የኢኮኖሚው ሪፎርም ቀጣይ የቤት ሥራዎች

23

በእድገትነት ብቻ ሳይሆን በፈጣንና ተከታታይ ዕድገቱ የሚገለጸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፤ በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የቆየውን የመልካም አስተዳደር ችግርና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ተከትሎ በመጣው የፖለቲካ ለውጥና ሪፎርምም ፍጥነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል። እናም እንደ ፖለቲካው ሁሉ ኢኮኖሚውም ትኩረት በማግኘት የተጀመሩ መልካም የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራት በቀጣይነት ሊከናወኑና ሌሎች ተደማሪ የቤት ሥራዎችም ሊሰሩ እንደሚገባ ምሑራን ይመክራሉ።

የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም አብረው እንጂ ተነጣጥለው የሚሄዱ ነገሮች አለመሆናቸውን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ፤ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ከሌለበት ፖለቲካው ሁሉንም ነገር ሊሰራ እንደማይችል ያነሳሉ። ይሄን ታሳቢ በማድረግም ለውጡን ተከትሎ እየተከናወነ ካለው የፖለቲካ ሪፎርም በተጓዳኝ በኢኮኖሚው በኩልም ብዙ ነገር እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ አሁንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደ አጠቃላይም ሆነ በተለይም ከጂ.ዲ.ፒና ሌሎች ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አንጻር ሲታይ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ያለ ነው።

ይህን ከማስቀጠል አኳያም መንግሥት የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩበትም ችግሮቹን ለመቅረፍ ሙከራ እያደረገ ነው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ ከዓለም ባንክ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር መገኘቱ አንዱ ሲሆን፣ የተጀመሩ የልማት መሰረተ ልማቶች ሊያልቁ የሚችሉበትን መንገድ የማፈላለግ ሥራም እየተከናወነ ነው። በተመሳሳይ የግል ዘርፉ መንቀሳቀስ እንዳይችል አድርጎት የቆየውን በውጭ ምንዛሪም ሆነ በአ ገር ውስጥ ገንዘብ እጥረት ችግር ከማቃለል አኳያም እየተሰራ ይገኛል። እነዚህን ባለሃብቶች ከማበረታታት አኳያም በአንድ አገር የቢዝነስ ሥራ ለማስራት ያለውን አመቺነት አስመልክቶ በዓለም ባንክ የቢዝነስ ኢንዴክስ መሰረት ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደመሆኗ ይሄን ለማሻሻል ተብሎ ብዙ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው።

እነዚህ ተግባራት ደግሞ መንግሥት የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ለማሳለጥ የሚቻለውን ያህል እየጣረ ለመሆኑ አመላካች ናቸው። በዶክተር ቆስጠንጢኖስ ሀሳብ የሚስማሙት የምጣኔ ሀብት ባለሙያና የፌርፋክስ አፍሪካ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ ለማቋቋም፣ለማካሄድና ትርፋማ ለመሆን ምን ያክል ከባድ/ ቀላል ነው ለሚለው ዓለም ባንክ በየዓመቱ የሚያወጣውን ደረጃ መነሻ በማድረግ የዘርፉን ማነቆ ለመፍታት አስር የሚሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተከናወነ ያለው ወሳኝ የእርምጃ ተግባር በኢኮኖሚው ዘርፍ የተሻለ ሪፎርም ለማምጣት የሚያስችል ወሳኝ ተግባር ተደርጎ መወሰድ የሚገባው ነው።

