የዛፍ ጥላ ስር ትውስታዬ

45

እ ናንተ የአሁን ዘመን ወጣቶች መቼም ይህን ርዕስ ስታነቡ ምን ትዝ ሊላችሁ እንደሚችል አላውቅም፡፡ ቢበዛ፣ ቢበዛ ‹‹ዛፍ ጥላ ሥር ሆነን ስንጨዋወት…›› የሚለውን የሙሀሙድ አህመድ ዘፈን ሊያስታውሳችሁ ይችላል፡ ፡ ለዛውም ቆየት ያሉ ዘፈኖችን የማዳ መጥ ልምድ ካላችሁ ነው። የድሮ ወጣቶች የዛፍ ጥላ ስር ትዝታችን ብዙ ነው፡፡ ጋሽ ሙሀሙድም የድሮ ሰው በመሆኑ ነው የዛፍ ጥላ ትዝታን በዘፈን የገለጸው፡፡

እውነት ነው የዛፍ ጥላ ስር ሲባል ሁላችንም እንደየ አጠቃቀማችን ትዝታዎቻችን ይለያያሉ፡፡ አንዳንዶቻችን በዛፍ ጥላ ስር አረፍ ብለን ከፍቅረኛችን ጋር ተጨዋውተን ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶቻችን ፊደል ቆጥረን ይሆናል፣ ሌሎቻችንም ዛፍ ጥላስር ተቀምጠን በሀገር ሽማግሌዎች ተመክረን ወይም ተዳኝተን ሊሆን ይችላል። ዝናብና ጸሐይን የተጠለልን ደግሞ ብዙዎች ነን ብዬ እገምታለሁ፡፡ ዛሬም ድረስ በተለይም በገጠሩ የሀገራችን ክፍል የዛፍ ጥላ እንደ ትምህርት ቤት፤ እንደ መኖሪያ ቤት፣ እንደ ፍርድ ቤት እና እንደ መዝናኛ ቤት ወዘተ ያገለግላል፡፡

በልጅነቴ በቄስ ትምህርት ቤት በየኔታ እግር ሥር ቁጭ ብዬ ፊደል መቁጠር የጀመርኩት በዛፍ ጥላ ስር ነው፡፡ የኔታ ከዛፉ ላይ ቅርንጫፉን እየዘነጠፉ ገርፈውኝ ሥርዓት ይዤ እንዳድግ አድርገውኛል፡፡ መቼም አንዳንድ አሽሟጣጮች አንተን ብሎ ሥርዓት አዋቂ ልትሉኝ እንደምትችሉ እገምታለሁ።

በተለይ እነ እከሌ ይህን ጊዜ ስንት ብላችሁኛል፤ አይዟችሁ ስማችሁን አልጠራም፡፡ ለማንኛ ውም ለጸባዬ ማማር ውለታ የዋሉልኝን የኔታንና ዛፉን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ አለንጋና ቀለም ጠግበን ስናበቃ መጨረሻ ወደ ቤት ልንሄድ ስንል ጠዋት በጸሎት የጀመርነውን ትምህርት ማታም በጸሎት እንዘጋለን። ከጸሎት በኋላ መጨረሻ ላይ ድምጻችንን ከፍ አድርገን ‹‹በየኔታ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆር በእኛ ጉሮሮ ቀለም ይንቆርቆር›› የምንለውን ምርቃት መሰል የጸሎት ማሳረጊያ አልረሳውም፡፡

አንድ ቀን ታድያ የኔታ አጠገቤ መሆና ቸውን ሳላውቅ በእኛ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆር በየኔታ ጉሮሮ ቀለም ይንቆርቆር ብዬ አባባሉን ገልብጬ ለመቀለድ ስሞክር ሰምተውኝ ኖሮ ጎትተው ጭናቸው ስር አስገብተው በቁንጥጫ አድብነው አድብነው የጣሉኝ አይረሳኝም። አይ የእኔ ነገር ትዝታዬን ለማውራት ብዬ ሙት ወቃሽ ሆንኩኝ፡፡ ነፍስ ይማር የኔታ። እንኳንም ቆነጠጡኝ፣ እንኳንም ገረፉኝ። የእርሶ ምክርና ቅጣት ነው ጥሩ ስብዕና እንድይዝ ያደረገኝ፡፡

ይሄው ዛሬ እኔም እንደእርሶዎ አስተማሪ ሆኜ ተማሪዎችን በጥሩ ስነምግባርና በእውቀት እየገነባዋቸው ነው። ይህ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በመሆኑ እርሶ ያደርጉ እንደነበረው ትምህርታችንን በጸሎት ጀምረን በጸሎት አንዘጋም። ተማሪዎች ተነሱና አንዴ ጸሎት እናድርግ ብላቸው ጉሮሯቸው እስኪሰነጠቅ እንደሚስቁብኝ አልጠራጠርም። ግብረገብነት ጠፍቷል፡፡ መምህርን ከማወደስ ይልቅ ማንኳ ሰስ ይቀናቸዋል፡፡ እንደ ተማሪና አስተማሪ ሳይሆን እንደሌባና ፖሊስ መተያየት ይዘናል፡፡

