ሕዝቡ ቃሉን ዳግም ያድስ፤ ለቃሉም ይገዛ !

24

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ሲሆን ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያውያን እውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ ሠርቶ ማጠናቀቅ ህልም እንጂ እውን የሚሆን የማይመስላቸው ብዙዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን የጦር ጀግንነት ብቻ ሳይሆን በልማትም ጀግንነታችንን ለዓለም እናሳያለን በሚል ቆራጥነት ወደ ሥራው ገብተዋል።

 ለፕሮጀክቱ እውን መሆንም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራውን አሳርፏል። ሴት ወንድ፣ ህፃን አዛውንት፣ ሀብታም ደሀ፣ ተማሪ ሠራተኛ ሳይል ሁሉም እኩል ተነቃንቋል። በሞራል፣ በፍቅርና በአገራዊ አንድነት ሰሜት «እንገነባዋለን» በሚል ራሱ ለራሱ ቃል ገብቶና ተግባብቶ፣ አጨብጭቦ በአድናቆት ጭምር የተቀበለው ፕሮጀክት መሆኑን ደጋግሞ አረጋግጧል። በገባው ቃል መሰረትም ቃሉን ሳያጥፍ ድጋፍ ሲያደርግ፣ ቦንድ ሲገዛ አለኝታነቱን አስመስክሯል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የአካባቢው ርቀት ሳይገድበው፣ የአየር ንብረቱ ሳይፈትነው ከትንሽ እስከ ትልቅ ረጅሙን ኪሎ ሜትር አቋርጦ ጎብኝቶታል። 284ሺ ሰዎች ቦታው ላይ ደርሰው በሥፍራው ለሚገኙት ሠራተኞችና ባለሙያዎች ሞራል ሰጥተው ተመልሰዋል። ይሄ ህዝቡ ለራሱ የገባውን ቃል በተግባር ሲፈፅመው እንደነበር አንዱ ማሳያ ነው።

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መሰረቱ ተጥሎ ወደ ሥራ የተገባው ይሄ ፕሮጀክት ስምንት ዓመቱን ሊደፍን የቀሩት ሁለት ቀናት ብቻ ናቸው። በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታሰብም በተለያየ ምክንያት ሥራው ዘግይቷል። ለመዘግየቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋነኛነት ግን የብረታ ብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን የያዘው ሥራ በገባው የስምምነት ውል መሰረት ባለመሥራቱ እና የተሠራውም ከጥራት ጋር ተያይዞ ችግር ያለበት በመሆኑ ነው። ይሄንንም ችግር መንግሥት በመረዳት ችግሮቹን በመለየት በአሁኑ ወቅት ልምዱ፣ እውቀቱና ችሎታው ባላቸው የውጭ አገር ኩባንያዎች ጭምር ሥራው እንዲሠራ አድርጓል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ቀደም ሲል በሥራው ላይ ያለው የጣሊያኑን ሳሊኒ፣ የቻይና እና የፈረንሳይ ኩባንያዎችን ጨምሮ ሌሎችም በሥራው ላይ ተሠማርተዋል።

ይሄ ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ ምክንያት ተስፋ ወደመቁረጥ ለገባው ህዝብ ተስፋን የሚያለመልም እና ዳግም በሞራል የሚያነሳሳ ነው። አሁንም ግን «የሠራነው እኛው ነን» ብሎ በኩራት ለመናገር፣ አንገትን ቀና አድርጎ ለዓለም ለማሳየት አሁንም ከእያንዳንዳችን ገና ብዙ ሥራ፣ ብዙ ድጋፎች ከፊት ለፊታችን ይጠብቃል።

ፕሮጀክቱ ዛሬ 66 ነጥብ 26 በመቶ ላይ መድረሱን የፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤት አረጋግጧል። ቀረው ሥራ ደግሞ በአራት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል። በ2012 ዓ.ም. ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዩኒቶች 750 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ተብሎ ግብ ተቀምጧል ።

የፈረንሳይና የቻይና ኩባንያዎች ከቅድመ ኃይል ማመንጫ ጋር በተያያዘ፣ ጎን ለጎን ሥራውን የሚሠሩ ሲሆን፣ በእቅዱ መሰረትም ሁለት ጀነሬተር ተርባይኖች ግድቡ ሳይጠናቀቅ ኃይል ለማመንጨት በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። የፈረንሳዩ ኩባንያ የተርባይኑን ሥራ ጀምሯል። የቻይና ኩባንያ ደግሞ የብረታ ብረት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል። ይሄን የሚያሳየው መጠናቀቁን በጉጉት ለሚጠብቀው ዜጋ ተስፋ ሰጪ ነገሮች መኖራቸውን ነው። ሥራው በታቀደው መሠረት በጥራት እንዲጠናቀቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል።

 ስለዚህ የታሰበውን ያህል ስኬታማ መሆን የሚቻለውና አሁንም ከእያንዳንዳች ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ ተጠናክሮ ከቀጠለ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ቦንድ በመግዛትም ሆነ በተለያየ መንገድ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል አለበት። ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያዊነታችን ጥንካሬ መገለጫ ጭምር በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊ ጀግንነታችንን እና አንድነታችንን ዳግም ማስመስከር ያለብን ድህነትን ሊዋጋ የሚችለውን ፕሮጀክት አጠናቀን በድህነት ላይ መዝመት ስንችል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ «እኛው እንደጀመርን እኛው እንጨርሰዋለን» ብለን የገባነውን ቃል ዳግም ልናድስ ይገባል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011