በልግ ላይ አሻራን ለመጣል

27

አገሪቱ አንድ እግር በሰማይ አንድ እግር በመሬት በሆነው አካሄዷ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የግብርናው ዘርፍ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያስመዘግብ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይቷል። በዚህም የአርሶ አደሩን ከእጅ ወደ አፍ የነበረ ሕይወት ከመለወጥ ባሻገር የመጡ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ግን ዘርፉ የሚጠበቅበት ደረጃ ላይ አለመድረሱ ይገለፃል። ለዚህም እንደ ምክንያት ተደርገው የሚቀርቡ ምክንያቶች አሉ። በሁሉም ወቅቶች ላይም እኩል ትኩረት ሰጥቶ ያለመሥራት ችግር እንደ ክፍተት ተደርጎ ይነሳል።

 በአገሪቱ የስነምህዳር መሠረት ተደርጎ ከሚመረትባቸው ጊዜያት አንዱ የበልግ ወቅት ቢሆንም እንደ ሌሎቹ የእርሻ ወቅቶች ሁሉ እየተሠራበት ባለመሆኑ ሊገኝ የሚገባው ምርትም እየተገኘ አይደለም። ይህንን መለወጥ ይቻል ዘንድም በየጊዜው ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት ያስገኙትን ውጤትና ያጋጠሙ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የ2011 በጀት ዓመት የበልግ እርሻ ልማት ሥራን ለመከታተልና ለመደገፍ የሚያስችል የማስፈጸሚያ ዕቅድ ተዘጋጅቷል። በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። እኛም በዚሁ ላይ ከግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ብርሃኑ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ።

ነባራዊ ሁኔታ

በአገሪቱ የሥነምህዳር አቀማመጥ በሦስት ከተከፈሉት መኽር በጋ መስኖ ሥራዎች ሌላኛው የበልግ ወቅት ነው። ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ የበልግ እርሻ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ነው። የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ደግሞ የትግራይ ደቡባዊ ዞን፣ አማራ ክልል ሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ፣ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞኖች ቦረና፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ አርሲ፣ ምዕራብ አርሲና ምዕራብ ሐረርጌን ያጠቃልላል። ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ደግሞ 60 ከመቶ ይሸፍናል። በተለይ ከፋ፣ ቤንች ማጂ፣ ሸካ፣ ዳውሮ፣ ደቡብ ኦሞ፣ የሰገን ሕዝቦች፣ ወላይታ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ሲዳማና ጌድኦ ዞኖችና የኮንታና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች በልግ አብቃይ ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ናቸው።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ በየዓመቱ ከሚሰበስባቸው መረጃዎች ዓመታዊ የበልግ እርሻ ምርት ድርሻው ከ0 ነጥብ 5 በመቶ ያልዘለለ እንደሆነ ያመላክታል። የመኸር ሰብል ማሳውን ፈጥኖ በማስለቀቅና በማልማት ከበልጉ ማግኘት የሚገባንን የምርት አቅም ከማግኘት አንፃር በትኩረት ያልተሰራበት መሆኑን ያሳያል። ይህንን ለመቀየር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ችግሮቹን በመለየት ተገምግሟል።

በዋናነት ባለሙያዎቹም ሆነ ተቋሙ ለመኸር እርሻ የሚሰጠውን ትኩረት ለበልግ ሥራ ካለመስጠቱ የተነሳ በዚህ ወቅት መገኘት ያለበት ከፍተኛ ምርት ሳይገኝ ቆይቷል። በመሆኑም ለመኸሩ እንደሚደረገው ሁሉ ለበልጉ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት በመታመኑ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። የበልግ ምርት በተለይ ለሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ለትግራይ፣ ለሰሜን ምስራቁና ለምስራቃዊ ደጋማ አካባቢዎች ከአምስት እስከ 30 በመቶ ከዓመታዊ ምርታቸው ይሸፍናል። ለደቡባዊና ደቡብ ምዕራቡ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙትን በልግ አብቃይ አካባቢዎች ደግሞ ከ30 እስከ 60 በመቶ ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርታቸው ይሸፍናል።

ሥራዎች

በ2009 ዓ.ም በበልግ ወቅት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ታርሷል። 18 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታልም ከዋና ዋና ሰብሎች ማግኘት ተችሎ ነበር። በ2010 ዓ.ም በተመሳሳይ ወቅት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ ሽፋን የነበረ ሲሆን፤ 20 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርትም ማግኘት መቻሉን መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህም በንጽጽር የተሻለ ሥራ እንደነበር ያሳያል። በዚህም በመሬት 4 ነጥብ 5 ከመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፤ በምርት ደግሞ 9 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በተሠራው ሥራም ልዩ ትኩረት ከተሰጠ ምርትና ምርታማነቱ ላይ ብሎም ለወጪ ገበያው የራሱን አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ነው የተገኘው ጭማሪው ያመላከተው። በግብዓት አቅርቦት፣ ለአርሶአደሮች አስፈላጊውን ሥልጠና ከመስጠትና ሌሎች ግብርናውን የሚደግፉ ግብዓቶች ከማቅረብ አንፃር ተጠናክሮ የሚሠራ ከሆነ በ2011 ዓ.ም የምርት መጠን ላይ ሰፊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ይጠበቃል። በዚህም 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ማልማት ይቻላል በሚል ታቅዷል። ከዚህም 29 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚሰበሰብም ተቀምጧል።

