የተባባሰውና መቋጫ ያጣው የቬንዝዌላ ችግር

20

እአአ 2019 ጥር 23 ጁአን ጓኢዶ እራሱን የቬንዝዌላ ፕሬዚዳንት አድርጎ ከሾመ በኋላ በአገሪቱ መንግሥት መቀየር ቀላል ነው ብሎ አስቦ ነበር፡፡ እሱና የአሜሪካ መንግሥት የማዱሮን መንግሥትና ደጋፊዎቹን አቅልለው መገመታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ የቬንዝዌላ መከላከያ ኃይል በአገሪቱ ሊካሄድ የታሰበውን መፈንቅለ መንግሥትና በድንበር አካባቢ ሊገባ የነበረውን የዕርዳታ ምግብ ማገት እንቅስቃሴ ላይ የቀረበለትን የተሳትፎ ጥያቄ ሳይቀበል ቀርቷል፡፡

የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ እንደሚናገሩት ከሆነ ለጓኢዶ ሊደረግ የነበረው ወታደራዊ ድጋፍ ሊከሽፍ የቻለውና በአገሪቱ የተቃዋሚ ቡድኖች ቁጥር በመጨመር የየራሳቸው ነፃ መሬት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራው ያልተሳካው በክልል መንግሥታት አለመተባበር ነው፡፡ በአሁን ወቅት ጓኢዶ ሊያደርገው ያሰበው መፈንቅለ መንግሥት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ቬንዝዌላ በከባድ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ትገኛለች። አሜሪካን የጣለችው ማእቀብ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ ቀጣዮቹ ወራት ለማዱሮና ለደጋፊዎቹ ከባድ የሆኑ የጉዞ ቀናት እንደሚሆኑባቸው ይጠበቃል፡፡

በአገሪቱ የሚደረገው የጦር ጣልቃ ገብነት በየጊዜው እያደገ ሲሆን የፖለቲካ ስልጣንን በመቀራመት ለቀጣይ ምርጫ አማራጭ ለማምጣት ትንቅንቆች ይስተዋላሉ፡፡ አሁን የቀረው አንዱ አማራጭ ችግሩን ለመፍታት ዳግም ምርጫ ማካሄድ ነው። በተቃዋሚዎችና በመንግሥት በኩል ብዙ ድጋፎች ስላሉ ህዝቡ መምረጥ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ቬንዝዌላውያን ለማዱሮ ድጋሚ ምርጫ ድምፃቸውን ከሰጡ ዓመት አልሞላቸውም፡፡ በዚህም አዲስ ምርጫ ማካሄድ ከባድ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የማዱሮን ድጋሚ ምርጫ የተቃወሙ ሲሆን ምክንያታቸውን ግን አልገለጸም፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ ቀኝ ዘመሞች በድጋሚ ምርጫው ማዱሮ ሊያሸንፍ እንደሚችል የተናገሩ ሲሆን በምክንያትነት ያስቀመጡት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው እንደማይሳተፉ በማሳወቃቸው ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች በወንጀል የተጠረጠሩ በመሆናቸው ከምርጫው ታግደዋል፡፡ የማዱሮ ደጋፊዎች የድጋሚ ምርጫውን ቢያደርጉ የሚያገኙትና የሚያጡትን ነገር ያዩት አይመስልም፡፡ ማዱሮም በድጋሚ ቢመረጥ ደካማና አደገኛ ሁኔታ ላይ ያለ ፕሬዚዳንት ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን የተቃዋሚ መሪ የሆነው ጓኢዶ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ምርጫውን ለምን እንደፈለገው ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡

ጓኢዶ ስልጣን ለመያዝ የሚጠቅሰው ህገመንግሥት ከጅምሩ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ማዱሮ ስልጣን ላይ ለመቆየት ጥረት ቢያደርግም በህገ መንግሥቱ አዲስ ምርጫ በ30 ቀናት ውስጥ ማካሄድ እንደሚቻል ያስቀምጣል፡፡ ተቃዋሚዎች በአገሪቱ የምርጫ ካውንስል እምነት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ተደርጎ ባለማወቁ ነው። ይህ የሚያሳየው አዲስ ምርጫ ለማከናወን ፈታኝ መሆኑን ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ምርጫውን ለማከናወን ማን ኃላፊነቱን ይውሰድ የሚለው ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የምርጫ ጥያቄው በአገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚዎቸችን ለሁለት ከፍሏል፡፡ በጎዳናዎች ላይ የነበሩ ብጥብጦችን የመሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስልጣን ለመያዝ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡

