የሶሪያው የእርስ በእርስ ጦርነትና ጦሱ

19

 

ዓለማችን በእርስ በርስ ፍጅት ትናወጥ ዘንድ የታዘዘ ይመስል ‹‹እዚህ ቦታ ቀረ›› ሊባል በማይቻል ደረጃ ትርምሱ የርስ በርስ ፍጅቱ በማያባራ ሁኔታ ቀጥሎ የእለት ተእለት የመገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ ርዕሰ ጉዳይ  በመሆን እነሆ እስከ አሁኑ ሰዓትና ቀን ድረስ ቀጥሏል።

ይህ ቅጥ ያጣ የርስ በርስ ግጭት ከፍ ሲልም ጦርነት ሰበበ ብዙ ሲሆን፣ ሲፈልግ ብሄርን፣ ሲያሻው ሃይማኖትን፣ ግለሰባዊ ማንነትን፣ ካስፈለገውም መልከአምድራዊ አቀማመጥ /ድንበር ቋንቋንም ጨምሮ የታሪኩ መነሻ ሊያደርግ ይችላል። ‹‹ይችላል›› ብቻ ሳይሆን ችሏልም።

ሰሞኑንም ከወደሶሪያ ያገረሸው ግጭት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አገሪቱ ከዛ ሁሉ ምስቅልቅል ህይወት ሳትወጣ ወደ ሌላ ምስቅልቅስ ህይወት በመሸጋገር ላይ ያለች ይመስላል። ‹‹እንዴት?›› ቢሉ ሰሞኑን ‹‹ነፃ አውጪ ነኝ›› በሚለው አማፂ ቡድን ያደረሰውና እየደረሰ ያለው ማህበራዊ ቀውስ፣ ቁሳዊ ውድመትና አገራዊ አለመረጋጋት  ለጥያቄዎ መልስ ይሆናል።

በዓለም መገናኛ ብዙሃን በስፋት ብቻ ሳይሆን በጥልቀት እየተራገበና እየተሰራጨ ያለውን፣  በትልቋ የሶሪያ ከተማ አሌፖ ላይ የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ ቁሳዊ ውድመትና ሰብዓዊ ጉስቁልና መመልከቱ በቂ ይሆናል። ይህ በመገናኛ ብዙሃን ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የፖለቲካ ተንታኞች፣ የአገራት መሪዎች … ወዘተ ዘንድ ውዝግብ እየተካሄደበት ያለው የሶሪያ የርስ በርስ ጦርነትና ያስከተለው ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ጉዳይ የበርካታ አገራትን፣ በተለይም ሩሲያ ፣ ቱርክንና እራሷ ሶሪያን ያልጠበቁት አታካራ ውስጥ በመክተት እያወዛገባቸው ይገኛል። ውዝግቡ በየአቅጣጫው ቢስተጋባም የርስ በርስ ጦርነቱ፣ የሶሪያ መንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደገለጸው፣ ያባራ አይመስልም። ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው የሶሪያው አማፂ ቡድን በንፁሃን ዜጎች ላይ በሚፈጽመው መርዛማ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ፣ ባደረሰው ሰብአዊ ቀውስና ቁሳዊ ውድመት ምክንያት ነው።

ባለፈው ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የሶሪያ አማፂ ቡድን በሶሪያ፣ አሌፖ ከተማ ላይ ባወረደው የመርዛማ ኬሚካል የጦር መሳሪያ ምክንያት በርካታ የከተማ ነዋሪዎች ላይ ኢ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመፈጸሙ ባለፈ የከፋ የጤና መታወክና መፈናቀል ደርሷል። ጉዳዩ ከአገሪቱም አልፎ የሶሪያ ወዳጅ አገራትንም ስሜት ፈንቅሎ ድርጊቱን በፈፀሙ አማፂ ወገኖች ላይ ክንዳቸውን እንዲያነሱ አስገድዷል፤ ለዚህም በቀዳሚነት ሩሲያ ተጠቃሽ ናት።

