ለአሳሳቢው የትራፊክ አደጋ መፍትሄ

13

“ከዛሬ አምስት አመት በፊት  አንድ ጓደኛዬ ከሚስቱ ጋር ለጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር ተጉዞ ነበር። በጉዞ ላይ እያሉ የተሳፈሩበት የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ የትራፊክ አደጋ ያጋጥመውና የሁሉም መንገደኞች ህይወት አለፈ። በአደጋውም  ጓደኛዬ ከነሚስቱ ላይመለስ በዛው ወጥቶ ቀረ”  በማለት የአደጋውን አስከፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አቶ ደነቀው በሪሁን ያስታውሳሉ።

አደጋው በደረሰ ማግስት ቦታው ድረስ በመሄድ የተፈጠረውን የትራፊክ አደጋ በአይኔ አይቻለሁ። አደጋውም በጣም ልብ የሚነካ  ከመሆኑም በላይ  የብዙ ሰዎች ህይወት ያለፈበት፣ ህጻናት ያለአሳዳጊ፣ አዛውንቶች ያለ ጧሪና ቀባሪ የቀሩበት ሆኗል።  ይህንን አስከፊ አደጋ ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት የሚያስችል  ቴክኖሎጂ « ዳክቴክ ሶሻል አይሲቲ ሶሉሽን» ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ይዞ ብቅ ብሏል።

ማህበሩ ከተቋቋመ ስድስት ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን  የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ላይ  ትኩረት አድርጎ  የሚሰራ  ነው። ስራዎቹንም የሚያከናውነው  ጨረታ በማወዳደር ሳይሆን የመንግስት የአሰራር ክፍተትና የማህበረሰቡን ችግሮች በመለየት ለመሙላት የሚያስችል ፕሮግራሞችን ያበለፅጋል። ማህበሩም በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ሰባት አዳዲስ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን በፈጠራ ባለቤትነት ማስመዝገብም ችሏል።

«ዳክቴክ ሶሻል አይሲቲ ሶሉሽን» ካበለጸጋቸው የኮምፒውተር ፕሮግራሞች መካከል በሀገራችን ብሎም በአፍሪካ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣውን፤ በየቀኑ ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት እየቀጠፈ የሚገኝውን የመኪና አደጋ ለመቆጣጠር የሚያስችል ፕሮግራም ይገኝበታል።

ያበለፀገው ፕሮግራምም አሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች የሚፈፅሙትን ጥፋት ሪከርድ በማድረግ በሞባይል አጭር የጽሁፍ መልዕክት ለደንብ አስከባሪዎች የሚያቀብል ሲሆን  ለሀገራችን የትራፊክ ህግና ደንብ ለማክበር፣ ሕይወትና ንብረትን ለመጠበቅ ያለው ጠቀሜታ  ምን እንደሚመስል ከማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅና የፕሮግራሙ ሀሳብ አመንጭ አቶ ደነቀው በሪሁን ጋር ቆይታ አድርገናል።

እንደ አቶ ደነቀው ገለጻ፤ ቀደም ሲል በሀገራችን የነበረው የትራፊክ ህግና ደንብ አንድ አሽከርካሪ ጥፋት ሲያጠፋ ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ቅጣት ይቀጣ ነበር። ነገር ግን ይህ የትራፊክ አደጋውን ከቀን ወደ ቀን እንዲባባስ ከማድረግ አላዳነም።   የትራፊክ ህጉን በመጣስ ተደጋጋሚ ቅጣት የተቀጡ አሽከርካሪዎችም ደግመው እዛው ጥፋት ሲሰሩ እንደሚገኙ   በተለያዩ  ጊዜያት በተጠኑ  ጥናቶች  ማወቅ መቻሉንም  ይገልጻሉ፤ እነዚህ አሽከርካሪዎች  ምናልባትም ብሬን ይጭነቀው የሚል ኢ-ሰብአዊ አመለካከት ያላቸውና ለሰው ልጅ ህይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምንም ደንታ የሌላቸው ናቸው በማለት ይገልጿቸዋል።

በሌላ በኩል እንደ አደጉት ሀገራት የጥፋት ሪከርዳቸው ሶስትና ከዛ በላይ የደረሰ አሽከርካሪዎች በራሳቸውና በንብረት እንዲሁም  በተሳፈሪዎች ላይ አደጋ ከመፍጠራቸው በፊት ከሶስት ወር እስከ ሁለት አመት የሚደርስ እገዳ ሊያስከትል የሚችል አዲስ የትራፊክ ህግና ደንብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2003 ዓ.ም መፅደቁ ይታወሳል።

