የወመዘክር ጉዞ- አንባቢን ፍለጋ

27

በ1936ዓ.ም ነበር፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ «የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር» በሚል ስያሜ የተቋቋመው። ሥራውንም የጀመረው ከንጉሡ በተገኘ የመጻሕፍት ስጦታ ነበር። የመንግሥት ስርዓት በተለወጠና በተቀየረ ቁጥር ይህም ተቋም ስምና መዋቅሩ ሲቀያየር ቆይቷል። ቀደም ብለው ተቋሙን የሚያውቁትና እግራቸው የሚመላለስበት ግን በቀደመ ስሙ «ወመዘክር» ብሎ መጥራቱ ይቀናቸዋል፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲን።

በቀደመ ስያሜው እየጠራሁ እንዳትት ይፈቀድልኝና እቀጥላለሁ። ወመዘክር ከተመሠረተበት ዓመት ጀምሮ የተለያዩ ለውጦች የተደረጉበት ቢሆንም፤ ከመጻሕፍትና ከመዛግብት ጋር ያለው ትስስርና ትውውቅ ግን ጸንቶ ቆይቷል። እንደየአመራሩ ጥንካሬና ብርታት፤ እንደተጠቃሚው ጠያቂነትና ተገልጋይነትም፤ «ጎሽ! ደግ ተደረገ!» የተባለለት እንዲሁም «ምነው?» ተብሎ የተወቀሰበት ጊዜም አለ።

ይህን ለመግቢያ አነሳሁ እንጂ ነገሬ ከዚህ ሳይሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተቋሙ ከጀመረው እንቅስቃሴ ነው። ይህም «ይበል! ይጠንክር» ብለን የምናነሳው በተቋሙ አንባቢን ፍለጋ የሚደረገው ጉዞ ነው። ወመዘክር ብሔራዊ ተብሎ የሚጠራና አገራዊ ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም እንደመሆኑ፤ ተጠርቶም ይሆን በተነሳሽነት የሚሠራው ሥራ የተለየ ምስጋናን የሚያስቸረው ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ተግባሩ አርአያነት ያለው በመሆኑ ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል።

የጉዞ መነሻ – ዓላማና ርዕይ

የወመዘክር የአንባቢን ፍለጋ ጉዞ የተጀመረው በ2006ዓ.ም ነው። «ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል» የሚል መሪ ሃሳብ ይዞ የሚካሄደው ይህ ጉዞ፤ መጻሕፍት አቅራቢዎችን፣ መጻሕፍትን፣ ደራሲዎችን፣ ጥናት አቅራቢዎችና የመገናኛ ብዙኅን ባለሙያዎችን ያሳትፋል። ተሰባስበውም በየክልል ከተሞች እየተንቀሳቀሱ ሰዎች ንባብን እንዲያዘወትሩ ብቻ ሳይሆን ስለ ንባብ እንዲያስቡ ለማድረግ አውደርዕዮች፣ የውይይት መድረኮችና የመጻሕፍት ልገሳ መርሃ ግብራትን ያካሂዳሉ።

 ጉዞ ምን ዓይነት ነው? ምን ተግባራትን ያካትታል? ምን ውጤት አስገኘ? የት የት ሄደ? ብለን እንጠይቃለን። ከዛ በፊት ግን፤ የትኛውም ጉዞ ዓላማና ርዕይ ሲኖረው ነውና መድረሻው የሚታወቀው፤ ተቋሙ ይህን ሥራ ለመሥራት እንዴት ተነሳ እንበል። የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሐፍት ኤጀንሲ የሕዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታዩ ለጥያቄዎቹ መልስ ሰጥተውናል።

ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ በዋናነት ጥንታዊ የጽሑፍ ሀብቶችን እና በየጊዜው የሚታተሙትን እያሰባሰበ ያደራጃል፤ ተንከባክቦና ጠብቆም ከትውልድ ትውልድ ያስተላልፋል። ይህ የተቋሙ መሪ ሃሳብም እንደሆነ ነው አቶ ሽመልስ የገለጹት። «ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሐፍት ያለፈውን፣ የአሁኑን እና መጪውን ትውልድ የሚያገናኝ ነው።» አሉ።

