«ስለክቡርነታችን»!

9

ለመጀመሪያ ጊዜ ለኖቬል ዓመታዊ መርሐ ግብር ሳይቀር በእጩነት የመቅረብ ሁነኛ ምክንያት በሆነው በ «መደመር» መሪ ፍልስፍና፣ ሙሉ በሙሉ ዕውነተኛ ዜግነታዊ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ዕኩልነት፣ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ ዴሞክራሲና ልማት ከጓዳችን ጀምሮ በኢትዮጵያችን አድማስ ሁሉ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ይደላደል፤ ይለመልም ዘንድ፣ የእያንዳንዳችን፤ የሁላችን ብርቱ ፍላጎት ነው። ምክንያቱም እነዚህን ጉዳዮች እያንዳንዳችን (ሁላችንም) ሳይሸራረፉ የምንፈልጋቸው ናቸውና።ምናልባት ልዩነትና መጠራጠር ቢኖር ከተጨ ባጭ ጥረትና ትጋት አንፃር ሊሆን ይችላል። ዕውነትም አሁን ቁልፉ ጉዳይ፣ ከምኞትና ከፍላጎት ባለፈ እያንዳንዳችን (ሁላችንም) በላቀ ስብዕና በቁርጠኝነትና በያገባኛል ስሜት በተገቢው ተነሳሽነት፣ ጥረትና ትጋት የየበኩላችንን አስተዋፅኦ በማበርከቱ ማለትም በንቁ ተሣታፊነታችንና በተግባራዊነታችን ላይ የሚወሰን መሆኑ ነው።

ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ዕውነተኛ ዜግነታዊ ነፃነት፣ፍትህ፣ ዕኩልነት፣ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ ዴሞክራሲና የልማት መፍትሔዎችን ከየተ ዋረድ መሪዎች፣ ባለሥልጣናትና ሹማምንት ብቻ የምንጠብቅ ከሆነ የተሟላ መፍትሔ ላይ መድረስ የሚቻል አይሆንም። የየተዋረድ መሪዎች፣ ሹማም ንትና ባለሥልጣናት ብሩህ ራዕይ የማመላከትና ዕለት ከዕለት በተጨባጭ ምሣሌም በመሆን ጭምር በብርቱ የመትጋት ዓይነተኛና ቀዳሚ የኃላፊነት ድርሻ ቢኖራቸውም፣ በተጓዳኝነት፣ እያንዳንዳችን የየበኩላችን የማይተካ ድርሻ ማበርከት እንዳለብን ለአፍታም ያህል ሊዘነጋን አይገባም። የእያንዳንዳችን የየበኩላችን ተቆርቋሪነት፣ ንቁ፣ ቅን፣ ቁርጠኛ፣ ብርቱ ትጋትና ጥረት ባልታከለበት ሁኔታ በንጽጽራዊ የሀሜት፣ የትችት የወቀሳ የዘለፋ የነውጥና የመሣሠሉት ዓውድ ዙሪያ መረባረቡ ወደ ዘመናዊ ልማትና ዕድገት ሊያራምደን አይችልም። ከአለፉት አያሌ ዓመታትና ዘመናት ልንቀስም ከምንችላቸው ዓይነተኛ ትምህርቶች መካከል አንደኛውና ዋነኛው ይኸው እንደሆነ በውል ልንተማመንበት ይገባናል።

 ታዲያማ እንደየዘልማዳዊ ግብታዊ መፈክሮቻችን ድንፋታዎቻችንና ዘመቻዎቻችን ብዛት ቢሆን ኖሮ እስካሁን ድረስ የትና የት በደረስን! ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ረጅም ሊባል በሚችል የጊዜ ወሰን ውስጥ፣ በተለይም በፖለቲካዊ፣ በአስተዳደራዊ እና በምጣኔ ሀብታዊ ረገድ፣ በተጨባጭ ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ትርጉም ያለው መዋቅራዊ ሽግግር ሳናከናውን በመንፏቀቅ አዙሪት ተተብትበን ቆየን፤ እንዲያውም አንዳንድ ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ከኋላችን ተነስተው በተወሰኑ መሥፈርቶች ረገድ ከፊታችን ሆነው ተገኙ። ይባስ ብሎም በዓለም ዙሪያ በተለይም በድርቅ፣ በረሀብ፣ በእርስ በርስ ግጭቶችና በመሣሠሉት ክስተቶች ረገድ ከዓይነተኛ ተጠቃሾች ጎራ ሆነን ቆየን። በመሆኑም በላቀ ህብረ-ብሔራዊ የአርበኝነት ቁጭትና ወኔ በአንድነት በቁርጠኝነት የምንተጋበት ጊዜ አሁን ነው!!

