የአዋጁ ለውጥና ቀጣይ ስጋቶች

25

በአገሪቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ወጥቶ የነበረው ‹‹የፀረሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001›› ክፍተቶች እንደነበሩበት ሲተች እንደነበር ይታወሳል። ዋነኛ መነሻ ተደርጎ ሲነሳ የነበረውም በአተገባበሩ ሂደት የዜጎች መብትና ነፃነት ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ነው። ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ድንጋጌዎች የተጎናፀፏቸውን መብቶችና ነፃነቶች ይበልጥ ለማስጠበቅ በሚያስችል ሕግ መተካት እንዳለበት በመታመኑም አዋጁን ለማሻሻል ሲሰራ ቆይቷል። ይህን ተከትሎ ስድስት ክፍሎችና 53 አንቀፆችን የያዘ ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ይሄም ቀድሞ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚረዳ ታምኖበታል። ይሁን እንጂ በትኩረት ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ይነሳል።

የቀድሞው

የፖለቲካ ጦማሪና ተንታኝ እንዲሁም በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር ስዩም ተሾመ፤ የቀድሞው አዋጅ የተለየ አቋም እና አስተ ሳሰብ የሚያራምዱ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ግለሰ ቦችና ጋዜጠኞችን የሚያሸብር እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም አዋጁ አሸባሪ ነበር ሲሉ ይተቹታል። በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የማሸበርና ፍርሃት የመፍጠር ዓላማ ነበረው። መንግሥትም ይህን ተጠቅሞ ሕዝብን ሲያሸብር በመቆየቱም የፈጠረው የፍርሃት፣ የጭንቀትና የስጋት ስሜ ት አለ። ይሄም ሕጎቹ በሚፈለገው ደረጃ ሳይብላሉ የመውጣታቸው ውጤት ሲሆን፤ ሲወጡም ከዚህ በፊት ምን ነበረ፣ በሚል መነሻ እንጂ በመርህና በነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሰረቱ አለመሆናቸውም አተገባበር ላይ ክፍተትን ፈጥሯል።

የአቶ ስዩምን ሃሳብ የሚጋሩት ጠበቃና የሕግ አማካሪ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተደረገ ባለው የሕግ ማሻሻያ ሂደት የፀረ ሽብር ሕጉን የማሻሻያ ሃሳብ እንዲያቀርብ የተሰየመው የሥራ ቡድን አስተባባሪ አቶ አምሃ መኮንን በበኩላቸው፤ የቀድ ሞው አዋጅ መጀመሪያ የወጣበት ዓላማና በኋላም በአተገባበር ላይ ሽብርተኝነት መዋጋት በሚል ሰበብ ተቃውሞን ለማፈንና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማጥበብ እንዲያግዝ ተደርጎ የወጣ እንደሆነ ይገልጻሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ሕጉ ሽብርተኝነትን መቆጣጠር በሚል እሳቤ ብቻ የተቀረጸ ነው። በዛው መጠን በቁጥጥር ሥር የዋሉና የተጠረጠሩ ግለሰቦች መብቶች አለአግባብ እንዳይጣሱ ምንም ዓይነት ጥበቃ የሚያደርግ አንቀጽ አልተካተቱበትም።

እንደ አቶ አምሃ ገለጻ፤ አዋጁ ለደህንነት ተቋሙ ያልተገባና ከፍተኛ ስልጣንንም ያጎ ናፀፈ እንደነበር አቶ አምሃ ያስታውሳሉ። የሰዎችን የስልክና በተለያዩ መረጃ መረቦች የሚደረግ ንግግርና ግንኙነቶችን የመጥለፍና ክትትል የማድረግ ስልጣንን ይሰጥ ነበር። ቅጣትን በተመለከተም አሰቃቂ የሚባል ቅጣት ይጥል ነበር። በዚህም ለጥቃቅን የወንጀል ተሳትፎ ሁሉ እስከ ዕድሜ ልክና ሞት የሚደርስ ቅጣት ሲያሳርፍ ነበር። አዋጁን በማስፈፀም ሂደትም አስፈፃሚ አካል ጥፋት ፈጽመው ቢገኙ የሚጠየቁበትን ሁኔታም ሆነ ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው ሊካሱ ስለሚችሉበት ሁኔታ አያስቀምጥም።

