‹‹ግንቦት 7›› የታሪክ ምስክር

223

• የመጽሐፉ ስም፡- ግንቦት 7

 – ኢትዮጵያ፡ እኮ ምን? እንዴት?

 • ደራሲ፡- ክፍሉ ታደሰ •

 የገጽ ብዛት፡- 243

• ዋጋ፡- 160 ብር

 የታሪክ ጸሐፊው ፍስሐ ያዜ ‹‹የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህአዴግ›› የተሰኙ ቅጽ 1 እና 2 መጽሐፎች አሉት። ቅጽ 2 መጽሐፉ ከልጅ እያሱ እስከ ኢህአዴግ ያለውን ይነግረንና የደርግ ዘመነ መንግስትን እንደጨረሰ ኢህአዴግ ገዥው መንግስት ስለሆነ ዜና እንጂ ታሪክ እንደማይሆን ይነግረናል። ሃሳቡ የሚያስማማ አይመስለኝም።

 የኢህአዴግ ዘመን በትክክል አልተጻፈም። በተደጋጋሚ እንደሚባለው በተቃዋሚዎችና በኢህአዴግ ደጋፊዎች መካከል ጽንፍ የያዘ አቋም ነው ያለው። በተለይ በኢህአዴግ ባለሥልጣናትና በደጋፊዎቻቸው ደግሞ ብዙም አልተጻፈም። ብዙ የተጻፉ መጽሐፎች ያሉት ከተቃዋሚዎች ጎራ ነው። በእርግጥ አልፎ አልፎ የጻፉ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ቢኖሩም አለመተማመን አለ። መጽሐፋቸው አይነበብም፤ አይታወቅም። በዚህ አጋጣሚ የአቶ በረከት ስምዖን ‹‹ትንሳኤ ዘ ኢትዮጵያ›› መጽሐፍ በቅርቡ በፍትሕ መጽሔት ላይ ዳሰሳ ተሰርቶበት አይቻለሁ።

በተቃዋሚዎች በኩል የሚጻፉ መጻሕፍትም በኢህአዴግባለሥልጣናትአይነበቡም። እውነትመስሎም አይታያቸውም፤ አለመተማመን አለ ማለት ነው። እንግዲህ በዚህ ሁኔታ በዘመነ ኢህአዴግ ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ መሃል ላይ ቀረ ማለት ነው። የመገናኛ ብዙኃን የሚያወጧቸው ዘገባዎችም እንደዚሁ ጫፍና ጫፍ የተካረሩ ስለሆኑ ቀጣይ የታሪክ ጸሐፊ መሃል ላይ ያለውን ነገር ሊያጣው ነው ማለት ነው። ምናልባትም መረጃ የሚገኘው ዘመኑን በመኖር ከሚያውቁት ሰዎች ሊሆን ነው።

ምርጫ 97 በኢህአዴግ ታሪክ ውስጥ በደማቁ የተጻፈ ክስተት ነው። ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም የተደረገው ምርጫ በኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ታሪክ ውስጥም ሰፋ ያለ ቦታ ይይዛል።

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የታሪክ ፀሐፊዎች የሚያስፈልጉን። ምርጫ 97 ብዙ ሰዎች በመኖር የሚያውቁት ነው። አንደኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ሆነው የሚያውቁት ነው። ለዚህም ነው በብዙ አጋጣሚዎች ስሙ ተደጋግሞ ይነሳል። ያም ሆኖ ግን ብዙ ሰው ያውቀዋል ማለት አይደለም።

ከ2008 ዓ.ም አካባቢ ጀምሮ አገሪቱ ውስጥ ጠንከር ያለ ግጭት እዚህም እዚያም መከሰት ጀምሮ 2010 ዓ.ም ላይ ኢህአዴግ ውስጥ ሌላ ለውጥ ተከሰተ። አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትርም ተሰየመ። የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት የነዚያ ግጭቶች ውጤትም ተደረገ።

