የመምህር ተከስተብርሃን መንክር – አዲስ ህይወት

29

ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት ሙያና በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ሕይወታቸውን አሳልፈ ዋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም ከመጀመ ሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ በመምህ ርነት ሠርተዋል፤ በአመራርነትም አገልግለዋል። በሚጽፏቸው ጽሑፎችና በሚያደርጓቸው ንግግሮች እንዲሁም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በርካታ ውጣ ውረድ አጋጥሟቸዋል። በእስር ቤት ስቃይና እንግልት ቀምሰዋል። በአሁን ወቅት በመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል እየተረዱም ደግሞም ባላቸው ዕውቀት እና ልምድ በጉዳይ አስፈጻሚነት፣ በእንግዳ ተቀባይነት እያገለገሉ ይገኛሉ። የዛሬ የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› እንግዳችን አቶ ተከስተ ብርሃን መንክር፤ መልካም ንባብ!

ልጅነት – ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ

በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ነበር ብርቱ፤ የአልሸነፍም ባይነት ምሳሌ የሆኑት አቶ ተከስተ ብርሃን መንክር በ1938 ዓ.ም የተወለዱት።ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም አባታቸው ካህን ስለነበሩ ዳዊት እንዲደግሙ ከጥንታዊው የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ትምህርት ጣዕም እንዲቀምሱ የተወሰነ ጥረት ቢያደርጉም እርሳቸው ግን ወደ ዘመናዊው ትምህርት ተሳቡ።

ቤተሰቦቻቸው ዝቅተኛ በሚባለው የኑሮ ደረጃ ውስጥ ሆነው እንዳሳደጓቸውም ያወሳሉ።በተለይ እናታቸው ጠላ እየሸጡ የቤተሰቡን ኑሮ ለማቆም ይታትሩ ነበር። ትምህርታቸውን በጥንካሬ ለማስኬ ድም ቤተሰቦቻቸው ጫና እንዳይሰማቸው “ፒስኮር” የተሰኘ ከአሜሪካ የመጣው እና የተቸገሩ ዜጎችን የሚረዳውን ድርጅት ተቀላቀሉ።“የፒስኮር ጓድ” በመሆን እና ከእነርሱም ጋር በመተባበር አንዳንድ ሥራዎችን በመሥራት ራሳቸውን ለመደገፍ ጥረዋል። አምስተኛ ክፍል እስኪደርሱ ድረስ ለእግራቸው ጫማ እንኳን እንዳልነበራቸው የሚናገሩት አቶ ተከስተብርሃን ስድስተኛ ክፍል ሲገቡ “ከፒስኮሮች” በአራት ብር ሸራ ጫማ ገዝተው ማድረግ እንደጀመሩ ያስታውሳሉ። እጀጠባብ ይለብሱ፤ ቁምጣም ይታጠቁ ነበር።

 የተማሩት በጎንደር ፋሲለደስ ሲሆን በትምህር ታቸው እጅግ ጎበዝ ነበሩ፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል በነበራቸው ቆይታ የክፍል ደረጃቸው ከአንደኛነት ዝቅ አላሉም።በጊዜው የእንዲህ ዓይነት ጎበዝ ተማሪዎች መጠሪያ እንደአሁኑ ‹‹ሰቃይ›› ሳይሆን ‹‹ሸምዳጅ›› ነበርና ይሄን ስም ለማግኘት የካህኑ አባታቸው ቃላዊ የሆነው የትምህርት እና የማስተማር ዘይቤ ጠቅሟቸዋል።

በዚያ የትምህርት ጅማሬ ዘመናቸው የሚታተሙ መጻሕፍትን ያነባሉ።ዛሬ ድረስ ላላቸው የማንበብ ፍቅርም መሠረቱ በዚያን ጊዜ የተጣለ እንደሆነ ነው የሚያስቡት።ይህ ሁሉ ሆኖ የአንደኛ ደረጃ እና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያገባድዱ የጎንደር እህል ውሃቸውም ለጊዜው ተቋረጠ።ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው ማዕከል አዲስ አበባ ሆነች።

