ተረት ተናጋሪው አባት

31

 ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት። መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል። ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል። አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል።ይህ የህይወት እውነታ ነው። በጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ። የህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ። በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹ እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ለተቸገሩት ያዝናሉ። ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ። በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ። በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤ ¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ። ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።

 የሐዋሳ ከተማን የውበት ካባ ወደአጎናፀፈው ፍቅር ሃይቅ አመራሁ። ከሀይቁ ዳር ከተገነባውና እጅ አጠሮች ለመዝናናት ብዙም ወደማይደፍሩት ቅንጡው ሌዊ ሪዞርት አቀናሁ። ከእንግዳ መቀበያ ክፍል ጎራ ብዬ ግቢ ውስጥ ተረት እየተናገሩ፤ ስለታሪክ እየመሠከሩ የሚኖሩት አባት ላገኛቸው እንደመጣሁ አስረዳሁ። ይሁንታቸውን ገለፁልኝ።

በመሰል ሪዞርቶችና ትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ ‹‹ውስኪ ቤት፣ ምግብ ቤት፣… ቤት… ቤት… ቤት›› ውጭ ‹‹ተረት ቤት›› ይኖራል ብሎ መገመት ቀልድ ይመስላል። ተረት ቤቱ ከውጭኛው እስከ ውስጠኛው ክፍል ሙሉ ለሙሉ የገጠር ቤት ገፅታን የተላበሰ ነው። ተረት ቤቱ ውስጥ ከገቡ በኋላ ከከተማ ርቀው ገጠር ውስጥ ያሉ እንጂ፤ ሐዋሳ ውስጥ ስለመሆንዎ ይጠራጠራሉ።

ተረት ተናጋሪው አባባ ታደሰ አሰፋ ይባላሉ። ብን! ብን! የሚለው ስስ ሸበቶ ሉጫ ፀጉራቸው ውበታቸውን አላጓደለባቸውም። ከፊት ለፊታቸውና ከታችኛው ድድ ላይ ካሉት ጥቂት ጥርሶች ውጭ ጥርስ አልባ ናቸው። ግን ፈገግ ሲሉ፤ የጠቆረን ፊት እንደ ጥዋት ጀንበር ያፈካሉ። ንግራቸው ሁሉ ያስቃል። እኔና የሥራ ባልደረባዬን ‹‹ልጆችዬ ግቡ›› ብለው ተቀበሉን። ብዙ ጊዜ ውሏቸው ከህፃናት ጋር ስለሆነ ‹‹ልጆችዬ›› የሚለው ቃል ከአንደበታቸው አይጠፋም።

አባባ ታደሰ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሃድያ ዞን ምስራቅ ባደዋቾ በምትባል አካባቢ 1953 ዓ.ም ነው የተወለዱት። በ1960 ዓ.ም በተወለዱበት አካባቢ ትምህርት ጀምረዋል። እስከ አራተኛ ክፍል እዚያው ሀዲያ ተምረዋል። 1966 ዓ.ም አብዮት ሲፈነዳ ነበር ትምህርታቸውን ያቋረጡት። ሐምሌ 1969 ዓ.ም ቀይ ሽብር ሲፋፋም ‹‹ሎንቺን›› በምትባል መኪና አንድ ብር ከ60 ሳንቲም ከፍለው ወደ ሃዋሳ አመሩ። አምስተኛ እና ስድስተኛ ክፍልን ሐዋሳ ከተማ ተምረዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ መጓዝ አልቻሉም።

ሐዋሳ እንደከተሙ ለሰው ባዳ፤ ለአገሩ እንግዳ ነበሩና ትንሽ ቢደነጋገሩም የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ሥራ አይንቁም። በወቅቱ ጫማ የማሳመር ሥራ ጥሩ ገቢ ያስገኝ ነበርና ሊስትሮነት ጀመሩ። ያኔ በአምስት ሳንቲም ነበር ጫማ የሚያሳምሩት። ተለቅ ያለ ጫማ ሲሆን ደግሞ በ10 ሳንቲም በቀለም ያስውባሉ። የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን በደረታቸው ይዘው በከተማዋ እየተሽከረከሩ ነግደዋል። እነዚህንና መሠል ሥራዎችን እየሠሩ ኑሮን ለማሸነፍ በርካታ ዓመታትን ተንገላተዋል።