እነዚያን ግጭቶች ያባባሳቸው ወጣቶች የሚሰሙትና የሚያዩት ነገር ነው። በሚያዩት ነገር በየአካባቢው የመሰረተ ልማት ችግር አለ፤ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ። በሚሰሙት ነገርም ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ የቆየው ምርጫ እያጭበረበረ ነው። በሚሰሙት ነገር ያልኩበት ምክንያት ወጣቶቹ ምርጫ 97ን በአንደኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭነት ሊያውቁት አይችሉም። እኔም አንድ ወጣት ነኝና መመስከር እችላለሁ። በ1997 ዓ.ም ፖለቲካዊ ጉዳይን የማወቅ ዕድሜ ላይ አልነበርኩም። ጉዳዩንም ያን ያህል አልከታተለውም። እኔን የሚያሳስበኝ የክፍል ደረጃዬ ብቻ ነበር። ይሄ የብዙ ወጣቶች ሁነት ይመስለኛል።

 ይህ ከሆነ የምርጫ 97 ታሪክ ለአሁኑ ወጣት መታወቅ አለበት ማለት ነው፤ አሁን ላለው ብቻ አይደለም፤ ለቀጣዩ ትውልድም የምርጫ 97 ታሪክ መቀመጥ አለበት። አብዛኛው ነገሩ እየተወራ ያለው በቃል ስለሆነ። ምርጫ 97ን የሚነግረን አንድ መጽሐፍ አግኝተናል።

ደራሲው ክፍሉ ታደሰ ነው። ክፍሉ ታደሰ የኢህአፓ መስራችና አመራር የነበረ ሲሆን ‹‹ያ ትውልድ›› የሚሉ መጽሐፎችን በቅጽ 1፣ 2 እና 3 አቅርቦልናል። ባለፈው ዓመት 2010 ዓ.ም ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፎቶ ያለበት ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ!›› የተሰኘ መጽሐፍም ለአንባቢ አድርሷል።

የዛሬው ጉዳያችን ግን ‹‹ግንቦት 7›› የተሰኘው የክፍሉ ታደሰ መጽሐፍ ላይ ነው። መጽሐፉ ስያሜውን ያገኘው ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ነው። ይዘቱ ስለዚያ ምርጫ ነው።

ስለ መጽሐፉ ማውራት ለምን አስፈለገ?

ይሄ መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ1998 ዓ.ም ነበር፤ በምርጫው ማግስት ማለት ነው። መጽሐፉ ግን አንባቢ ዘንድ ደርሶ እምብዛም አልታወቀም። የመጽሐፉ ደራሲም ከአገር ውጭ ነበር። በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሁኔታም እንዲህ አይነት መጽሐፎች እንደልብ የሚዘዋወሩበት አልሆነም። እንዲህ ተደብቆ 14 ዓመታት ተቆጠሩ።

 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት ብዙ ነገሮችን ቀየረ። በውጭ የሚኖሩ ተቃዋሚዎች ወደ አገር ቤት ገቡ፤ ተዘግተው የነበሩ መገናኛ ብዙኃን እንደገና ሥራ ጀመሩ። ይህን ተከትሎ ‹‹ግንቦት 7›› የተሰኘው የክፍሉ ታደሰ መጽሐፍም በቅርቡ በድጋሜ ታተመ።

መጽሐፉን ያሳተሙት በሱፈቃድ ታደሰ እና ኤሚ እንግዳ ናቸው። ጋዜጠኛ ኤሚ እንግዳ እንደምትለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ለውጥ ባይኖር ኖሮ መጽሐፉ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ አይታተምም ነበር። እስካሁንም ያልታተመው ባለፉት ዓመታት የነበረው ሁኔታ ምቹ ስላልነበረ ነው።

መጽሐፉ ምን ይዟል?

