የሠዓሊ ለማ ጉያ – የሥራና የጥበብ ሕይወት

53

የክብር ዶክተር ሠዓሊ ለማ ጉያ ገመዳ ኢትዮጵያ ከአፈራቻቸው ታላቅ የጥበብ ሰዎች ተርታ በግንባር የሚሰለፉ ባለሙያ ናቸው፡፡ የዘመናችን እውቅ የሥዕል ባለሙያ ከመሆናቸው ባሻገር የቅንነት፣ የደግነት፣ የጨዋነት፣ የጀግንነት፣ የአባትነት፣ የአርቆ አስተዋይነት መንፈስ የአላቸው አባት ናቸው። ጨዋታ አዋቂ፤ የፍቅር ሰው፤ ቀልደኛ፤ የሰውን ልጅ ሁሉ የሚያከብሩና አገር ወዳድ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የለውጥ አስተሳሰብ የአላቸው ዜጋ ናቸው፡፡ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ጡረታቸውን አስከብረው በቢሾፍቱ ከተማ በመኖር ላይ ያሉት ሠዓሊ ለማ ጉያ በአሁኑ ሰዓት የ91 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡

በ1921 ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ ጉያ ገመዳ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ማሬ ጎበና የተወለዱት በቀድሞ አጠራሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር አድኣ ሊበን ውስጥ ልዩ ስሙ ደሎ ገበሬ ማኅበር ነው፡፡ ሠዓሊ ለማ ጉያ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አስቴር በቀለ መካሻ ጋር የሚኖሩት ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ በትዳር ዘመናቸው ከአብራካቸው ትዕግሥትን፤ ነጻነትን፤ ደረጀን፤ ሰላማዊትን፤ ዳዊትን የወለዱ ሲሆን ሁሉም ልጆቻቸው ሠዓሊዎች ናቸው፡፡

የአውሮፕላኑ ትውስታ
ቢሾፍቱ ከተማ በስማቸው በተሠየመው የሥነ ጥበብ ማዕከላቸውና ቋሚ የሥዕላት ማሳያ ሙዚየማቸው (ጋሌሪያቸው) ውስጥ እንደተገናኘን፤ ሠዓሊው በትዝታ መነጽር ወደ ኋላ እያዩ እንዳጫወቱኝ የተወለዱባት ዶሎ መንደር የዛሬ 90 ዓመት ማለት ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም በዕለተ ሚካኤል አንድ ታሪክ ተስተናግዶባታል፡፡ ይኸውም በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው አውሮፕላን ከጂቡቲ በጠዋት ተነሥቶና የባቡር ሐዲዱን ተከትሎ እየበረረ ድሬዳዋ ይደርሳል፡፡

ወሬውም በነፋስ ስልክ ገፈርሳ ላይ አቀባበል ለማድረግ ከነመኳንንቶቻቸው ከአብራሪው ሚስት ጋር ተሰልፈው ሲጠባበቁ ለነበሩት ለአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ይደርሳል፡፡ ንግሥት ዘውዲቱም ወሬውን በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሆነው ይጠባበቃሉ፡፡ የፈረንሳዊው አብራሪ ባለቤት አስቀድማ ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ በባቡር የገባችው ታሪካዊውን አውሮፕላን የሚያበርረውን ባለቤቷን ከኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ጋር ተሰልፋ ለመቀበልና ብራቮ ብላ አድናቆቷን ለመግለጽ ነበር፡፡

አውሮፕላኑም ሐዲዱን እያነጣጠረና ከድሬዳዋ እየበረረ አዋሽ ይደርሳል፡፡ በአጋጣሚ ከጠዋቱ 5 ሰዓት ላይ ናዝሬት (አዳማ) ሲደርስ ጥቁር ደመና መንገዱን ይዘጋበታል፡፡ ለማየት የማይችልበት ሁኔታ እንደተፈጠረ አብራሪው መድረሻ ያጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ የተጨነቀው ፈረንሳዊው አብራሪ በድንገት ገላጣ ቦታ ሲያይ አውሮፕላኑን ቁልቁል እያምዘገዘገና ባወጣ ያውጣው እያለ ሠዓሊው ከተወለዱባት ዶሎ የገጠር መንደር ላይ በሚገኘው በበጅሮንድ ውብእሸት መሬት ላይ ያሳርፈዋል፡፡