ቀጣይ ተግባራት

ዕቅዱን ለማሳካት የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አሉ። በመጀመሪያ ከዋና ዋና ሰብሎች ለማግኘት የታቀደውን የምርት መጠን ለማሳካት በበልግ ወቅት የሚኖረውን እርጥበትና ዝናብ በአግባቡ ለበልግ እርሻ መጠቀም አስፈላጊ ይሆናል። ለዚህም የክትትልና ድጋፉ ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን በአግባቡ በለየና ውጤታማነት ላይ ያተኮረ ሊሆን እንደሚገባ ታምኗል።

ግብዓት አቅርቦቱም ከ15 በመቶ በላይ ጭማሪ ሊደረግበት እንደሚገባም አቋም ተይዟል። በተመሳሳይ ምርጥ ዘርን በዕጥፍ መጨመርና ማሳደግ በቀጣይ ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ ዋናው ነው። ትልቁ ሥራ በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ነው መጠናቀቅ ያለበት። ከሚደረጉ ዘርፈ ብዙ የድጋፍ ሥራዎች በተጨማሪ ለበልጉ ወቅት የሚያገለግሉ ግብዓቶች የማቅረብ ሥራ አንዱ ነው። ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ስርጭቱም በወቅቱ እንዲቀርቡ ተደርጓል። በተያያዘ ለአርሶ አደሩ ምርታማነቱን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየተሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ከዚህ ቀደም በስፋት ሥራ ላይ ያልዋሉ ነገር ግን ደግሞ የሚያጭዱና የሚወቁ ከተወቃ በኋላም ለብክነት የማያጋልጡ የብረት ጎተራዎችን ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅ ሥራዎች በስፋት ይሠራል። ይህን የሚመራ በኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጀኔራል የሚመራ ኮሚቴ በተያዘው ዓመት በሚኒስቴር ደረጃ ተዋቅሮ እስከ ታች ድረስ ክትትልና ድጋፉን አጠናክሮ የሚያስኬድ አግባብ አቅጣጫ አለ። በሌላ በኩል በአጭር ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን በመምረጥ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ አስፈላጊ ነው። ከዚህም ጎን ለጎን ለእንስሳት የሚሆን በአጭር ጊዜ የሚደርስ መኖ ላይ ትኩረት በመስጠት መሥራት ያስፈልጋል። በገበያ ተፈላጊ የሆኑና በቶሎ የሚደርሱ በተለይም ደግሞ ለውጭ ምንዛሪ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ከተሠራ በዚህ ዓመት የበልግ ወቅትን ውጤታማ ማድረግ ይቻላል።

ክልሎችም በወቅቱ ለማልማት ያቀዱትን መሬት መጠን አቅደዋል። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል 822 ሺህ 859 ሔክታር መሬት በማልማት 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።በአማራ ክልል ከ193 ሺህ 674 ሔክታር መሬት በማልማት 2 ሚሊዮን 147 ሺህ ኩንታል ምርት፣ ኦሮሚያ 910 ሺህ 555 ሔክታር በማልማት ከ 13 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ይታሰባል።

በተመሳሳይ በትግራይ 9 ሺህ 121 ሔክታር መሬት ለምቶ 160 ሺህ 411 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ በዕቅዳቸው አሳውቀዋል።ሚኒስቴሩም በዚህ መሠረት የሥልጠናና መሠል ድጋፎችን ጨምሮ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ለማመቻቸት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል። ሥራውን ለማከናወን የወቅቱ የዝናብ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ በተለይ በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ መሠረት ለበልግ ወቅት የተሻለ የዝናብና የእርጥበት ሁኔታ አለ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ግን በትንበያው መሠረት የማይገኝ ከሆነ አስፈላጊው ዝግጅቶች መደረግ አለባቸው።

ዝናቡ በእጥረት የሚያጋጥም ከሆነ ውሃን በማሳ ውስጥ የማቆየትና የማሰባሰብ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው በተቃራኒው ዝናብ መብዛት ካጋጠመ ደግሞ ማሳ ውስጥ ውሃ እንዳይቆይ ማፋሰሻ ቦዮችን በማዘጋጀት ለምርቱ በሚመጥን መልኩ ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ይሆናል። ይህንን ምክረ ሃሳብም በየጊዜው ለሚመለከታቸው አርሶ አደሩን ለሚደግፉ ለልማት ጣቢያ ባለሙያዎችና የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ይሰጣል። በልግ በባህርይው በቆላማ አካባቢዎችና የሙቀት መጠን ይዋዥቃል። መጨመርና የዝናቡ መጠን ስርጭት ጋር ስለዚህ ደረቃማ ቀናት የሚበዙበት ሁኔታ ስለሚታይ በተለይ የውሃ ማቆር የማሰባሰብ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

ባለፉት ጊዜያትም የታዩ ክፍተቶች በተለይ ለበልግ እርሻ ሥራ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ ወይም ደግሞ ትኩረት ያለመስጠት ክፍተቶችን ይታረማሉ። በተያዘው ዓመት ባለፉት የመኸር ወቅቶች በተለያዩ አየር ንብረት መዛባት የተጓደለ ወይም ደግሞ ሊቀንስ የሚችለውን የምርት መጠን በዚህ የበልግ ወቅት ለማካካስ በከፍተኛ ርብርብ ወደ ሥራ ተገብቷል።

 አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011

ፍዮሪ ተወልደ