በዚህ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደ አንኳር የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራ መወሰዱ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቱ በኢትዮጵያ ለሚኖራቸው የኢንቨስትመንት ሥራ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙና ስኬታማ ሥራ እንዲያከናውኑ የሚያ ስችል ነው። ይህ ደግሞ የግል ዘርፉና ባለሃብቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተገንዝቦ መስራት መጀመሩንና ባለሃብቱንም ከቃል ባለፈ በተግባር የመጋበዝ ጅማሮ ተደርጎ የሚወሰድ፤ ሁሉን አቀፍ የተጠናከረ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ተፈላጊነትን የሚናገርም ጠንካራ መልዕክት ነው። እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ፤ ተቋማትን ፕራይ ቬታይዝ ለማድረግ የተወሰደው እርምጃም በጉልህ የሚጠቀስ ሌላ የኢኮኖሚው ሪፎርም አካል ሲሆን፤ ኢትዮ ቴሌኮም፣ መብራት ኃይልና ሌሎችም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ ትልልቅ ድርጅቶች በከፊል ፕራይቬታይዝ እንዲደረጉ መወሰኑ ለኢኮኖሚው የተሻለ ለውጥ እንዲያመጡ ያስችላል።

 ትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ኩባንያዎችም መጥተው እንዲሳተፉ ዕድል ይሰጣል። የፋይናንስ አቅምን ለማጎልበት ያግዛል፤ የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነትንም ይፈጥራል። ከዚህ ባለፈ የግል ዘርፉ እየተስፋፋ በሚሄድበት ጊዜ ባለሃብቱ የኢንቨስትመንት ካፒታል ይፈልጋል። ከዚህ አኳያ ደግሞ ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የአክሲዮንና የካፒታል ገበያ ይኖራል መባሉም ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ከሳሀራ በታች ካሉ አገራት ሦስተኛው ጠናካራ ኢኮኖሚ መሆኑ ደግሞ በአገሪቱ በየጊዜው የኢኮኖሚ ለውጦች መደረግ እንዳለባቸው አመላካች ስለሆነ፤ ባለፉት አስር ወራት ውስጥ በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራዎች ወቅታዊና ጊዜውን ጠብቀው የመጡ ናቸው።

 ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው እንደ ሚሉት፤ ከላይ የተጠቀሱ መልካም የሪፎርም ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው ኢኮኖሚውን ለማሻሻል እና ያለውን ውጥረት ለማርገብ በትኩረት ሊሰራቸው የሚገቡ ተግባራት አሉ። ከእነዚህ መካከል አንደኛው፣ የውጭ ምንዛሪውንም ሆነ የካፒታል እጥረቱን ችግር መፍታት መቻል ነው። ለምሳሌ፣ በተለያየ መልኩ (በውጭ አገር ካሉ ኢትዮጵያውያን፣ በእርዳታና ብድር እንዲሁም ከኤክስፖርት ገበያ) ወደአገር ውስጥ የሚገባው ገንዘብ አንዱ የካፒታል ችግር መፍቻ እንደመሆኑ መንግሥት ይሄን ለማሻሻል መስራት አለበት። አገሪቱም የፋይናንስ ሪፎርም ያስፈልጋታል። ይህ ሪፎርም ደግሞ ዝም ብሎ የሚሆን ሳይሆን ሰፊ ውይይት ተደርጎበት፣ ልምድ ተወስዶና እን ዴት ቢሆን አዋጪ እንደሚሆን ተመዝኖ መሆን ይኖርበታል። በዚህ ላይ ሊተገበር የወሰነውን የፕራይ ቬታይዜሽን ጉዞ በቃል የተባለውን ወደተግባር ለመቀየር በትኩረት መስራት ይገባል። ይህ ማለት ግን እነዚህ የፋይናንስም ሆኑ ቴሎኮምን የመሳሰሉ ተቋማት ዝም ብለው ሊበራላይዝ ይሁኑ፤ ዝም ተብሎም ይሸጡ ማለት አይደለም። ይሄን ተግባር የሚከታተልና የሚቆጣጠር የራሱ የሆነ ሬጉላቶሪ አካል ያስፈልጋል። እነዚህ ተቋማት በዚህ መልኩ በአክሲዮን ሲሸጡ ደግሞ ገዢው ድርጅት የግድ አገር ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ሳይጠበቅበት ባለበት ቦታ ሆኖ እንዲገዛና ገንዘቡ እንዲገኝ የሚያስችል ነው። ይሄም ተቋማቱ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የመሰረተ ልማት መዋጮ ለማምጣት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ለማሳደግ የሚጠቀሙበትን ዕድል ይፈጥራል። በተመሳሳይ የወጭ ምንዛሪ እጥረቱ አባባሽ የሆነውን የወጪና ገቢ ምርቶችን ሚዛን አለመጣጣም ሂደትን ማስተካከልና ሚዛኑን ማስጠበቅ ተገቢ ይሆናል። እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ ደግሞ፤ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ባሻገር የፋይናንስ ሴክተሩ በተለይም የባንክ ዘርፉ ሪፎርም ይፈልጋል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ 16 ትንንሽ የግል ባንኮች አሉ። እነዚህ ቁጥራቸው ብዙ ቢሆንም፤ አቅማቸው ግን በጣም ትንሽ ስለሆነ በአገሪቱ እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ መደገፍ አይችሉም። እናም 16ቱን ባንኮች በፍላጎት ላይ በተመሰረተ ማዋሀድ ተለቅ ወዳሉ አራትና አምስት የግል ባንኮች ማምጣት እንደ ዓላማ መያዝ አለበት።

