የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና አሰራሩ

114

የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በሁሉም ሀገር ውስጥ የሚገኝ ተቋም ሲሆን፤ ስያሜውም ዓለም አቀፍ ነው፡፡ የዚህ ተቋም ዋና ዓላማ በሁሉም ዘርፍ የንግዱን ማህበረሰብ መወከል ነው፡፡ በኢትዮጵያም ከ70 አመት በፊት ተቋቁሞ ተመሳሳይ ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በአደረጃጀቱና በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ስላለው ሚና ከምክርቤቱ ዋና ፀሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ስለ ምክርቤቱ አደረጃጀት ቢገልጹልኝ?
አቶ እንዳልካቸው፡- በዓለምአቀፍ ደረጃ የንግድ ምክር ቤት የሚቋቋመው በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንዱ የመንግሥት አዋጅና ህግን መሰረት አድርጎ የሚቋቋም ሲሆን፣ሁለተኛው ነፃ ማህበር ሆኖ የሚመሰረት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተከተልነው ሞዴል በመንግስት አዋጅና መመሪያ መሰረት የሚቋቋም ሆኖ ስራውን የሚመራውና አመራሩን የሚያዋቅረው በራሱ ነፃ በሆነ መንገድ ነው፡፡

በዚሁ መሰረት ንግድ ምክር ቤቱ ተግባሩን በመወጣት ላይ የሚገኘው ቀድሞ የነበረው አዋጅ ተሽሮ ከ16 አመት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በፀደቀው አዋጅ 341/95 መሰረት ነው፡፡ በስራ ላይ ያለው አዋጅ የንግድ ምክር ቤት በሶስት ደረጃ እንዲቋቋም ይደነግጋል፡፡ በከተማ፣በክልልና በሀገርአቀፍ ደረጃ፡፡ የከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያቋቁማሉ፡፡ ክልሎች ደግሞ ተሰባስበው ሀገር አቀፉን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ያቋቁማሉ፡፡ ምክር ቤቱ በዚህ መልኩ ነው እየሰራ የሚገኘው፡፡

አዲስዘመን፡- ቀድሞ የነበረው አሁን በስራ ላይ ካለው አዋጅ ጋር ልዩነቱ ምንድን ነው?
አቶ እንዳልካቸው፡- ቀድሞ የነበረው አዋጅ በሶስት ደረጃ የተዋቀረ አልነበረም፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ላይ አንድ ተቋም ተቋቁሞ በቅርንጫፎቹ አማካኝነት ነበር ስራውን የሚያከናውነው፡፡ በተሻሻለው አዋጅ ግን የፌዴራል ስርአት አወቃቀርን ተከትሎ ክልሎችም የየራሳቸውን የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት አዋቅረው ሀገር አቀፉን እንዲመሰርቱ ነው የደነገገው፡፡አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የተደረገውም በተሻሻለው አዋጅ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የንግድ ተቋማት አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በንግድ ምክርቤት መዋቅር ውስጥ የተካተቱት 527ሺ ይደርሳሉ፡፡