አዲስ አበባ በ1962 ዓ.ም ሲደርሱ የንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከፈተበት ጊዜ ነበር።ያኔ ታዲያ በዚያ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።በጊዜው የነበረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ጠንካራ ስለነበር ትምህርትን በጥንካሬ ለመወጣት መትጋት የግድ ነበር።በጊዜው በትምህርት ቤት ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ንቁ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ተከስተብርሃን የሻይ ክበብ፣ የውይይት ክበብ፣ የጋዜጠኝነት፣ የሥነ ጽሑፍ ክበብ ወዘተ እየተባሉ በሚቋቋሙ ተጓዳኝ ትምህርት እና ስልጠና ክበባት ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በተለይ የነበራቸው የተሻለ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ንግግር ችሎታ ተማሪዎች እና መምህራኑን ቀልብ ይስብ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በሀገራዊ ጉዳዮች

ቀጣዩ የትምህርታቸው ምዕራፍ ኮተቤ የሚገኘው መምህራን ኮሌጅ ሆነ። አቶ ተከስተ ብርሃን ኮሌጁን የተቀላቀሉት በኢትዮጵያ የዘውድ ሥርዓት ላይ ታላቅ ተቃውሞ እየተቀሰቀሰ በነበረበት፣ የለውጥ ጥሪዎች በመላው ሀገሪቱ እየተስተጋቡ በመጡበት በ1966 ዓ.ም ነው። በአቶ ተከስተ ብርሃን ታሪክ ውስጥ በሀገራዊ ጉዳዮች አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉበትን ዕድል ያገኙት ገና ወደ ኮሌጁ እንደተቀላቀሉ ነበር።በነበራቸው ንቁ ተሳታፊነት ምክንያት የተማሪዎች ፕሬዚዳንት በመሆን የኮሌጁ ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ለመዘወር ሰፊ ዕድል አገኙ።

በዚያን ጊዜ ኃላፊነትን መቀበል ቀላል አልነበረም፤ ሰፋ ያለ የፖለቲካ ግንዛቤና አመለካከት ያስፈልጋል። ከዚያ ባለፈ ደግሞ ጥላሁን ግዛው በ1962 ዓ.ም ከሞተ በኋላ በኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች መማክርት እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ ከመቆየቱም በላይ ፕሬዚዳንት መርጠው የሚንቀሳቀሱበት ዕድል አልነበረም። በ1966 ዓ.ም ግን በድጋሚ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ መደራጀት እና በአግባቡ መምራቱን ቀጠለ።

በዚያን ጊዜ የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር አቶ ሚሊዮን ነቅንቅ ይባላሉ።እርሳቸው የሚመሩት መሥሪያ ቤት በአጋጣሚ “ሴክተር ሪቪዉ” የሚባል ትምህርት ፖሊሲ በአሜሪካን ኤክስፐርቶች ተጠንቶ ተዘጋጅቶ ቀረበ።ፖሊሲው ትምህርትን እስከ አራተኛ ክፍል የሚገድብ ሆኖ የተዘጋጀ ነበር።ፖሊሲው የደሃ ልጆች በትምህርት እንዳይገፉ፣ የፊውዳል ልጆች ብቻ በትምህርቱ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ እና የሀገሪቱንም የኢኮኖሚ ልማት የሚጎዳ ነው በሚል ተቃውሞ ተነሳበት።ያንን እንቅስቃሴ በኮሌጅ ደረጃ የሚመሩት ደግሞ አቶ ተከስተ ብርሃን ነበሩ።

ሌላው ከፖሊሲ ጋር ተያይዞ በመንግሥት በኩል የነበረው ችግር በሀገሪቱ ከነበሩ አራት የመምህራን ኮሌጅ ተምረው የሚወጡ ተመራቂዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ የሚስተናገዱበት ፍትሐዊ ያልሆነ አሠራር መታየቱ ነው።በጊዜው የነበሩት አራቱ የመምህራን ማሰልጠኛዎች ሐረር፣ አሥመራ፣ ኮተቤ እና ደብረብርሃን ነበሩ።በእነዚህ ማሰልጠኛዎች ውስጥ መምህራን የሚሠለጥኑበት ሁኔታ ሁለት መልክ ነበረው።አንዱ ዐሥር ሲደመር ሁለት እና ዐሥራ ሁለት ሲደመር አንድ ነበር።ደብረ ብርሃን ዐሥር ሲደመር ሁለት በሚባለው መንገድ ከዐሥረኛ ክፍል ተቀብሎ ለሁለት ዓመታት የሚያሠለጥን ሲሆን፣ ሌሎቹ ግን በዐሥራ ሁለት ሲደመር አንድ የሚሠለጥኑ ነበሩ።