አዲሱ

የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ከመጀመሪያው አስፈላጊ እንዳልሆነ ነው አቶ ስዩም የሚናገሩት። የሽብር ወንጀል በመደበኛ የሕግ አግባብ ሊዳኝ ቢችልም ሕግ ተብሎ ከወጣ ግን ሊስተካከሉ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ። በአሁኑ ወቅት የተደ ረገው ማሻሻያና ለውጥም መሠረታዊ መሆኑ ንም ይናገራሉ። አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከቀድሞው ይልቅ ከይዘቱ ጀምሮ ዓላማው ሽብርን መከላከል ነው። በዚህም በሽብር የተሳተፉ ሰዎችን የመቅጣትና የማስተካከል እንዲሁም ደግሞ የበፊቱ አዋጅ የፈጠረውን መጥፎ አመለካከት ለመለወጥ ታስቦ የወጣ ቢሆንም ተፅዕኖዎችም ይስተዋሉበታል። ቀድሞ የነበ ረው አዋጅ የፈጠረው የፍርሃትና ስጋት እንዳ ይደገም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት መሆኑም ይታያል።

አቶ ስዩም፤ ችግሩ ዳግም እንዳይፈጠር ፖለቲካ ድርጅቶች በሽብርተኝነት የሚፈረጁበትን አግባብ ለማስቀረት ከመጠንቀቁና የነበረውን እሳቤ ለማስወገድ ባዳረገው ጥረት ለጦርነት ዕውቅና የሰጠ ረቂቅ በማለት በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደ ክፍተት የተመለከቱትን ጉዳይ ያብራራሉ። አምስተኛው አንቀጽ ላይ በጄኔቫ ኮንቬንሽን መሠረት በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መልኩ ከመንግሥት ጋር የሚካሄዱ ጦርነቶች የሽብር ተግባር ተደርገው እንደማይወሰዱ ያስቀ ምጣል። በአዲሱ ‹‹የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ በአንቀጽ አምስት ልዩ ሁኔታ በሚል በሽብር የማይያዙ ተግባራት በዝርዝር ሰፍረዋል። በዚህም ከተቀመጡት ሦስት ነጥቦች ውስጥ ‹‹በጄኔቫ ኮንቬንሽንና ፕሮቶኮሎቹ መሠረት በመደበኛ ወይም መደበኛ ባልሆነ መልኩ ከመንግሥት ጋር ጦርነት ማካሄድ የሽብር ድርጊት ሆኖ አይቆጠርም›› የሚለው ይገኝበታል።

የጄኔቫ ኮንቬንሽን በጦርነት ውስጥ ከለላ ለሚሰጣቸው ምርኮኞች፣ ለሴቶችና ለህፃናት በሚል የሚያስቀምጥ የጦርነት ሕግ መሆኑን የሚያስረዱት መምህሩ፤ የቀድሞ አዋጅ መንግሥት ለራሱ ዓላማ አንሻፎ ተጠቀመበት እንጂ እሳቤው የመጣው ከአሜሪካኖች መሆ ኑንም ይገልፃሉ። አሜሪካውያኑ የሽብርተኝነት ተግባር በኮንቬንሽኑ መታየት የለበትም የሚል ጥያቄ ያነሱት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የያዟቸውንና የጠረጠሯቸውን አሸባሪዎች በዓለም አቀፉ የጄኔቫ ኮንቬንሽን ሕግ እንዳይ ዳኙ ለማድረግ ነው።