ይህም ለራስ ተፈሪ መኮንን በነፋስ ስልክ ይነገራቸዋል፡፡ አውሮፕላን ቀርቶ መኪና በቅጡ አይቶ የማያውቀው የዶሎ ሕዝብም ምን ጉድ ነገር መጣ እያለና እየተጠራራ ወደ አውሮፕላኑ በደመ ነፍስ ሲሮጥ የሕፃን ለማም ቤተሰቦች የተፈጠረውን ጉድ ለማየት ጥለዋቸው ወደ አውሮፕላኑ ይሮጣሉ፡፡ ያኔ ለማ የስድስት ወር ልጅ ነበሩ፡፡ እናም ዶሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጀመሪያውን አውሮፕላን ከሰማይ ተቀብላና አሳርፋ ያስተናገደች የገጠር መንደር ኤርፖርት ናት ማለት ነው፡፡

ይህን የታሪክ ክሥተት እየሰሙ ያደጉት ለማ ጉያም አውሮፕላኑ የሕይወታቸው ምዕራፍና የእድላቸው ምልክት እንደሆናቸው ያስታውሳሉ፡፡ ይህም ወደፊት የምናየው ጉዳይ ነው፡፡ ሠዓሊ ለማ እንዳጫወቱኝ ቀደም ሲልም ተገጣጥሞ የሚበርር የአውሮፕላን ዕቃ በባቡር ተጭኖና ከፈረንሳይ ጂቡቲ፤ ከጂቡቲ አዲስ አበባ ገብቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ሳይከፈትና ተገጣጥሞ ሳይበርር ወደመጣበት እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ቀሳውስቱና መሳፍንቱ የእግዚአብሔር መዓት ሊመጣብን ይችላል ብለው እንዳይከፈት ስለተቃወሙ ነው፡፡እናም ዶሎ ያረፈው አውሮፕላን ከፈረንሳይ ዕቃው (ቦዲው) መጥቶ የተገጣጠመው ጂቡቲ ውስጥ ነው፡፡

ነሐሴ 12 ቀን 1921 ከሰዓት በኋላ ማለት ከቀኑ 7 ሰዓት ሲሆን ደመናው እየተገፈፈና ሰማዩም እየጠራ ቀኑ ብሩህ በመሆኑ አውሮፕላኑ ተነሥቶ አዲስ አበባ ገፈርሳ ላይ ሲያርፍ የተሰለፈው ሕዝብ በእልልታና በጭብጨባ ይቀበለዋል፡፡

በጥበብ መለከፍ
ሠዓሊ ለማ ጉያ በልጅነታቸው በዶሎ የገጠር መንደር ውስጥ የቤተሰቦቻቸውን ከብቶች ሲጠብቁ ዐፈሩን፣ ዐመዱን፣ ጠጠሩን እየሰበሰቡና እያድቦለቦሉ ዱላ የያዙ እረኞችን መሥራት ይለማመዳሉ፡፡ የሰው ሥዕል ግድግዳ ላይ መሣል ይጀምራሉ፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ከከተማ ወደ ገጠር ዶሎ ሰዎች ይመጡ ስለነበር የእነርሱን የአለባበስ ሁኔታ ያያሉ፡፡ በተጨማሪም ከቡልጋ፤ ከምንጃርና ከመንዝ ወደ ዶሎ የሚመጡ ባላገሮች ነበሩ፡፡ እርሳቸው ይኖሩበት የነበረውም ቦታ የቡልጋ ባላባት ርስትና ጉልት ነበር፡፡

የሠዓሊ ለማ ጉያ ወላጅ እናት ወይዘሮ ማሬ ጎበና የተወለዱት ለገዳዲ አብቹ ከተባለ ቦታ ነው፡፡ የአባታቸው አባት አያታቸው አቶ ገመዳ ኮርሜ ደግሞ ከሰላሌ ወደ ዶሎ የመጡ ሰው ናቸው፡፡ ወላጅ እናታቸው ወይዘሮ ማሬ ጎበና እንዲሁ የእጅ ሥራ ዐዋቂና ባለሙያ ነበሩ፡፡ ሸክላ፣ጋን፣ እንስራ፣ጀበና፣ ምጣድ ይሠራሉ፡፡ በግድግዳ ላይ ሥዕል ይሥላሉ፡፡