በመቀጠል ለ16 ዓመታት ዓሳ በማጥመድ ሕይወታቸውን ገፍተዋል። ብዙ ሰዎች ጀልባዎችን እየተጠቀሙ ነው ዓሳ የሚያጠምዱት። እርሳቸው ግን ከ20 እስከ 40 ሜትር ድረስ ‹‹ውርዋሮሽ›› በሚባል መንጠቆ ነበር የሚያጠምዱት።

የሐዋሳ ፍቅር ሃይቅን ዙሪያውን እያካለሉ ዓሳ እያጣመዱ ሲኖሩ ከበርካታ የዱር እንስሳት ጋር ተላምደዋል። በተለይም ከዘንዶ፣ የባሕር ውሻ፣ ጉማሬ እና ጅብ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዳላቸው ያስባሉ። እርሳቸው ዓሳ ሲያጠምዱ አራዊቶቹ ዙሪያቸውን እየከበቡ ይመለከቷቸው እንደነበር ይናገራሉ። «እንስሳት ሰው ካልተተናኮላቸው ሰው አይተናኮሉም»ይላሉ።

አቶ ታደሰ ለ16 ዓመታት ዓሳ እያጠመዱ የዕለት ጉርሳቸውን ቢሸፍኑም ኑሮ ሊቃናላቸው አልቻለም። 1998 ዓ.ም ላይ ይህን ሥራ እርግፍ አድርገው ተዉት። በ1999 ዓ.ም አሁኑ የሚሰሩበት ‹‹ሌዊ ሪዞርት›› ግንባታ ላይ ስለነበር በጥበቃ ሙያ ተቀጠሩ። በ2002 ዓ.ም ሪዞርቱ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ሲጀመር እርሳቸውም የበለጠ እንጀራቸውን የሚያበስሉበት አጋጣሚ ተፈጠረላቸው። ማስፋፊያዎቹ እየተሠሩ ሪዞርቱም እየተስፋፋ ሲመጣ አባባ ታደሰም የእንጀራ ገመዳቸው ከዚሁ ቤት ጋራ በሰፊው እየተሳሰረ መጣ። አካባቢው ዳያስፖራዎችና ቱሪስቶች የሚያዘወትሩት ነው። ኢትዮጵያዊ ቀለም ያላቸውን ትውፊቶች ለማሳወቅ ሲባል ሪዞርቱ ለልጆች ተረት የሚነገርበት ቤት አስገነባ። ተረት ቤቱም ጥቅምት 23 ቀን በ2005 ዓ.ም የተረት አባት አባባ ተስፋዬ ሳህሉ በተገኙበት ተመረቀ።

የዚህ ተረት ቤት መከፈት ከልጅነታቸው ጀምረው ከእሳት ዳር ቁጭ ብለው ቆሎ እየቆረጠሙ፣ ንፍሮ እየቃሙ ከቤተሰቦቻቸውና ታላላቆቻቸው የቀሰሙትን ተረት ለቀሪው ትውልድ ለማስተላለፍ ዕድል ሰጣቸው። በመሆኑም በዚህ ተረት ቤት እንደ ቅኔ አስተማሪ አትሮኑስ ዘርግተው ያለ አንዳች ክፍያ ለትውልድ ታሪክ እያጋሩ፣ ልጆችን እየመከሩ፣ ከጨዋታ እየቆነጠሩ፣ ባህል እያስተማሩ ኢትዮጵያዊውን አሻራ ማሳረፍ ጀመሩ።