ይህ የትውልድ ትስስርና ግንኙነት በመረጃ ልውውጥ የሚፈጠር ነው። ለዚህ ቁልፍና ወሳኝ ሚና ያላቸው ደግሞ መዛግብትና መጻሕፍት ናቸው። እናም እነዚህን መዛግብትና መጻሐፍት ከተጠቃሚ ጋር ማገናኘት ያስፈልጋል ማለት ነው። አቶ ሽመልስ እንዳሉትም፤ በትውልድ መካከል በንባብ የተዋቀረ የመጻሕፍት ድልድይ ካልተሠራ በቀር ቅብብሉ ስለማይኖር፤ መረጃዎችን አንድ ቦታ ማከማቸት ብቻ ውጤታማ እንደማያደርግ በተቋሙ ታመነ።

ሌላው ለጉዞው ደጋፊ የሆነው ደግሞ የተቋሙ ርዕይ ነው። አቶ ሽመልስ እንዲህ አሉ፤ «አንዱ ርዕያችን በአፍሪካ ካሉ ታላላቅ አምስት አብያተ መዛግብት አንዱ መሆን ነው። እነርሱ እውቅ ሊሆኑ የቻሉት ደግሞ በክምችት ብዛት፣ በዘመነ አሠራራቸው፣ በአደረጃጀትና በተደራሽነት እንዲሁም በተጠቃሚ ብዛት ነው።»  እንግዲህ በአፍሪካ ተጠሪ የሆነ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት እንዲኖረን ለማስቻልም አንባቢን ፍለጋ መጓዙ ትክክል ሆኖ ይገኛል።

ከዚህ ሃሳብ አንድ ነጥብ ስንነጥቅ፤ ባለብዙ ታሪክና ቅርስ የሆነች አገር ኢትዮጵያ የመዛግብትና የመጻሕፍት ክምችቷ አንደኛ ሊሆን እንደሚገባ ግልጽ ነው። ከመሠረቱ በቅብብል ያልተሠራ ነገር ቢኖር እንጂ፤ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከኢትዮጵያ የላቀ «የእኛ» የሚሉት ቅርስ ይኖራቸዋል ብሎ መገመት ይከብዳል። ይሁንና አልሆነም፤ መዛግብት በብዛት የተጻፉበት የግዕዝ ቋንቋ እንኳ የተሰጠው ትኩረት ከቃል የዘለለ አይደለም። ይህ ይቆየንና ወደ ነገራችን እንመለስ።

ወመዘክር በዚህ ርዕይ መሰረት መጻሕፍትና መዛግብቱን የሚጠቀም ሰው ለማብዛትና ርዕዩን ለማሳካት አንድ እርምጃ ለመራመድ ይህን ጉዞ መርጧል። «ተወዳዳሪ ለመሆን እንደ አንድ መስፈርት የምንይዘው የተጠቃሚን ብዛት ሲሆን ተጠቃሚያችን አንባቢ ነው። በአሁኑ ጊዜ የአንባቢ ቁጥሩ ቢጨምርም በሚፈለገው ደረጃ አላደገም። ሰው እንዲያነብና መረጃውን እንዲጠቀም ማድረግ የእኛ ኃላፊነት ነው ብለን ወስደናል።» ይላሉ፤ አቶ ሽመልስ።

አንባቢ የት ተገኘ?

በዚህ መነሻነት ነው እንግዲህ ወመዘክር ወይም ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ጉዞውን የቀጠለው። በዚህም መሰረት ከ2006ዓ.ም ጀምሮ በጥቅሉ አሥራ ዘጠኝ የሚሆኑ መጻሕፍትና ንባብ ላይ ያተኮሩ መርሃ ግብራት በተለያዩ ከተሞች ተደርገዋል። አቶ ሽመልስ እንደነገሩንም በዚህ ጉዞ ውስጥ በእቅድ የሚያዙት የመጻሕፍት አውደርዕይ፣ የውይይት መድረኮች፣ የንባብ ክበባትን የማቋቋም እንቅስቃሴዎችና የመሳሰሉት ናቸው።