እንደ አቶ ስዩም ገለጻ፤ ዓለም አቀፉ የፀረ ሽብር ጦርነት በሚል አውጀዋል። በዚህም ምርኮኞቹ በኮንቬንሽኑ በጦር ምርኮኞች ሕግ አይዳኙም። አሜሪካ ሄደው በመደበኛው ሕግ እንዳይዳኙ ደግሞ ጓንታናሞ ተሰርቷል። ጓንታናሞ ደግሞ የአሜሪካ ግዛት አይደለም። በዚህም በአሜሪካ ሕግም ሆነ በዓለም አቀፉ ሕግ የመዳኘት ዕድልን ያሳጣል። ይህ ልምድም ባለማወቅ ነው ወደ አገሪቱ ለመተግበር የተገለ በጠው። በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከመንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ ያሉ ወገኖች ተግባራቸው የሽብር ተግባር አይደለም በሚል እንዲታሰብ ያደረገም ነው።

መምህሩ እንደሚሉት፤ ከመንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ ያለ አካል የሚለው በራሱ የተለያየ ትርጓሜን ይይዛል። ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ ኦነግ፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት እና መሰል ድርጅቶች የሕዝብን መብት ለማስከበር ነውና ሲታገሉ የነበሩት በሽብርተኝነት እንዳይፈረጁ የሚል እሳቤንም ያዘለ ነው። ነገር ግን አንድ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ጦርነት ሽብር መሆኑን ነው። በምንም አግባብ መደበኛም ይሁን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ጦርነት ከተነሳ መግደል፣ አካል ማቁሰል ተፈጥሯዊና የግለሰብን ንብረት ማውደምና ሌሎች ጥፋቶችን ያስከትላል።

 ጦርነት ሽብር በመሆኑም በምንም አግባብ ተግባሩ ሽብር አይደለም በሚል በፀረ ሽብር አዋጅ ውስጥ ዕውቅና ሊሰጠው እንደማይገባም አቶ ስዩም ይሞግታሉ። በረቂቁ አንቀጽ አምስት ላይ በተቀመጠው መሠረትም ማንኛውም አሸባሪ የወከለውን ቡድን ነፃ አውጪ ቡድን ሆኖ ጥቃት ቢፈፅምም የነፃ አውጪ ጦርነት ተደርጎ ነው የሚታየው። አገሩን ነፃ ለማውጣት እንደሆነ ሊገልጽ ይችላል። በዚህም በሽብር ወንጀል ሊጠየቅ ስለማይችል በመደበኛው በጄኔቫው ኮንቬንሽን በጦርነት ፍርድ ቤት ሊዳኝ ነው ማለት ነው። ይህም ለጦርነት ተግባር ዕውቅና በመስጠት ተፅዕኖ ያሳድራል።

ጦርነት በቡድን የሚካሄድ በመሆኑ ድርጅቱን በሽብር መፈረጅና አለመፈረጅ አግባብና አካሄድ አለው። በተግባሩ ተሰማርቶ የሚገኝ አካል ሽብርተኛ ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል። በዚህም በሽብር ወንጀል ይዳኛል። ይህ ካልሆነና የነፃነት ታጋይ ነው በሚል በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤቱ ውድቅ ከተደረገ ጉዳዩ በጦር ሕግ ይታያል። ይህን ሂደት ወደ ረቂቁ ወስዶ የጦርነት ተግባርን ሽብር ተግባር ነው ወይስ አይደለም? በሚል ጥያቄ ውስጥ መክተት አይገባም። ተግባሩ በአጥቂው አልያም በተጠቂው ላይ ሽብር በመሆኑ ይህን መፃረር ቅቡል አይደለም፤ ለጦርነትን ዕውቅና መስጠትም እንደሆነም ነው መምህሩ የሚናገሩት።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ አምስት ላይ በተቀመጠው መሠረት ማንኛውም አካል በተግባሩ ተሰማርቶ ቢገኝ እንኳ ለህዝብ መብት በሚል ሰውን መግደልም ትክክል ይሆናል ማለት ነው። ሽብር እንደ ሽብር ሊቆጠር እንደማይገባም አመላካች ነው። ይሁን እንጂ ለህዝቡም መብት በሚል ይሁን ለራስ መብት የኃይል እርምጃ ሲወሰድ ንብረት እንዲወድም ሲደረግ በአካባቢው ባለ ማህበረሰብ ላይ ሽብር እየተፈጠረ መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበትም አቶ ስዩም ያሳስባሉ።

