“ህዝብ የሚጠቀመው የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ቢገቡ ነአቶ ተመስገን ዘውዴ

152

የተወለዱት በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን ቡልቂ ወረዳ ነው፡፡ በንግድ ስራ ትምህርት ቤት (ኮሜርስ) በጽህፈት ስራ አገልግሎት እ.ኤ.አ 1969 ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ ለአራት ዓመታትም በተማሩበት ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ የትምህርት ዕድል በማግኘት ወደ አሜሪካ ተጉዘው በንግድ አስተዳደር እ.ኤ.አ በ1976 በዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

ለ22 ዓመታት ከኖሩበት አሜሪካ የተመለሱት አቶ ተመስገን ዘውዴ፤ በ1997 ዓ.ም በምርጫ ተወዳድረውና ህዝብን ወክለው ፓርላማ በመግባት አገልግለዋል፡፡ ከአቶ ተመስገን ጋር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዳይ እንዲያዋዩን ቆይታ አድርገናል። የሰጡን አስተያየት እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አጠቃላይ ሁኔታ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነጻና ገለልተኛ በሆኑ ባለሙያዎች እየተመራ አልነበረም፡፡ ባለሙያዎቹ በፖለቲካ ጫና ስር ነበሩ፡፡ ከዚህም በላይ ብዙ ለኢትዮጵያ ህዝብ የማይጠቅም ነገር እየተደረገ ነው እዚህ የተደረሰው፤ አንዱ እዳ ነው፡፡ እዳው ልንከፍለው ከማንችለው በላይ ሄዷል፡፡ ከአገራችን ምጣኔ ሃብት ደረጃ የልጅ ልጆቻችን ከፍለው የማይጨርሱት እዳ ተከማችቷል፡፡ ይህ እየታወቀ ነው፡፡

እነ አቶ መለስ የነበሩበት የኢኮኖሚ ሂደት በተከታታይ አድጓል እያሉ ሌላው ነገር ተደብቆ ቆይቷል፡፡ በዚያን ጊዜ ቢያንስ የሶስትና የአራት ወራት የዶላር ክምችት ሊኖረን በሚገባ ጊዜ የሳምንታት እንኳን ያልነበረበትና በጣም ችግር የነበረበት ጊዜ ነበረ፡፡ የዋጋ ግሽበቱ የኢትዮጵያን ህዝብ አንበርክኮት ቆይቷል፡፡

ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክና ባግባቡ መመገብ ተስኗቸው የነበረበትና የስራ አጥ ወጣት ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ዘመን ነበር፡፡ ያ ሁሉ ተደብቆ ብሄራዊ ምርት በተከታታይ አድጓል እየተባለ ሲታወጅ ነበር። ብሄራዊ ምርት እድገት በተከታታይ እውን ሆኖ ከሆነ እንደህዝብ የተከፈለ ዋጋ አለ፡፡ የዋጋ ግሽበቱ በሁለት እጥፍ እየናረ ከህዝብ አቅም በላይ ደርሶ ነበርና፡፡

በዚህ ረገድ አሁን ያለውን የዶክተር አብይን መንግስት ለመገምገም ቀድመናል፡፡ ምክንያቱም የእርሳቸው አስተዳደር የሚገመገምበት ጊዜ አይደለም። በርግጥ ችግሩን የተረዱት ይመስላል። እዳውን ያወቅነው አሁን ነው። ስለዋጋ ግሽበት፤ ስለወጣቶች ስራ አጥነትና ስለድህነት እያወራን ነው፡፡ እነ አቶ መለስ በማወቅ እንዳላወቁ ዘሩት፤ እነዶክተር አብይ ደግሞ እያጨዱት ነው፡፡

ይህንን ለማስተካከል ጥረት መደረግ አለበት፡፡ መንግስት እንደፈለገው ገንዘብ ማውጣት አይችልም፡፡ ስርዓትና ደንብ አለው፡፡ ለመስራት የምንፈልጋቸው ብዙ ቢሆኑም፤ በአንድ ጊዜ መስራት አንችልም፡፡ 26 ቢሊዮን ዶላር ተበድረን እያለማን ነው ቢባል አያስኬድም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የልጅ ልጆቻችን በእዳ ይያዛሉ፡፡

