ዕምቅ አቅማችን በእጅ የያዙት ወርቅ … እንዳይሆንብን!

130

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ባለፈው ጊዜ በብሔራዊ ቴያትር ቤት ተገኝተው ያደረጉት ንግግር ብዙ ሰዎችን ያሰደመመ ነበር። ውስብስብ የሆነውን ነገር በቀላሉ የገለጹበት እና ያስረዱበት ንግግራቸው በቀዳሚነት የሚያሳየው መፍትሔ ለማግኘት የአስተሳሰብ ለውጥ ምን ያህል ከፍተኛ መሆኑን ነው።

በአንድ ወቅት አልበርት አንስታይን “ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ በመጠቀም ለዚሁ ችግር መፍትሔ ማግኘት አይቻልም፤ችግሩን ለመፍታት ራስን መቀየር፣ በአዲስና ባልተለመደ መልክ መሥራት ያስፈልጋል» ሲል ተናግሮ ነበር። በዘመነ ዲጅታል በአውሮፓ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑን በማመን በቴክኖሎጂ የመጠቁት አገራት በከፍተኛ ምርምር ላይ ይገኛሉ። ተቋማትና ካምፓኒዎችም እራሳቸውን እያዘጋጁና በከፍተኛ ቅፅበት እየተቀየሩ ናቸው።

 በቅርቡ በመስሪያ ቤቴ ለሠራተኞች በተዘጋጀ ሴሚናር ላይ አንድ የሥነ አዕምሮ ተመራማሪ (neuroscientist & brain researcher) ተገኝቶ ነበር። ከዶ/ር አብይ የሚለየው ለንግግሩ ብዙ ሺ ዩሮ መከፈሉና ለየመስሪያ ቤቱ የሚሆነውን አተገባበር ማሳየቱ ብቻ ነው። ዶክተር አቢይ መሰጠትን፣ ዕውቀትንና ልምድን በፈቃደኝነት የማካፈልን እንዲሁም የመተባበርን ጠቀሜታ ገልጸዋል። ቀሪው የሚሆነው ይህንን ንግግር ሰምተን እንደ ጥሩ መፅሐፍ በአዕምሮ ቤተመፅሐፍ ውስጥ ማስቀመጡ ሳይሆን በምን ዓይነት መልኩ መተግበር እንደምንችል መተለሙ ላይ ነው። የዚህ ሁሉ መሠረቱ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ መንሸራሸር ነው።

ለአስተሳሰብ ለውጥ ተግባራዊነት የሚረዱን ብዙ መንገዶች ሲኖሩ አንዱና ዋነኛው የብዝሃነትና ማካተት ማኔጅመንት (Diversity & Inclusion Management) ነው። ይህም ራሳችንን፣ የሥራ ባህላችንን፣ የፕሮጀክት አሠራራችንን ለመመርመርና ለመቀየር ወደ ተግባርም ለመለወጥ ይረዳናል።

 ዶ/ር አብይ “ቅጠል የሌለው ዛፍ ጥላ አይሆንም ወይም ሀገር ከሌለ መንደር ሊያስጠልል አይችልም” እንዳሉት የተለያዩ ሰዎች፣ የተለያዩ ችሎታዎችና ክህሎቶች ውጤታማ የሚሆኑት ሲሳለጡ ወይም እንደ አዲሱ የኢትዮጵያ የለውጥ ፍልስፍና ሲደመሩ ነው።

የተለያዩ አካሎች ሲተባበሩና ሲቀናጁ ነው አንድን ተግባር ማሳካት የሚችሉት። ይህንንም በግል፣ በሥራ ህይወታችን፣ በፕሮጀክት አወቃቀር ላይ አልፎም በሀገር ጉዳይ ላይ ልናስቀምጠውም እንችላለን። አንድን ሀገር ማሳደግ የሚቻለው ሁሉም በችሎታውና በክህሎቱ ሳይናናቅ ሲተባበር ነው የታወቀው የማኔጀመንት ምሁር መረዲዝ በልቢን የአፓሎ ሲንድሪም ብሎ በሚጠራው ፍልስፍና አንድ ሥራ (ፕሮጀክት) ውጤታማ የሚሆነው የተለያዩ ሰዎች በዘጠኝ ክፍሎች ባስቀመጧቸው ችሎታዎች እና ባህሪይዎች አጣምረው መሥራት ሲችሉ ነው።

