በኡሁሩ ኬንያታ ሥም ያጭበረበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

33

የኬንያ ፖሊስ እንዳስታወቀው የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ሰባት ባለስልጣናትን እየመሰሉ በተለያዩ አካባቢዎች ባለሀብቶችን ያጭበረብሩ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ቢቢሲ የኬንያ አካባቢያዊ መገናኛ ብዙኃንን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከተጠርጣሪዎች አንዱ ለአንድ ኩባንያ ባለቤት በመደወልና ድምጹን የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በማስመሰል ለሥራ ጉዳይ ገንዘብ እንዲያወጡ ሲወተውታቸው ቆይቷል፡፡

ምንም እንኳ የገንዘብ መጠኑ በትክክል ባይገለጽም ዴይሊ ኔሽን የተባለው የኬንያ መገናኛ አውታር እስከ 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ግለሰቡ መጠየቃቸውን አስነብቧል፡፡

ታዲያ እንዲህ በባለስልጣናት ድምጽ የሚያታልሉት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፤ ክስ ግን ገና አልተመሠረተባቸውም፡፡
ፖሊስ ክስ ለመመሥረት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡ ‹‹ከወንጀሉ ውስብስብነት፣ ከተጠርጣሪዎቹ ብዛት፣ ያልተያዙ ተጠርጣዎች ከመኖራቸውና የምርመራ ሂደቱ የድምጽ ቅጅዎችንና የባንክ ሰነዶችን መፈተሽ ከመጠየቁ አንጻር ጊዜ ያስፈልገኛል›› ብሏል፡፡

በፕሬዝዳንቱ ስም በሀሰት የተጭበረበሩት ባለሀብት ናውሻድ ሜራሊ ከኬንያ ታዋቂ ባለሀብቶች መካከል በኢንፎርሽን ቴክኖሎጂና ሪል ስቴት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ነገር ግን ተጭበርብረው ገንዘቡን ስለመስጠት አለመስጠታቸው ዘገባው ያለው ነገር የለም፤ ምን ያህል ግለሰቦች እንደተጭበረበሩም አልተጠቀሰም፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