ከፖስታ አመላላሽነት ወደ ፋብሪካ ባለቤትነት ያሸጋገረች የሻይ ማሽን

155

በልጅነቱ ፈጣን አዕምሮ ነበረው። ገና በወጣትነቱ አንድ የቅርብ ስጋ ዘመዱ የመንግስት ደህንነት ቢሮ ሰራተኛ እንዲሆን አጩት። እርሱ ግን ዝንባሌው ወደቴክኒክ እና የተበላሹ ዕቃዎችን ወደመፈታታቱ ያደላ ነበር። የስለላ ስራው ብዙም ከነብሱ ጋር ዝምድና እንዳልነበራት ያወቀው ከባከኑ ብዙ ጊዜያቶች በኋላ ነበር።

 ወርቅነህ አዳሙ ይባላል። በአዲስ አበባ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው። በልጅነቱ ፊልም ሲመለከት ቴክኖሎጂ የሚሰርቁ ሰላዮችን አይቶ ልቡ እንደነሱ ለመሆን መከጀል ጀምሮ እንደነበር ያስታውሳል።

አጎቱ ደግሞ በደርግ ዘመን የኢኮኖሚ ደህንነት ቢሮ ውስጥ ይሰሩ ስለነበር በእርሳቸው ጥቆማ ለደህንነት ሰራተኝነት መመልመሉ ይገርመዋል። የካቲት 12 ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀ ለኢኮኖሚው ደህንነት ቢሮ ሰራተኝነት የሚያበቃውን የስድስት ወር ስልጠና በ1980 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲወስድ ይደረጋል።

ቅልጥፍናው እና ነገሮችን ቶሎ የመረዳት ችሎታውን የታዘቡት ከስልጠናው በኋላ ለስራ ብቁ መሆኑን ገምግመው ያሰማሩታል። እዚያው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ ፕሮክተር ወይም ተማሪዎችን ተቆጣጣሪ አድርገው ይመደቡታል። የስለላ ስራውን አሃዱ ብሎ በጀመረበት ዩኒቨርሲቲ ከተማሪዎች ጋር በመግባባቱ የስልጠና ክፍላቸው ድረስ እየሄደ አንዳንድ ማሽንኖች እንዴት እንደሚፈታቱ ማየት ይጀምራል።

የደህንነት ስራው ላይ እንዳለ መንግስት ተቀየረ። ኢህአዴግ ወደስልጣን በመምጣቱ የቀድሞው የስለላ መዋቅር ስለፈረሰ ወጣቱ ወርቅነህ በዛው ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የፖስታ ሰራተኛ ሆኖ መስራት ቀጠለ። በወቅቱ በፖስታ አመላላሽነት በቀን ሶስት ብር ደመወዝ ይከፈለው ነበር።

 በዚህ የዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከአንድ የሳይንስ ፋኩልቲ ተማሪ ያወራው የባቡር የእንቅስቃሴ ምንጭ እና የሻይ ማሽን አሰራር አዕምሮው ውስጥ ይመላለስበት እንደነበር ያስታውሳል። አንድ ጊዜ የተገነዘበውን ነገር የማይረሳው ወርቅነህ ከወዳደቁ ብረቶች የሰራውን የሻይ ማሽን ለተማሪው ያሳየዋል። ይሁንና የሻይ ማሽኗ ብዙም ትኩረት ባለማግኘቷ መኖሪያ ግቢው ውስጥ እንድትቀመጥ ይፈረድባታል።

 ፖስተኛ ሆኖ አራት ዓመታት እንደሰራ የኋላ ታሪኩ መታየት ይጀምራል። የቀድሞ ደህንነት ስራው በመታወቁ ከዩኒቨርሲቲው እንዲሰናበት የሚል ደብዳቤ ተጻፈበት። በወቅቱ የቆጠባት ስድስት መቶ ብር ነበረችውና እሷኑ ይዞ ባለችው ጥቂት ዕውቀት ታግዞ የግሉን የማሽን ጥገና ለመስራት ይወስናል። ከስራ ከተባረረ በሁለት ሳምንት ውስጥ ትርፍ አንጀት በመታመሙ ምክንያት ለህክምና እና ለተለያዩ ወጪዎች ከያዛት ስድስት መቶ ብር ላይ ከፍሎ ያመናምናታል።