መጽሐፉ በአንደኛ ደረጃ የታሪክ ምስክርነት ነው የተጻፈው። አብዛኛው ሁነት ደራሲው በአይኑ ያየውና በጆሮው የሰማው ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ በወቅቱ ከሚታተሙ ጋዜጦችና የብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን የተወሰዱ መረጃዎች አሉት። ደራሲው ለየድርጊቶቹ ቀንና ቦታ፤ ሰዓት ሳይቀር እየጠቀሰ ነው የሚነግረን።

አተራረኩ እንደ ወረደ ነው። የስነ ጽሑፋዊ አጻጻፍ ውበት የለውም። እንዲያውም ጸሐፊው የጋዜጠኝነት ተፅዕኖ ያለበትም አስመስሎታል። ምክንያቱም የራሱ አተያይ አምብዛም የለበትም። በታሪክና ፖለቲካ መጽሐፎች ውስጥ የደራሲውን ስሜት ማግኘት የተለመደ ነበር። ከድርጊቱ ተነስተው የራሳቸውን ትንታኔና ትርጓሜ ይሰጣሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ግን የደራሲው ሃሳብ ብዙም አይታወቅም። የጽሑፉ አብዛኛው ክፍል ሀቅ ማስቀመጥ ብቻ ነው። እንዲያውም በአይኑ ያያቸውን ነገሮች ራሱ በአንደኛ መደብ (እኔ) ከመግለጽ ይልቅ ‹‹የመጽሐፉ ደራሲ›› እያለ ይገልጸዋል።

ደራሲው የፖለቲካ አቋሙ ምንም ይሁን ምን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ገለልተኛ መሆኑ ለታሪክ ጸሐፊዎች ጥሩ ትምህርት ይሆናል። እንደሚታወቀው ክፍሉ ታደሰ ፖለቲከኛ ነው። የፓርቲ መስራችና አባል ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲጽፍ ግን ከራሱ አተያይ ነጻ መሆኑ መጽሐፉን ሚዛናዊ ያደርገዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ የፖለቲካ መጽሐፎች ላይ አንድ ተደጋጋሚ አስተያየት አለ። ይሄውም ጸሐፊዎቹ የራሳቸውን አጀንዳ ብቻ ማራመዳቸው፤ ሚዛናዊ አይደሉም ማለት ነው። የመንግስት ባለሥልጣናት ሲጽፉ መንግስትን ያንቆለጳጵሱና አገር ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን ያገጠጠ ጥፋት ያልፉታል፤ ይባስ ብሎ እንዲያውም ዋሽተው ያሞካሹታል።

 በተቃዋሚዎችም በኩል ይሄው ነው። ገዥውን መንግስት አፈር ድሜ ሲያበሉት ተቃዋሚዎች ውስጥ ያለውን ችግር ግን አይጠቅሱትም። ለምሳሌ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ችግራቸውን ሁሉ ኢህአዴግ እንደፈጠረው ነው የሚናገሩት።

 ከታሪክ ጸሐፊ ደግሞ እንዲህ አይነት አድሎ አይጠበቅም። ትውልድን ማሳሳት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሌላም ሰው ሊጽፈው ስለሚችል የሚጣረሰው ነገር ይበዛል። ያኔ የታሪክ ጭቅጭቅ ይፈጠራል ማለት ነው።

 ክፍሉ ታደሰ በዚህ መጽሐፉ ተቃዋሚዎችንም አይምርም። እርግጥ ነው የምርጫ 97 ጥፋት የተፈጠረው በገዥው ፓርቲ አጭበርባሪነት እንደሆነ ይነግረናል። በንጹሃን ላይም የግፍ ጭፍጨፋ ያደረገው ኢህአዴግ ነው። ሆኖም ግን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ሆነ በግጭት ጊዜ በሚሰጡት መግለጫ ተቃዋሚዎች የነበረባቸውን ችግር ይነግረናል። ከተቃዋሚዎች የሚጠቀሟቸውን ቃላት ራሱ ‹‹ፀያፍ›› እስከማለት ድረስ ይተርክልናል።