የዓድዋችንን ዓለም አቀፍ ታላቅ ጀብድ ገድልና ጀግንነት ድል ቅርስ በውል መዘከር አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ በስንቅነት መጠቀም ደግሞ ሌላው ገፅታ መሆን አለበት!! በተነፃፃሪው በቀደሙት አያሌ ሺህ ዓመታት ውስጥ በአመዛኙ ከመሪዎቻችን ብሎም ከየተዋረድ ባለሥልጣ ኖቻችንና ሹመኞቻችን በኩል የ «ከእኔ ወዲያ ላሳር አዋቂ አድራጊ ፈጣሪ» ደዌ አባዜ የተጠናወተን ሆነን መቆየታችን እሙን ነው። እጅግ ሩቅ ሳናማትር የንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ጃንሆይ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ «ለኢትዮጵያ ያለናት እኛው ነን፤ …»፤ የርዕሰ ብሔር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም «ዘራፍ ያለ እኔ …»፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ «ከቶ ማነው …» አጓጉል ብሂሎች ዓበይት መገለጫዎች እንደነበሩ ይታሰቡናል።

የአሁኖቹም እንዳንደግመው ከፍተኛ ጥንቃቄና ብልህነት ይፈለግብናል። ታዲያ እንደ አንድ የጤና ባለሙያ፣ መምህርና ተመራማሪ አጠቃላይ የወል ጤንነትና ደህንነት መረጋገጥ እጅግ በጣም ትኩረት ሊሠጠው የሚገባ ዓብይ ሀገራዊ ጉዳይ ሆኖ ይታሰበኛል። በዓለም የጤና ድርጅት መመሥረቻ ስምምነት መሠረት፣ የጤና ፅንሰ ሐሳብ አድማሰ ሠፊና ጥልቅ ነው፤ በቀጥታ ከሚታየውና ከሚዳሰሰው ከአካላዊ ክፍለ ወሰን ባሻገር የግልም ሆነ የወል ሥነ ልቦናዊ፣ መንፈሳዊና ማህበራዊ ጤንነት መጠበቅ ልዩ ትኩረት ሊሠጠው የተገባ ሆኖ ተሠምሮበት እናገኛለን።

በዚሁ መሠረት አልፎ አልፎም ቢሆን፣ ብቻ በወቅታዊነት ለምልዓተ ሀገር ወገን ጠቋሚነት ያላቸው አንዳንድ መልዕክቶችን በማዘጋጀት የበኩሌን መጠነኛ «ጠብታ» ወይንም «ጠጠር» የመወርወር ያህል ጥረት ማድረጉን አስፈላጊነት አምኜበት እንካችን ለሁላችን ማለት እደፍራለሁ። ከዚህ ቀደምም ለክብ ርት የኢ. ፌ. ዴ. ሪ. የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና ለአሁኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወቅታዊ ሀገራዊ ብሔራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በተመለከተ አጋዥ ትንታኔዎችና ምክረሃሳቦችን ለማካፈል ጥረት አድርጌያለሁ።

ዛሬ ደግሞ በዋነኛነት በተለይም ጥቂት ከማይ ባሉ የወቅቱ «ከእኔ ወዲያ ላሳር አዋቂ አድራጊ ፈጣሪ» አንጋፋ ተብዬ የፖለቲካ ድርጅቶችና አመራሮች አቅጣጫ፣ ዕለት ከዕለት ሊባል በሚችል መልኩ፣ በአጓጉል ቀቢፀ ተስፋ እልኸኝነት መንፈስ በሚያስተባብሩት አሉታዊ ማደነጋገሪያዎችና ዘመቻዎች «የትግል» መሥመርን ግምት ውስጥ ስናስገባ፣ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ በምልዓተ ብሔራዊ ሀገር ደረጃ የወደፊት ታሪካዊ ቦታቸውን ብቻም ሳይሆን ቀደምት ክብራቸውን ሳይቀር ጥላሸት እየቀቡና እያቆሸሹ እንዳሉ ልንመክራቸው የግድ ሆኖብናል። ምክንያቱም ይዋል ይደር እንጂ ለዝንተ ዓለም የውርደትን ማቅ በመከናነብ በታሪክ ተወቃሽነት የመዳረግ ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም፤ የተፈጥሮ ህግ ጉዳይ ነውና።