ጠበቃና የሕግ አማካሪው አቶ አምሃ፤ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ አስፈላጊ አለመሆኑ መነሳት ከጀመረ ቆየት እንዳለ ያስታውሳሉ። የፀረ ሽብር ሕግ ልዩ ሕግ ሆኖ ሲወጣ በጣም ጥብቅና በተጠረጠሩና በተከሰሱ አካላት ላይ ጫና የሚያሳድር መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር ይህንን ሕግ የሚተረጉሙ ተቋማት አቅማቸው ጠንካራ መሆን ይጠበቅበታል።

በዚህም በፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና በፍርድ ቤት አካባቢ የሚደረገው ማሻሻያ አንድ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ሕጉ ባይኖር የሚል ሃሳብም ይንፀባረቃል። በሌላ በኩል ግን አገሪቱ በዓለም አቀፍ ህብረተሰቡ አባልነቷ ሽብርተኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የመተባበር ግዴታ አለባት።

 የተባበሩት መንግሥታትም ሁሉም አገራት ሽብር ተኝነት በብቃት የሚከላከል ሕግ እንዲ ያወጡ ያስገድዳል። የአፍሪካ ሕብረትም በተመሳሳይ ይህንን የሚጠይቅ ሕግ አለው። አገሪቱ ያለችበት ቀጣና በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት የተፈረጁ አልሸባብን መሰል ኃይሎች በቅርብ እርቀት የሚገኙባት አገር መሆኗም ለአስፈላጊነቱ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ የአቶ ስዩምን ሃሳብ በመቃረን ያስረዳሉ። ከዚህም አንፃር የተሟላ ሕግ ኖሮ ተዘጋጅቶ መጠበቁ ተገቢነቱ አጠያያቂ አይደለም።

በአሁኑ ወቅት የረቀቀው አዲስ አዋጅ የነበሩትን ክፍተቶች እንዲሞላ ተደርጎ መዘጋ ጀቱን የሚጠቁሙት አቶ አምሃ፤ ሕግ ሲወጣ በመርህ ደረጃ የሚወጣው ዘላቂ እንዲሆን ነው ይላሉ። የትኛውም ኃይል የመንግሥት ሥልጣን ቢይዝ ያለአግባብ ሊጠቀምበትና መጨቆኛ መሳሪያ ሊያደርገው የማይችል በዜጎች ላይም በማናቸውም ጊዜ ጉዳት ሊያስከትል የማይችል ሆኖ እንዲወጣ ማረጋገጥ ይገባል። ይህም ሕግ በአሁኑ ወቅት ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ከግምት ውስጥ በማስገባት የወጣ ሳይሆን በማናቸውም ጊዜ የፈለገ ኃይል ቢመጣ በአግባቡ ሊጠቀምበት የሚችል ሕግ እንዲሆን ተደርጎ የወጣ ነው።

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ አምስት ላይ የተቀመጠው ሃሳብም በአንድ ወቅት በሰላማዊ መንገድ መንግሥትን ወደ ዴሞክራሲ አቅጣ ጫ ለማስገባት ትግል ማድረግ የማይቻል ቢሆንና ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት እንደሆነው ዜጎች መንግሥትን መታገል ብቸኛ አማራጫቸው ቢሆን መንግሥት ይህንን ሕግ ለማፈኛ ሊጠቀምበት አያስችለውም ማለት ነው ሲሉ ከአቶ ስዩም የተለየ ሃሳብ ያራምዳሉ። በሕጉ ውስጥ የተቀመጠውም ከመንግሥት ፀጥታና ከመከላከያ ኃይል ጋር ፊት ለፊት የሚጋጠሙትን ብቻ ነው። እነርሱን በተመለከተ ጦርነቱ እንዴት ይካሄዳል? ምን ዓይነት መሳሪያስ ጥቅም ላይ መዋል አለበት? በጦርነቱ ሰው ሲማረክ እንዴት መያዝ አለበት? የሚለውን የሚገዛ ዓለም አቀፍ ሕግ የጄኔቫ ኮንቬንሽን አለ። ይህም በዛው ይዳኛል።