አሁን ስለፕራይቬታይዜሽን እየተወራ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሩ ድርጅት ውስጥ ሼር እንዲኖረውና አብሮ እንዲያድግ ይፈልጋል። የውጭ ባለሃብት መጥቶ የተሻለ ደረጃ ቢያደርሰውም ደስ ይለናል፡፡ ግን ህዝቡ አብሮ ማደግ ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም፤ የህዝቡን አቅምና ተጠቃሚነት ያገናዘበ እንዲሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡

አሁንም ያለው አመለካከት ሁለት ቦታ የረገጠ ነው፡፡ አንዱ ነጻ ገበያ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ የመንግስት ረጅም እጅ ገበያውን እየተቆጣጠረ የሚያስተካክልበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በየትኛው መንገድ ይሄዳል የሚለው የኢትዮጵያ መንገድ ግልጽ አይደለም፡፡ እንደተከታተልኩት ከሆነ የዶክተር አብይ መንግስት በኢኮኖሚ፤ በማህበራዊ፤ በፖለቲካዊ ግንኙነት ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖረው የሚፈልግ ይመስላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ፍላጎት፤ አቅርቦት፤ ዋጋና ነጻ ገበያ የምንለውን እርሱ እየወሰነ ሃብት የማከፋፈሉን ስራ መስራት የሚፈልግም ይመስለኛል፡፡ የህዝቡ፤ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ሚና ምን ያህል ይሆናል የሚለውን ርግጠኛ ለመሆን የሚቻልበትን ጊዜ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን የውጭ ጫና በኢኮኖሚና እየበዛ በሚሄድበት ጊዜ አንዱን መስመር ይይዛል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ነጻ የገበያ ኢኮኖሚ በሚከተሉ አገሮች የገበያ ዋጋ የሚወሰነው በፍላጎት እና በአቅርቦት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ሁለቱንም እየተከተለች ትገኛለች፡፡ የመንግስት ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ነጻ ገበያም በተወሰነ መልኩ አለ፡፡ ከጊዜ በኋላ የምናውቀው ይሆናል፡፡

 የውጭ አገራት ፍላጎትና አጋርነት

ሁሉም አገራት ከራሳቸው ጥቅም አኳያ ነው የሚንቀሳቀሱት፤ ቻይናም፤ አሜሪካም፤ እንግሊዝም ቢሆኑ፡፤ ማናቸውም የኢትዮጵያ ደህንነትና የወደፊት ልማት ስሜት የሚሰጣቸው አይደለም፡፡ እኛ ስለራሳችን ማወቅ አለብን፡፡ ከእነዚህ አገራት ጋር ወዳጅነታችን የላቀ ነው፡፡ ይሄ ዶክተር አብይ የጀመረው አይደለም፡፡

በኃይለ ስላሴ ዘመንም ከአሜሪካኖችና ከተለያዩ አገራት ጋር ወዳጅነቱ ነበረን፡፡ አሁን ቻይና ሰፋ ባለ መንገድ በተመጣጣኝ ወለድ እያበደረችን ነው፡፡ የተረጋጋና የሚሰራውን የሚያውቅ መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያዋጣውን ነገር ያያል፡፡ ወለዱ ትንሽ ስለሆነ ዝም ብለህ አትበደርም፡፡ ፕሮጀክቶችንም አትጀምርም፡፡ በትውልድና በአገር ላይ የሚያመጣውን ጠንቅም ትመዝናለህ፡፡

“26 ቢሊየዮ ዶላር ዕዳ አለብን፤ እንዴት ይከፈላል?” መባል አለበት፡፡ በወጪ ንግዳችን ቡናና፤ ሰሊጥ ሸጠን የምናገኘው ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዩን ዶላር አካባቢ ነው፡፡ ሌላውን ነገር ትተን ለነዳጅ ብቻ ሶስት ቢሊዮን ዶላር በዓመት እናወጣለን፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ዕዳ የምንከፍለው? ስለዚህ ሃላፊነት የሚሰማው አመራር እነዚህን ሁሉ ይመለከታል፡፡