 በአሁኑ ጊዜ ጥቂት በማይባሉ ሊህቃን ተብዬዎች ቀጥተኛ አጋፋሪነትና አዝማችነት እየተከሰቱ ያሉትን ነውረኛ የእርስ በርስ የመጠላለፍና የመነቋቆር አልፎም የመጠፋፋት ነቀርሳ ግምት ውስጥ ስናስገባ፣ ከእኛ በፊት የቀደሙትን ያለፉትን መሪዎቻችንና አጋዥ ባለሥልጣናትን ብሎም ተከታዮቻቸውን እንደ አጠቃላይም ወገኖቻችንን ለመንቀፍም ሆነ ለመተቸት የሚያስችለን ምንም ዓይነት የሞራል ልዕልና (ብቃት) ሊኖረን ይችላል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም ለስሙ በሠለጠነ ወቅት ላይ እንገኛለን ብለን ዝባዝንኬ ሐተታ እየዘከዘክን ባለበት ሁኔታ፣ በሌላ በኩል ግን ጭራሽ ቢብስ እንጂ ከቀደሙት ምንም ባልተሻለ መልኩ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያችን የወገን ህይወት እንደ አልባሌ እስከመቅጠፍ ሥነ ልቦና እስከማቁሰል፣ ንብረት እስከማውደም፣ ወዘተ የሚደርስ የኋላቀርነት ተርታ ተሠልፈን በውርደት አዙሪት ዳግመኛ ተጠልፈናል።

እንደ አጠቃላይ የአደጋውን ደረጃ ማለትም የውድመቱን ሥፋት፣ ጥልቀት እና መጠን እያንዳንዱ ቤተሰብ ይቁጠረው በማለት ከንፈር በመምጥጠ ብቻ እንደ ተራ መናኛ ጉዳይ ካለፍነው ደግሞ የበለጠ ውርደትና ክህደት ይሆንብናል!! ስለዚህ ኧረ «ስለክቡርነታችን» መባል ካለበት ዛሬና ዛሬ ብቻ ነው!! ዕውነትም በአሁኑ ጊዜ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ዓይነተኛውና ዋነኛው የድህነት ጋሬጣ የሊህቃን ተብዬዎችና የባለሟል ጋሻጃግሬዎቻቸው የአዕምሮ የሥነ ልቦና ድህነት (ስልብነት) ነው።

 ስለዚህ ሳይውል ሳያድር ደግሞም በፍፁም እከሌ ከእከሌ ሳንፎካከር እያንዳንዳችን (ሁላችንም) ከየህሊናዎቻችን ጋር በጥሞና በመመካከር «ማስተዋል» ካለብን ዛሬና ዛሬ ብቻ እንጂ ለነገ ቀጠሮ በመስጠት ዳግም ለመጃጃልና ስህተት ለመድገም መሞከር የለብንም!! አርቆ አሳቢነታችንና የማስተዋላችን ሁነኛ መገለጫ ሊሆን የሚችለው «እኔ ሊደረግልኝ የምፈልገውን ማንኛውንም መልካም የሆነ ሁሉ፣ እንዲሁ በተመሣሣይ … አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ» በሚለው የዕምነቶቻችን ሁሉ መሠረታዊ «ወርቃማ» መርሐግብር ረገድ ባለማወላወል በፍፁም ቁርጠኝነትና ፅናት መትጋት አለብን።

 በተለይም ርኩስ የቂም የበቀል የጥላቻ የመጠላለፍ ተንኮሎች፣ደባዎች፣ ሸፍጦች፣ ቅጥፈቶች፣ ምዝበራዎች (ስርቆቶች)፣ የመሣሠሉት ሁሉ ከየተዋረደ የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ሥርዓቶቻችን ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በአስነዋሪነት፣ በጠያፍነት ተይዘው እንዲወገዱልን የየበኩላችንን ንቁና ብርቱ አስተዋፅኦ ማድረግ የግድ ይለናል፤ ፖለቲካዊና ከአስተዳደራዊ ሥርዓቶቻችን ከተወገዱልን ደግሞ በዜጎች መካከል የመክሰማቸው ጉዳይ አጠያያቂ ሊሆንብን አይችልም። የቀጣይ ትውልዶቻችን ብሎም የተረካቢዎቻችን የተስፋ ዋስትና ሊረጋገጥም ሊለመልምም የሚችለው፣ እያንዳንዳችን (ሁላችንም) በየተዋረዶቻችን ዛሬውኑ ብቻ ሳይሆን አሁኑኑ ጀምረን በላቀ አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት (በ«ማስተዋል») ማከናወን ስንችል ነው፤ ምንም አይሳነንም፤ ብቃቱም አቅሙም አለን፤ ይቻላል፤ በእርግጠኝነት ስለሚቻል!! በአያሌ መመዘኛዎች ወደር የማይገኝለት የአድዋ የላቀ የአርበኝነት ወኔ፣ ጀብድ፣ የጀግንነት ገድልና ድል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ሁነኛ ስንቃችን በመሆኑ፣ በአድማሰ ሠፊ ሀገራዊ ብሔራዊ፣ ቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአስተሳሰብ ዓውድ መለምለም እንችላለን።