ሩሲያ የሶሪያ አማፂያን የአገሪቱ ትልቋ ከተማ በሆነችው አሌፖ ከተማ ላይ ባደረሱት ጥቃትና በፈፀሙት ኢሰብአዊ ወንጀል ተደሳች አልሆነችም፤ በመሆኑም ከሶሪያ መንግስት ጋር ያላትን የቀረበ ወዳጅነት ምክንያት በማድረግ አፀፋውን በአማፂያኑ ላይ ሰንዝራለች። አማጽያኑ በሶሪያ መንግሥት ይዞታ ላይ በፈፀሙት የኬሚኮል የጦር መሣሪያ ጥቃትና ላደረሱት መጠነ ሰፊ ቁሳዊና ሰብአዊ ቀውስ ከመወንጀል ባለፈ የአፀፋ ምላሽ ሰጥታለች።

ሶሪያና ወዳጇ ሩሲያ ባለፈው ቅዳሜ በአማጽያኑ አማካይነት የተጣለው መርዛማ ኬሚካል የጦር መሣሪያ በ100 ንፁሃን የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል። የሶሪያ መንግሥት ሚዲያ በአደጋው የተጐዱ የከተማዋ ነዋሪዎች በሆስፒታል አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸውና መተንፈስ አቅቷቸው ሲያቃትቱ የሚያሳይ ምስል ይፋ አድርጓል።

አማጽያኑ በበኩላቸው ምንም አይነት የኬሚካል የጦር መሣሪያ ጥቃት አለማድረሳቸውን የገለፁ ሲሆን ወንጀሉም ሆን ተብሎ በእነሱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘርና በእነሱ የተያዙ አካባቢዎችን ለማጥቃት የታሰበ መሆኑን ገልጸዋል። ድርጊቱንም ሰበብ ፍለጋ ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

ታይም ዶት ኮም የተባለው ድረ ገጽ እንደገለጸው ከፊል የአሌፖ ከተማ አካባቢዎች እንዲሁም የሀማና ኢድሊካ አጐራባች አውራጃዎችን የቱርክ መንግሥት ደጋፊዎች ባላቸው አማጽያንና ጂሀዲስቶች ቁጥጥር ሥ ይገኛሉ። ይህንኑ የቱርክ አማፂያን ድርጊት ተከትሎ የሩሲያ  መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው እሁድ የጦር አውሮፕላኖቹን በተመረጡ የሽብርተኞቹ የጦር ካምፕና ምሽጐቹ  እንዲሁም መሳሪያዎቻቸው ባሉባቸው ቦታዎች ላይ ተገቢው ወታደራዊ ርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል። በተወሰደው     እርምጃም ሁሉም የአማጽያኑ ምሽጐች መውደማቸው ተመልክቷል። በወቅቱ በተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ  አማካይነት ስለደረሰው ዝርዝር ጉዳይ ግን የተገለጸ ነገር የለም።

የተወሰደውን  የማጥቃት ርምጃ  በተመለከተ የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢና ግጭቱን በቅርበት የሚከታተለው የአክቲቪስቶች ቡድን ኔትዎርክ እንደሚሉት አማፃያኑ በፈጸሙት ድርጊት ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ ከ100 በላይ ንጹሐን ዜጐች አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፤ በተለይም በመርዛማው ኬሚካል  አማካይነት የደረሰባቸውን  የ መተንፈስ ችግር መቋቋም እንዳቃታቸው ይህንንም ለመታደግ በየሆ ስፒታሎች  አስፈላጊው እርዳታ እየተደረገላቸው እንደነበር  ገልጸዋል።

እንደሩሲያ ሁሉ የደማስቆ መንግሥትም አማፂያኑ በንጹሐን ዜጐች ላይ መርዛማ ኬሚካል በተለይም ክሎራን ጋዝ መጠቀማቸውን በማረጋገጥ ከሶሪያ መንግሥት ጐን ለመቆም የሚችል መሆኑን በተዘዋዋሪ ዛሂር ባታል የተባሉ፣ በአሌፖ ከተማ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ህክምና የሚሰጡ ሐኪሞች ተወካይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል «ይህ በአሌፖ ንፁሃን ዜጐች ባይ የተፈፀመው የመርዛማ ኬሚካል የጦር መሳሪያ ጥቃት ግጭቱ ከተጀመረበት 2011 ጀምሮ ሲፈፀም በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።