ያንን መነሻ በማድረግ በተዘጋጀው የደመወዝ አከፋፈል ሁኔታ ሲታይ ግን ከደብረ ብርሃን ለሚመረቁት 230 ብር ከሌሎቹ ተቋማት ለሚወጡት ግን 153 ብር ይከፈል የሚል ዕቅድ ተዘጋጀ።እናም ለዕኩል ሥራ የተለያየ ክፍያ መፈጸም ተገቢ አይደለም በሚል ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። የዚህ እንቅስቃሴ በኮተቤ ኮሌጅም እንዲስፋፋ ካደረጉት ሰዎች አንዱ አቶ ተከስተ ብርሃን መንክር ነበሩ።

አቶ ተከስተ ብርሃን በተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዴት ንቁ ሆነው ይንቀሳቀሱ እንደነበር ሲያስታውሱ «ይህ ጉዳይ በተማሪዎች መካከል የውይይት ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ እያለ አጋጣሚ ጃንሆይ ወደ ሰንደፋ ለጉብኝት እንደሚሄዱ ሰማሁ፤ የሚያልፉት በእኛ በኩል ስለሆነ፤ ተማሪዎችን አስተባብሬ መንገድ ዘግተን ባንዲራ አንጥፈን ጠበቅናቸው።እንቅስቃሴያቸውን የማገት ያህል ነበር፤ ወደ ኮሌጁ ገብተው ለማነጋገር ተገደዱ።

ጃንሆይ ብዙ ጊዜ ጉብኝት ሲያደርጉ አንድ፣ አንድ አዳዲስ ብር የማደል ልምድ ነበራቸው፤ እርሱን ለማግኘት የሚደክሙ የሚለፉ ብዙዎች ናቸው፤ ከተቀበሉ በኋላ ለዘመናት እንደ ቅርስ ይዘውት እንደሚቆዩ አውቃለሁ።እርሳቸውም ተማሪዎችን አሰልፈው ብር እየሰጡ ሳለ መካከል ላይ እኔ ዘንድ ሲደርሱ ‹አልቀበልም› አልኳቸው፤ ከንጉሡ ገንዘብ አልቀበልም ማለት በዚያን ጊዜ ከባድ ነገር ነው፤ ክብር ለመስጠት ግን እግራቸው ላይ ወድቄ ነበር፤

 ‹ምንድነው ችግርህ?› አሉኝ፤ ‹ግርማዊነትዎ አቤቱታ አለኝ› አልኳቸው። ያን ጊዜ ጀግናው አብዲሳ አጋ በጡረታ ጊዜው የእርሳቸው አጃቢ ሆኖ አብሯቸው ይንቀሳቀስ ነበር፤ እንደዚያ የተቃውሞ ስሜቴን ሲረዳ ከሌሎች አጃቢዎች ጋር ሆኖ ሳብ አድርጎ ወደ ጎን አቆመኝ፤ ንጉሡ ብር ሰጥተው እስኪጨርሱ መጠበቅ ነበረብኝ።

 መጨረሻ ላይ ‹ምንድነው ችግርህ?› አሉኝ፤ እኔም ‹ግርማዊ ሆይ እኔ የተማሪዎች ወኪል ነኝ፤ በእርስዎ ግዛት ውስጥ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መታየት ሲገባው እኛ ግን መብት መጓደል ደርሶብናል፤ በተለይ ከዚህ ዓመት ተማሪዎች ጀምሮ ደመወዝ ክፍያ ላይ እኩል እንዳንሆን የሚያደርግ መመሪያ ወጥቶብናል፤ ይህ እንዲስተካከልልን ለመጠየቅ እንፈልጋለን› አልኳቸው።በዚያን ጊዜ አቶ ተካልኝ ሰሎሞን የሚባሉ ምክትል ሚኒስትር ነበሩ።እርሳቸውን ተጠርተው ጠዋት ቤተ መንግሥት እንዲመጡ አድርጓቸው ብለው አዘዟቸው።» በማለት የሆነውን ያስታውሳሉ።

እንደተባለውም አቶ ተከስተብርሃንና ሌሎች የተማሪ ተወካዮችን ደብዳቤ ጽፈው ጠዋት በጋራ ወደ ቤተ መንግሥት ተጓዙ።ከአቶ ተከስተ ብርሃን ጋር የነበሩት የተማሪዎች ተወካዮች ሦስት ነበሩ።በቤተመንግሥት የሆነውን ሲያወሱ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤

