ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በየቀኑ 40 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ ቆሻሻ መሰብሰብና ማጣራት ተጀምሯል

28

አዲስ አበባ:- አዲስ አበባ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻን በመሰብሰብና በማጣራት ላለፉት ዓመታት ከነበረችበት በቀን 7 ሺህ 500 ሜትር ኪዩብ አቅም በቅርቡ በተሰሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ምክንያት እለታዊ አቅሟን ወደ 40ሺህ ሜትር ኪዩብ ማሳደጓ ተገለፀ። የከተማው የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክቶችም በተያዘላቸው እቅድ መሰረት በመካሄድ ላይ መሆናቸውን የከተማው ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የፍሳሽ ጥናት፣ ዲዛይን ቁጥጥር ንዑስ ስራ ሂደት መሪ አቶ አብዱል ሀኪም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ባለስልጣኑ 18 ፕሮጀክቶችን የመገንባት እቅድ ይዞ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 15ቱ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቀዋል፤ ሶስቱ ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ። የስራ ሂደት መሪው እንዳብራሩት በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 10 በመቶ የነበረውን የማጓጓዝ አቅም 50 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ሲሆን ይህንንም የእቅድ ዘመኑ ሲጠናቀቅ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ከእስካሁኑ ሂደቱ መረዳት ይቻላል።

የህብረተሰቡን ግንዛቤ በተመለከተም ከፍተኛ ለውጥ መኖሩን ነው ከስራ መሪው መረዳት የተቻለው። ለዚህም ከስምንት ወር በፊት በቀን 7ሺህ 500 ኪዩቢክ ሜትር የነበረው የሚጓጓዘውና የሚጣራው ፍሳሽ መጠን በስምንት ወር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ወደ 40ሺህ ኪዩቢክ ሜትር መድረሱ ጥሩ ማስረጃ ነው ብለዋል። በከተማው ከተገነቡት የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች መካከል ከዓለም ባንክ በተገኘ 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር የተገነባውና በግዙፍነቱ የሚጠቀሰው የ”ቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ” በቀን 100ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ፍሳሽ የመቀበልና ማጣራት አቅም እንዳለው አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ራሳቸውን የቻሉና 27ሺህ ኪዩቢክ ሜትር የማጣራት አቅም ያላቸው ጣቢያዎች ተገንብተዋል ያሉት ኃላፊው በተለያዩ የኮንዶ ሚኒየም ሳይቶች 12 ያልተማከሉ ማጣሪያ ጣቢያዎች መገንባታቸውን፤ የተወሰኑት ስራ ጀምረው ቀሪዎቹ ዝግጁ ሆነው የነዋሪዎችን ወደ አካባቢው መምጣት እየተጠባበቁ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ማጣሪያዎቹ ዋና ዓላማቸው ፍሳሾችን ማጣራት ቢሆንም ከማጣራት በኋላ የተለያዩ ተረፈ-ምርቶች እንደሚኖራቸው የሚናገሩት አቶ አብዱል ባዮጋዝ፣ ዝቃጭ እና ውኃ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውንና እነዚህንም በሌሎች ገቢ አስገኚ ዘርፎች ላይ በማዋል ጥቅም የሚገኝበትን ሁኔታ ለመለየት ጥናቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ይህ ከየቤቱ እየተቀባበለ ዋናው ማጣሪያ ውስጥ እንዲገባ ሆኖ የተዘረጋው የማጓጓዣ መስመር የሚመለከተው ማንኛውንም ፍሳሽ ሳይሆን ከሰው ልጅ አመጋገብ ጋር በተያያዘ የሚወገደውንና ከቤት ውስጥ የሚወጣውን ቆሻሻ(Sewage) እንጂ በየመንገዱ የሚደ ፋውን፣ የሚጣለውን፣ የሚፈሰውን ፍሳሽ (Drainage) ሁሉ አይደለም የሚሉት አቶ አብዱል የዘርፉን ተግባርና ኃላፊነት፣ እንዲሁም የሚሰጠውን አገልግሎት ከዚሁ አኳያ ለይቶ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

እንደ የስራ ሂደት መሪው ማሳሰቢያ የቤት ውስጥ የፍሳሽ ቆሻሻን እስከ ዛሬ ከነበረውን ተለምዷዊ የቆሻሻ አወጋገድ ዘዴን ማለትም ህገወጥ በሆነ መልኩ ወደ ወንዝ ከመልቀቅ፣ በመኪና ከማጓጓዝ የቆየ አሰራር ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የቆሻሻ ማጠራ ቀሚያን ከመስመር ጋር ለማገናኘት በሚደረገው አድካሚና አስቸጋሪ የቁፋሮ ሂደት አስፈላጊውን ትብብር ማድረጉን መቀጠል ይጠበቅበታል።

የባለስልጣኑን እቅድና ራዕይ በማገናዘብ ሀሳባቸውን የሰጡት አቶ አብዱል ሀኪም እንደሚሉት ይህ ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ስርአት የከተማዋን የፍሳሽ ክምችት ችግር በዘላቂነት ከመፍታቱም ባሻገር ዘመናዊና የተሻለች አዲስ አበባን ከመገንባትና ጤናማ ከባቢንና ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብን ከመፍጠር አኳያ የራሱ ጉልህ ድርሻ አለው።

አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011

ግርማ መንግሥቴ