ባግባቡ እንዲከናወን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አ.ብ.ን) አሳሰበ፡፡

አብን ትናንት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ‹‹የአማራ ህዝብ በ1999 ዓ.ም የህዝብና ቤት ቆጠራ የት ደረሰ?›› በሚል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር ሲሳይ ምስጋናው ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ በጥናታዊ ጽሁፉ እንዳመለከቱት፤ የ1999ዓ.ም በአማራ ህዝብ ይፋ የወጣው ሪፖርት ስህተት ነበረበት፡፡ በትክክል አልተቆጠረም ወይም ቁጥሩ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡

በአሁኑ ቆጠራም መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎቹን የሚያዘጋጁትና የሚቀምሩት ነባሮቹ ሰዎች፣ ቆጠራውን የሚያከናውኑት የስታትስቲክስ ኤጀንሲና የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ኃላፊዎቹና ሠራተኞቹ መሆናቸው አሁንም ስጋት እንደሚፈጥር በመጠቆምም፤ ባለሙያዎቹ ነጻና ገለልተኛ

 ሆነው እንዲሠሩ መክረዋል፡፡ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የአማራ ህዝብ ተሳትፎውን ሊያጠናክር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በሦስተኛው ዙር የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የአማራ ህዝብ እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ያደረገው የተቋማዊና የሥርዓቱ ችግሮች ናቸው፡፡ አሁን ሆን ተብሎ የአማራን ህዝብ አሳንሶ በመግለጽ ስህተት እንደማይፈጠር ተስፋ እናደርጋለንም ብለዋል፡፡

የቆጠራው ውጤት ሪፖርት የተደረገበት መንገድ የተሳሳተ በመሆኑ እንጂ የአንድ ህዝብ ቁጥርን ሊወስኑ የሚችሉ የሞት፣ የውልደትና ስደት ውጤት ልዩነት እንዳልነበረው አስታውሰው፤ ስህተቱ እንዳይደገም መሠራት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

የአብን ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊው አቶ መልካሙ ሹምዬ እንዳሉትም፤ ቆጠራውን የሚያከናውኑ ተቋማት ሥራቸውን ባግባቡ እንዲያከናውኑ መንግሥት ጫና ሊያደርግና መመሪያ ሊያስተላልፍ ይገባል፡፡ ሙያዊ ደረጃን የጠበቀ ሥራ እንዲሠራ፣ የመረጃ አሰባሰብና የመረጃ ትንተና ሥራውም በትክክለኛው መንገድ እንዲተገበርም ጠይቀዋል፡፡

ቆጠራው ሊጀመር የቀሩት ሁለት ወራት መሆናቸውን በማስታወስም፤ የተቋም አስተዳደር ለውጦች፣ ተቋማዊ እና የተቋማት ኃላፊዎች ለውጦች እንዲሁም የባለሙያዎች ገለልተኝነት ላይ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡ የመንግሥት ቁርጠኝነት ካለው ታማኝነት በተሞላበት መንገድ ቆጠራውን ማስቆጠር፣ ችግር ቢፈጠር እንኳን ማስተካከል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በቀሪ ጊዜ መንግሥት ለውጦችን ማሳየት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ቆጠራው የማህበራዊ፣ ኢኮኖ ሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚወስን በመሆኑ በክልልና ከክልል ውጪ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ቆጠራው ሲከናወን በትክክል ብሄራቸውን መናገር እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ የአማራ ህዝብ ቁጥሩ በትክክል እንዲታወቅ በቁጥሩ ልክም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የልማት እቅዶች ሲታቀዱ መሰረት የሚያደርገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት በመሆኑ የሚመለከተው ሁሉ የአማራን ህዝብ በማንቃት እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡

አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት፣ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ሦስት የህዝብና ቤት ቆጠራዎች በተሻለ ሁኔታ ለማካሄድ፣ ውጤቱም የበለጠ ጥራትና ተዓማኒነት እንዲኖረው ለማድረግ ሰፊ ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ፀሐፊ አቶ ቢራቱ ይገዙ ለአዲስ ዘመን ገልጸዋል፡፡

ቆጠራው በህዝብ ዘንድ ተአማኒ፣ በሁሉም ቦታ ተደራሽ እንዲሆንና መረጃ አሰባሰቡም እያንዳንዱ ሰው ሳይቆጠር እንዳይታለፍ በሚያስችል ሁኔታ ዝግጅቶች በመገባደድ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በቆጠራው የሚሳተፉ ቆጣሪዎች፣ ተቆጣጣሪዎችና ባለሙያዎች ቃለ መሃላ ፈጽመው የሚሰማሩ መሆኑን አመልክተዋል።

 ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011