 አማራጭ በማጣት ከመንግሥት ጋር በኃይል የሚጋጠሙ ኃይሎችን ማንኛውም መንግሥት የሽብርተኝነት ሕጉን በማንሳት ባለፉት ጊዜያት ሲደረግ እንደነበረው እየፈረጀ ከትግል ውጭ ሊያወጣቸው አይገባም የሚል አቋም የያዘ መሆኑን አቶ አምሃ የነበረውን ችግር ለማቃለል ታስቦ መውጣቱን ያነሳሉ። በዚህ መንገድ የትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገቡ ከሆነም በአንቀጽ አራት ላይ ሽብርተኛ ድርጊት በሚል የተቀመጡትን ተግባራት ፈፅመው ከተገኙ በሽብርተኝነት ከመጠየቅ አይሸሹም። የታጠቀ ኃይሉ ከመንግሥት የፀጥታና መከላከያ ኃይል ጋር መጋጠሙን ትቶ ጎን ለጎን በንጹሃን ዜጎች ላይ በመንግሥት ንብረት ላይ ውድመት ቢፈጽም አልያም በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ ሦስት ላይ የተለዩት የሽብር ተግባር በሚል የተዘረዘሩትን ተግባራት ቢፈጽም ከተጠያቂነት አይድንም።

በሕጉ ላይ የተቀመጠው ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት የፀጥታና የመከላከያ ኃይል ጋር ግጥሚያ ውስጥ የሚገቡ ኃይሎችን ነው። እነርሱንም በአገር ውስጥ የሽብርተኝነት ሕግ አይጠየቁም ማለትም በሌላ ወንጀል ተጠያቂ አይደረጉም አለማለት እንደሆነ ከግንዛቤ መክተት እንደሚያስፈልግም ነው አቶ አምሃ የሚጠቁሙት።

ማንኛውም ጦርነት ሽብር አይደለም የሚሉት ጠበቃና የሕግ አማካሪው፤ ለዕውነትና ለነፃነት የሚደረግ ጦርነትን በመግለፅም በተለያየ ጊዜ ከጭቆና ለመውጣትና ዓለም ለተቀበለው ነፃነት ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ ማራመድ ሳይቻል ቀርቶ ዜጎች ወደ ኃይል አማራጭ ሲያመሩ ምንም እንኳ በድርጊታቸው ሙሉ በሙሉ ከሕግ ተጠያቂነት ውጪ መሆን ባይችሉም ሽብር መባል ግን የለበትም ሲሉ የተለየ ሃሳብ ያራምዳሉ። ሽብር በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ አራት ላይ እንደተተረጎመው የአንድ ርዕዮተ ዓለምና ሃይማኖታዊ ዓላማዎችን ለማራመድ የንጹሃንን ደም እንዲሁም የሕዝብን ሠላም እንደ ማስገደጃ በመጠቀም መንግሥትን ማንበርከኪያ ማድረግ አይቻልም።