ሆኖም ማስፈጸሚያ መሳሪያዎችና  ህጉን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል ነበራዊ ሁኔታው ሳይኖር ህጎች የሚጸድቁ በመሆኑ፤  መሬት ወርዶ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የሚያስችል የአሰራር ዘዴም ሆነ ቴክኖሎጂ የለም። የመንጃ ፍቃድ ህጉ ሲወጣም  ህጉን ለማስከበር የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) አገልግሎት በየቦታው ለመግጠም ቢታሰብም ወጭው በጣም ከፍተኛ በመሆኑና መሰረተ ልማቶች  ያልተሟሉ በመሆናቸው ተግባራዊ ስራ አለመሰራቱን  ጠቁመዋል።

በመንጃ ፍቃድ አሰጣጡና  በትራፊክ ህግና ደንቡ ላይ ጥናትና ምርመር ያደረጉት የማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅ፤ አዲሱ የትራፊክ ህግና ደንብ የተንቀሳቃሽ ስልክን በመጠቀም በአጭር የጹሁፍ መልዕክት በትንሽ ወጭና መሰረተ ልማት ባልተሟሉበት ቦታዎች ሁሉ ህግና ደንቡን ማስከበር የሚያስችል ፕሮግራም መሆኑን ይናገራሉ አቶ ደነቀው።  

በአደጉ ሀገራት የጥፋት ሪከርድ የሚመዘገበው በመኪና ሰሌዳው ነው። በኢትዮጵያ ደግሞ የጥፋት ሪከርዶች የሚመዘገቡት በአሽከርካሪው የመንጃ ፈቃድ ቁጥር ነው። በተለያዩ ቦታዎች መንጃ ፍቃድ የሚሰጥ በመሆኑና ቁጥሮችን በአግባቡ አደራጅቶ የሚይዝ ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ  የአንድ ሰው የመንጃ ፈቃድ ቁጥር 151 ጊዜ ተደጋግሞ ይመዘገባል። ይህ  ማለት ደግሞ  151 አሽከርካሪዎች አንድ አይነት የመንጃ ፍቃድ ቁጥር አላቸው እንደማለት ነው።

የፕሮግራሙ አንዱ ጠቀሜታ  በአንድ አጭር የጽሁፍ መላኪያ መስመር ( ሰርቨር)  በሀገሪቱ የሚገኝውን የመንጃ ፍቃድ ቁጥር አደራጅቶ በመያዝ  ቁጥሮቹ እንዳይመሳሰሉ አድርገናል። የአሽከረካሪና የተሽከርካሪ መረጃዎችን መዝግቦ መያዝም ያስችላል።

እንዲሁም አንድ አሽከርካሪ ጥፋት ካጠፋ ደንብ አስከባሪው የጥፋቱን  አይነትና የቅጣቱን ልክ፣ ምን ያክል የጥፋት  ነጥብ እንደሚያስይዝና  አሽከርካሪው ከዚህ ቀደም ያለበትን የጥፋት ሪከርድ  በቀላሉ  በማወቅ ለመቅጣት ያስችለዋል። አሽከርካሪው መቼና በማን የት እንደተቀጣ  ድረ ገጽ ላይ ስለሚቀመጥ ማንኛውም ሰው መረጃውን ማግኘት ይችላል። በተጨማሪም  ባለሀብቶችና ሌሎችም  የሚቀጥሩት አሽከርካሪ  መንጃ ፍቃድ ምን ያህል ህጋዊ እንደሆነም  በቀላሉ   በስልካቸው  ተጠቅመው ማረጋገጥ ይችላሉ።

በሌላ በኩል አሽከርካሪው የትራፊኩን የሚስጥር ቁጥር ወደ አጭር የጽሁፍ መልክት መላኪያ አድራሻ በመላክ   የስራ አድራሻውን፣ የአጠፋው ጥፋት ምን ያክል ቅጣት እንደሚያስቀጣው፣ ምን ያክል የጥፋት ሪከርድ እንደሚያስመዘግብበት ማወቅ ያስችለዋል። አሽከርካሪው ያለበትን የጥፋት ሪከርድ አውቆ በቀጣይ መንጃ ፍቃዱ እንዳይታገድበት ጥንቃቄ ለመድረግ የሚያስችልም መረጃ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል።

አሽከርካሪው በቅጣቱ ቅሬታ ካለው ወደ ሚመለከተው አካል ሄዶ በማመልከት ችግሩን የሚፈታበት  አሰራር አለ። ቅሬታውም ከተስተካከለ ወዲያውኑ በማን እንደተስተካከለና በየትኛው የበላይ አካል እንደታየ ማየትም ያስችላል።

በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ የደረሰን የትራፊክ አደጋ መንስኤዎቹን  አይነታቸውንና መቼ እንደተከሰቱ  መዝግቦ መያዝ የሚችል ሲሆን  በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ያስከተለውን የጉዳት መጠንና የአደጋ ደረጃ ምን እንደሚመስል ለማወቅ ያስችላል።

በሌላ በኩልም የስራ ኃላፊዎች  የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም በየትኛው  ቦታና ሰዓት ስንት ሰው እንደተቀጣና እንደታገደ ምን አይነት የትራፊክ አደጋ እንደደረሰ ማወቅ ያስችላል። የተለያዩ የትራፊክ አደጋ ሪከርዶችን ለመመዝገብና ሪፖርቶችን ለመስራትም ምቹ ነው።

ጥፋት ሰርቶ የሚያመልጥ አሽከርካሪ ካለ ወዲያውኑ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ለሁሉም ትራፊክ ፓሊስ መረጃው እንዲደርስ በማድረግ ወንጀለኛውን በቀላሉ ለመያዝና  በአጠቃላይ በአጭር የጽሁፍ መልእክት የትራፊክ ህግና ደንብን ለማስከበር የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑንም ይናገራሉ።

የቀድሞው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአሁኑ ኢኖቬሽንና ቴክኖጂ ሚኒስቴር ለፈጠራ ስራው 50 ሺ ብር፣ የዋንጫና ሜዳሊያ ሽልማት አበርክቷል፤ ለፈጠራ ስራው እውቅና መሰጠቱ ሌሎች ስራዎችን ለመስራት ጉልበት እንደሆናቸው አቶ ደነቀው ገልጸዋል። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ ክልሎችም የፈጠራ ስራውን አምነውበት ቴክኖሎጂውን ተቀብለው እየተጠቀሙበት ነው።

”የክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮቹ የሚሰጡ መንጃ ፍቃዶች  የራሳቸው መለያ ኮድ እንዲኖራቸው አድርገናል። በመቀጠል እያንዳንዱን ትራፊክና ደንብ አስከባሪ ስልክ ቁጥር በመመዝገብ የሚስጥር ቁጥር በመስጠት የራሳቸው የሆነ አድራሻ እንዲኖራቸው ከማድረግም በላይ  በኢትዮ-ቴሌ ኮም አማካኝነት በድሮው 8584 በአሁኑ 8556  አጭር የጽሁፍ መልዕክት ማስተላለፊያ አድራሻ  የማውጣት ተግባር አከናውነናል» ሲሉ አቶ ደነቀው አብራርተዋል።

እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላ ትራፊክ ፖሊስም ሆነ ደንብ አስከባሪ ስልኩን በመጠቀም ያለምንም ውጣ ውረድ  ህግና ደንብ እንዲያስከብር ለማድረገም  የቋንቋ ችግር እንዳያግድ  በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎቱ ይሰጣል።   በተጨማሪም በሞባይል አፕሊኬሽን ሁሉም  ሰው የትራፊክ ህግና ደንቡን እንዲያውቅ በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ህጎች እንዲጫኑ  በማድረግ ፕሮግራሙን አዘጋጅተን ለደንብ አስከባሪዎች ተሰጥቷል፤ በቀጣይ ለማህበረሰቡ ለማድረስ በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ቴክኖሎጂው ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ የትራፊክ ህግና ደንቡ እንዲከበር ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ በአማራና ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግስት  ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በሌሎችም ክልሎች ወደ ስራ ለማስገባት በሂደት ላይ እንገኛለን  ብለዋል።                    

የኔትዎርክና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የኮምፒውተር ፕሮግራሙን ለማበልጸግ ተግዳሮት እንደሆነባቸው የገለጹት ምክትል ስራ አስኪያጁ፤ “ፕሮግራሙን አበልጽገን ወደ ስራ እንዲገባ ካደረግንበት ጊዜ ጀምሮ በተግባር ያሉትን ክፍተቶች በማየትና ከዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ጋር እኩል እንዲራመድ  በማድረግ ለማሻሻል መቻሉን ገልጸው  ለአብነትም የድሮው የሞባይል አፕሊኬሽን ህጋዊ ያልሆነ መንጃ ፍቃድ የሚለይበት በሌላ ፕሮግራም ነበር።

ይህንን በአንድ ፕሮግራም ሁሉንም መረጃዎች እንዲሰጥ መደረጉንና  እንዲሁም የሞባይል አፕሊኬሽኑ መረጃ እንደ ክልል እንዲሰጥ ነበር የተደረገው። አሁን ላይ እንደሀገር አቀፍ መረጃ እንዲሰጥ ማድረግ ችለናል።