አገራት ገንዘብ አለና ተበደር ስላሉት ብቻ አይወስንም፡፡ በፊት ለፖለቲካ ፍጆታ ይደረግ እንደነበረው አይወሰንም፡፡ አሁን ያለን አማራጭ እዳችንን በረጅም ጊዜ መክፈል እንድንችል አገራትን መለማመጥ ነው፡፡ ይህ እንዳይደርስ ኢትጵያንና ህዝቦቿን እወዳለሁ፤ አከብራለሁ፤ ልማቱንም እፈልጋለሁ የሚል አመራር ብዙ ነገር መዝኖ ነው እዚህ ውስጥ መግባት ያለበት፤

 የፋይናንስ ዘርፉ እና የውጭ ባለሃብቶች

መንግስት የውጭ ባንኮችንና የውጭ የፋይናንስ ዘርፎችን አግዶ ማቆየት አይች ልም። ኢትዮጵያ በአ ንድ በኩል የአለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል እሆናለሁ ብላ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በሌላ በኩል፤ እስካሁን የኢንሹራንስ፤ የባንክና የፋይናንስ ድርጅቶች ከውጭ እንዳይገቡ ገድ ባለች፡፡ ይህ ቀጣይነት የለውም፡መለ ቀቅ አለባት። የተለያዩ ጫናዎች እየመጡ በመሆኑ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልም መሆን አለባት።

ባንኮችና የተለያዩ የፋይናንስ ድርጅቶች ቢገቡ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ለመቅሰም ያስች ላል፡፡ አሁን ተጠቃሚ እየሆንን አይደለም፡፡ ምክንያቱም መንግስት ለአገር በቀል ፋይናንስና የኢንሹራንስ ድርጅቶች በእግራቸው እንዲቆሙ እድል ለመስጠት ሲባል እነርሱ እንዳይገቡ በመ ደረጉ ነው። የውጭ ባለሃብቶች በሚገቡበት ወቅት በሚፈጠረው ውድድር የአገር ውስጥ የፋይናንስ ድርጅቶች ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ እንጂ፤ ህዝብ የሚጠቀመው የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ቢገቡ ነው፡፡ አገር በቀል ባንኮችና የኢንሹራንስ ድርጅቶች ይህንን አውቀው አቅማቸውን ማደርጀትና ብቁ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ መንግስት ይህንን ገድቦ ማቆየቱ ህጋዊ ተቀባይነትም አይኖረውም፡፡

 ማክሮ ኢኮኖሚ

የማክሮ ኢኮኖሚ ነገር በጎበዝ ባለሙያ ወጥ እንደመስራት ያለ ነው፡፡ የጣፈጠ ወጥ ለመስራት ብዙ ነገር ያስፈልጋል፡፡ አንዱን አሳንሰህ ሌላውን ጨምረህ የሚጣፍጥ ወጥ መስራት አትችልም፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚውም እንደዚያ ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስራ አጥ፤ የዋጋ ግሽበት፤ ብሄራዊ ዕዳ፤ በንግድ የሚመጣ ቀውስና የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ፡፡ ልክ እንደወጡ ይሄም ተጣጥሞ ካልሄደ አንደኛው በሌላው ላይ ቀውስ ያስነሳል፡፡

የሰዎች ገንዘብ የማስቀመጥ አቅም መጨመር አለበት። የውጭ ኢንቨስትመንት ሊጨምር ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ፤ ዝም ብሎ ገንዘብ ማተም ወረቀት ማብዛት ነው የሚሆነው፤ ጥሩ ማክሮ ኢኮኖሚ ያለበት ቦታ የተጣጣመ ሂደት ነው ያለው፤ ምርትንና የግብር ከፋዩን ቁጥር ማሳደግና ህዝብ ግብሩን በትክክልና በሰዓቱ እንዲገብር በማድረግ እያጣጣሙ መቀጠል አስፈላጊ ነው፡፡ ከሌሎች አገራት እየተደጎሙ መቀጠል አያዋጣም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ አንድ ቦታ መቆሙ አይቀርም፡፡ ግሽበቱ ተሻግሮ መጥቷል። በመሆኑም ከፍተኛ