እነዚህም፦ ሃሳብ ተኮር (ሃሳብ ፈጣሪ፣ ተቆጣጣሪ፣ ባለሙያ)፣ ተግባር ተኮር(አስተግባሪ፣ ፈፃሚ፣ አጠናቃቂ)፣ ሰው ተኮር (አቀናጅ፣ በቡድን የሚሠራ፣ አግባቢ) ተብለው ሲቀመጡ፤ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ እነዚህ ባህሪዎች/ተስጥኦዎች/ በተለያየ መጠን እንደሚገኙ፣ ዋናው ጥበብ ግን ችሎታዎች እና ባህሪዎችን በተመጣጠነ መልኩ ማካተቱ ላይ እንደሆነ ያብራራል። ይህን ሲያሟላ ነው አንድ ቡድን ውጤታማ መሆን የሚችለው።

ሌላው መፍትሔ ለመፍጠር፣ ለውጤትና ለዕድገት መሰረት የሚጥለው በአንድ ቡድን ውስጥ ወጣት፣ በዕድሜ የገፉ፣ ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች ከተለያዩ አገሮች ወይም ብሔረሰቦች የተውጣጡትን አመጣጥኖ ሲይዝ ነው። ለምሳሌ ወጣቶች ፈጣኖች ናቸው፤ ጉልበት አላቸው ቢባልም፣ በዕድሜ የገፉት ደግሞ አቋራጩን እንደሚያውቁ መዘንጋት አያስፈልግም።

በዚህ አጋጣሚ አንዳንድ ብልህ ኩባንያዎችና ተቋማት ለሚያከናውኑት ተግባራት የኦቲዝም ተጠቂዎችን እየቀጠሩ ይገኛሉ። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በተለይም በሶፍትዊር ማበልፀግና በሂሳብ ሥራ ላይ የኦውቲዝም ተጠቂ ካልሆነው ሰው የበለጠ ውጤት ማምጣት ይችላሉና ነው። በጀርመን አገርም የኦውቲዝም ተጠቂዎችን የሚቀጥር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሥራውን ጀምሯል።

 እዚህ ላይ ልበ ብርሃን የሆኑትና ማየት የተሳናቸው ወገኖቻችን ምን ያህል ልዩ ችሎታ/ተሰጥዎ/ እንዳላቸው ይታወቃል። በደመነፍስ መፍረድ (unconscious bias) ሲሆን፤ ጥቅም ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ እባብ የተባለ ሁሉ በደፈናው ሰው ይናደፋል ብለን አስቅድመን ስለደመደምን እባብ ስናይ ብዙም ሳናስብ እንድናመልጠው ይረዳናል። በሥራና በማካተት ላይ ግን ጉዳቱ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።

ከአንድ አካባቢ የመጣን ሰው ወይም አስተሳሰብን በአንድ በመጥፎ ምሳሌ ወይም ጥርጣሬ ከታወቀ የአካባቢው ድርጊት፣ አስተሳሰብ ጋር በተመሳሳይነት በመፈረጅ አድሎአዊነት ይደረጋል። ወይም ቅቡልነትን ይነፈጋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ረሃብተኛ ነው፣ ጀርመን ሁሉ ናዚ/ዘረኛ/ ነው፣ አፍሪካ ሁሉ ኋላ ቀር፣ ጃፓን ሁሉ ካራቲስት ነው፣ ውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራ) ሁሉ ሀብታም ነው ወዘተ… ብሎ እንደመፈረጅ ይሆናል።

ለሃሳቦች ቅደም ተከተሎችን ሰጥቶ መጠበቅ ከሚሮጠው ጊዜ አኳያ የሚከብድ ነው። እነ ጉግል፣ ፌስ ቡክና ኡበር የመሳሰሉት እዚህ የደረሱት ከመዘጋጀት በፊት መጀመር (start before ready) በሚሉት በተለይም በደመነፍስ ከምንፈርጀው አመለካከትና ከተለመደው ቢሮክራስያዊ አሠራር በፀዱ አካሄዶች ነው። ከቀድሞ የፕሮጀክት ማኔጅመንት አሠራር በተሻለ መልኩ ራዕይን፣ ተጠቃሚውን ያማከሉና «በስህተት መሻሻልን» የሚቀበሉ እንደ የሃሳበ ቀረፃ (design thinking) ዓይነት አካሄዶች እየበዙ መጥተዋል። በእርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በድህነት ውስጥ ሆኖና ኋላ ቀር አመለካከቶች ይዞ ከዚህ ለመውጣት ቅድሚያ ሰጥቶ ሁሉንም በትይዩ መጀመር ያስፈልጋል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ በመብረቃዊ ፍጥነት የመጣው ለውጥ በተለምዶ አሠራር ቢኬድ ኖሮና እስኪወሰን እንጠብቅ ቢባል ዛሬም ባላለቀ ነበር። ሰው አስቦ ራሱን እንዲተካለት የፈጠረው ኮምፒውተር ሰውን ከመምሰሉ ይልቅ፣ ሰው ኮምፒውተርን እየመሰለ መምጣቱን እንረዳለን።