ለማም ሁልጊዜ የእናታቸውን ሥራ አተኩረው ይመለከታሉ፡፡ እናት የሸክላ ዕቃዎችን ከመሥራትና ልዩ ልዩ ሥዕሎችን ከመሣል አልፈው ስፌትም ይሰፋሉ፤ ሥጋው ተበልቶ አጥንቱ የሚቀመጥበት ገበቴ ይሠራሉ፡፡ ሁሉ ነገር ሥርዓት እንዲይዝ ያደርጋሉ፡፡ በዚያ ዘመን ባቡር፣ መኪና አልነበረምና የሸክላ ምርታቸውን ከለገዳዴ በአጋሰስና በአህያ ጭነው ወደ አድኣ እያመጡ ይሸጡ ነበር፡፡

የእናታቸው ወንድም ኦርዶፋ ጎበናም እንዲሁ በዘመኑ የልብስ ስፌት መኪና ሳይኖር ልብስ በመርፌ ይሰፉና ሞፈር፣ ቀንበር፣ ድግር ለገበሬዎች ያበጁ ነበር፡፡ ቤተሰባቸው ሁሉ ጥበበኛ ነበር ማለት ነው፡፡ ሠዓሊ ለማ ጉያ እንዲያስታውሱት በልጅነታቸው የከብት እረኛ በነበሩ ጊዜ በአካባቢያቸው ሞጃ ከተባለ ቦታ የረር ወንዝ ላይ ባቢቾብ የተባለ ሩሲያዊ በውኃ ኃይል የሚንቀሳቀስ የእህል ወፍጮ ሠርቶ ስለነበር ወደ ድንጋይ ቋት የገባውን ጥሬ እህል በአንዴ ዱቄት አድርጎት ሲመለከቱት ይገረሙ ነበር፡፡

ያኔ መኪናም፣ የመኪና መንገድም ስለአልነበረ። በተለይ በክረምት ሁሉ ነገር በእንስሳና በሰው ጉልበት በከባድ ጭቃ ውስጥ ከቦታ ወደ ቦታ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ጣሊያኖች በ1928 በመኪና ቢሾፍቱ ገልቻ ወንዝ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ጭቃ ይዟቸው ስለተገኙ ተገድለዋል፡፡
ሠዓሊ ለማ ጉያ ሞፈርና ቀንበራቸውን ሰቅለው ደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) ዓፄ ልብነ ድንግል ተብሎ ይታወቅ ወደነበረውና ዛሬ ስሙ ወደተቀየረው ዘመናዊ ትምህርት ቤት የገቡት በ17 ዓመታቸው ነው፡፡ ሀ ብለው ፊደል ከቆጠሩ በኋላ በ1943 ዓ. ም 7ኛን ክፍል ጨርሰው ናዝሬት (አዳማ) ዓፄ ገላውዴዎስ (ዛሬ ስሙ ወደተቀየረው) ትምህርት ቤት ይገባሉ፡፡ እዚያም በመምህርነት ሠልጥነው በ70 ብር ደመወዝ ይቀጠራሉ፡፡ ወዲያው ሥራውን አልፈልግም ብለው ይተውታል፡፡