በአጠቃላይ ህጉ ቢሻሻል፣ እርከኖች ቢጨመሩ፣ የቅጣት መጠኑ ቢጨምር ቢቀንስ፣ ነጥቦች ቢጨምሩ ቢቀንሱ በሚፈለገው መልኩ ለማሻሻልና አዳዲስ ሀሳቦችን መጨመር እንዲያስችል አድርገን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር  አስተሳስረን መሰራቱን አብራርተዋል።

የትራፊክ ህግና ደንብ ዋና ትኩረት አደጋ እንዲቀንስና የጥፋት ሪከርዶች መመዝገብ ቢሆንም አንዳንድ ደንብ አስከባሪዎችና ትራፊኮች ከፍተኛ የብር መጠን መቅጣት መፈለጋቸው፣ አሽከርካሪዎች ደግሞ ሪከርድ እንዲያዝባቸው ስለማይፈልጉ ቴክኖሎጂው ተግባራዊ እንዳይሆን መፈለግ፣ ስራ አጥነትን ያስፋፋል የሚል የተዛባ አመለካከት  መኖር እንዲሁም በየክልሉ ያለው የትራፊክ ህግና ደንብ መለያየት ቴክኖሎጂው እንደሀገር ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻለም።

መንገድ ትራንስፖርት በኢንተርኔት መረብ የትራፊክ ህግና ደንቡን ለመተግበር ቢያስብም ሰፊ መሰረተ ልማት የሚፈልግ በመሆኑ እስካሁን ወደ ስራ አልገባም። ይህን ያህል መፍትሄ መስጠት መቻሉ እየታወቀ የመንገድ ትራንስፖርት አመራሮች ቴክኖሎጂውን ወደ መሬት ወርዶ እንዲሰራበት ቁርጠኛ አቋም የላቸውም በማለት ይናገራሉ።

የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን ሰርተን የተጠበቀውን አገልግሎት እንዳይሰጥ ካደረጉት ነገሮች ሌላው የቴሌ ችግር ነው።  በመብራት አቅርቦት መቆራረጥ የኔትወርክ አገልግሎት ይቋረጣል። ስለዚህ ለረጅም ጊዜ ኔትወርኩ በሚቆራረጥበት ጊዜ ሀላፊነቱን ወስዶ ተጠያቂነት ቢኖር በጣም ጥሩ ነው። በመሆኑም በተገቢው መንገድ ተቆጣጣሪዎች ስራቸውን ለመስራት ተቸግረዋል። የፈጠራ ስራዎቻችን ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲያጭር  አድርጓል።

ስልጠና ስንሰጥ ቴክኖሎጂን የመጠቀምና የመፍራት፣ ቴክኖሎጂው ከስራ ያስወጣናል ብሎ በማሰብ ያለመጠቀም ችግር፣ በመንግስት ቢሮ ያሉ  ሀላፊዎችና  ሰራተኞች ቴክኖሎጂው ተግባራዊ እንዲሆን ያለመፈለግ ለተግባራዊነቱ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነባቸው አቶ ደነቀው ተናግረዋል።

በሀገራችን ቴክኖሎጂ እንዲያድግና እንዲበለጽግ መንግስት ችግሮችን መፍታት የሚያስችለው ሶፍትዌሮች ወደ ተግባር ለመቀየር  የፋይናንስ  ችግር፣  ህጉ በራሱ ትክክል አይደለም። ሶፍትዌርን እንደማንኛውም ቁሳቁስ ለመሸጥና ለመግዛት ያስቸግራል። መንግስት ያለውን አሰራር ማሻሻል አለበት።  የትራፊክ ህግና ደንብ ማክበር ለራስ በመሆኑ መንግስት ስልጠናውን እንዲያገኙ በማድረግ ለቴክኖሎጂው ያላቸው አመለካከት እንዲቀየር ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።

ሰው ህግ የሚያከብረው ትራፊክና ህግ አስከባሪዎችን ሲመለከት ብቻ ነው። መንግስት ጂፒኤስ አቅጣጫ አመልካቾችን በየመኪኖች ላይ ለመግጠም የፌዴራል ትራንስፖርት እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ በጋራ በመተባበር የትራፊክን ህግ የሚያስከብር ሶፍትዌር አብረን በመስራት አጭር የጽሁፍ መልክትን ከዚህ ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ሊሰሩ እንደሆን ገልጸዋል። እንዲሁም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ ቆጣሪ አንባቢዎች በሞባይል ማንበብ እንዲችሉ የሚያስችል ፕሮግራም ለመስራት ጨረታ አሸንፈው ፕሮግራሙን እያበለፀጉ መሆናቸውንም ጠቁመውናል። እንደ ሀገር ይህ ቴክኖሎጂ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ ሆኖ ቢሰራ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ያስችላል።

አዲስ ዘመን የካቲት22/2011

በሶሎሞን በየነ