በአምራች ዘርፍ ላይ የተሰማሩት ድምጻቸውና ውክልናቸው እንዳይሳሳ የተመረጡ ስድስት ዘርፎች የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት አባል እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ የተመረጡት ዘርፎች በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ጨርቃጨርቅ አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣አበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ፣ስጋ፣የቅባት እህሎችና ስኳር ናቸው፡፡ ምክርቤቱ 6ቱ የአምራች ዘርፎች፣ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮችና ዘጠኙ ክልሎች እንዲሁም የብረታብረት፣ የጋራዥ፣ የፋርማሲቲካልና ሌሎችንም አጠቃልሎ የያዘው የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክርቤት፣ በድምሩ18 አባላትን ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ አባላቱ ተቋማት እንጂ በግላቸው ሱቅና ፋብሪካ ከፍተው በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩት አይደሉም፡፡
ለምሳሌ ሀዋሳ ላይ ዳቦ ጋግሮ ለተጠቃሚው የሚያቀርብ ነጋዴ የሀዋሳ ከተማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት አባል ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ደቡብ ክልል ውስጥ 101 ከተሞች አሉ፡፡ በየከተማው ላይ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ 101 ከተሞች ተሰባስበው የደቡብ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ይመሰርታሉ፡፡ ክልሉ ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት አባል ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የተሻሻለው አዋጅ ከላይ በተጠቀሱት መልኩ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ክፍተትስ የለውም?
አቶ እንዳልካቸው፡- የተሻሻለው አዋጅ ቀድሞ ከነበረው የተሻለ ቢባልም ክፍተት የለውም ማለት አይደለም፡፡ ከአደረጃጀት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ ፍላጎት በትክክል እየተወከለ ነው ወይ? ሲባል ውስንነቶች አሉ፡፡ አንድ የንግድ ተቋም እንደፋብሪካም እንደነጋዴም ሆኖ ገበያ ውስጥ ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡ይህ ሲሆን ደግም አንድ ሰው የዘርፍ ማህበራት እና የንግድና ዘርፎች ማህበራት አባል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም ወጥነት ያለው አንድ የንግድ ማህበረሰብ ተወካይ የሚገኝበት የተጠናከረ አደረጃጀት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
በአባላት በኩልም የሚጠበቅባቸውን የመዋጮና የተለያዩ ግዴታዎች በመወጣት በአመራርነት ለማገልገል ያለው ፍላጎት፣ በምክክር መድረኮች ላይ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ፣መንግስትንም ሞግቶ አማራጭ ፖሊሲ እየሰጡ በመሄድ በኩል ገና ብዙ ይቀራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አዋጁ ሲሻሻል የምክርቤቱ አባላት ተሳትፎ አልነበራቸውም?
አቶ እንዳልካቸው፡- መድረኮች ተዘጋጅተው ነበር፡፡ነገር ግን በቂ በሆነ ሁኔታና የንግዱ ማህበረሰብ ግብአት ተካትቶበት ነው ወደስራ የተገባው ለማለት አንችልም፡፡ አዋጁ ከወጣበት ማግስት ጀምሮ ችግሩ መታየት ሲጀምር በአደረጃጀቱ ላይ ቅሬታዎች መነሳት ጀመሩ፡፡ በወቅቱም ውይይቶች ተደርገዋል ግን መፍትሄ አልተገኘም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የምክቤቱ አባላት ምን የመፍትሄ ሃሳቦች አቀረቡ?
አቶ እንዳልካቸው፡- የጀርመንና የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች በአንድነት የአፍሪካና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮን መሰረት አድርገው በጥናት ክፍተቱ ተለይቶ አዋጁ እንዲታይ ለመንግስት ቀርቧል፡፡ ከመንግስት ጋር ለማገናኘት በሚዘጋጁ የተለያዩ የምክክር መድረኮች ላይም በማንሳት የንግዱ ማህበረሰብ ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል፡፡በተለይም የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ማቋቋሚያ አዋጅ 341/95 በባለቤትነት ከሚከታተለው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ስንሰራ ነው የቆየነው፡፡