የፅሑፍ እና የንግግር ቋንቋ መቀየር፣ ያለስማርት ፎን ቀኑ የሚጨልምብን መምሰሉ፣ ያለጎግል መልስ መቸገር፣ በአጠቃላይ ከፈጠረው ኮምፒውተር ውጪ መኖር የሚያቅተው እየሆነም ነው። ኮምፒውተር ምሉዕ ሲሆን አይሳሳትም፣ በሴኮንድ መልስ ይኖረዋል። ሰው ግን ተሳሳች ነው፣ በሴኮንድ መልስ ለመስጠት ይከብደዋል። ግን ሰው በተሳሳተ ቁጥር ራሱን የሚያርም፣ የሚያሻሻልና በመፍጠር የተሻለን ለመሥራት ያስችለዋል።

ሕፃናት በፍጥነት የሚማሩት በመሳሳትና በመድገም ሂደት ነው። ኮምፒውተር ግን ከተሳሳተ፣ ከወረደ (crash) ካደረገ ያለሰው አይነሳም። የተሰጠውን መረጃ፣ የተሠራለትን ፕሮግራም ተከትሎ መልስ ይሰጣል። ኮምፒውተር ስሜት፣ ራዕይ እና ሃሳብ መፍጠር አይችልም። ሰው ግን ራዕይ አለው፣ ይፈጥራል፣ በስሜቱ ያሸንፋል፣ በስሜቱ ይሸነፋል። የሰውን ልጅ አስገድዶ ፍጠር ማለት ግን አይቻልም። ሰውን በስብሰባ፣ በቢሮ ጠረጴዛ ላይ ወይም የሃሳቦች ልውውጥ ቴክኒክ (brain storming) አድርጋችሁ ሃሳብ አፍልቁ ማለት ውጤታማ አያደርግም። አብዛኛው ሃሳብ የሚፈጠረው ብቻችንን ስንሆን፣ በመኝታ ሰዓት፣ ስናርፍ፣ ስንጓዝ ወዘተ… ትልቁ አንጎል አርፎ ትንሹ መሥራት ሲጀምር ነው። በሌላ በኩል ግን በጋራ ሃሳብን የማንሸራሸር ዘዴ እና የመሳሰሉት ችግርን ለመጠቆም ይረዳሉ። ፈጠራ በበጎፈቃደኝነትና በመስጠት ላይ የተመሰረተ ሲሆን ደግሞ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሚሆን ከመኪና ፈጠራ (innovation) መማር ይቻላል።

 አንድ መኪና አምራች የተጓዥን ደህንነት የሚያሻሽል፣ መጋጨትን የሚቀንስ አዲስ ግኝት ሲፈጥር ከሌሎች ጋር ይጋራል። ምክንያቱም ከሌሎች ኩባንያዎች የሚመረቱት መኪናዎች ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ ካላችው የመጋጨት ዕድሉ መቀነሱ ውጤታማ እና ተግባራዊ ስለሚሆን ነው። የሃሳብን ፈጠራ እና የአስተሳሰብን ለውጥ ለመተግበር ከሚያስችሉ መንገዶች በጥቂቱ፦

• ሃሳብን የመፍጠርና የማንሸራሸር ባህልን የሚያስችሉ የክርክር ክለቦች (debate clubs) በግል፣ በመስሪያ ቤት፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በትምህርት ቤቶች ማመቻቸት፣ ከእነዚህም ውስጥ የወደፊቱ ፖለቲከኞች፣ ጠበቆች የመናገርና የማሳመን ችሎቻ ያላቸው፣ የነገሮችን መጠላለፍ በቅጽበት አፍታቶ በቀላሉ የማቅረብ ክህሎትን የሚያዳብሩ ይወጡበታል። በሃሳብ ሲሸነፉ የሚቀበሉና በስሜት የማይነዱ፣ ሰውን ከነገሩ የሚለዩ፣ በሚደርስባቸው ግላዊ ጥቃት የማይረበሹ “የዝሆን ቆዳ” የሚኖራቸውን ያፈልቃል።