ወደ ሪዞርቱ ልጆቻቸውን ይዘው ለሚመጡ እንግዶች ኢትዮጵያዊ ባህልና ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ተረት ይተርቱላቸዋል። የበርካታ እንስሳትን ድምፅ እያስመሰሉ ልጆቹን በሳቅ ያስፈነድቋቸዋል። እሁድና ቅዳሜ ተጠቃሚዎች በብዛት ልጆቻቸውን ወደ ተረት ቤቱ ይዘው ይመጣሉ። የአገር ቤት እና የከተሜውን አኗኗር እየተረኩላቸው፤ ልጆቹን ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከኢትዮጵያ እስከ ባህር ማዶ በሃሳብ ውስድ ምልስ እያደረጓቸው በደስታ ማዕበል ውስጥ ያስዋኟቸዋል። አባባ ታደሰ ምንም እንኳን ዕድሜያቸው እየገፋ ቢሆንም የጥበቃ ሥራንም ደርበው ይከውናሉ።

«ተረት በክፍያ መናገር ነውር ነው» የሚሉት አባባ ታደሰ፤ ባህላዊ እሴት በመሆኑ ትውልድ ማወቅ አለበት ስለዚህ ተረት የሚነገራቸው ልጆችም ሆኑ ወላጆቻቸው ምንም ክፍያ አይጠበቅባቸም። ከማናቸውም ቦታ ወደዚያ ሥፍራ የሚመጣ ማንኛውም ሰው ተረት አዳምጦ፤ ከኢትዮጵያዊ ትውፊት ተካፍሎ አዕምሮውን የማደስ መብት እንዳለው ያምናሉ። ይህን በማድረጋቸውም ብዙ ትዝታ እያሳለፉ ነው። ከአምስት ዓመታት በፊት ተረት ያወሩላቸው የዳያስፖራ ልጆች፤ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ሲመጡ ተረቱን ደግመው ለተረት አባት አባባ ታደሰ ይነግሯቸዋል።

ልጆቹ በየመሃሉ እርጅና እየተጫናቸው ያሉትን አባባ ታደሰን እየተሻሹ በመመለጥ ላይ የሚገኘውን ፀጉራቸውን እየነካኩ ‹‹አባባ ፀጉርዎ የታለ?›› እያሉ ይጠይቋቸዋል። እርሳቸው ደግሞ ለልጆቹ ጥያቄ ቀጥታ መልስ ከመስጠት ይልቅ ከጉዳዩ ጋር የሚጣጣም ተረት ይነግሯቸዋል። ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› እንዲሉ ተረት እየነገሯቸው፤ ለጥያቄያቸው መልስ ይሰጣሉ። በውጭው ዓለም የተወለዱ ህጻናት ኢትዮጵያዊ ለዛ ያለው ተረትን ጨምሮ ብዙ ነገር አዲስ እንደሚሆንባቸው አስተውለዋል።

አባባ ታደሰ ተረት ከመናገር በተጨማሪም ዱሮ ተስፋ ገብረስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ ‹‹መሃይምነት የጨለማ ጉዞ ነው›› ብለው በርካቶችን ከመሃይምነት ቀንበር ለማላቀቅ ለኢትዮጵውያን በአበረከቱት የፊደል ገበታ ፊደል ያስቆጥራሉ።

በተረት ቤቱ ውስጥ ያሉ እንደ አለንጋ፣ ማድጋ፣ ማሰሮ፣ እንስራ፣ ወንፊት፣ መሶብ፣ ወጪት፣ ገሳ፣ ቅል፣ ቁርበት፣ መጫኛ፣ በርጩማ፣ ድስት፣ ደበሎ፣ ሞፈርና ቀንበር እንዲሁም ሌሎች አርሶ አደሩ የሚጠቀምባቸውን ቁሶች ከአሠራራቸው ጀምሮ ግልጋሎታቸውን ሰፋ አድርገው ያብራሩላቸዋል። አባባ ታደሰ ከአንበሳ እና የፈረስ ድምፅ በስተቀር የበርካታ የቤትና ዱር እንስሳትን ድምፅ ያስመስላሉ። እንደ ቆቅ እያሽካኩ ህፃናቱን በደስታ ያስፈነድቋቸዋል። እንደ አህያ እያናፉ፤ በሀሴት ይሞሏቸዋል።