በዚህ መልኩ ተለቅ ሲሉ ያላቸውም ንብረት ከፍ ስለሚል ሪስክ ለመውሰድና የግል ዘርፉን ለመደገፍ ፈቃደኞች ይሆናሉ። አሁን ግን ትንንሾች ናቸው፤ ከንግድ ባንክ በስተቀርም ሌሎቹ ትልልቅ የሚባሉት ሦስትና አራቱ እንኳን በዓለም ደረጃ ቀርቶ በአፍሪካ ደረጃ ካሉ ባንኮች አንጻር ሲታዩ በጣም ትንሽ የሚባሉ ናቸው። እነዚህ ባንኮች በ25 ዓመት ውስጥ ማመንጨት የቻሉት ካፒታል 30 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። እናም ከብዛት ይልቅ አቅም ላይ በማተኮር እያደገ የመጣውን የአገር ኢኮኖሚ መሸከምና መደገፍ በሚያስችላቸው መልኩ ማደራጀት፤ ከኮላተራል የብድር ስርዓት እንዲላቀቁ ማስቻልና ሪስክ መውሰድንም እንዲለማመዱ ማድረግ ይገባል። ብሔራዊ ባንክም በዚህ ላይ እንዲደግፋቸው መስራት ያስፈልጋል።

 እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ፤ የፋይናንስ አስ ተዳደሩም ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋራ አብሮ መራመድ ይኖርበታል። ለዚህም ዓለም አቀፍ ልምዶችን እየቀሰሙና አሰራሩን እያዘመኑ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም መሄድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም እ.አ.አ በ2000 ስምንት ቢሊዮን ዶላር የነበረን የኢኮኖሚ ጂ.ዲ.ፒ. ዛሬ ላይ ከ80 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሶም ያኔ በነበሩና ምናልባትም ጥቂት ማሻሻያ የተደረገባቸው መመሪያዎችና አሰራሮች አሁን ያገለግላሉ ለማለት ያስቸግራል። የውጭ ምንዛሪ አሰጣጡም ሊፈተሽና ሊታረም ይገባዋል። ለምሳሌ፣ 10 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የቤት መኪና ለማስገባት ኤል.ሲ እየተከፈተ፤ በአንጻሩ መድኃኒት አምጪው ይቸ ገራል። እናም በደካማው ኤክስፖርትም ሆነ በሌላ መንገድ የሚገኝን የውጭ ምንዛሪ በሚረባውም በማይረባውም ኢንፖርት መልሶ የሚወጣ ከሆነ ጥቅም አይኖረውም። በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉና የአገር ውስጥ ገበያውን ፍላጎት ከማሟላት አልፈው ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚችሉ ምርቶችን ከውጭ ማስገባትም ከብክነት ውጪ ጥቅም ስለሌለው እነዚህን ተግባራት የማያበረታቱ፤ በአንጻሩ የአገር ውስጥ ምርቶችን የሚያበረታቱ አሰራርና ፖሊሲዎችን መዘርጋት ይገባል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011

በወንድወሰን ሽመልስ