• የፊልምና የቲያትር አካዳሚዎች ወይም ኮሌጆችን መክፈት ያስፈልጋል። ሰው ራሱን ሊገልጽ፣ ሃሳቦችን ሊተውንባቸው የሚችልባቸው የቲያትር ክለቦችን በመስሪያ ቤት፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በትምህርት ቤቶች እንዲቋቋሙ ማበረታታት ጠቃሚ ነው። በጀርመን ከ13 በላይ የፊልምና ቲያትር ዩኒቨርሲቲዎችና አካዳሚዎች፣ 6800 ሙዚየሞች፣ 1672 ሲኒማ ቤቶችና በዓመት ከ39 ሚሊየን በላይ ተመልካቾች የሚጎበኙ ከ490 በላይ ቲያትር ቤቶች አሉ።

• በአንድ የሥራ ቡድን ውስጥ ያሉት ሰዎች ፆታቸውን፣ ዕድሜያቸውን፣ አመጣጣቸውን ማሰባጠር። • የፈጠራ ሀብትን የሚጠብቅ፣ የሚደግፍ፣ የሚያበረታታና የሚያከማች ተቋም መፍጠር።

• የቅደም ተከተል አስተሳሰብን መቀነስ፣ ነገሮች የተለያየ ክብደቶች ቢኖሩዋቸውም በትይዩ መጀመር።

• “ከመዘጋጀት በፊት መጀመር” (start before ready) እንደሚባለው ያለብዙ ፈቃድና ቢሮክራሲ መጀመር፣ ፈቃድ ካስፈለገ ከጀመሩ በኋላ ማውጣት፣ የመታገስ የስራ ባህል መፍጠር፣ የደንበኞችንና የባለጉዳይን ሃሳብና ፍላጎትን በየጊዜው መጠየቅና መከታተል፣ አለቃና ሠራተኛንም በእርከን የለሽ መልኩ በፕሮጀክቱ ማሳተፍ፣ ተገልጋዩን እንደ ሥራ ሰጪ አለቃ መቁጠር፣ ለተገልጋይ ተኮር ሥራዎች ክብደት መስጠት።

• ሰዎችን ሳያስፈቅዱ ወይም ሳያስገድዱ መልካም ነገር እንዲያደርጉ የሚያስችል አካሄድን ማበረታታት።

• የቢሮ ባህሎችን መቀየር ዝግ ከሆኑ ክፍሎች ወደ የጋራ ክፍት ቢሮዎች (open space) ባህል መቀየር።

• ከጠበቀ የቁጥጥር፣ የመጠራጠርና “ምን ከጀርባው አለ” ባህል ወደ የመተማመን ባህል ለመቀየር ራዕይ መያዝ።

• በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ሃሳብ የማመንጨት ኃይላቸውን እንዲያዳብሩ ወደታች ወርደው የተለያዩ የማህበራዊ ግልጋሎቶችንና የሚያቀራርብ ሥራ ለተወሰነ ቀናት እንደማንኛውም ሰው የሚሳተፉበት ፕሮግራም ማዘጋጀት። (ለምሳሌ ጀርመን ለአንድ ሳምንት ያህል ከፍተኛ የኩባንያ/ተቋም/ አመራሮች ለማገገም የማይችሉ ታማሚዎች በሚያርፉበት ስፍራ በመሄድ፣ በማስታመም የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች አብሮ በማሳለፍ፣ በማጽናናት፣ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በማገልገል፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ምግብ በማደል ወዘተ… በበጎ ፈቃደኝነት ያገለግላሉ)።

 • ሰዎች በበጎ አድራጎት ማህበራት እንዲሳተፉ ማበረታታት። በጀርመን ወደ 580.000 የበጎ ፈቃድ ማህበራት ሲኖሩ፤ ለምሳሌ ከ4 ሰዎች አንዱ 90.000 በሚሆኑት የስፖርት ማህበራት በአንዱ በበጎ ፈቃደኛነት ያገለግላል።

• ስፖርት ሰውን እኩል የሚያደርግ፣ ዘርንና ቋንቋን የማያውቅ፣ እኩል ደንቦች ያሉት፣ ጠንካራ ዲስፕሊን የሚጠይቅ እና ሰውን ለመልካም የሃሳብ ፈጠራ የሚያዘጋጅ ነው። ትኩረት በመስጠት በታቀደው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ማካተት፣ አልፎም ስፖርትን ከ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አንዱ ማድረግ።

 • በኢትዮጵያ ከተለመደው የምርጫ (single choice) የፈተና ስርዓት መውጣት። ለተፈታኞች ሊያመራምር እና ፈጠራን ሊያዳብር የሚችል ነፃ የቃልና የፅሑፍ ፈተና መቅረጽ።