 በአዋጁ ላይ ማሻሻያና ለውጥ መደረጉ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ካለችበት አለመረጋጋትና ግጭቶች እንዲሁም ቀጣናዊ ሁኔታ አንፃር ሲፈተሸም ምንም እንኳ አገሪቱ እንደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት፣ ሶማሌያና ሴሪያ የተጋለጠች ናት ባይባልም ከሽብር ስጋት ግን ሙሉ በሙሉ ነፃ ናት ማለት አይቻልም። አቶ አምሃ፤ አያይዘውም በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ከሽብር ጋር እንደማይያያዝ ይገልፃሉ። በአገሪቱ የሚስተዋለው የፖለቲካና የአመለካከት ልዩነት ነው። ነገር ግን ልዩነቱን ኃይል በሚያመዝን መልኩ ለማራመድ የሚሹ ኃይሎች አሉ። ሆኖም ግን ዜጎች ናቸው። አለመግባባት ሁልጊዜም ቢሆን በመነጋገርና በሰለጠነ መንገድ መፈታት ነው የሚገባው። በአገር ውስጥ የሚፈጠርን አለመግባባት በሽብር እየፈረጁ ለማስቆም መሞከርም መታሰብ እንደሌለበትም አቶ አምሃ ተገቢነት የጎደለው ትክክለኛ ያልሆነ ተግባር በማለት ይኮንኑታል።

 እንደ መፍትሔ

ጦርነት በሙሉ ሽብር ነው በሚልም ደግሞ ሊቀመጥ አይችልም። ወራሪ ጠላት ሲመጣ ያንን ለመመከት ውጊያ ይኖራል። በመሆ ኑም መፍትሔ የሚሆነው ጦርነት ሽብር ነው አይደለም የሚለው ሌላ ጉዳይና በጦር ሕግ የሚዳኝ ሆኖ ፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ውስጥ በማስገባት ማካተት እንደማይገባ አቶ ስዩም ያስረዳሉ። ከረቂቅ አዋጁም መውጣት አለበት። ሕጉም በባለሙያ መረቀቅና ተደጋጋሚ መድረ ኮች በማዘጋጀትና የሕግ ባለሙያዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነው እንዲተች ማድረግ እንደሚገባ አቶ ስዩም ለችግሮቹ በምክረ ሃሳብነት ያቀርባሉ። መድረኮች ሲፈጠሩም የመንግሥት ተወካዮች የሚነሱ ሃሳቦችን ለመመከትና መልስ ለመስጠት ሳይ ሆን ለማድመጥና ለመፍትሄ ዝግጁ መሆን አለባቸው።

ሕግ በተቻለ መጠን የተሟላ እንዲሆን ተደርጎ ይወጣል። ይህ ማለት ግን ተግባር ላይ ሲውል ምንም እንከን ሳይገጥመው ተፈፃሚ ይሆናል ማለት አይደለም። በመሆኑም ሕዝቡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲያደርግ እንደነበረው በአዋጁ አተገባበር ላይ የሚመለከታቸውን ችግሮች በተለመደው መልኩ መታገል እንዳ ለበት አቶ አምሃ መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ሃሳብ ያስቀምጣሉ። ያለችግር ሊፈፀም ወይንም ከዚህ ቀደም ተከስተው የነበሩ መሰል ችግሮች ፈፅሞ እንደገና ላይከሰቱ ዋስትና ሊሆን የሚችለው አዋጁን በመፈፀም በኩል ሚና ያላቸው ተቋማት ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤትና የደህንነት ተቋሙ ሲሻሻሉ በመሆኑ በዚህ ላይ በትኩረት መሰራት አለበት። በዚህም ተከታታይ ሥልጠናዎች ሊሰጥ ይገባል። የዚህና መሰል ሥራዎች ድምር ውጤትም ሕጉ ተግባር ላይ ሲውል ሊያጋጥም የሚችለውን ጉዳት በእጅጉ ይቀንሳል።

ስጋት

መምህሩ፤ በእሳቤ ደረጃ ሕጎች ክፍተት ካላቸው አተገባበራቸው ላይ ለችግር እንደሚ ጋለጡ ያመላክታሉ። ላልተፈለገ ዓላማም ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ ሲሉም በቀጣይ ሊያጋጥም የሚችለውን ችግርም ይጠቁማሉ። አቶ አምሃ በበኩላቸው፤ ቀድሞ በነበረው የተቋማቶቹ ቅርጽና ቁመና መቀየር ካልተቻለ የፈለገ የተቀደሰ ሕግ ቢወጣ ችግር ላለመፈጠሩ ዋስትና እንደሌለም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011

ፍዮሪ ተወልደ