«በዚያን ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ በአፍሪካ በነበራቸው ክብር እና የመሪነት ሥፍራ ምክንያት የሦስተኛው ዓለም /የአፍሪካ/መሪ ኮከብ ይባሉ ስለነበር እኛም በደብዳቤያችን መግቢያ ‹የአፍሪካ/የሦስተኛው ዓለም/ አንጸባራቂ መሪ ኮከብ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ……› የሚለውን ክብር ሰጥተን ነበር።ከዚያም በደብዳቤው የመምህራን የደመወዝ አቤቱታ በሥርዐት ተካቶ ነበር።አቤቱታችንን በንባብ አሰማን።»

የተማሪዎች አቤቱታ በቤተመንግሥት ከቀረበ በኋላ ንጉሡ አማካሪዎቻቸውን እነራስ መስፍን ስለሺ፣ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ብላታ አድማሱ ረታ እና ሌሎች የትምህርት ሚኒስቴርም ሰዎች በነበሩበት በጉዳዩ ተወያዩበት። ከዚያ ውይይት በኋላ ውሳኔ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶ በክብር መሸኘታቸውን ይገልጻሉ።

 «አሁን ሂዱ ተባልን፤ በሦስተኛው ቀን ውሳኔው መጣ። ደመወዛችን ከ153 ብር ወደ 182 ብር ተሻሽሎ እንዲከፈለን ነው ውሳኔው። ለአራቱም መምህራን ማሰልጠኛዎች በዚሁ መንገድ እንዲከፈል ተደረገ። በዚህ የለውጥ እና የማሻሻያ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ነበረኝ።» ይላሉ።

የሥራ ዓለም

አቶ ተከስተብርሃን በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው በኅብረተሰብ ትምህርት ተመርቀው ወደ ሥራው ዓለም ሲገቡ የተመደቡበት ክፍለ ሀገር አርሲ ነበር።ወዲያውኑ እንደተመረቁ የአርሲዋ አሰላ በክብር ተቀበለቻቸው። በትምህርት ዓለም እያሉ የነበራቸው ንቁ የዜግነት እና የኃላፊነት ስሜት ሳይለያቸው በደረሱበት በአሰላ ከተማ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አቋቁመው በዚያ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በመሆን ማገልገል ጀመሩ።

ያቋቋሙት ትምህርት ቤት «ቲቢላ» ይባል ነበር። እናም በዚህ የሥራ ኃላፊነታቸው ሳይወሰኑ አድማስ የሚሻገር ሀገራዊ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉበት አደረጃጀት ውስጥ መሳተፋቸውን ቀጠሉ፤ ያም አደረጃጀት የመምህራን ማኅበር ነበር።ስለዚህ ገና በትምህርት ተቋም እያሉ ያደርጉት የነበረውን ለሙያተኞቹ የመታገል ጅምር አጠናክረው ቀጠሉ።ማኅበሩ በየዓመቱ ስብሰባ ያዘጋጅ ስለነበር እርሳቸውም የመሳተፉን ዕድል ያገኙ ነበር።

 በ1967 ዓ.ም የመምህራን ማኅበሩ በጂማ ከተማ ጉባኤ አዘጋጅቶ ነበር።በዚህ ረገድ የሚያስታውሱት የ1966 ዓ.ም የእርሳቸውን ዘመነኛ ተመራቂዎችን በመወከል ማኅበሩ አዘጋጅቶት በነበረው ጉባኤ ተሳትፈው ነበር።ከዚያም ቀጣዩ ነቀምት ላይ ሲዘጋጅ በዚያም ተሳትፈዋል።በዚያ ጉባኤ ከተደረጉት ነገሮች የማይረሱት ‹‹ዘውድና ሕገ መንግሥት›› የሚል አንድ የመፍትሔ ሃሳብ ተዘጋጅቶ ነበር። ደርግ ጃንሆይ ከስልጣን ሲወርዱ በንባብ ያሰማው የድል መግለጫ ያኔ መምህራን ማኅበር ነቀምት ላይ ያረቀቀውን ነበር።

