የአየር መንገድ ክራሞት

81

 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አወሮፕላን መከስከስ የሰማሁት ኢሲኤ አዳራሽ ውስጥ ስብሰባ ውስጥ ሆኜ ነበር። ባልደረባዬ በቢሾፍቱ አቅራቢያ አውሮፕላን ተከስክሶ ሰዎች ማለቃቸውን ሲያረዳኝ ድንጋጤው ክው አድርጎኛል። እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ይገኙበታል የተባለው የምክክር መድረክ ላይ የተገኘሁት ማልጄ ነበር። ይሁን እንጂ ጠቅላዬ አልተገኙም። የስብሰባው አዘጋጆችም በግምት 3፡ 30 ገደማ ወደ መደበኛ ስብሰባ ማስጀመር ገቡ። በዚያች ቅጽበት ግን አገር ሐዘን ላይ መሆኗን ማንም አልተረዳም ነበር። ምናልባትም ዶክተር ዐብይ በድንገት ከስብሰባው የቀሩበት ምክንያት ይህ ሊሆን እንደሚችል የገባኝም ዘግይቶ ነው።

አዎ! የኢትዮጵያ አየር መንገድ 73 ዓመታን ያስቆጠረ አዛውንት ድርጅት ነው። በአቪየሽን ኢንዱስትሪ ስመ ጥር ነው። በዕድሜም በልምድም ጎልምሰናል ከሚሉት አየር መንገዶች ተርታ የተሰለፈ ነው። አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኩራት ነው ሲባል የሚሰማውም አንዱ ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።

በአገር ግዙፍና ዘመናዊ አውሮፕላን ተሳፍሮ፣ በአገር ልጆች ተስተናግዶ የሚፈልጉበት ቦታ/አገር መድረስ የሚሰጠው ውስጣዊ በጎ ስሜት እያንዳንዱ ሰው የሚያውቀው ነው። ከአንድ ዓመት በፊት ለሥራ ከሄድኩበት ጀርመን፣ ፍርንክፈርት አየር ማረፊያ ውስጥ ቁጭ ብዬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በቅጥር ግቢ ውስጥ ሲንጎማለል በማየቴ ብቻ የተሰማኝ ኩራትና ደስታ በቃላት ልገልጸው የማልችለው ነበር።

ይህ ዓመታትን የዘለለው የአየር መንገዱ ክብርና ዝና ግን ያለእንቅፋት አልጋ በአልጋ የመጣ ነው ማለት አይቻልም። አየር መንገዱ ባለፉት 73 ዓመታት ብዙ እንቅፋቶችን ተሻግሯል። መውደቅ፣ መነሳትም ቢሆን እንደሌሎቹ ሁሉ ለአየር መንገዱ አዲስ ነገር አልነበረም። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ጎላ ካሉ የቅርብ አደጋዎች (በጠለፋና በቴክኒክ ብልሽትና በሌሎች) አንዳንዶቹን አለፍ አለፍ ብለን እንቃኛቸው።

ህዳር 14/1989፤ ኮሞሮስ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET 961 (ቦይንግ 767- 260ER ) ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ 175 መንገደኞችን አሳፍሮ በመጓዝ ላይ ሳለ ሶስት ኢትዮጵያን ወደ አውሮፕላኑ መቆጣጠሪያ ክፍል በኃይል ጥሰው ገቡ። ለአብራሪዎቹ የበረራ አቅጣጫቸውን ወደ አውስትራሊያ እንዲያደርጉ ቀጭን ትዕዛዝም አስተላለፉ። ሶስቱ ጠላፊዎች «አውስትራሊያ አድርሱን!… ካልሆነ አውሮፕላኑን በቦምብ እናጋየዋለን» ሲሉ ዛቱ። የአውሮፕላኑ ካፒቴኖች ተጨነቁ። መሳሪያ ተደቅኖባቸውም በቂ ነዳጅ እንደሌላቸውና በአቅራቢያ ባለ አውሮፕላን ማረፊያ አርፈው ነዳጅ እንዲቀዱ እንዲፈቅዱላቸው ጠላፊዎቹን ተማፀኑ። ሆኖም በነፍሳቸው የቆረጡት ጠላፊዎች ፈቃደኛ አልሆኑም። ወደ ናይሮቢ የሁለት ሰዓት ተኩል ጉዞ ለማድረግ ከአዲስ አበባ የተነሳው አውሮፕላን ከአራት ሰዓት በላይ አየር ላይ በመቆየቱ ነዳጁን ጨረሰ።