ጓኢዶ እራሱ የጎዳና ነውጦችን ሲመራ የነበረና በአሁን ወቅት በቤት ውስጥ እስራት ላይ የሚገኘውን ሌፖልዶ ሎፔዝን ይደግፋ፡፡ በዚህም ለጓኢዶ ምርጫ በእቅድ ውስጥ እንደሌለ ፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ አሜሪካና ተቃዋሚዎች ፍላጎታቸው የስልጣን ሽግግር እንዲካሄድ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ማዱሮ ጓኢዶ ምርጫ እንዲካሄድ የጠራበትን መንገድ በማናናቅ በምርጫው ማንነታችንን እናሳየዋለን የሚል ንግግር አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ ይሁኔታ ማዱሮ ምርጫው እንዲካሄድ ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለውን እንቅስቃሴ ጀምሯል። ስለምርጫው አጠቃላይ ሁኔታም ሃሳብ እየሰበሰበ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ጓኢዶ እራሱን ፕሬዚዳንት አድርጎ መሾሙ የሚታወስ ሲሆን ሜክሲኮ እና ኡራጋይ ድርድር እንዲደረግ ጥረት አድርገዋል፡፡

ሁለቱ አገራት በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ በቬንዝዌላ ያለው ችግር የሚፈታበት መንገድ ሊበጅ እንደሚገባ ሃሳብ ሰጥተው ነበር፡፡ በድጋሚ ማዱሮ ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር ለማድረግ ጥሪ ቢያቀርብም ጥሩ ምላሽ አላገኘም። እንደሚታየው ነገር ከሆነ ሜክሲኮ ያቀረበችው የድርድር ሃሳብ ወደ ሁለትዮሽ የማድላት አዝማሚያ ታይቶበታል።፡ ጓኢዶ ያቀደው መፈንቅለ መንግሥት ሊማ ከተባለ ቡድን ጋር በመነጋገር ሲሆን ቡድኑ የቀኝ ዘመም የፖለቲካ አመለካከት ያለው ነው፡፡ ጓኢዶ ከቡድኑ ጋር በመተባበር አገሪቷን የማስተዳደር እቅድ አለው፡፡ ነገር ግን የሊማ ቡድን ከሜክሲኮ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሲሆን አንድሬ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር ከሉማ ቡድን እንዲወጣ የተደረገው ለጓኢዶ ፕሬዚዳንትነት እውቅና መሰጠት የለበትም በማለቱ ነው፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች ተቃዋሚዎች የኡራጋይና የሜክሲኮን ጥሪ ችላ ብለው አልፈውታል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ሁለቱ አገራት ለማንም ሳይወግኑ መሥራት አይችሉም የሚል ትችት አቅርበዋል፡፡ ይህ ሁኔታ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም የቀድሞ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴ ሉዊስ ሮድርጌዝ ጃፓትሮ በተቃዋሚዎችና በማዱሮ መካከል ስምምነት እንዲመጣ ዓመታት የለፉ ሲሆን እአአ 2018 አቅራቢያ የተቃዋሚ አመራሮች በመጨረሻው ሰዓት አንፈርምም ብለው ጥለው ወጥተዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ልምዶች እንደሚያሳዩት ተቃዋሚዎች ለድርድር በጠረጴዛ ዙሪያ ሲቀመጡ ማዱሮን ለማጥቃት አስበው ነው፡፡ ጓኢዶ እና የአሜሪካ መንግሥት አስተዳደር ይህን አመለካከት በስፋት ያራምዳሉ፡፡ በስተመጨረሻ በቬንዝዌ የሚታየው ችግር ትክክለኛ አማራጭ ለመምረጥ አንዱን መንገድ እንጂ ሁሉንም አማራጭ መንገድ እየተከተለ አይደለም፡፡ ይህን ጉዳይ ለማስረዳት በቅርቡ የተከሰተ ሁነት ማንሳት ይቻላል።በአሜሪካና በማዱሮ መንግሥት ላይ የተነሱ ትችቶች የቬንዝዌላን ተቃዋሚዎች ከጨዋታ ውጪ አድርጎት ነበር፡፡ በቬንዝዌላ መሀል ሰፋሪ የሚባሉ ፖለቲከኞች ሲኖሩ በዚህ ውስጥ ስመጥር ሰዎች ተካተውበታል፡፡