ችግሩ የአመራር ለውጥ ተለዋዋጭነት ፍጥነት ስላለውና ለጉዳዩ ትኩረት ካለመስጠት ጋር ተያያዞ እንዲሁም የተቋማት አደረጃጀት ለውጥ የታሰበውን ለማሳካት አላስቻለም፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከመቀላቀላቸው በፊት በቅርቡ ከሁለቱ ተቋማትና ከንግድ ምክርቤቱ የተውጣጡ አባላት ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት ለሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ቀርቦ ነበር፡፡ አሁን ሁለቱም ተቋማት ስለተዋሀዱ ጉዳዩን ለማንቀሳቀስ ለውይይት እየጠየቅን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው የተሻሻለውና አሁን በረቂቅ ደረጃ ያለውን አዋጅ አንድነትና ልዩነት ቢገልጹልን?
አቶ እንዳልካቸው፡- የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ምክርቤት ማቋቋሚያ አዋጅ፣የተሻሻላው ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ማቋቋሚያ አዋጅ፣በረቂቅ ላይ ያለውና እንዲሻሻል ለጥያቄ የቀረበው የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ የሚል ነው፡፡ አደረጃጀቱ ሲቀየር ስሙም አብሮ ይቀየራል፡፡ አባላት ሁለት ቦታ አባል ለመሆን የሚገደዱበት ሳይሆን አንድ ቦታ አባል የሚሆኑበት አሰራር እንዲኖር ነው ጥረት በማድረግ ላይ ያለነው፡፡ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ግን ትኩረት የተሰጣቸው የአምራች ዘርፎች በአገልግሎት ሰጭዎች እንዳይዋጡ ውክልናቸው ተፈላጊወ ቦታ ሁሉ እንዲደርስም ለማስቻል ነው ጥረታችን፡፡ አሁን በተበታተነ ሁኔታ የሚንቀሳቀሰው ወጥ የሆነና በአንድነት እንዲንቀሳቀስ እንዲሁም የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ ያግዛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጥናት የተደገፈው አዲስ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የአባላትን ተሳትፎ አካትቷልን?
አቶ እንዳልካቸው፡- በአመት ሁለት ጊዜ በምናካሂደው የአባላት ፎረምና በተለያየ አጋጣሚ በሚዘጋጅ መድረክ ላይ አባላት እንዲሳተፉ በማድረግ ግብአቶች ተሰብስበዋል፡፡ በዋናነት የማሻሻያውን ስራ ሲሰራ የነበረው የቀድሞዎቹ ኢንዱስትሪና ንግድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ንግድ ምክርቤቱ በተዋናይነት ነው በማገዝ ላይ የሚገኘው፡፡ አሁን ሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተዋህደዋል፡፡ ጉዳዩም ለሁለቱም አዲስ አይደለም፡፡ ስለዚህ አዋጁ እንዲፀድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሚያቀርቡት ከሆነ አባላት በክልል ደረጃ ሳይቀር በረቂቅ አዋጁ ላይ እንዲመክሩበት ይደረጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በረቂቅ ላይ የሚገኘው አዋጅ የአባላትን ቁጥር ለመጨመር የሚረዳ ከሆነ አባልነት በግዴታ ነው የሚኮነው?
አቶ እንዳልካቸው፡- በማስገደድ ሳይሆን በማበረታትና ጥቅሙን በማስረዳት እንጂ በማስገደድ አባል እንዲሆኑ አይደረግም፡፡ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ትላልቆቹ ኩባንያዎች እንዲገቡ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ግን አለ፡፡ በዚህ ላይም ውይይት ተደርጎበታል፡፡ መንግስት በዚህ ላይ ምን አቅጣጫ ሊኖረው እንደሚችል ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን ባለው አሰራር የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ ለምን ጥረት አልተደረገም?
አቶ እንዳልካቸው፡- አሁን ባለው ሁኔታ ወጪያችንን የምንሸፍነው አጋር ድርጅቶች በሚያደርጉልን ድጋፍና ከህንጻ ኪራይ ከምናገኘው ገቢ ነው፡፡ ከአባላት የሚገኘው መዋጮ አነስተኛ ነው፡፡ ሌላው አባላት በእኔነት ስሜት አለመንቀሳቀሳቸው የሚሰጠው አገልግሎት አዳዲስአባላትን የሚጋብዝ አይደለም፡፡ሌላው አባላት በተለያየ መንገድ የመንግስት አካላትን ማግኘት ከቻሉ ወደ ምክርቤቱ አይመጡም፡፡ ይሄን ሁሉ ክፍተት በመለየት ነው አዲስ አደረጃጀት ያስፈልጋል የምንለው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ምክርቤቱ ባለበት የገንዘብ አቅም ውስንነትና በተለያየ ምክንያት የአባላቱን ቁጥር ለማሳደግ ካላስቻለው የአዋጁ መሻሻል ምን ፋይዳ አለው?
አቶ እንዳልካቸው፡- የአዋጁ መሻሻል በራሱ የሚፈጥረው አቅም አለው፡፡ ተከትለው በሚመጡ አቅሞችና ግብአቶች አገልግሎቶችን ማሳደግ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ንግድ ምክርቤቱ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ምን አስተዋጽኦ አለው?
አቶ እንዳልካቸው፡- ጠንካራ ኢኮኖሚ መፍጠር አስፈላጊነቱ አያጠያ ይቅም፡፡ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙትን ተቋማት ወደ ግል ለማዞር የሚደረገው እንቅስቃሴ ማሳያ ነው፡፡ እንደ ንግድ ምክርቤት ያሉ አደረጃጀቶች ደግሞ ጥረቱን በማገዝ ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ለአብነትም ጀርመንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ጀርመን 84 ሚሊዮን ህዝብ ነው ያላት፡፡ ከ23ሚሊዮን በላይ ጠንካራ የሆኑ የንግድ አይነቶች ናቸው በሀገሪቷ የሚንቀሳቀሱት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግን ከአንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ አንጻር ሲታይ ውስን ነው፡፡ ስለዚህ በርካታ የንግድ ዘርፎች እንዲፈጠሩ መስራት ይጠበቃል፡፡በሀገሪቷ የተጀመረውን መልካም የኢኮኖሚ አፈፃፀም ለማስቀጠል ጠንካራ የግል ዘርፍ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም አደረጃጀቱን ለማጠናከር የአዋጅ ማሻሻያው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ምክርቤቱ እስካሁን የሰራውን ስራ እንዴት ይገመግማል?
አቶ እንዳልካቸው፡- የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረክ አላቸው፡፡ አመርቂ የሚባል ስራ ተሰርቷል፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት የሚያግዝም ሌላ መድረክ አለ፡፡ የሌላ ሀገር ባለሀብቶች ኢትዮጵያ እንዲመጡ፡፡ የኢትዮጵያ ደግሞ ወደሌሎች ሀገሮች እንዲሄዱ በማድረግ፣ልምድ ልውውጥና የንግድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡ በአመት እስከ 20 የሚደርሱ ግንኙነቶች ይደረጋሉ፡፡ በዚህ የንግድ ልውውጥ ውስጥ ከትላልቅ ኩባንያዎች ጋር የመገናኘት ዕድል ተገኝቷል፡፡