የተረት አባት አቶ ታደሰ በብዙ ትዝታ ምዕራፍ ውስጥ አልፈዋል። በልጅነት ዘመናቸው ከሰውነታቸው ጋር ጥብቅ ብሎ ከተሰፋላቸው ጥብቆ ደረት ኪስ ውስጥ ቆሎ እጭቅ አድርገው፤ ሁለት ሠዓት ሙሉ በባዶ እግራቸው እየተመላለሱ ተምረዋል። ለ16 ዓመታት ዓሳ ሳጠምድ ትዕግስት ተምሬያለሁ፤ የውሃ ውስጥ እንስሳት ምንም እንኳ አደገኛ ቢሆኑም ሥራዬ ብለን ካልተተናኮልናቸው እንደማይነኩን ሁሉ፤ ሰውም ሳልደርስበት እንደማይደርስብኝ ተረድቻለሁ ይላሉ።

አባባ ታደሰ ከትውልድ መንደራቸው ድንገት እንደወጡ ሳይመለሱ 40 ዓመታትን አስቆጥረዋል። እንደ አጋጣሚ ግን በያዝነው ዓመት ቀን ሞላላቸውና ድንገት ወደ ትውልድ መንደራቸው ጎራ ብለው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኙ። ከ40 ዓመታት በፊት ጥለውት የመጡት መንደር ጥቂት ሰዎችና ሰፊ ጫካ ብቻ ነበር። አሁን ግን ሰው በርክቷል፤ ጫካው ጠፍቷል። በርካታ የልጅነት ጓደኞቻቸው እስከ ወዲያኛው አሸልበዋል። ከወንድምና እህቶቻቸው ውስጥ ብዙዎቹ ትዳር ይዘው ወልደው ከብደዋል። የዕድሜ እኩዮቻቸው ወልደው ስመዋል። የልጅ ልጅ አድርሰዋል።

አባባ ታደሰ ግን ዛሬም ጥሩ ትዳር ይመኛሉ። ድል ባለ ድግስ ከውሃ አጣጫቸው ጋር ተጣምረው ልጅ መውለድ ይፈልጋሉ። ፈጣሪ እስኪጠራቸው ድረስ ተረት እየተናገሩ፤ ስለ ቀድሞ ታሪክ የሚያውቁትን እየመሰከሩ፤ የሕፃናትን ሰብእና እያነፁና እየመከሩ ሕይወታቸውን መምራት ምኞታቸው ነው።

በአሁኑ ወቅት በወር እስከ 1ሺ500 ብር ያገኛሉ። ግን በየወሩ ለቤት ኪራይ 900 ብር እየከፈሉ መኖር አንገሽግሿቸዋል። «ከ40 ዓመት በፊት በሐዋሳ ከ100 እስከ 200 ብር ሰፊ የቤት ቦታ ይገዛ ነበር። ዛሬ ግን በሚሊዮኖች ካልሆነ ቤት መግዛት አይታሰብም። ታዲያ በወቅቱ ልባም ሆኜ ቆጥቤ አንገት ማስገቢያ ቢኖረኝ ይሄኔ በቤት ኪራይ ከመንከራተት በዳንኩኝ ነበር» ይላሉ። ትናንትን የኋሊት ተጉዘው ራሳቸውን በቁጭትና በብስጭት ይገስፃሉ። ከምንም በላይ የሚያንገበግባቸው ነገር ቢኖር ትምህርታቸውን ማቋረጣቸው ነው። ወዲህ ደግሞ አምላኬ በፈቀደው መንገድ እየኖርኩ ስለሆነም ብዙም አልወቅስም ሲሉ ከፈጣሪ ጋር ላለመጣላት የወሰኑ ይመስላል። ብቻ አባባ ታደሰ የኑሮ ውጣ ውረድ ፈታኝ መሆኑን በማመን በፀጋ ተቀብለው እንዲህ እየኖሩ ነው።

አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2011

 ክፍለዮሐንስ አንበርብር