የመቀሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በምክርቤቱ አባላት ጥያቄ አስነሳ

1142

ለፕሮጀክቱ ከ229 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ተገኝቷል

የመቀሌ ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ከቻይና የተገኘው የብድር ድጋፍ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄዎች ተነሱበት።

ለፕሮጀክቱ ከ229 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር መገኘቱ ተገልጿል።

የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክርብ ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ለመቀሌ ከተማ የውሃ አገልግሎት አቅርቦት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ የተገኘውን ብድር በተመለከተ የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ የተመለከተ ሲሆን፤ በተገቢነቱ ዘሪያ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

የምክር ቤቱ አባል በዚሁ ወቅት ባነሱት ጥያቄ፤ የከተማዋ የመጠጥ ውሃ ጥያቄ በተደጋጋሚ የቀረበና ውሳኔ የተሰጣቸው ፕሮጀክቶች ነበሩ፤ የእስከዛሬው ገንዘብ የት ደረሰና የአሁኑ ፕሮጀክት ዳግም ሊቀርብ ቻለ ሲሉ ተከራክረዋል።

ሌሎች የክልል ከተሞችም በመጠጥ ውሃ ችግር ምክንያት የተለያዩ ጥያቄዎችን ከመቀሌው ባልተናነሰ ሁኔታ አቅርበዋል። ነገር ግን ምንም አይነት ፕሮጀክት ሲፈቀድላቸው አልታየም። በመሆኑም መቀሌ ለምን አሁንም ተመረጠ የሚለው መመርመር አለበት ሲሉም የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ አንስተዋል።

ምክርቤቱ በዚህ በጀት አመት አዲስ ፕሮጀክት እንዳይሰጥ የወሰነ ቢሆንም አዳዲስ ፕሮጀክቶች እየመጡ መሆናቸው አግባብነት እንደሌለውም አባላቱ አንስተዋል።

ምክር ቤቱ የቀረበለት የብድር ረቂቅ አዋጅ ከተመለከተ በኋላ በ16 ድምፀ ታቅቦ በ4 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

ለፕሮጀክቱ የተገኘው የብድር መጠንም 229 ሚሊዮን 784 ሺህ 582 ዶላር መሆኑ ታውቋል።

በጽጌረዳ ጫንያለው