የንግድ ባዛር በማካሄድም በተሰሩት ስራዎች ምርትና አገልግሎትን ከማስተዋወቅ ባለፈ የሀገር ገጽታን በመገንባት ድርሻ እያበረከተ ነው፡፡ የአባላቱን የንግድ ክህሎት ለማሳደግ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በንግድ ምዝገባ፣ በመደበኛ መስተንግዶና አያያዝ፣ውል ሲፈራረሙ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በአጠቃላይ ከስራቸው ጋር የተገናኘ አቅም በመገንባት ምክርቤቱ ሚናውን እየተወጣ ነው፡፡ ለማህበራት ላፕቶፕና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረግ፤ ቢሮ እንዲያገኙ ማመቻቸት የመሳሰሉ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡የበለጠ መስራት ይጠበቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከሌሎች ሀገሮች ጋር ከሚደረገው ግንኙነት ምን ተሞክሮ ተገኘ?
አቶ እንዳልካቸው፡- ምክርቤቱ የዓለምአቀፍ ንግድ ምክርቤት አባል ነው፡፡በየጊዜው በሚያደርገው ግንኙነት የአምራች ሀገሮች የምስክር ወረቀት ሲሰጡ የሚከተሉትን አሰራር ተሞክሮ አግኝቷል፡፡ ምክርቤቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመርተው ለወጭ ንግድ የሚላኩትን ምርቶች አረጋግጦ የምስክር ወረቀት ሲሰጥ ያገኘውን ተሞክሮ መሰረት በማድረግ ያከናውናል፡፡ የሌሎች ሀገሮች ነጋዴዎች ከመንግስታቸው ጋር ያላቸው ግንኙነትና መንግስታቸውን በምን አይነት ስርአት እንደሚሞግቱ የተገኘው ተሞክሮ በሀሜትና ባልተጨበጠ ነገር የሚደረግ ክርክርን ለማስቀረት አግዟል፡፡ ችግሮች ሲኖሩ በምክንያታ ዊነትና መፍትሄ በሚያስገኝ ነገር ላይ እንዲሆን እንዲሁም በጥናት እንዲደገፍ በማድረግ አሰራራችንን ለማሻሻል ጥረት እያደረግን ነው፡፡