ያልተሳካው የአብራሪነት ህልም
ስለ አውሮፕላን ነገር በልጅነታቸው የሰሙትና ሲያድጉም በቢሾፍቱ ሰማይ ላይ ሲበርር የሚያዩት የአየር ኃይል ጀት መንፈሳቸውን ስለማረከው የተለየና ያማረ የአውሮፕላን ሞዴል ቅርፅ ሠርተው ግርማዊ ጃንሆይ ለሽርሽር ወደ ቢሾፍቱ በሚመጡበት ዕለት ለማበርከት ስለፈለጉ ቀን ይጠባበቁ ጀመር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ግርማዊ ጃንሆይ ለጉብኝትና ለሽርሽር ቢሾፍቱ አየር ኃይል ሲደርሱ ለማ ልክ እንደወታደር ቀጥ ብለው በመቆም ለንጉሡ የክብር ሰላምታ ይሰጣሉ፡፡ ንጉሡም «ምን ትፈልጋለህ?» ብለው ይጠይቋቸዋል፡፡ «ግርማዊ ሆይ አየር ኃይል ያስገቡኝ» ይላሉ፡፡ ንጉሡም ያኔ ግራዝማች ሣህሉ ድፋየን ጠርተው «በል በአስቸኳይ ለጂኒናር አሰፋ አያና ንገርና ይህንን ልጅ ያስገባው» ብለው መመሪያ ይሰጣሉ፡፡ 60 ብርም ለለማ ጉያ ይሰጡዋቸዋል፡፡ ለማም በ60 ብሯ አንዲት ላም ገዝተው ለዘመዶቻቸው ይሰጣሉ፡፡ በጃንሆይ ብር የተገዛ ከብት ደግሞ በዘመኑ አይሰረቅም ነበር፡፡ በጃንሆይ ብር የተገዛች የጃንሆይ ላም ናት ከተባለ ማን አባቱ ነክቶ? የትስ ሊገባ? ሌሎች ከብቶች ሲሰረቁ እርስዋ በሰላም ኖራለች፡፡

ወጣቱ ለማ ጉያ በጀኔራል አሰፋ አያና ትእዛዝ ወደ አየር ኃይል ገብተው የመካኒክነት ሙያ ማለትም አውሮፕላን የመፍታትና የመግጠም ትምህርት ይማራሉ፡፡ ማታ ማታ ደግሞ በእንግሊዝ መምህራን እንግሊዝኛ ቋንቋን የመማር እድል ያገኛሉ፡፡ ከሁለት ዓመት ጥናት በኋላም በመካኒክነት ይመረቃሉ፡፡ እርሳቸው ግን አብራሪ እንጂ መካኒክ መሆን አልፈለጉም ነበርና «ለምን መካኒክ ሆንኩ ለምንስ አብራሪ አልሆንኩም? የላኩኝ እኮ ራሳቸው ንጉሡ ናቸው?» ብለው ለኃላፊዎች ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ በወቅቱ አብራሪ መኮንኖች ይሄዱ የነበሩት በመኪና ሲሆን ለማ ግን ወደ መኖሪያቸው ይመላለሱ የነበረው በእግራቸው ስለነበር በዚህ ተናድደዋል፡፡

ይህንኑ ምክንያት አድርገው አሰፋ ከተባለ የድሬ ሰው ጋር ይጠፋሉ፡፡ ወላጅ አባታቸው አቶ ጉያም እሳት ለብሰውና እሳት ጎርሰው «ከዛሬ ጀምሮ ልጄ አይደለህም፡፡ ኃይለ ሥላሴ ራሳቸው እንድትማር አስገብተውህ እንደዚህ ማድረግ አልነበረብህም፡፡ የጠፋኸው እኔን ልታስገድለኝ ነው እንዴ? የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰህ ሽፍታ ልትሆን ነው? » ብለው ሲቆጡዋቸው ለማ እሺ ብለው ወደ አየር ኃይል ይመለሳሉ፡፡

በአጋጣሚ ግን ኃላፊዎች አንዴ ጥለህ ሄደሃልና አናስገባህም ይሏቸዋል፡፡ ወጣቱ መካኒክም ብልህ ስለሆኑ «እስከ አሁን የጠፋሁት አባቴ ታሞብኝ ስለነበረ ነው፡፡ እምቢ ካላችሁ ለግርማዊ ጃንሆይ ሄጄ እነግራቸዋለሁ» ሲሉ የአየር ኃይል ኃላፊዎችም ይኸማ አይሆንም» ብለውና ተደናግጠው ያስገቧቸዋል፡፡
ደመወዛቸውም 40 ብር ነበር፡፡ በጊዜው ይህ ብር ተዝቆ አያልቅም ነበር፡፡ ሠዓሊው እንደሚሉት ያኔ ከደብረ ዘይት ወደ ናዝሬት ይወርዱና በ25 ሳንቲም ሥጋ ወጥ በልተውና 1ብር ባልሞላ ቀኑን ሙሉ ተዝናንተው ወደ ትንሺቱ የአየር ኃይል መንደር ይመለሱ ነበር፡፡ ለማ በመካኒክነት ደብረ ዘይት ከሠሩ በኋላ ወደ ጂጂጋ ( ጂግጂጋ) ተልከዋል፡፡