 በአንድ ወይንም በሌላ ምክንያት ለዘመናት ያመለጡን አያሌ መልካም አጋጣሚዎች የባከኑትን ግምት ውስጥ ስናስገባ ደግሞ በእርግጥም ዛሬም ሆነ ወደፊትም ከብቁ የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ምርጫችን በስተቀር ዳግም በኋላቀርነት አዙሪት የምንተበተብበትና የምንዳክርበት አሳማኝ ምክንያት ሊኖረን አይችልም። ደግሞ እኮ፣ አይደለም እኛ ከሥር መሠረቱ ከጠዋቱ ህብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያውያን ወንድማማቾች እህትማማቾች የሆንን እርስ በራሳችን ይቅርና፣ በየዘመናቱ በዕኩይ መሠሪ ተልኮዎቻቸው ምክንያት ለግምት አዳጋች የሆነ ቀጥተኛም ሆነ የእጅ ጥቃቶች፣ መርዘኛ መከፋፈሎች፣ መጨካከኖች፣ ጥፋቶችና ውድመቶች ካደረሱብን የውጭ ሀገራት ጋርም በእርቀ ሰላም መንፈስ በልዩ ልዩ ትብብርና የወዳጅነት ማዕቀፎች ዓውድ ውስጥ መኖር የግድ ብሎናል፤ ዓለማችንም የጋራችን የሁላችን ናትና።

አሁንም ቢሆን ግን መልካቸውን በመቀያየር ልዩ ልዩ ዕኩይ ሴራዎችን በማቀነባበር ዳግም በከፋፋይ እንዳይተበትቡን ብርቱ ጥንቃቄ የማድረጋችን ጥረት ለአፍታም ያህል ሳይዘነጋና ሳያሰልስ ማለት እንደሆነ በተገቢው ይሠመርበታል። ከወዴት ፀነስናቸውና!! ልዩ ልዩ ጉራማይሌነታችን፣ ዥንጉርጉርነታችን፣ ህብረ ቀለማችን ሁሉ አንድነታችንን የሚያጠናክሩ ልዩ ገፀበረከቶቻችን ውበቶቻችንና ድምቀቶቻችን ዕምቅ አቅሞቻችን እንጂ ፈጽሞ የመጠቋቆም፣ የመነቋቆር እና የመከፋፈል ምክንያት ሊሆኑብን አይችሉም። በቅድሚያ ግን፣ ከእንግዲህ አይነት ወጥመዶችንና እንቅፋቶች ሁሉ ራሳችንን ነፃ ማድረግ ይጠበቅብናል፤ በቅድሚያ በመሠረታዊነት እያንዳንዳችን ኃላፊነትን የመውሰድ ድርሻ ይጠበቃል ማለት ነው። ምናልባት የቀደሙት ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ፍትኃዊነት የጎደላቸው ስለነበሩ ለአመፅ ተገፋፋን ቢባል እንኳን፣ ዛሬ ግን፣ በተለይም ምልዓተ ነፃነታችንንና ዴሞክራሲያዊ ዕኩልነታችን በተረጋገጡበት ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ዓውድ ውስጥ፣ ለህግ የበላይነት አለኝታ ሆነን የማንፀናበት ምንም ዓይነት ሚዛን የሚደፋ አሳማኝ ምክንያት ሊኖረን አይችልም። መሠረታዊ የሚባሉት መብቶቻችን ያለምንም ዓይነት መሸራረፍ በዘላቂነት ከተረጋገጡ ቁሳዊ ድህነትን ለማጥፋት ብቻ ሳይሆን በብልፅግና ጎዳና ለመገስገስም ብርቱ ኃይልና ጉልበት ማቀናጀት እንችላለን ማለት ነው።