 • በየመስሪያ ቤቶቹ የሃሳብ ፈጠራ ማኔጅመንት (idea management) ተወካይ መምረጥ፣ አዲስ የሥራን ባህሪይ የሚያሻሽል የፈጠራ ሃሳቦችን ላመጡ ማበረታቻ መስጠት፣ ከውጤቱም ተካፋይ ማድረግ።

• የመስሪያ ቤቶች ተደራሽነትን ማበረታታት (የሚነሱ ስልኮች፣ የሚመለሱ ኢ-ሜይሎች፣ የሚያነጋግሩ፣ አስተያየት የሚጠይቁ፣ የመመለስ ብቃት ያላቸውን ሰዋች ማስቀመጥ)። ከላይ የተረዳናቸውን ቁም ነገሮች ለማጠቃለል እንዲጠቅመን የጀርመኑ ፈላስፋ ዮሃን ወልፍጋንግ ገት እንዳለው “ማወቅ ብቻ ሳይሆን መተግበር፣ መፈለግ ብቻ ሳይሆን ማድረግ ያስፈልጋል”።

ጀርመኖች ከከሰል በስተቀር ይህ ነው የሚባል ማዕድን የላቸውም። የሌላቸውን የሚያካክሱት ሃሳብን በማፍለቅ እና በመፍጠር፣ እንዲሁም አስገራሚ በሆነ ህብረት በመተጋገዝና አገራችውን እስከ የትኛውም ጫፍ ድረስ በመውደድ ነው። “በኢትዮጵያ 13 ወር ፀሐይ ወይም “Land of Origin” እንደምንለው ጀርመንን “የፈጠራ አገር” (Land of Ideas) ይሏታል። ጀርመኖች አገራቸውን የፈጣሪዎች አገር የሚሉት ያለምክንያት አይደለም። በአስከፊ ታሪክ ውስጥ ያለፉ ቢሆንም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ግኝቶችን በመፍጠር አለም እንዲቀየር ትልቅ ድርሻ ወስደዋል። ቦሽ የተሰኘው ኩባንያ ብቻ በየዓመቱ 4 ሺህ ግኝቶችን በባለቤትነት ማረጋገጫ (patent) ያስመዘግባል። በመኪና ቴክኖሎጂ ብዙ ሺህ ፈጠራዎችን አበርክቷል።

 በአጠቃላይ ጀርመኖች ዓለምን ሊቀይር የሚችል ምን ፈጠሩ ካልን የሚከተሉተን በጥቂቱ እናገኛለን፦ መኪና፣ ሄሊኮፕተር፣ ታንክ፣ ሮኬት፣ ብስክሌት፣ የኤሌክትሪክ ባቡር፣የመፅሐፍ ህትመት፣ ኤክስሪይ፣ አምፖል፣ ቴሌቪዥን፣ ማቀዥቀዣ፣ ኮምፒውተር፣ የኒዩክልየር ውህደት፣ ኢንተርኔት፣ ኮምፒውተር፣ ላፕቶብ፣ ኤም.ፒ.ስሪ.፣ ዩ.ኤስ.ቢ. ስቲክ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። ፈጠራ የኢኮኖሚ እና የብልጽግና አንዱ የነርቭ ሲስተም ነው። አንድን ማህበረሰብ ወደፊት የሚያሸጋግር፣ የኑሮን እና የአስተሳስብ ደረጃን የሚያሻሽል ነው። በዚህ የእውቀት ሽግግር ሁሉንም አንድ በአንድ በመገልበጥ ወይም ይህ ብቻ የተሻለ ነው ለማለት ሳይሆን አስቀድሞ በአዕምሮ ደረጃ መዘጋጀትና ማወቁ ተገቢ ነው።

 የአገራችን ምድር ብዙ ማዕድናት የተከማቸባት፣ የብዙ አዕዝርት ባለቤት፣ የብዙ ጉልበት /ሐይል/ ባለቤት፣ አኩሪ ታሪክና ባህል ያላት፣ ሠርተው ለማደግና ዕውቀትን ለመቅሰም ብቃቱ ያላቸው ልጆች ባለቤት ስትሆን ፤ በእጃችን ያለውን ወርቅ ከመዳብ ሳንቆጥር መልካም የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥን፣ ቅንነትን፣ በጎ ፈቃደኝነትና የሃሳብ ፈጠራ ባህልን፣ መልካም አስተዳድርና መተባበርን ብንጨምርበት ወደ ላቀ የዕድገትና የተፈላጊነት ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችለን ዕምቅ ሀብትና አቅም እንዳለን በማመን ይህንን ያገኘነውን መልካም አጋጣሚ ለላቀ ውጤት ልንጠቀምበት ይገባል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011

በዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ጉግሳ ከበርሊን