ጂግጅጋ ደግሞ ሌሊት ሌሊት ጊንጥ እየነደፈች ሰው ትገድል ስለነበር ሞኝሽን ፈልጊ ብለው አውሮፕላን ውስጥ እየገቡ ያድሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ያኔ ነዳጅ ወደ አውሮፕላን ይሞላ የነበረው በበርሜል በሰው ኃይል ተቀድቶና ተሞልቶ፤ እንደገና በፓምፕ እየተገፋ ነበር፡፡
በመካኒክነት ሲያገለግሉ የቆዩት ለማ ጉያ እአአ በ1952 በአየር ኃይል አርማሜንት ክፍል ለአምስት ዓመት ኮርስ (ሥልጠና) ወስደው ተመርቀዋል፡፡ ትምህርቱ በጦር መሣሪያ ኃይል ጠላትን እንዴት መከላከል፤ ማጥቃትና ማሸነፍ እንደሚቻል፤ እንዴት ጥይቱን፤ ረሹን ገዝተው እንደሚሠሩ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው፡፡ ይሠሩ የነበረውም በስዊድን ቢ17 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ላይ ነበር፡፡

ሠዓሊ ለማ አሥመራን ከጥቃት ለመከላከል በደቀ መሐሪ 40 ኪሎ ሜትር ላይ ልምምድ ያደርጉ ነበር፡፡ በ1966 ዓም ደብረ ዘይት «ያለምንም ደም…» ብለው የተነሡትና የመጀመሪያውን ደርግ ያቋቋሙት ሠዓሊ ለማን ጨምሮ የአየር ኃይል መኮንኖች ናቸው፡፡ በወታደራዊ ማዕረግ ከታች ጀምረው እስከ ሻምበልነት የደረሱት ለማ ጉያ በ40 ደራስያን የተጻፈ የኮሚኒስት መጽሐፍም ለወጣት መኮንኖች ስለአሠራጩ ኮሚኒስት ነህ ተብለውና በጀኔራል አሰፋ አያና ተጠይቀው ታሥረዋል፡፡

በጥረት ሠዓሊነት
ሠዓሊ ለማ ጉያ የሠዓሊነት ሙያቸውን ያዳበሩት ሥዕል ትምህርት ቤት ገብተው በመማር ሳይሆን በግል ጥረታቸው ነው፡፡ ከሠዓልያን ሁሉ ለየት ያለ የአሣሣል ጥበብን ይከተላሉ፡፡ በዋነኛነት ትኩረት የሚያደርጉትም ቪዡዋል አርት በሚባለው የአሣሣል ጥበብ ላይ ነው፡፡ ይኸውም የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥ የጥበብ ሥራ ሲሆን የሚጠቀሙበት ቁሳቁስ የፍየል ወይም የበሬ ቆዳ፣ የውኃ ቀለም፣ የዘይት ቀለም፣ ከሰል (ቻርኮል) ነው፡፡
በቆዳ ላይ መሣል የጀመሩት ከደርግ ዘመን ጀምሮ ሲሆን በዘመነ ደርግ ብሩሽና ቀለም እንደልብ አይገኝም ነበርና የፍየል ቆዳ ልብስ ስለሚሆን ለምን የፍየል ቆዳን በሞዛይክ አልሠራም ብለው በመነሣሣት ሥራውን ይጀምራሉ፡፡ በመጀመሪያ በፍየል ቆዳ ላይ የሣሉት ሮበርት ሙጋቤን ነው፡፡ በጊዜው ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር የነበረው የዚምባብዌው አምባሳደርም በጣም ደስ ስለአለው ሥዕሉን ከሠዓሊ ለማ ተቀብሎ ለሮበርት ሙጋቤ ይሰጣቸዋል፡፡ በኋላ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሁለተኛ የመሪዎችን ሥዕል እንዳትሠራ፤ ገንዘብ እኔ እሰጥሃለሁ በማለት ለሠዓሊ ለማ ይነግሯቸዋል፡፡ የመንግሥቱ ሐሳብ ሠዓሊው በቀጥታ ከመሪዎች ጋር በሥራ እንዳይገናኙና እንዳይቀርቡ ለማድረግ ነበር፡፡ በሌላ ጊዜ መንግሥቱ ኃይለማርያም በትእዛዝ የኮርያውን ፕሬዚዳንት ሥዕል እንዲሥሉ ካደረጉ በኋላ ወስደው ለፕሬዚዳንቱ ይሰጡዋቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ተቀብለው ለኮርያ ሙዚየም ይሠጣሉ፡፡