የሐኪሞች ቡድት ተወካዩ ይህን ይበሉ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት ያገኘ አይደለም። በአካባቢው  ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት  አብዱ ሰላም አብዱል ራዛክ የተባሉ ግለሰብ የቀረበውን ኪስ «ፍጹም ሀሰት» ሲሉ ያጣጣሉት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል። የምዕራቡ አገራትና የተባበሩት መንግሥታት የኬሚካል መሣሪያዎችን መጠቀምን የርስ በርስ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሲያወግዙት ቆይተዋል። ሩሲያና ቱርክ በአድሊብ አውራጃ የመንግሥት ኃይሎችና አማጺያኑን መለያየት የሰላም ቀጣና ለመፍጠር የተስማሙ ቢሆንም እስካሁን ድረስ አንድም ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ነገር አልታየም።

የአማፅያኑን ጥቃት ተከትሎ ባለፈው እሁድ የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜን ሶሪያ የሚገኙና አማፂያኑ የተቆጣጠሯቸውን ቦታዎች ኢላማ ያደረገ ጥቃት መሰንዘራቸውን ታይም መጽሔት ዘግቧል። የሩሲያ ባለሥልጣናት ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት አማፂያኑ ባደረሱት ጥቃትና በተጠቀሙት የኬሚካል ጦር መሣሪያ ምክንያት ከ100 በላይ ንፁሃን የአሌፖ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርገዋል።

የሩሲያ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል ኢጐር ኮናሼንኮቭ ሞስኮ ለሚገኙ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መርዛማ ጋዝን በመጠቀም ንፁሃን ዜጎችን ለጉዳት የዳረጉትን አማፅያንን አውግዘው፤ የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች ወደ አካባቢው በመሰማራት በድርጊቱ ፈፃሚ አሸባሪዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን በአካባቢው የሚገኘውን የአማፂያኑን የጦር ሰፈር ሙሉ በሙሉ ማውደማቸውን ገልጸዋል።

ይህ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና በሰሜን ኮሪያ ላይ የተፈጸመው የአየር ድብደባ እስካሁን ተወዳዳሪ የሌለው አደገኛና በሩሲያና ቱርክ መካከል የተደረገውን ስምምነት የጣሰና ስምምነቱም በአካባቢው ላይ አምጥቶት የነበረውን ሰላም ያደፈረሰ ነው በማለት ድርጊቱን አለመፈፀማቸውን የገለጹት አማፂያን የሩሲያን ያልተገባ  እርምጃ «የሰላም ስምምነቱን ያለማክበር ሙከራ» በማለት አጣጥለውታል።

መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው የሶሪያ ሰብአዊ መብቶች ተዛቢ እና ቲግ የዜና ወኪል እንደስታወቁት በሩሲያ የተወሰደው ወታደራዊ ርምጃ ቀደም ሲል በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ሥምምነት ለመጀመሪያ ጊዜ የጣሰ ነው።

የሶሪያ አረብ የዜና ወኪል በበኩሉ የሶሪያ ወታደሮች በአሌፖ አቅራቢያ የሚገኘውን የአማፂያኑን ምሽግ በቦንብ መደብባቸውን በሽብርተኞቹ ላይም ከባድ ኪሳራን ማድረሳቸውን አስታውቋል። የዜና ወኪሉ በአሌፖ ከተማ የደረሰው ጥቃት የተፈፀመው በሽብርተኞቹ ቡድን መሆኑን የተጠቀሙትም የኬሚካል የጦር መሳሪያ መሆኑንና በንፁሀን ዜጐች ላይ አደጋ መድረሱንም ይገልጻል፡፡

የሩሲያው ወታደራዊ ቃል አቀባይ የሩሲያ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ባለሙያዎች የምርመራ ውጤትም አማፂያኑ መርዛማ ጋዝ መጠቀማቸውን ያመለከተ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ የተወሰደው እርምጃም ይህንኑ መሰረት ያደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ፀረ ሽብርተኞቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ሊሰማሩ የመቻላቸው ጉዳይም ሩሲያ የፕሬዚዳንት በሽር አለሳድ የቅርብ ወዳጅና አጋር በመሆኗ እንደተከናወነ አስታውቀዋል።

ግርማ መንግስቱ