 ህክምናውን በሰላም ሲጨርስ እጁ ላይ 60 ብር ብቻ ይቀረዋል። «ዋናው ነገር ጤና ነው» ብሎ ምን እንደሚሰራ እያሰላሰለ ሳለ በመንደሩ ከሚገኙ ጮርናቄ ቤቶች መካከል ሻይ ለመጠጣት ወደ አንዱ ቤት ጎራ ይላል። በወቅቱ የቀረበለት ሻይ ደግሞ በማሽን ብልሽት ምክንያት ጣዕሙን የቀየረ ነበር። ወዲያውም ባለቤቱን ያስጠራና «እኔ የሰራሁት የሻይ ማሽን አለኝ ለምን በነጻ አትሞክረውም» ይለዋል።

የጮርናቄ ቤቱ ባለቤት ግን የመጀመሪያ መልሱ የነበረው «የሰራኸው ማሽን ቢፈነዳስ?» የሚል እንደነበር 24 ዓመታትን ወደኋላ በሀሳብ ተጉዞ ሲያስታውስ ይደንቀዋል። በእራሱ እጅ የሰራትን የሻይ ማሽንም በነፃ ሰጥቶ እየሰራ ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል ካሳየ እና እንደማትፈነዳ ካረጋገጠለት በኋላ ባለቤቱ እራሱ ይጠቀምባት ጀመር።

 ከዚህ በኋላ ማሽኗን የሚጠቀመው የሻይ ደንበኞች መጉረፍ ጀመሩ። ባለቤቱም የጎረቤቶቹን ደንበኞች ጭምር መሳብ ቻለ። ገበያው ስለደራለት ምስጋናውን ለአቶ ወርቅነህ ማቅረቡን ቀጥሏል። በዚህ ወቅት ነበር የሻይ ማሽኗ ጠቀሜታ ወደገንዘብ የሚቀይርበት አጋጣሚ የተፈጠረው። ጉዳዩን የሰማና ደንበኞቹ የራቁት ከጮርናቄ ቤቱ ጎን የሚገኝ የሻይ ቤት ባለቤት ወርቅነህን ያስጠራና «አንተ በነጻ የሻይ ማሽን ሰርተህ ለጎረቤቴ እንደሰጠህ ሰምቻለሁ፤ በዚህ ምክንያት ገበያው ስለራቀኝ እኔ ማሸኑን በወር በ250 ብር ልከራይህ» የሚል ብስራት ያሰማዋል። ይህን የሰማውና ቀድሞ ማሽኗን በነጻ ይጠቀም የነበረው የጮርናቄ ቤት ባለቤትም በወር 250 ብር ለመክፈል ፍላጎቱን ያሳያል።

 ከዚህ በኋላ አቶ ወርቅነህም ሌላ ማሽን ከወዳደቁ ብረቶች ሰርቶ ለጎረቤታሞቹ እያከራየ ከሁለቱም በወር 500 ብር መቀበሉን ይጀምራል። አንዱ ለአንዱ እያጫወተ ከጣሊያን ከሚመጣው የሻይ ማሽን ይልቅ በአቶ ወርቅነህ ግቢ የሚሰራው ማሽን በዋጋም ሆነ በጥንካሬ እንደሚያይል የተረዱ ሰዎች ይበዛሉ። የማሽኗ ተፈላጊነትም ካሰበው በላይ ጨመረ።

 ፈላጊው ሲበዛም ከግቢው ወጥቶ ካዛንቺስ አካባቢ አንድ ቦታ ላይ መስራት ይጀምራል። አቶ ወርቅነህ ከሻይ ማሽኗም በተጨማሪ በየቦታው የሚያያቸውን የተለያዩ ማሽኖች በአገር ውስጥ መስራት እንደሚቻል ተረድቷል። በተለይ የዳቦ ማቡኪያና መጋገሪያ፣ የውሃ ማሞቂያ፣ የቡና እና የሽንኩርት መፍጫዎችን እንዲሁም የተለያዩ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ማሽኖችን ማምረቱን ተያይዞታል። ገበያውም ገበያ እያመጣ ከማሽን ስራው በተጨማሪ የማሽን ጥገና ስራ ውስጥም ገብቷል።

 ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረስ የተለያዩ ተቋማትን በርካታ ማሽኖች ማደሱን ይናገራል። ለአቶ ወርቅነህ ሱስ የሚባል ነገር ሲያልፍም አይነካካውም። ቁጠባም ዋናው ተግባር በመሆኑ አንዱን ማሽን በ10ሺ ሌላውን በ20ሺ እየሸጠ በሀብት ላይ ሀብት መጨመሩን ቀጠለ። በዚህ ወቅት ግን የቀበሌ አስተዳደሮች ወርክሾፑን «እኛ ነን የሰራነው» በሚል ሰበብ የኪራይ ውል ለማዋዋል እና እጅ መንሻ ለመቀበል ይፈልጋሉ።

 ከካዛንችሱ ወርክሾፕ ወጥቶም ኮተቤ አካባቢ ለአነስተኛ አምራቾች የተዘጋጀ ሼድ ውስጥ ለመግባት ያመለክታል። በወቅቱ ሼዱ ዝናብ ያፈረሰው በመሆኑ ሰርቶ እንዲገባበት ይፈቀድለታል። 40ሺ ብር አውጥቶ ካደሰና መስራት ከጀመረ በኋላ ግን እዚህም የቀበሌ ሰራተኞች ይነሳበታል። «ሼዱን የገነባሁት 80 ሺ ብር አውጥቼ ነው በልና የኪራይ ውሉን ለረጅም ዓመት አራዝምልሃለሁ፣ ለእኔም የተወሰነ ጉቦ ትሰጠኛለህ» ቢባልም አቶ ወርቅነህ አልፈልግም በማለቱ ወርክሾቹ በግፍ እንደተዘጋበት ያስታውሳል።

ተስፋ የማይቆርጠው ወርቅነህ ታዲያ ኡራኤል አካባቢ ቆሻሻ አንስቶ ባዶ መሬት ላይ የስራ ቦታውን ያዘጋጃል። በ1994 ዓ.ም ኡራኤል አካባቢ ሲሰራ ከሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ማሽኖች በተጨማሪ 300 የሚደርሱ የሻይ ማሽኖችን በ250 ብር የወር ክፍያ ያከራይ ነበር። የማሽን ስራውም እየተስፋፋ በመምጣቱ የሊዝ ማሽን፣ ቶርኖ ማሽን እና የተለያዩ ማጠፊያና መቁረጫ እንዲሁም እንደብረት ማቅለጫ የመሳሰሉ ግዙፍ ማሽኖችን ገዛ።

 ከትራክተር መገጣጠም ጀምሮ ሲሚንቶ ማቡኪያ እና ብሎኬት ማምረቻ፤ እንዲሁም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ማሽኖችን በማዘጋጀት ስራውን ማስፋፋቱን ተያያዘው። ለሰራተኞቹ ዕውቀቱን አይቆጥብም። በሙከራ በታጀበ ስራ አስተማማኝ እውቀት እንዲኖራቸው አድርጓል። ለዚህ ደግሞ ምስክሩ በአንድ ወቅት የነበሩት 18 ሰራተኞች የግል ስራቸውን እየጀመሩ መውጣታቸውንና እራሳቸውን መቻላቸውን ነው።

ከትምህርት ቤት ለሚወጡ የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎችም በእራሱ አነሳሽነት እያሰለጠነ ይገኛል። ይህን ሁሉ ሲሰራ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ እንዳልነበሩ አቶ ወርቅነህ ይናገራል። በየወቅቱ ከደረሰበት የቀበሌ አስተዳደሮች የእጅ መንሻ ጥያቄ ፈተና በተጨማሪ የኪራይ ውል ማፍረስ ለስራው እንቅፋት ሆኖበት ቆይቷል። ከሁሉም በላይ ግን የኮተቤው ወርክሾፕ ከነእቃው ለአምስት ዓመታት በግፍ እንዲዘጋ የተደረገበትን አጋጣሚ አይረሳውም። ከአምስት ዓመታት ንትርክ በኋላ ግን 17 ሺ ብር ከፍሎ እቃውን በዕጁ አስገብቷል።

በሌላ በኩል የሻይ ማሽን ያከራያቸው አንዳንድ ሰዎች ኪራይ አለመክፈል ክህደት የአንድ ወቅት ፈተናዎቹ እንደነበሩ ይገልጻል። በነዚህ ሁሉ ጊዜያት ግን ሰርቼ አገኘዋለሁ የሚል እንጂ አንድም የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዳልነበረው ይመሰክራል። ከማሽን ስራው በተጓዳኝ ደግሞ የፈጠራ ስራዎች ላይ በየዕለቱ ሙከራ ያደርጋል።