 ስራ መስራት አለበት፡፡

የምክር ቤት ቆይታ

በፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ ይደረግ ነበር፡፡ በተለይ ትዝ የሚለኝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹ፊዚካል ፖሊሲ›› እና ‹‹ፊስካል ፖሊሲ›› በሚለው አተረጓጎም ላይ ያነሱት ነው፡፡ እኔ በታክስ ስርዓቱ ላይ አሁን እንደታየው አይነት ቀውስ እንዳይፈጠር ለታክስ ስርዐቱ ምን አይነት ስልት እንዳላቸው ጥያቄ አቀርብ ነበር፡፡ ‹‹ፊዚካል ፖሊሲ›› እና ‹‹ፊስካል ፖሊሲ›› የሚለውን በመያዝ ጨርሶ የጥያቄውን አቅጣጫ ለመቀየር ባደረጉት ሙከራ እርሳቸውም ሆኑ ሚኒስትሮቻቸው አንገታቸውን ደፍተው እንዲወጡ አድርጌያለሁ፡፡ መተባበር የሌለበት የሚያስመርር ክርክር የሚደረግበት ፓርላማ ሂደት ነበር፡፡ በኢኮኖሚው ላይ ለሚጠየቁት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ ላለመስጠት የዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ በነበረበት ጊዜ የአንድ ዲጂት ግሽበት ነው አገር ውስጥ ያለው ሲሉ ነበር፡፡

አንድ መንግስት ፊሲካል ፖሊሲና ሞኒተሪንግ ፖሊሲ አለው፡፡ የገንዘብ ፍሰት ፖሊሲና የግብር /የታክስ/ አሰባሰብ ፖሊሲ ማለት ነው፡፡ እርሳቸው እነዚህን ሁለቱን አደበላልቀው ራሳቸው ነበሩ የሚመሩት፤ አሜሪካን አገር የገንዘብ ፍሰቱን የሚመራው አካል ነጻና ገለልተኛ ሆኖ በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ ብዙ ስራዎችን ይሰራል፡፡

ብሄራዊ ባንኩ በአቶ መለስ ስር ነበር። አሁን በዶክተር አብይ መንግስትም በስራ አስፈጻሚው ስር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የዋጋን ግሽበት፤ የወለድን መጠን፤ ማነስና መብዛትን፤ እንዲሁም በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን ሊቆጣጠር አይችልም፡፡ ምክንያቱም፤ የሚቆጣጠረው ለፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀምበት የሚፈልገውና ከፍተኛ የገንዘብ ጥማት ያለበት ስራ አስፈጻሚው ነው፡፡ ስራ አስፈጻሚውን እንዲህ አድርግ ብሎ መናገር በማይቻልበት አገር ብሄራዊ ባንኩ በእርስዎ ስር ወድቋል እያልኳቸው ነበር፡፡ እርስዎ መምራት ያለብዎ የፊሲካል ፖሊሲውን ነው፡፡ ታክስና ግብር ማስከፈል፤ የከፋዮቹን ቁጥር ማብዛትና የበጀት እጥረት እንዳይፈጥር ማድረግ ነው፡፡ ሞኒተሪንግ ፖሊሲው ግን ነጻና ገለልተኛ በሆነ አካል መተዳደር አለበት ነው ያልኳቸው፤ እርሳቸው ግን ከእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎችና ገለጻ ውስጥ ያወጡት ‹‹ፊዚካል ፖሊሲ›› እና ‹‹ፊስካል ፖሊሲ›› የሚለውን ነው፡፡ ‹‹ፊዚካል›› ብዬም ከሆነ ቃሉ በኤፍ (F) የሚጀምረው ነው ግን እንደ እርስዎ አላፏጨሁበትም ብዬ ነገርኳቸው፡፡

አፈ ጉባኤው አንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣንን እንዲህ መናገር አይችሉም አሉኝ፡፡ ምክር ቤት የገባነው እኔና ጓደኞቼ የህዝብ ተመራጭ ነን፡፡ የፌዴራል መንግስቱ የከፍተኛ እርከን ላይ ነው ያለነው፤ ይህንን መገንዘብ ያስፈልጋል ስላቸው ድምጽ ማጉያውን ዘጉብኝ፡፡

አዲስ ዘመን  መጋቢት 18/2011

ዘላለም ግዛው