በዚህ የቀድሞ የመንግሥት ባለስልጣናት የህገመንግሥቱ ጠበቂዎች ነን የሚል ስም ለራሳቸው ሰጥተዋል፡፡ ለአገሪቱ ደህንነትም ንግግር ሳይሆን የማዱሮን መንግሥት መቀየርና ህዝበ ውሳኔ መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ይህ አካሄድ አገሪቱን የሚበታትን መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞቸች ይናገራሉ፡፡ በምን ዓይነት መንገድ አሁን ያለውን የቬንዝዌላ መንግሥት መተካት እንደሚቻል የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ 10 በመቶ የህዝቡን የድጋፍ ፊርማ የሚሰበስበው ማን እንደሆነ አልተወሰነም፡፡ በሌላ በኩል ማዱሮ ስልጣን ላይ እንዳይቆይ ድምፅ የሚሰጡ ዜጎች የሚመርጡት ሌላ ፓርቲ አላዘጋጁም፡፡

በእነዚህ ሁኔታዎች የአገሪቱ ችግር እየተባባሰ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በሚነሱ ሃሳቦች መካከል ተቃርኖዎች በዝተዋል፡፡ የአገሪቱ ነዋሪ የሆነው ሶሶሎጂስት ኤድጋርዶ ላንደር እንደሚለው፤ በአገሪቱ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የለም፡፡ ለዚህ ማሳያ ደግሞ በአገሪቱ ሊካሄድ የነበረው መፈንቅለ መንግሥት በአሜሪካ መንግሥት፣ በሊማ ቡድን እና በአክራሪ ቬንዝዌላውያን መመራቱ ነው።፡ ላንደር እንደሚለው መፈንቅለ መንግሥት ከመካሄዱ ቀደም ብሎ ውይይት ተደርጎ የነበረ ሲሆን ህዝቡ ጓኢዶን እንደማይፈልግ ተናግሮ ነበር፡፡

በውይይት ችግሩን ለመፍታት አማራጭ መንገዶች ሁሉም ዝግ ሆነዋል፡፡ የቬንዝዌላ ተቃዋሚዎች ከድርድር ይልቅ መፈንቅለ መንግሥት አማራጭ ነው ብለው ተቀብለዋል፡፡ ድርድርን አልቀበልም ያለ ተቃዋሚ በምን ዓይነት መንገድ ማስተናገድ እንደሚቻል አይታወቅም። በዚህ አደገኛ ሁኔታ ቀላል መፍትሔ ማግኘት አይቻልም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጉዳዮች ግልጽ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ አሜሪካ የጣለችው ማዕቀብ እያለ ምርጫ ማካሄድ አደገኛ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ኒካራግዋ እአአ 1990 ላይ በማእቀብ ውስጥ ሆና ምርጫ ስታካሂድ በነፃነት አልነበረም፡፡

በወቅቱ የአሜሪካ መንግሥት አስተዳደር ተቃዋሚዎች ምርጫውን እንዲያሸንፉ ድጋፍ አድርገው ነበር። በአሁኑ ወቅትም በአሜሪካ አስተዳደር ውስጥ አብዛኛው ሰዎች በፖሊሲ አውጭነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በቬንዝዌላም የተጣለው ማዕቀብ ሳይነሳ ምርጫ ማካሄድ አሜሪካ የፈለገችውን ፓርቲ እንድታስመርጥ ዕድል መስጠት ነው።በቬንዝዌላ የማዕቀብ መጣል ዋነኛው ችግሩ ኢኮኖሚ እንዲወድቅ ከማድረጉ ባለፈ የነዳጅ ዘይቶችን በማገት ችግሩ እንዲባባስ በር ከፍቷል፡፡

አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011

በመርድ ክፍሉ