 የብረት መቁረጫ «ግራይንደር ዲስክ» እና የትራንስፎርመር ፊውዝ ማምረት የሚችልበትን የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ምዝገባ ለማከናወን ደፋ ቀና እያለ ይገኛል። ሁለቱንም ምርቶች በአገር ውስጥ ከሚገኙ አፈሮች የሚያዘጋጃቸው በመሆኑ እና ጥንካሬያቸውን አስተማማኝ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ ሰፊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይገልጻል። በተለይ የትራንስፎርመር ፊውዝ ስራው ላይ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ከኤሌክትሪክ ዘርፍ ጋር የተያያዙ ተቋማት በራቸውን ቢያንኳኳም የሰጡት ትኩረት አነስተኛ ሆኖበታል። «ጉትጎታ የሚፈልጉ ተቋማት በመበራከታቸውና እኔም አብዛኛውን ጊዜ ወርክሾፕ ውስጥ ስለማሳልፍ ለአገር ኢኮኖሚ እና ለስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው የፊውዝ እና የግራይንደር ዲስክ ስራዎች ተጓተውብኛል» በማለት ያማርራል።

ከዚህ በተጨማሪ ግን «የፌሮ ስቱኮ» የተባለ ኬሚካል ለማምረት የሚያስችል ሙከራ እና ጥናት እያደረገ ይገኛል። በስራው ከረካባቸው ቀናት መካከል የእጁ ውጤት የሆነው የጫጩት ማስፈልፈያ ማሽን የመጀመሪያውን ጫጩት ሲፈለፍል ሲያይ የነበረውን ደስታ አይረሳውም። ከ21 ቀናት በኋላ የመጀመሪያው ሙከራ ሰርቶ አንድ ጫጩት ስትፈለፈል በደስታ መሬት ላይ መንከባለሉን ይናገራል። ሃሳብ ብቻ ይዘው መጥተው ወደማሽን የተቀየረላቸው አነስተኛ የሳሙና እና የኬሚካል አምራቾች የተሰራላቸውን ማሽን ተጠቅመው ውጤታማ ሲሆኑም ለእርሱ ትልቁና የማይዘነጋው የደስታ ምንጭ ነው።

 አቶ ወርቅነህ አሁን ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ አምራችነት በመሸጋገሩና የደንበኞቹ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ቃሊቲ አካባቢ ሁለት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ ገዝቷል። ቦታው ላይ ለተለያዩ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆኑ መለዋወጫዎችን ለማምረት የፋብሪካ ግንባታ እያካሄደ ይገኛል። ፋብሪካው ሲያልቅ ከአንድ መቶ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚችል ዕቅድ ይዟል።

የፋብሪካው መጠናቀቅ ደግሞ ከትንሽ እስከ ትልቅ ፋብሪካዎች የሚሆኑ የማሽን መለዋወጫ ዕቃዎችን በማምረት የውጭ ምንዛሪን ማዳን እንደሚችል ያምናል። ሩብ ምዕተ ዓመት ከሚጠጋ የማሽን ስራ ሙያ ጋር የቆየው አቶ ወርቅነህ ለሁለት ልጆቹ እና ለባለቤቱ የሚሆን ዘመናዊ መኪና እና ሶስት ቤቶችን ገዝቷል።

 ወርክሾቹ እና እየተገነባ ያለው ፋብሪካው ተደማምረው እስከ 25 ሚሊዮን ብር እንደሚደርሱ ይናገራል። የሆነው ሆኖ ከፖስታ አመላላሽነት ተነስቶ አሁን ላይ የውጭ ምንዛሬ የሚያድን የመለዋወጫ እቃዎች ፋብሪካ እየገነባ መሆኑ ሰው ከሰራ መለወጥ እንደሚችል ህያው ምስክር ሆኗል። አቶ ወርቅነህ ከምክሩ ሲያካፍል፤ ለስራ የተነሱ እጆች ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ለሰሩ እጆች ማበረታቻው ደግሞ የአገር ምርትን መጠቀም ነው። የውጭ ዕቃ መጠቀም እንደስልጣኔ የሚታይበት ዘመን አብቅቷል። ለዚህ ደግሞ ጣሊያናውያንን እና ህንዶችን ምሳሌ ማድረግ እንደሚቻል ይናገራል። ቸር እንሰንብት!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011

ጌትነት ተስፋማርያም