አብራሪዎቹ ዋና ካፒቴን ልዑል አባተና ረዳት አብራሪው ዮናስ መኩሪያ መላ ዘየዱ። ምንም ምርጫ ስላልነበራቸው አውሮፕላኑን ውሃ ላይ ጥለው የተወሰነ ሰው እንዲተርፍ መሞከር እንዳለባቸው በዓይን ጥቅሻ አወሩ። በደቡብ ምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው ኮሞሮስ ደሴት ህንድ ውቅያኖስ ላይ አውሮፕላኑን ጣሉት። በዘርፉ ኤክስፐርቶች የጨዋ አነጋገር «አውሮፕላኑ ተከሰከሰ»

ኮሞሮስ፣ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ሲዝናኑ የነበሩ ጎብኚዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በከፍተኛ ድንጋጤ ተመቱ። አንዳንዶች ይህንን አሳዛኝ ክስተት በካሜራቸው ቀርጸው ለማቆየት ሲጣደፉ አንዳንዶች ደግሞ በነፍስ አድን ሥራ ላይ ወዲያውኑ በመሰማራታቸው ብዙ ሰዎችን በሕይወት መታደግ ቻሉ።

በወቅቱ የአውሮፕላኑ አካል ከውሃው ጋር በመላተሙ ተሰባብሮ በርካቶች ህይወታቸውን እንዲያጡ ምክንያት ሆነ። አውሮፕላኑ 175 ተጓዦችንና የበረራ ቡድን አባላትን አሳፍሮ የነበረ ሲሆን በአብራሪዎቹ ብስለት የተሞላበት ውሳኔ ጥቂት ሰዎችም ቢሆን መትረፍ ቻሉ። በአደጋው 125 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ 50 የሚሆኑት ደግሞ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። እንደዕድል ሆኖ ጠላፊዎቹ ከአደጋው ተርፈው ለከባድ ጥፋታቸው ቅጣታቸውን ለመቀበል አልታደሉም፤ እነሱም ከሟቾቹ ወገን ነበሩና።

ጥር 17 ቀን 2002 ቤይሩት

ከሊባኖስ ርዕሰ መዲና ቤይሩት ወደ አዲስ አበባ እያመራ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 730-800 አውሮፕላን አየር ላይ ተበታትኖ ሜዲቴራንያን ባህር ላይ ወደቀ። በዚህ አደጋ 90 ሰዎች አልቀዋል።

አየር መንገዱ አደጋው ከሽብር ወንጀል ጋር ግንኙነት እንደሌለው በይፋ ከመግለጽ ባለፈ እስካሁን ስለአደጋው መንስኤ በይፋ የገለጸው ነገር ስለመኖሩ ያገኘሁት መረጃ የለም።

በበረራ ዋስትናው ዝና ካተረፉ አየር መንገዶች የሚጠቀሰው አየር መንገዱ እ.አ.አ ከ 1980 በኋላ ሶስት አሰቃቂ የአውሮፕላን አደጋዎችን አስተናግዷል።

የአየር መንገዱ ስኬት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት አየር መንገዱ ባለፉት ስምንት ዓመታት ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ መሆኑን በህዳር ወር 2011 ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር። በራዕይ 2025 ላይ የተቀመጡትን አብዛኞቹን ግቦች በማሳካት ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ በአውሮፕላኖች ብዛትና በበረራ መዳረሻዎች የተቀመጡትን ግቦች ከዕቅዱ ዘመን ሰባት ዓመት ቀደም ብሎ ማሳካት መቻሉን፣ በአቪዬሽን አካዳሚው ላይ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ሰፊ የማስፋፊያ ሥራ ማከናወኑን፣ ዘመናዊ የምግብ ማደራጃ፣ የአውሮፕላን ጥገና ሐንጋሮች መገንባቱን፣ በራዕይ 2025 የተቀመጡ ግቦችን ማሳካት በመቻሉ ዕቅዱን በመከለስ ራዕይ 2030 በመዘጋጀት ላይ እንደሆነ ተነግሯል።