«በዓመት ሁለትና ሦስት እንዲሁም አራት ጉዞዎችን እናደርጋለን። የምንሠራውም እንደ ክልሎች የመቀበልና አብሮ የመሥራት ፈቃድ ነው። በቅንጅት ካልሆነ በቀር ለብቻ ውጤታማ አያደርግምና።» ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በዚህ መሰረት ሰላም ባለባቸውና መረጋጋት በሰፈነባቸው ከተሞች ጉዞው ተደርጓል። በፈቃዳቸውና በፍላጎታቸው፤ እንዲሁም በትብብር ለመሥራት ባሳዩት እሺታ፤ በአፋር፣ መቀሌ፣ ባህርዳር፣ ሐዋሳ፣ አርባምንጭ፣ አሶሳ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር፣ ጎንደር፣ ድሬዳዋ ጨምሮ በሌሎችም የተለያዩ ክልል ከተሞች ጉዞ ተካሂዷል።

እንደ ሀዋሳ፣ ጎንደር፣ ባህርዳርና መቀሌ ደግሞ በድጋሚ ጉዞው ከደረሰባቸው ከተሞች መካከል ይጠቀሳሉ። አቶ ሽመልስ እንዳሉት በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ እንዲሁም በጋምቤላ ከሰላምና መረጋጋት ጋር ተያይዞ ጉዞ ታጥፏል፤ አልተካሄደም። ወደፊት ተቋሙ ይህን ሥራ አጠናክሮ ሲቀጥልና የታሰበው ውጤት ከመጣ ግን ሁሉም ከተሞች የሚናፍቁት ዝግጅት መሆኑ አይቀሬ ነው።

ምን ተገኘ?

«የንባብ ባህላችን ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም እንደሚታየው አድጓል ለማለት አይቻልም።» ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ከመሃል ከተማ እየተራቀ በሄደ ቁጥር ነገሩ የባሰ እንደሚሆን ያነሳሉ። ተማሪዎችም በተለያየ ምክንያት ለመማሪያ አጋዥ ከሆኑት ውጪ ሌሎች መጻሕፍትን ሲያነቡ አይታይም። ይህ በጊዜው መሆን ያለበትን የትውልድና የታሪክ ቅብብል ያዘገየዋል። ታድያ ነገሩን ለማስተካከል የሚደረገው የወመዘክር ጉዞ አንዳች መፍትሄ እንደሚያመጣ የሚጠበቅ ነው።

በአገር ደረጃ ንባብ ከተነፈገው ትኩረት አንጻር በዚህ ሥራ በአንድ ጊዜ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት አስቸጋሪ እንደሚሆን አቶ ሽመልስ ይናገራሉ። «በተከታታይ የምንሠራውም ለዚህ ነው።» ሲሉ፤ ጥሩ ጅምር የታየባቸውና ጥያቄ የመጣባቸው ቦታዎች ላይ ደግሞ ጉዞው በተደጋጋሚ እንደሚደረግ ያነሳሉ።

ለዚህ ባህርዳርና መቀሌ ከተሞች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። በእነዚህ ከተሞች በነበሩ የንባብ ጉዞዎች የከተማው ሰው በትኩረት ተሳትፎ በማድረግና መጻሕፍትን በመሸመት፤ ቢቀርብለት ሊያነብ የሚችል ሕዝብ እንዳለ አሳይቷል። መጻሕፍት አቅራቢዎችም አስቀድሞ ከያዙት የጊዜ ገደብ አልፈውና መጻሕፍትን ከየመደብራቸው በድጋሚ አስልከው ከሳምንት በላይ አውደ ርዕይና የመጻሕፍት ሽያጭ አካሂደዋል።

የተቋሙ ዋና ዓላማ መጽሐፍ ሽያጩ ሳይሆን መጻሕፍትን የሚገዛ ማህበረሰብ መኖሩ ነው። ይህ ደግሞ «የሚያነብ ሰው አለ» የሚል ምልክት ሰጪ ነውና እንደ መልካም ውጤት ይታያል። በአንጻራዊም ቢሆን ሲጀመር የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውሱት አቶ ሽመልስ፤ ተጠርተው በግድ ይሄዱ የነበሩ መጻሕፍት አቅራቢዎች፤ «አትርሱን አስታውሱን!» ማለታቸውና ፍላጎት ማሳየታቸው ሌላው ተስፋ ሰጪ ምልክት ነው።

«ይሁንና እንደ አጠቃላይ ምን ለውጥ መጣ የሚለው ላይ ዳሰሳ መሥራት እንዳለበን አይተናል። ከዛም ውጤቱን አይተን ራሳችንንና አሠራራችንን ለመመልከት እንችላለን። ውጤቱም የበለጠ ጥሩ እንዲሆን የምናቅዳቸው ሌሎች ሥራዎች ይኖራሉ።» ብለዋል፤ የሕዝብ ግንኙነቱ አቶ ሽመልስ።

ወደፊት ምን ታሰበ?