በዚህ አሰራርም ወደ 120 ከሚደርሱ ጉዳዮች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከመንግስት ጋር ሆነን መፍትሄ እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ለአብነትም በቱሪዝም ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶች እንዲታዩና የቱሪዝም ቦርድ እንዲቋቋም፣የንግድ ፈቃድ አወጣጥ በዘመናዊ አሰራር እንዲታገዝ፣አላስፈላጊ በሆኑ የንግድ ዘርፎች ላይ ሲሰራበት የነበረው የብቃት ማረጋገጫ መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረግ የተሰሩት ስራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በጥናትና በመድረኮች ተወያይተን ችግሮች እንዲፈቱ መግባባት ላይ የደረስንባቸው ጉዳዮች አፈጻጸም ላይ ችግሮች ያጋጥሙናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የንግዱ ማህበረሰብ በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ እንጂ የዋጋ ቅናሽ ሲያደርግ አይስተዋልም ይሄ እስከመቼ ይቀጥላል?
አቶ እንዳልካቸው፡- ስግብግብነት ላይ የተመሰረተውን የዋጋ ጭማሪ ትተን ጤናማ በሆነ የኢኮኖሚ እድገት ዋጋ እየጨመረ መሄድ እንዳለበት ሳይንሳዊ ትንተናዎች ያስረዳሉ፡፡ የሸማቹ ኑሮ ሲያድግ የሚፈልገው አገልግሎትና ምርት በጥራት እንዲቀርብ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ጥራት ደግሞ ለዋጋ መጨመር ምክንያት ይሆናል፡፡ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም የዋጋ መናርን ያስከትላል፡፡

የሀገሪቷ ኢኮኖሚ እያመነጨ ያለው የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባውን ፍጆታ እየሸፈነ አይደለም፡፡ለአብነትም ባለፈው አመት የተለያዩ የወጪ ንግዶችን ልከን ገቢ ያገኘነው 3ነጥብ2 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ያስፈለገን ዶላር ግን 16ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከውጭ የምናስገባው ሸቀጥ ወደ ውጭ ልከን ከምናገኘው ዶላር በላይ በፍጥነት እያደገ ነው፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ሀገር ውስጥ እየተመረተ ባለመሆኑ ነው፡፡ ፋብሪካዎች እየተጠናከሩ አይደለም፡፡ የዋጋ መጨመር ከነዚህ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን የብዙ ነገሮች ድምር ነው፡፡
ሌላው አጋጣሚ ጠብቆ ዋጋ ማናር ከስግብግብነት ጋር ይያያዛል፡፡ይሄን ለማስቆም በሀገር ውስጥ በማምረት አቅርቦትን ማሳደግ ዋና መፍትሄ ነው፡፡ንግድ ምክርቤቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንዱ ንግድና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት በመሆኑ የውጭ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ፋብሪካ ከፍተው እንዲያመርቱ፣ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች በዋጋና በጥራት የተሻለ አማራጭ ፈልገው እንዲያቀርቡ በማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ዘላቂ መፍትሄ ግን በሀገር ውስጥ እንዲመረት ማበረታታት ነው፡፡