ታዲያ! ለአቶ ተከስተብርሃን ከሚቆጯቸው የሕይወት አጋጣሚዎች አንዱም ሆኖ ይጠቅሱታል።በዚያ የመፍትሔ ሐሳብ ረቂቅ ዝግጅት ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው ዛሬ ይቆጫቸዋል።ምክንያቱም ጊዜውን ያገናዘበና ችኩልነት የተሞላበት ዕርምጃ ስለነበር ነገሩን ዛሬ ላይ ሲያጤኑት የጸጸት ስሜት ያሳድርባቸዋል። የሥራ ዓለማቸው ደግሞ በአርሲ ሳይወሰን በጅማ፣ በሐረርጌ ክፍለሀገር ተዘዋውረው ሠርተ ዋል። በኋላ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ለመማር ዕድሉን ባገኙ ጊዜ ሶሲዮሎጂ ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1972 ዓ.ም ያዙ።ወዲያውም ተመልስው የተመደቡትም ወደ አርሲ ክፍለ ሀገር ነበር።

በዚያ በመምህርነት መሥራታቸው እንዳለ ሆኖ የመምህራን ማኅበር ረዳት ጸሐፊ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ከመምህርነቱም ባሻገር ፖለቲካዊ ሥራዎች የሚያመዝኑበት እንቅስቃሴ ለማድረግ ተገደዱ።በጊዜው የወጣውንም የመፍትሔ ሃሳብ ለማስተግበር በየቦታው መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነበር።በየትምህርት ቤቶችም መመላለስ ግድ ነበር። በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ እንቅስቃሴው በፈረስ በበቅሎ ስለነበር ይፈትናሉ።በተደጋጋሚም ከበቅሎ መውደቃቸውን ያስታውሳሉ።

በአርሲ የፈረቀሳ/ ወምባ/ን ተራራማ እና ኮረብታማ ስፍራዎች እንዴት እንደተመላለሱባቸው አይዘነጉም።የሚያስገርማቸው ደግሞ ይህ ሁሉ ተግባር ሲከናወን እንቅስቃሴቸው ያለምንም ከፍያ የሚፈጽሙት ነበር።በጊዜው ከ8-12 ብር አበል ይከፈል ነበር፤ ይሁን እንጂ ኑሮው ለክፉ የሚሰጥ ስላልነበር ለሁሉም እንቅስቃሴ ተከታትሎ፣ ተጠያይቆ አበል ለመውሰድ አይንደረደሩም። በጊዜው መምህር የሚከበርበት ዘመን ስለነበር ከአስተዳዳሪ እስከ ተማሪ ሁሉም በአቅሙ ጋባዥ እና ተንከባካቢ ነበር።በሂደት የአቶ ተከስተብርሃን ሀገራዊ ተሳትፎ ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ሆነ።ይህ ሁሉ የሆነው እስከ 1976 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር።

የዩኒቨርሲቲው መምህር

ከዚያ በኋላ ስለሆነው ደግሞ እንዲህ እያሉ ያወጉናል፤ «በ1976 ዓ.ም ላይ የውጭ የትምህርት ዕድል አግኝቼ ወደ ጀርመን ሄድኩ።» በዚያም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሶሲዮሎጂ ሠሩ።ቀጥለውም አሉ፤ «ተመልሼ በባህርዳር ፔዳጎጂካል ስኩል ሱፐርቫይዘር ሆኜ ሠራሁ።ከዚያ በኋላም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ለአራት ዓመታት አገለገልኩ።”

አቶ ተከስተ ብርሃን ይናገራሉ የ1970ዎቹ መጨረሻ የ1980ዎቹ መጀመሪያ በሀገሪቱ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውጥረት ነበር፤ በዚያን ወቅት ከጎንደር አካባቢ ወደ በረሃ ሄደው ደርግን ለመጣል ይታገሉ ለነበሩ ሰዎች ድጋፍ ይሰጡ ነበር።ጎንደር እያሉ የራሳቸውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር።በተለይ ዛሬ ከፍተኛ ሹማምንት ከሚባሉት እና ደርግን ለመጣል ከታገሉ ግለሰቦች ታዋቂዎቹን ወደ በረሃ በመላክ በኩልም ተሳትፎ ማድረጋቸውን ያወሳሉ።