መጻሕፍትን ይዞ በየከተማው መንቀሳቀስ፤ ደራስያን ልምዳቸውን ለተማሪዎች እንዲያካፍሉ ማድረግ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በማሳተፍ ተማሪውን ማነቃቃት፤ በጥቅሉ በምክንያት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር ነው። ሰው ምክንያታዊ የሚሆነው ሲያውቅ ስለሆነ፤ በተጓዳኝ ማወቅ ደግሞ ጽንሰ ሃሳብ በመሸምደድ ሳይሆን በመረዳት ነው። ይህም በንባብ ይዳብራል።

ዓመታዊና ወቅታዊ ንቅናቄዎች ለውጥን ለማምጣት ጊዜ ይወስድባቸዋል። የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሐፍት የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አቶ ተሾመ እንዳሉትም፤ ተቋሙ ሁሉም ቦታ እየተንቀሳቀሰ ይህን ሥራ ሠርቶ አይዘልቀውም። ክዋኔውን ተጠባቂና ተናፋቂ ማድረግ አንድ ጉዳይ ሆኖ፤ ለውጥ የሚያመጣው ሥራ ግን ክልሎችና የክልል ከተሞች እንዲሁም ትምህርት ቤቶች በየደረጃው ኃላፊነት ወስደው ሲሠሩበት ነው።

«ከጸደቁ አይቀር ይንጋለሉ» እንዲል፤ ወመዘክር እዚህ ላይ ክልሎችንና ከተሞችን ወክሎ አይሠራምና፤ ራሳቸውን ችለው እንዲሠሩ በማድረግ በኩል በክትትልና በድጋፍ እንዲገኝ ይጠበቃል። ከዚህ ባሻገር ግን አቶ ሽመልስ እንዳሉት፤ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ በጉዞው እንዲፈጠር የሚፈልገው መነቃቃትና የንባብ ፍላጎት፤ ብሎም ንቅናቄው እንዲቀጥል የሚያደርግ በክልልም የመንግሥት አካል መኖር አለበት። ለጊዜው ይህን ለመፍጠር ግን ከክልሎችና ከከተሞቻቸው ጋር የሚሠሩት በቅንጅት ነው።

«ጉዞ በምናደርግባቸው አካባቢዎች ባለሙያ አሰልጥነን፤ ክበባትን አደራጅተን መጻሕፍት የመለገሱን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን።» ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ቅንጣት የሚመስሉ ተስፋዎችን ወደ ለውጥ ለመቀየር የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ማደራጀት አስፈላጊነቱ አያጠራጥርም። እንደ ብሔራዊ ተቋም ትላልቅ የሆኑ ነገሮችን መሥራት እንዳለ ሆኖ ከታችም አቅም ፈጥሮ ማስቀጠል የቤቱ ኃላፊነት መሆኑን አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።

በዚህ እናብቃ! የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ አንባቢውንና ተጠቃሚውን ፍለጋ እየተንቀሳቀሰ ነው። ከሳምንት በፊት በነበሩት ቀናትም በጎንደር ከተማ ይኸው የንባብ ሳምንት በድምቀት ተካሂዷል። ቀጥሎም በቅርቡ ተመሳሳይ ጉዞ ወደ ጅማ እንደሚደረግ ታውቋል። አንባቢ የተገኘ እንደሆነ ስኬቱ ለወመዘክር ብቻ አይደለም፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ መረጃ ተላልፏል፤ እውቀት ተሻግሯል ማለትም ነውና፤ ከትላንት የበረታች፤ ከዛሬ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መንገዱ ጨርቅ ይሆናል። እናም ጉዞውን መልካም ያድርገው እንላለን። ሰላም!

አዲስ ዘመን የካቲት 17/2011

ሊድያ ተሰፋዬ