በዚህ ዓይነት መንገድ የደርግ መንግሥት አማካሪዎች ሠዓሊ ለማ ጉያ በሙያቸው ከመሪዎች ጋር እንዳይገናኙ ያደርጉ ነበር፡፡ ሠዓሊው እንዳወጉኝ ይንን ተንኮል በቀጥታ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ነግረዋቸዋል፡፡ ታየ ታደሰ ስለ አንዳንድ የኢትዮጵያ ሠዓልያን አጭር የሕይወት ታሪክ እንደጻፈው ከሠዓሊ ለማ ቀዳማውያን ሥራዎች ውስጥ የሸክላ ገበያ፣ የወሎ ድርቅ፣ የደንከል ልጃገረድ የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ዓለም ዓቀፋዊ እውቅና
ቀደም ሲል ሥራዎቻቸውን በግል በአሥመራ፣ በአዲስ አበባ፣ በደብረ ዘይት ለእይታ አቅርበዋል፡፡ በውጭ አገር ደግሞ በሌጎስ፣ በዳካር ወዘተ በኅብረት ሥራዎቻቸውን አሳይተዋል፡፡ ሠዓሊው እንደገለጹልኝ ቀደም ሲልም በልጃቸው ሠዓሊት ነጻነት ለማ አማካይነት በአሜሪካ ኒዎርክ ከተማ ሥዕሎቻቸውን ለእይታ ያቀረቡ ሲሆን ኤግዚቢሽኑን የከፈቱት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ናቸው፡፡
በኤግዚቢሽኑ ላይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የጆርጅ ቡሽና የሌሎች መሪዎች ሥዕሎች ለእይታ ቀርበው ተሸጠዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሠዓሊው ከ20 በላይ ለሆኑ የአፍሪካ መሪዎች፤ ለበርካታ አምባሳደሮች፤ ከአፍሪካ ውጭ ለሆኑ መሪዎች፤ ለኢትዮ- ሩሲያዊው ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን ሥዕል ሠርተው ያበረከቱ ሲሆን በቅርቡም ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ለአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ሥራቸውን ማበርከታቸው አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትና ልዩ ልዩ ድርጅቶች አስደናቂዎች የሆኑ ልዩ ልዩ ሥራዎቻቸውን በመመዘን ሰርቲፊኬትና ሌሎች ሽልማቶችን አበርክተውላቸዋል፡፡ በሥራቸው ሁልጊዜ ደስተኛ የሆኑት ሠዓሊ ለማ ከዓፄ ቴዎድሮስ እስከ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድረስ የነበሩትን የኢትዮጵያ መሪዎች ሥዕል በቆዳ ላይ ሰርተዋል። ሥዕላቱ በቢሾፍቱ ከተማ በሦስት ክፍሎች በተደራጀው የሥዕል ማሳያ ሙዚየማቸው ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በኦሮሚያ ክልልም ከሐሰን አሊ እስከ ሙክታር ከድር ድረስ ሕዝቡን የመሩ ርዕሰ መስተዳድሮች ሥለው አቅርበዋል፡፡ በካድሬዎችና በአማካሪዎች ክፋት የሚቀበል ሰው ባይገኝም የጋምቤላን ክልል መሪዎች ሥለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካድሬዎች ለውጥ አራማጆችና የሕዝብ ፍቅር ያላቸው የሕዝብ አገልጋዮች ቢሆኑም የእኛ አገር ካድሬዎችና አማካሪዎች ግን ሥራ እንደሚያበላሹና መለኪያ እንደሌላቸው ያወሳሉ፡፡ ሠዓሊ ለማ ጉያ በእንስሳት ቆዳ ላይ የሚሠሩት ሥዕል እስከ 60 ሺህ ብር የሚያወጣው ነው፡፡