ኢህአዴግም ለማጭበርበር የሚጠቀማቸውን ዘዴዎች ይነግረናል። አንድ ምሳሌ ብቻ እንውሰድ። ብዙዎች እንደሚሉት ኢህአዴግ ምርጫ የሚያጭበረብረው ኮሮጆ በመገልበጥ ነው። ከዚህ በተለየ ግን ክፍሉ ታደሰ እንደሚነግረን ምርጫው ፍትሐዊ ቢሆን እንኳን ኢህአዴግ በሌላ ዘዴ መራጭ ያገኝ ነበር። የምርጫ ትኩረቱን ከከተማ ይልቅ ገጠር ላይ ነው ያደረገው። ገጠር ላይ የየቀበሌ ካድሬዎቹን እየሰበከ አስቀሰቀሰ። ይሄ ደግሞ ተቃዋሚዎችን አንድ ነገር ጎድቷል። የገጠር ነዋሪ የመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ አይደሉም። ስለተቃዋሚዎች ምንም የሚያውቁት ነገር የላቸውም፤ ስለዚህ ከኢህአዴግ የተሻለ ፓርቲ ቢኖር እንኳን አያውቁም ማለት ነው።

 በሌላ በኩል ግልጹን ለመናገር የገጠር ነዋሪ ጥልቅ የፖለቲካ ግንዛቤውም የለውም። ኢህአዴግ የሰበከው ሁሉ እውነት ነው የሚመስለው። ኢህአዴግ በተፈጥሮ ያሉ ነገሮችን ሁሉ ‹‹እኔ ነኝ ያመጣሁልህ›› ቢለው እውነት የሚመስለው ማህበረሰብ ይኖራል። የእጅ አዙር ማጭበርበር ቢሆንም ኢህአዴግ ኮሮጆ ከመገልበጥ ይልቅ ይህን ዘዴ ተጠቅሞ መራጭ ያገኛል ማለት ነው። የፖለቲካ ግንዛቤው ቢኖራቸውና ተፎካካሪዎችን ቢያውቋቸው ኖሮ ቅንጅት በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልልም ያሸንፍ ነበር ማለት ነው።

 በመጽሐፉ ላይ የተገለጸ አንድ ገጠመኝ ልጥቀሰው። አንድ ስለአመራረጥ ሁኔታ ብዙም ግንዛቤ የሌላቸው ሴትዮ ወደምርጫ ጣቢያው ገቡ። ልክ እንደገቡ ‹‹የቱ ነው የቅንጅት ሳጥን?›› ብለው ጠየቁ። እንግዲህ ይሄ ማለት በኢህአዴግ ተማረው ነበር ማለት ነው።

 ሃሳቤን ከመቋጨቴ በፊት ስለዚህ መጽሐፍ አንድ ነገር ልበል (እንደማሳሰቢያም ጭምር ያዙት!)። መጽሐፉ የሁነት ሰነድ መጽሐፍ ነው። በዚያን ወቅት የነበሩ ሁነቶችን በቀንና በቦታ ግልጽ አድርጎ የሚያሳውቅ። ከመግቢያውና መውጫው አካባቢ በስተቀር የደራሲው ሃሳብና ስሜት አይስተዋልም።

ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ ላይ ዳሰሳ ሳደርግ ከመጽሐፉ ገጽና ምዕራፍ እየጠቀስኩ ማስቀመጡ ምቹ አልነበረም። ምክንያቱም የቱ ተጠቅሶ የቱ ይተዋል? በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሙያዊ አስተያየት ሳይሆን የመጽሃፍ ዳሰሳ ነው። በዚያ ላይ መጽሐፉ የስነ ጽሑፍ መጽሐፍ ቢሆን የሃሳብ ልዩነትም ይኖረው ነበር። ስለዚህ ማለት የሚቻለው መጽሐፉ የ1997 ዓ.ም ምርጫን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይ አንብቡት ብቻ ነው!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011

ዋለልኝ አየለ