መረጃ ለዓይን ግፊት (ግላኮማ) ታማሚዎች

51

በጤና ባለሙያ የዓይን ግፊት ህመም (ግላኮማ) እንዳለብዎት ወይም ለእዚሁ ችግር ከሌሎች በበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ ተነግሮት ይሆናል። አልያም ደግሞ በዓይን ህመም የተጠቃ ሰው ያውቁ ይሆናል። ምናልባትም ስለ ግላኮማ ሰምተው አያውቁ ይሆናል እስቲ እነዚህን ነጥቦች ይመልከቱ።

ግላኮማ የምንለው የዓይን ህመም በዓይናችን ነርቭ ላይ ችግር የሚያስከትል ሲሆን በዓይናችን ውስጥ የሚገኘው ግፊት መጨመር ምክንያት የሚከሰት ነው። የእዚህ ግፊት መጨመር በዓይናችን የምናያቸውን ምስሎች ወደ አንጎል የሚወስደውን የዓይናችንን ነርቭ ይጎዳል። ይህም በቀጣይነት ቋሚ ለሆነ የዓይን ብርሃን እጦት ይዳርጋል።

 ግላኮማው በሚጀምርበት ጊዜ የሚያሳየው ቀዳሚ ምልክት ወይንም የህመም ስሜት ስለሌለ ማንኛውንም ሰው መደበኛ የሆነ ዓይን ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይህም ዓይናችን ለከፋ ጉዳት ከመጋለጡ በፊት ህክምና እንድናደርግለት ይረዳናል። ከ40 ዓመት እድሜ በላይ ያሉ ሰዎች በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ሀኪም በመሄድ ምርመራን ማድረግ አለባቸው።

የዓይን ውስጥ ግፊት ለምን ይጨምራል?

ግላኮማ የሚከሰተው በዓይናችን ውስጥ የሚገኘው ግፊት ሲጨምር ነው። ይህ ደግሞ በዘር፣ በኢንፌክሽን፣ በዓይን ቀዶ ህክምና ምክንያት በፊተኛው የዓይናችን ክፍል ውስጥ የሚገኘው ፈሳሽ በጤናማ ሁኔታ መንሸራሸር ሲያዳግተው ነው። በአብዛኛውን ጊዜ ሁለቱንም ዓይኖች የሚያጠቃ ሲሆን የህመሙ ክብደት ሊለያይ ይችላል።

በብዛት የሚያጠቃው እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ፣ በቤተሰብ የተጠቃ ሰው ያላቸው( family history of glaucoma )፣ የስኳር ህመምተኛ፣ የዓይን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በዋናነት ይካተታሉ።

 ምልክቶቹ ፦ በቅድሚያ የህመም ምልክት ባያሳይም በሂደት ግን በጥግ በኩል የሚከሰት የዓይን ብርሃን ችግር፣ ድንገተኛ የሆነ የዓይን ህመም፣ ከፍተኛ የራስ ምታት፣ የዓይን ብዥታ፣ ጥርት ያለ እይታ አለመታየት፣ የዓይን መቅላት፣ የዓይን ብርሃን ማጣት ።

መከላከያ፦ ግላኮማ እንዳይከሰት ሙሉ ለሙሉ መከላከል ባይቻልም በቶሎ የህመሙ መኖር ከታወቀ እንዳይባባስ ለመቆጣጠር ይረዳል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011