አየር መንገዱ በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት ዘጠኝ የትርፍ ማዕከላት ያሉት የአቪዬሽን ቡድን መስርቷል። ዓለም አቀፍ አየር መንገድ፣ የአገር ውስጥና ክልላዊ አየር መንገድ፣ ካርጎ፣ ኬተሪንግ፣ ጥገና ማዕከል፣ አቪዬሽን አካዳሚ፣ ግራውንድ ሃንድሊግ፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች፣ ሆቴልና የጉዞ አገልግሎት ዘርፍ ናቸው። የኤሮስፔስ ማምረቻ ተቋም ለመመሥረት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።

አየር መንገዱ በ65 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በቅርቡ አስመርቋል።

የተለያዩ ክልላዊ መናኸሪያዎችን ለማቋቋም በታቀደው መሠረት በቶጎና በማላዊ በሽርክና አየር መንገዶች ማቋቋሙን፣ በሞዛምቢክ፣ በዛምቢያ፣ በቻድና በጊኒ አዳዲስ አየር መንገዶች ለማቋቋም ስምምነቶች ተፈርሞ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገዱ ገንዘብ በሚበደርበት ወቅት ግልጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ባንኮችን አወዳድሮ እንደሚበደር፣ ብድሩንም በአግባቡ በመክፈል ላይ እንደሆነ ተጠቅሷል። የብድር መጠኑም 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ተብሏል።

ከ100 በላይ አውሮፕላኖች ባለቤት

አየር መንገዱ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር 100ኛ አውሮፕላኑን የተረከበው በከፍተኛ ሥነሥርዓት ነው። ግንቦት 30 ቀን 2010 በተከናወነው ሥነሥርዓት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ100 አውሮፕላኖች የበረራ አገልግሎት መስጠት በመጀመር በአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ አዲስ ታሪክ ማስመዝገቡ ተነግሯል። በዕለቱም አየር መንገዱ 100ኛ የሆነውን ቦይንግ 787-900 አውሮፕላን ተረክቧል።

በ100 አውሮፕላን አገልግሎት መስጠት በመቻሉም አየር መንገዱ በአፍሪካ በዘርፉ እየተጫወተ ያለውን የመሪነት ሚና ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የሆኑትን ቦይንግ 787 እና ኤርባስ 350 አውሮፕላኖችን በመግዛት ለተሳፋሪዎች ምቹ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ለደንበኞች አፍሪካን ከሌላው ዓለም ጋር የማገናኘት ተግባር በስፋት እያከናወነ ነው።

በቀጣይ ተጨማሪ የአውሮፕላን ግዢዎችን በማከናወን በአፍሪካ ያለውን የጉዞ ፍላጎት ለማሟላትና የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የንግድ ፍሰቱን በማመቻቸት ለአህጉሪቷ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ትስስር እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው 100 አውሮፕላኖች 72ቱ የአሜሪካው የአውሮፕላን አምራች መሆኑን ጠቁመው ይህ የሚያሳየው ሁለቱ አየር መንገዶች ያላቸውን ትብብር እንደሆነም ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓት አየር መንገዱ አውሮፕላኖች ቁጥር 111 ደርሷል። አየር መንገዱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2012 ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን እንዲሁም በ2016 ኤር ባስ ኤ350 ደብሊው ኤክስ ቢ አውሮፕላንን በመግዛትና በመጠቀም በአፍሪካ የመጀመሪያው አየር መንገድ እንደሆነም ይታወቃል።

6 ነጥብ 87 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ

አዲስ አበባ ነሃሴ 4/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አምና (እ.አ.አ 2017/18 ) በዘንድሮው ዓመት 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል። ትርፉ የተገኘው መንገደኞችን በማጓጓዝ፤ በእቃ ጭነትና በሌሎች የሎጅስቲክስ አገልግሎቶችን በመስጠት ነው።

አየር መንገዱ በ2017/18 የፈረንጆች ዓመት 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ተገልጿል። ከአምናው ጋር ሲነጻጻር 25 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። አየር መንገዱ በዓመቱ 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን መንገደኞችን ያጓጓዘ ሲሆን በመንገደኞች ብዛት ከአምናው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ21 በመቶ እድገት አሳይቷል።

በእቃ ጭነትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ደግሞ 400 ሺህ 339 እቃዎችን በማጓጓዝ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ እድገት አስመዝግቧል።