ያኔ እርሶ አራት የትምህርት ዓይነቶችን በአንድ ግዜ ያስተምሩን ነበር፡፡ እኛን ፊደል ያስቆጥራሉ፣ እነተሻለን ዳዊት ያስደግማሉ፣ እነግዛውን አቡጊዳ ሄውዞ ያስጠናሉ፣ እነአብዩን ወንጌል ያስነብባሉ፡፡ በዚህም ላይ ቁጭ ብለው ቆብዎን እየሰፉ ያለበለዚያም ነጠላዎን እየቋጩ ሁሉንም ተማሪዎች እየተቆጣጠሩ የሚሰጡት ማስተካከያ ያስገርመኛል፡፡ የኔታ እኔ ዛሬ አንድ ትምህርት እያስተ ማርኩ ተማሪዎቼን በቅጡ መቆጣጠር አልቻ ልኩም። የተማሪዎቼን የትምህርት ፍላጎት አይና ሀሞቴ ይፈሳል፡፡

 እነሱስ ልጅነትና የአዕምሮ ያለመብሰል ችግር ስላለባቸው ነው። እኔ ኃላፊነቴን ለምን መወጣት ያቅተኛል? እያልኩ እበሳጫለሁ፡፡ በእርግጥ እራሴን ከእርሶ አንጻር ስመለከት ጥፋተኛ ነኝ፤ መታረም ይኖርብኛል። ከእኔ የሚጠበቀውን ሁሉ በማድረግ እነዚህን እንቦቀቅላ ልጆች ለፍሬ እንዲበቁ የማድረግ ኃላፊነቴን መወጣት ይኖርብኛል። ለነገሩ የኔታ እነዚህ ተማሪዎች የእርስዎ ተማሪዎች ቢሆኑ ኖሮ ዓለም በቃኝ ብለው ይመንናሉ፤ ካልሆነም በዱላ አስተካክላቸዋለሁ ብለው ያንን ዛፍ ካለ ቅርንጫፍ መለመሉን ያስቀሩት ነበር፡፡ ነገረ ሥራቸው ሁሉ እንደሚያናድዶት አስባለሁ፡፡

እርሶ እኮ ለምን ውሀ ቀጠነ ብለው ነበር የሚገርፉን። ድሮ የተቀደደ ልብስ ለብሰን ስንመጣ‹‹ ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ›› እያሉ የሚተርቱብንና በማግስቱ ሰፍተን ካልመጣን የሚጨርሱብን ልምጭ ይታወሰኛል፡፡

ዛሬ የኛ ተማሪዎች ሆነ ብለው ጸጉራቸውን ያንጨባርራሉ፣ ጆሯቸው ላይ ሎቲ ያንጠለጥላሉ፣ የተቀደደ ቦላሌ ይለብሳሉ፤ እሱንም እጉልበታቸው ድረስ አውርደው ይተውታል፡፡ በተለይማ የደንብ ልብስ በማይለበስ ቀን ጉድ ይታያል፡፡ ሱሪ የሚለብሱ ሴቶች እንደ አሸን ፈልተዋል፤ መልበሱን እንኳን ይልበሱ ግን ጭናቸውን የሚያሳይ ሱሪ ካልሆነ አይለብሱም፡፡ ይህ የእኔን ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የዘመኑን ወጣቶች በሙሉ የተጸናወታቸው በሽታ ነው፡፡ እንዲህም ሆነው እነሱ ደስተኞች ናቸው፡፡ በሆነው ባልሆነው መሳቅ ይወዳሉ፡፡ እውነት ለማለት ሳቃቸው ያስቀናኛል፡፡

ያኔ እዛ እዛፍ ስር ስንማር አንድ ቀን መሳቄ ትዝ ይለኛል፡፡ ለዛውም ተሻለ ግንባር ላይ ወፎች ኩሳቸውን ጥለውበት አይቼ ነው፡፡ ወዲያው ታድያ እርሶ ሳቃችንን እስቁመው ሂድ ጅረት ወርደህ ታጠብ ብለው ከእኔ ጋር ላኩት፡፡ በዚህ ዘመን በተለይ በከተማ የቄስ ትምህርት ቤት ምን ማለት እንደሆነ አይታ ወቅም፡፡