ምክንያታዊነት በሌለው ሁኔታ ዋጋ በመጨመር በአቋራጭ የመክበር ፍላጎት ያለውን ደግሞ ለማስተማር ምክርቤቱ ለንግዱና በአምራች ዘርፍ ላይ ለተሰማራው የስነምግባር መመሪያ ሰነድ አዘጋጅቶ በማሰራጨት ችግሩን በማስተማር ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ሰነዱ ድርጅቶች የራሳቸውን የስነምግባር መመሪያ እንዲያዘጋጁ ያግዛቸዋል፡፡ ሰነዱ መረጃው የሌለውን ያነቃዋል፡፡ መረጃው እያለው ለመስረቅ የሚንቀሳቀሰውን ደግሞ መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ መረጃ በመለዋወጥ ከንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ጋር እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እውነቱ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ነው?
አቶ እንዳልካቸው፡- አንዱ አማራጭ የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብና የንግድ ቀጣናዊ ትስስሮችን በማጠናከር የሚከና ወኑት ስራዎች ከወድድር እንደሚያወጡት ደጋግሞ ለነጋዴው በመንገርና የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣ ማስተማር ነው፡፡ ተቀብሎ ወደ መስመር የማይገባውን ደግሞ በህግ መጠየቅ ነው፡፡ የንግድ ምክርቤቱ ማስተማር፣ ማሳወቅና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመረጃ ልውውጥ ነገሮች እንዲስተ ካከሉ ከማድረግ ውጪ እርምጃ የመውሰድ ስልጣን የለውም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የንግዱ ማህበረሰብ በግብር ክፍያ ላይ ታማኝ አይደለም ለሚባለው ምላሽዎ ምንድን ነው?
አቶ እንዳልካቸው፡- እየተጠየቀ ያለው ግብር ፍትሐዊነት ሳይንሳዊ የሆነ አሰራር አለመከተልና ግብር የመክፈል ባህል አለመኖር በግብር ከፋዩና በግብር ሰብሳቢው መካከል አለመግባባቶች እንዳይኖሩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ችግሩ ጎልቶ የሚስተዋለው ተገማች ግብሮች በሚበዙባቸው ‹‹ለ›› እና ‹‹ሐ›› ላይ ነው፡፡ የንግዱ ዘርፍ ኢትዮጵያ ላይ ምንያህል ጠንካራ ነው፡፡ በሁለት አሀዝ በማደግ ላይ ያለው የሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከየትኛው ዘርፍ ነው የመጣው፡፡ የተሳካ ንግድ ነው እድገቱን ያመጣው? የሚለው ሳይንሳዊ የሆነ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡

በግብር ከፋዩ በኩልም በመንግስት ላይ ያለው እምነት፣ለከፈለው ግብር ቀጥተኛ ተጠቀሚነቱን የሚያረጋግጥበትን፣ ግብር መክፈል የዜግነት ኃላፊነት እንደሆነ በማስተማርና የሚጠብቀውንም ለማስተ ናገድ ዝግጁ መሆን ይገባል፡፡ ምክርቤቱ ከመንግስት ጋር በሚያዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ጉዳዩ ይነሳል፡፡በሂደት ይፈታል የሚል እምነት ነው ያለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ የሆነ የብድር አቅርቦት አለ?
አቶ እንዳልካቸው፡- ያለውን ምቹ ሁኔታ ለማየት በሀገር ውስጥ ካሉ ባንኮች ጋር የምክከር መድረክ አዘጋጅተን ነበር፡፡ ባንኮቹ የሚጠይቁት ወለድ ከአቅማቸው ጋር የሚጣጣም እንዳልሆነ ነው የንግዱ ማህበረሰብ የገለጸው፡፡ ምክርቤቱ ግን ያለውን የገንዘብ አማራጭ መረጃ ለንግዱ ማህበረሰብ በማቅረብ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች ሀገር ውስጥ ገብተው ቢንቀሳቀሱ ሊሰጡ የሚችሉትን ዕገዛ ከኢትዮጵያ ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመምከርና ጥናት በማቅረብ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የምክርቤቱን የወደፊት ዕቅድ ቢገልጹልኝ?
አቶ እንዳልካቸው፡- ምክርቤቱ ሁለተኛው አምስት አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ማብቂያ ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹የግሉ ዘርፍ የእድገት ስትራቴጂ›› በሚል የ2012 በጀት አመት ዕቅድ ዝግጅት ላይ ነው፡፡ የኢንቨስትመነት ድርሻውና የፋይናንስ አቅርቦቱ የተረጋገጠለት የግል ዘርፍ በመፍጠር በሀገሪቷ እየተመዘገበ ያለው ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ፣ ምክርቤቱ የጀመራቸውን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እና የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት፣ የውጭ ባለሀብቶችን የመሳብ ጥረቶች ማጠናከር፣የንግዱ ማህበረሰብ ለፖሊሲ አውጪዎች በጥናት የተደገፈ ግብአት በማቅረብ ሚናውን እንዲወጣ ማስቻል፣ ሴቶችና ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ከመንግስት ጋር የተናበበ ስራ መስራት፣ ሀገራዊና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ከዕቅዱ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡በዚህ መልኩ እየተዘጋጀን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፣ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ እንዳልካቸው፡- የምክርቤቱን እንቅስቃሴ ለህዝብ ለማሳወቅ ወደእኛ ስለመጣችሁ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አንተነህ ቸሬ