ሠዓሊ ለማ ጉያ በሻምበልነት ማዕረግ ለ11 ዓመታት አሥመራ በአገለገሉበት ወቅት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኤርትራን ለመጎብኘት አሥመራ ሲገቡ እንዲሁ የንጉሡን መልክ የያዘ ሥዕል ያበረከቱ ሲሆን ንጉሡም ሥዕሉን ለኤርትራ ዩኒቨርሲቲ በማስታወሻነት እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሦስቱም ሙዚየሞቻቸው ውስጥ በርካታ ሥዕሎች ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ዓለማየሁ ቴዎድሮስ፣ ዓፄ ቴዎድሮስ፣ መቅደላ፣ ንግሥት ቪክቶሪያ፣ ዊንስተን ቸርቺል፣ ዓፄ ዮሐንስ፣ ዓፄ ተክለ ጊዮርጊስ፣ አየር ኃይል፣ ግብርና፣ የረር ተራራ፣ ቢሾፍቱ ትላንትና ዛሬ፣ የመቀሌ መስጊድ፣ አልበርት አይንስታይን፣ ንግሥት ኤልሳቤጥ፣ እናት ኦሮሚያ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ኃይለ ሥላሴ፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ መለስ ዜናዊ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ማርሽ ቀያሪው የተባለው ምሩጽ ይፍጠር፣ የፋሲል ግምብ፣ የሶፎኦማር ዋሻ፣ የአክሱም ሐውልት ቋንጣ በስስት የሚመለከቱ ድመቶች — ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሠዓሊ ለማ ለዚህ ሁሉ ሥዕል ከነምክንያቱ ማብራሪያ ሲሰጡ አይታክታቸውም፡፡

የአፍሪካ የሥዕል ሙዚየም ትልም
ሠዓሊ ለማ ከ1983 ዓ ም ጀምሮ በአሥር ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለማ ጉያ የሥዕል ትምህርት ቤት የሚል በግላቸው አቋቁመው ከሙዓለ ሕፃናት እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ልጆችን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት 400 ተማሪዎች አሉዋቸው፡፡ በይዞታቸው ላይ የመንግሥት እጅ የለበትም፡፡ ያ ሁሉ ሕንጻ የተሠራው በግል ሀብታቸው እንጂ በባንክ ብድር አይደለም፡፡ እንደእርሳቸው አባባል የባንክ ቤትን ብድርና እሳተ ገሞራን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡

ወደፊት የአፍሪካ የሥዕል ሙዚየምን ለማቋቋም ለሚያደርጉት ጥረት እንዲረዳቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት 20 ሺህ ካሬ ቦታ ሰጥቷቸዋል፡፡ በሠዓሊ ለማ ጉያ የሥነ ጥበብ ሙዚየም ውስጥ የኔልሰን ማንዴላ ሐውልት ቆሞ ይታያል፡፡
ሠዓሊ ለማ ቀደም ሲል ማለት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የሥዕል መማሪያ መጽሐፍ ያሳተሙና ያሰራጩ ሲሆን በተጨማሪ «የሥራ ፈጠራ» የተሰኘ መጽሐፍም ደርሰው ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሕይወት ታሪካቸውና ሥራዎቻቸው ላይ ያተኮረና ባለ 350 ገጽ የሆነ መጽሐፍ ለኅትመት አዘጋጅተዋል፡፡ መጽሐፉ በቅርቡ ታትሞ ገበያ ላይ እንደሚውልም አስረድተውናል፡፡

በዶ/ር ታደለ ገድሌ ጸጋየ