ህጻናት ትምህርት የሚጀምሩት በመዋዕለ ህጻናት ነው፤ ፊደል እንዲቆጥሩ የሚበረታቱትም በእንግሊዘኛ ነው፡፡ ለምን ቢባል ዓለም ወደ አንድ መንደር እየመጣች ስለሆነ ወደፊት ከዓለም ህዝብ ጋር በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለመግባባት እንዲያመቸን ተብሎ ነዋ። አንዳንድ አሽሟጣጮች ግን ኢትዮጵያ ራሷ መች አንድ ሆነችና ነው ከዓለም ህዝብ ጋር አንድ ልትሆን ያሠበችው እያላችሁ እንደምታንሾካሽኩ አልጠራጠርም፡፡

እናንተ ሰዎች ግን የህዝባችን በተለይም የወጣቱ ንቃተ ህሊና ያልገባችሁ ናችሁ። መጀመሪያ ከዓለም ህዝብ ጋር ከመቀላቀላችን በፊት ምናልባት ሁኔታው ሳይመቸን ቀርቶ እንለያይ ብንል እንዴት መለያየት እንዳለብን በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንውሰድ በሚል ነው ወጣቱ ሙከራ እያደረገ ያለው፡፡ ስለዚህ አሁን በየክልሉ አንዱ አንዱን የሚገፋው የስልጠናው አንድ አካል ስለሆነ ነው፡፡ ከፈለጋችሁ የስልጣኔው አንድ አካል ነው ብላችሁ አስተካክሉት፡፡

አይ የእኔ ነገር የተነሳሁት የዛፍ ሥር ትውስታችንን መለስብለን እንድናይ ለማድረግ ነበር፤ ሳላስበው ሌላ ጉዳይ ውስጥ ከተታችሁኝ። የጀመርኩላችሁን ወግ ልጨርስላችሁ፡፡

ዛሬ ዘመኑ ተለውጧል። ሰውም ሰልጥኗል፡፡ ከተሞች አድገዋል፤ ትምህርት ተስፋፍቷል በሚባልበት በዚህ ወቅት ልቤን የሰበረኝ ነገር ያደግሁባት መንደር ምንም እድገት ያለማሳየቷ ነው፡፡ በዚች የገጠር ቀበሌ አንድ የመለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኝ ሲሆን ስምንት የመማሪያ ክፍሎች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ ግድግዳና የቆርቆሮ ክዳን ያላቸው ሶስቱ ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የመምህራን ቢሮና ማረፊያ ነው። በተረፈ የተቀሩት አምስቱ ሶስቱ በዳስ ሁለቱ ደግሞ በዛፍ ጥላ ስር ትምህርት የሚሰጥባቸውና እንደ መማሪያ ክፍል የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እናንተ የከተማ ልጆች በመንግሥት ትምህርት ቤት ያውም በዚህ ዘመን ዛፍ ጥላ ስር የሚማሩ ተማሪዎች አሉ ስትባሉ ታምናላችሁ ብዬ አልገምትም፡፡ ግን የምነግራችሁ እውነት ነው።

 በአንድ የክረምት ወቅት ወደ ቤተሰቦቼ ሄጄ ያለሥራ ከምቀመጥ አልኩና ፊደል በቆጠርኩበት ዛፍ ስር የሰፈሩን ልጆች ሰብስቤ ማስተማር ጀመርኩኝ፡፡ ታድያ አንድ ቀን እያስተማርኩ እያለሁ በመሀል አንድ ሁለት ተማሪዎች እንቅልፍ ይዟቸው ጭልጥ አለ፡፡ ላነቃቃቸው በማሰብ ቀልድ ብጤ ላወራላቸው ሞከርኩኝ፡፡ ‹‹ተማሪዎች መምህር በጀኔሬተር ተማሪ ደግሞ በአንፑል ይመሰላል፡፡ ይህ ማለት መምህር ሞተር ሆኖ ለተማሪዎቹ ኃይል ሲሰጣቸው ተማሪዎቹ ደግሞ አንፑል ሆነው ያበራሉ ማለት ነው ›› አልኳቸው። በመሃል አንዱ ተማሪ መምህር ጄኔሬተርን እንኳ አውቃለሁ ውኃ ከወንዝ እየሳብን መስኖ እያለማንበት ነው፤ አምፑል ማለት ግን ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም አለኝ፡፡ እውነቱን ነው፤ ሰፈራቸው መብራት ሳይገባ አንፑልን ማወቅ አይጠበቅበትም፡፡ ስለዚህ አንፑል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስረዳሁት፡፡ እንዳሰብኩት እንደምንም ብዬ አሳቅኳቸውና ተነቃቅተው እንዲማሩ አደረግ ኳቸው፡፡ አይ የልማቱ ተቋዳሽ ያልሆኑት የመንደሬ ልጆች።

አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011

ኢያሱ መሰለ