 በእርግጥም ከቁሳዊ ድህነት ይልቅ ብርቱ የማጣት ደዌ ማለት ያለማስተዋል ነው። በተያያዥነትም ለላቀ ሥነ ሥርዓት፣ ሥነ ምግባርና ለግብረገብነት ልዩ ቦታ ልንሠጥ የግድ ይለናል፤ እንደዚሁም የሥራ ባህላችንን እና የጊዜ አጠቃቀማችንን በማበልፀግ ረገድም ቁርጠኛ ውሳኔ ከአሁኗ ቅፅበት ጀምረን መወሰን ይኖርብናል። እኛ ኢትዮጵያውያን እኮ ዘመኑ በሚጠይቀው ደረጃ በሚገባ በሥርዓት ቀምረንና አደራጅተን ባለማቅረባችን ካልሆነ በስተቀር ከቀደምት የሥልጣኔ ቆንጮዎች ውስጥ በውል መመደብ የሚገባን አያሌ መገለጫዎች ያሉን ብርቅዬዎች መሆናችንን መጠራጠር ባልተገባን ነበር!! ከፈርጀ-ዓይነተ ብዙ «ምድር ቀደምትነት» ጋር በአያሌ መመዘኛዎች ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ወደር ያልተገኘለትን የአድዋን የላቀ ድል ሥልጣኔ ጥበብ ሁሉ የሚጨምር ነው።

 የዘመናዊ ሥልጣኔ ባለቤቶች የሚበልጡበት ዓይነተኛ ዋነኛ ነገር ቢኖር በጊዜ አጠቃቀማቸው፣ በሥነ ሥርዓቶቻቸው፣ በብርቱ የምርምር ብሎም የፈጠራ ትጋቶቻቸው እና በጥራት ለማከናወን ከፍተኛ ትኩረት ከመሥጠታቸው አንፃር ነው ማለት ያስደፍራል። ታዲያማ እኛስ ለምንና እንዴት ወደ ኋላ እንቀራለን? እኛ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ በጣም የተሻለ ዕድልና ተስፋ አለን፤ «ስለክቡርነታችን» ስንል በሚገባ በላቀ የማስተዋል የኃላፊነት መንፈስ እስከተጠቀምንበት ድረስ!! «የእኔ/የእኛ የኢትዮጵያዊነት ዕፁብ ድንቅ ፀዳል ስብዕና፣ ምጡቅ የህሊና ልዕልና ብልፅግና» በማለት ህብረ-ብሔር ቃል ኪዳናችንን አፀናን፤ በላቀ ቁርጠኝነት ፅናትና ትጋት የሥልጡንነት ግስጋሴውን አለመለምነው።

 ስለዚህ እያንዳንዳችን (ሁላችን) ኢትዮጵያውያን «ስለክቡርነታችን» ደግሞም የውዴታ ጉዳይ ብቻም ሳይሆን፣ ይልቁንም ምንም ዓይነት ሰበብ አስባብ ምክንያቶችን ከመደርደር በመቆጠብ፣ የጊዜ ቀጠሮም መስጠት ሳያስፈልገን፣ ዛሬውኑ ብቻም ሳይሆን በአሁኗ ቅፅበት በቁርጠኝነት ወስነን በተግባር የመለወጥ ጉዳይ ዋነኛ ግዴታችን ሆኖ ይታያል። ምናልባት ደግሞ እጅግ በጣም ጥቂቶች በማፈንገጥ በተላላነት በዋዛ ፈዛዛ የጭካኔ ዝንባሌ ዓውድ ውስጥ የሚዳክሩ ቢሆን እንኳን፣ ብዙዎቻችን በላቀ ቁርጠኝነት በጽናትና በትጋት እስከተገበርን ድረስ ስለስኬቶቻችን የቅንጣት ያህል የስጋትም፣ የጥርጣሬም መንፈስ ሊገዳደረን አይችልም።

በአይበገሬነት በነፃነትና በሉዓላዊነት ፈር ቀዳጅ ፋና ወጊ ሆነን እንደምናስታውሰው እንደምንዘክረው ሁሉ «ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያችን ያልተሸራረፈ የነፃነት፣ የዕኩልነት፣ የፍትህ፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነት፣ የልማትና የብልፅግና ‘ደሴት’ ፀዳልነታችንን» ማረጋገጥ ቀጠሮ የማይሠጠው አስቸኳይ ዓብይ ሀገራዊ ጉዳይ ነው። በእርግጠኝነት እንችላለን!! «ስለክቡርነታችን» በክብር!!

አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011

(ሙሉጌታ በትረ ገብረማርያም (ተ/ፕ/ር-ዶ/ር)፣ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)