 ፈታኝ ዘመን

በኋላ ነገሮች አልፈው በ1983 ዓ.ም ሥርዓቱ ሲለወጥ ጡረታ ወጡ። በጊዜው የተወሰነ ገንዘብ ስለነበራቸው በአንዳንድ ኢንቨስትመንት ሥራዎች ውስጥ ለመሳተፍ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ።ጡረታ ሲወጡም ያለፍላጎታቸው /በተጽእኖ/ እንደነበር ይጠቅሳሉ።ከለውጡ በኋላ ለሰባት ዓመታት በእስር ቤትም ቆይተዋል። ይህ ጊዜ ግን ለአቶ ተከስተ ብርሃን ቀላል አልነበረም።በእስራት እና በእንግልት ማሳለፋቸው ለጤና ችግርም አጋልጧቸዋል።በተለይ ደግሞ ወደ ኢንቨስትምንቱ ሲገቡ ለጊዜው ሊገልጹአቸው ባልፈለጓቸው አንዳንድ ምክንያቶች ሳይሳካለቸው መቅረቱ ለአዕምሮና ለስኳር ሕመም እንደዳረጋቸው ያስታውሳሉ።

 ከኢንቨስትምንቱ የተረፋቸውን ገንዘብም ያዋሉት የስኳር ሕምማቸውን ለመታከሚያነት ነው።አሳዛኙ ነገር ከህመማቸው ጽኑነት የተነሳ ሳይደክሙ ለአንድ ሰዓት በተከታታይ የሜዳ ቴኒስ ይሯሯጡበት የነበረ እግራቸውን ለመቆረጥ ተገደዱ።በዚያም ምክንያት አንድ እግራቸው ተቆረጠ።«ይህ በፈጣሪ ፈቃድ የሆነ ነው» ይላሉ። ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ማዘር ቴሬዛ የእንክብካቤ ማዕከል ገቡ።

ለአንድ ዓመት በእዚያ ቆዩ። ‹‹መሐል ላይ የመቄዶንያ መሥራች የክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ባለቤት ወ/ሮ እሌኒ ገብረኢየሱስ ታሪኬን ሰምታ ልትጎበኘኝ መጣች፤ አዋየችኝ። ከዚያ ከማዘር ቴሬዛ ብወጣ መጨረሻዬ ጎዳና ላይ መውጣት ነበር።እግሬን ከተቆረጥኩ በኋላ የምሔደው በዊልቼር ነው።ከዚያ በምክር ወደ መቄዶንያ መጣሁ።በጊዜው እጅግ በጣም ሰውነቴ ተጎድቶ ነበር።ስኳር ሲጀምረኝ አንደ መቶ ዐሥራ ሦስት ኪሎ ነበርኩ ፤ያን ጊዜ ግን ከጉዳቴ ብዛት የተነሣ አርባ አምስት ኪሎ ሆኜ ነበር።በዚህ በመቄዶንያ ከፍተኛ የህክምና ክትትል ተደረገልኝ። በተጨማሪ ለተቆረጠ እግሬ ሰው ሠራሽ እግር አስተከለልኝ እኔም እየዳንኩ መጣሁ።»

ዕድሜ ያልገደበው ተሳትፎ

አቶ ተከስተ ብርሃን ዛሬ ዕድሜ ሳይበግራቸው፤ ህመም ሳይፈትናቸው በትልቅ የሥራ ኃላፊነት ተሰማርተው በመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በጉዳይ አስፈጻሚነትና በእንግዳ ተቀባይነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

 «እኔ አሁንም ሀገሬን እያገለገልኩ ነው። ሀገርን ሲያገለግሉ ኖረው፤ ዛሬ በእርጅና በድካም፣ በሕመም፣ በማጣት ለመረዳት በዚህ ማዕከል የገቡትን ማገልገል ራሱ ሀገርን ማገልገል ነው።ብዙዎቹ ትናንት ቤተሰብ ነበራቸው፣ እኔ ነኝ ያሉ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱን በማገለገል እበረታለሁ።» ብለውናል።ያላቸውንም ቀሪ የሕይወት ዘመን ለዚህ በጎ ሥራ ሰጥተዋል።

አቶ ተከስተብርሃን በሕይወታቸው የተረዱት አንድ ታላቅ ነገር አለ፤ ይሄውም «የአካል መቆረጥ ወይም ገንዘብ እና ንብረት ማጣት የሕይወት ፍጻሜ አለመሆኑን።» በእርግጥም ከዚያ ወጥተውም ዛሬ ላይ የአረጋውያን ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።«ትናንት ሞቼ ነበር።ከዚያ ተነስቼ አሁን አለሁበት ደረጃ ከደረስኩ አረጋውያንን በማገዝ መቄዶንያን በማገልገል እኖራለሁ፤ ይህ ለእኔ አዲስ ሕይወት ነው፤ ከዚህ በላይም ደስታ ሊኖረኝ ወይም ላገኝ አልችልም።» ይላሉ።