እንደመውጫ

ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ተነስቶ ወደ ኬንያ በማምራት ላይ የነበረው አውሮፕላን እሁድ ዕለት ባጋጠመው አደጋ የ157 ሰዎች ሕይወት ቀጥፏል። ከእነዚህ መካከል 18ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የአስከሬን መፈለጉና ወደቤተሰብ መላክ እንዲሁም የአደጋውን መንስኤ የሚመረምር ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ በውጭ አገር ባለሙያዎች ድጋፍ ጭምር እየተከናወነ መሆኑ ከአየር መንገዱ የሚወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።

በተጨማሪም አየር መንገዱ በእጁ የሚገኙት አራት 737- 8 ማክስ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ላተወሰነ ጊዜ ማገዱን አስታውቋል። ካለፈው ሰኞ ዕለት ጀምሮ የተጣለው ይኸው እገዳ ምናልባትም የአደጋው መንስኤ ተጣርቶ እስኪታወቅ ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ተገምቷል።

ቻይናም በሀገሯ የሚገኙ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቿ በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኗም ተነግሯል። የቻይና የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የቻይናን አየር መንገዶች ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖችን ለበረራ መጠቀም እንዲያቆሙ አስታውቋል።

ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኘው አውሮፕላን ባለፉት አምስት ወራት የመከስከስ አደጋ ሲያጋጥመው የትናንቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።ከአምስት ወራት በፊት ላዮን ኤየር የተሰኘ የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ ሞዴል አውሮፕላን ለበረራ በተነሳ በደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሶ 189 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም አየር መንገዱ የገጠመው የመከስከስ አደጋ ከአውሮፕላኑ የምርት የቴክኒክ ብቃት ችግር ጋር በማያያዝ ሰፊ ትንታኔ ሲሰጡበት ሰንብተዋል።

አደጋው ምንም እንኳን በቀላሉ የሚታይ ባይሆንም በበረራ ደህንነት ብቃቱ ዓለም የመሰከረለትን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ይበልጥ እንዲበረታ፣ ይበልጥ ለበረራ ደህንነት እንዲጠበብ፣ እንዲጨነቅ ከማድረግ በዘለለ ከባድ አሉታዊ ጫና አለማድረሱን በየዕለቱ ሰዓታቸውን ጠብቀው እየተከናወኑ የሚገኙ በረራዎችኛ ተያያዥ ሥራዎች በራሳቸው ጮኸው የሚናገሩ ናቸው።

ባለፈው ሰኞ ዕለት ከካናዳ ሞንትሪያል 189 መንገደኞችን ይዞ ወደአሜሪካ ፍሎሪዳ ሲጓዝ የነበረ ይኸው መዘዘኛው 737- 8 ቦይንግ ማክስ አውሮፕላን በካርጎው በኩል በተነሳ ጢስ ምክንያት በረራውን አቋርጦ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ኒውጀርሲ አውሮፕላን ጣቢያ ለማረፍ ተገዷል። አብራሪዎቹ ፈጥነው በወሰዱት እርምጃ መንገደኞችን ከአስከፊ አደጋ መታደግ ችለዋል።

ከአምስት ወራት በፊት በኢንዶኒዥያ የተከሰከሰው ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን እና የአዲስ አበባው የሰሞኑ አደጋ አውሮፕላኖቹ በተነሱ በጥቂት ደቂቃዎች መከስከሳቸውና ከፍተኛ እልቂት ማስከተላቸው ያመሳስላቸዋል። የእነዚህ የአውሮፕላን ሞዴሎች በቀጣይ የእልቂት ምንጭ እንዳይሆኑ ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ዕለት ድረስ የቻይና፣ የኢንዶኔዥያ፣ የሲንጋፖር፣ የካይመን፣ የኮንኤየር ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች እርምጃ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል። እስካሁን አሜሪካንን ጨምሮ አስር ሀገራት 737 – 8 ቦይንግ ማክስ አውሮፕላን እንዳይበር አግደዋል።

(የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ይህን መጣጥፍ ለማዘጋጀት በግብዐትነት የቢቢሲ፣ የጀርመን ድምጽ፣ የዊኪፒዲያ፣ የሪፖርተር፣ የኢዜአ፣ የፋና፣ የዋዜማ ራዲዮ፣ የኢት/አየር መንገድ መግለጫና ዘገባዎችን ተጠቅሜአለሁ)

አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2011

 ፍሬው አበበ)