ለምን? ያለ ቤተሰብ

«ለምን ቤተሰብ ሳይመሠርቱ ኖሩ?» የአቶ ተከስተብርሃን መልስ ተከታዩ ነበር፤ «በእርግጥ በዕጣ ፈንታም አምናለሁ።ይሁንና… ከሁለተኛ ዲግሪዬ በኋላም የፒኤች ዲ ትምህርት ለመከታተል እቅድ ነበረኝ፤ በጊዜው በነበረኝ ስሌት ቤተሰብ ያልመሰረትኩትም ከዛሬ ነገ እያልኩ ነበር፤ የፍቅር ጊዜ ሰጥቶ፣ በአግባቡ አግብቶ ወልዶ ለማሳደግ ጊዜ አልነበረኝም። ንባብ እና ፖለቲካ ተጫጭኖኝ ኖሯል።ለሰዎች በቂ ምክንያት ላይመስል ቢችልም ለእኔ ግን ጊዜ አልነበረኝም።

አንዳንዴ ደግሞ ለምን ብዬ ስጠይቅ ለራሴም የማይገባኝ ምስጢር አለ፤ ወልዶ መሳም የሚገባ እና የተሟላ ስብእና መገለጫ ሆኖ እያለ ወደ ዚያ ያልደረስኩበት ምስጢር ለምንድነው የሚለውን ልረዳው አልችልም፤ቁጭትም ይፈጥርብኛል።»

የንባብ ሕይወት

 ሌላው የአቶ ተከስተብርሃን ማራኪ የሕይወታ ቸው ገጽታ አንባቢነታቸው ነው። 870 መጻሕፍትን ማንበባቸውን ይናገራሉ። ዛሬም እንኳን በእጃቸው 840 መጻሕፍት አሏቸው። በማደሪያ ክፍላቸው በክብር ተቀምጠዋል።ማንበብ መማር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ተከስተብርሃን አሁንም ዘርፈ ብዙ ዕውቀትን ትምህርት ቤት ሳይሄዱ ከመጻሕፍት ገብይተዋል፤ እየገበዩም ነው።

መልዕክትና ምክር

 አቶ ተከስተብርሃን የቀጣዩ ትውልድ ዕጣ ፈንታ ያሳስባቸዋል።ስለዚህ ለትውልዱ የሚሰጡት ምክር አለ፤ «ከሀገር የበለጠ ምንም ነገር የለም፤ ሁሉም ሰው ሀገሩን ቢያስቀድም ደስ ይለኛል። አንድ ሀገር ያላት ዋናው ሀብት ህዝብ ነው፤ የህዝብ ጥቅም እንዲጠበቅ ደግሞ ዋናው ሰላም ነው፤ እስከዛሬም ያለንን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ያልቻልነው ሰላም ስላልነበረን ነው፤ ኢትዮጵያ አንድነቷ ከተጠበቀ ሰላም ካላት የማታድግበት ምንም ምክንያት የለም።

 ስለዚህ ቀጣዩ ትውልድ ለሀገሩ ቅድሚያ ይስጥ። ቀደም ሲል ‘ቻይናዎች ጠፍር ይበሉ ነበር’፤ ዛሬ ላይ ግን ከፍተኛ ደረጃ ደርሰዋል፤ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ለአሜሪካ 65 ሺህ ዶላር ዕርዳታ የሰጠችበት ጊዜ ነበር፤ኢትዮጵያ አሜሪካንን ረድታለች፤ ዛሬ ግን የት ነው ያለነው? ያንን ማስቀጠል አልተቻለም። ይህንን ትውልዱ ሊያስብብት ይገባል። ነገ ኢትዮጵያ አሜሪካንን የምትረዳበት ዘመን እንደሚመጣ ተስፋ አድርጋለሁ፤ ይሄንን እውን የሚያደርገው ይህ ትውልድ ነው።ይህ የሚሆነው ለሀገር በማሰብ እና ፍቅር እና ሰላምን ማጽናት ከተቻለ ነው።›› ብለዋል። እኛም ዕድሜ ከጤና ጋር ያብዛልዎት አልን።

 ሰላም!

አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011

አብርሃም ተወልደ