የማሕበራዊ ድረ ገፅ የጥፋት መልዕክተኞችን በጋራ መታገል ያስፈልጋል!

38

እንደ ‹‹ኢንተርኔት ወርልድ ስታተስ› መረጃ በአሁኑ ወቅት በአለም ሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን በላይ ህዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ነው፡፡ ከእነዚህ ማህበራዊ ሚድያ መካከል ከ170 ሚሊዮን በላይ የውሸት የፌስቡክ አካውንቶች አሉ፡፡ ከ20 ሚሊዮን በላይ ቲውተርም የውሸት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለጥፋት ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በግብፅ የተቀጣጠለው አብዮት፣ በሊቢያ የተነሳው አመፅ፣ በሶሪያ የተፈጠረው ቀውስ መነሻው በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚቀነባበር የአመፅ ጥሪ ነበር፡ ፡

ስንቶቹ ችግሩን ተቋቁመው በድል አልፈውት እንደሆነ ግን ጉዳቱን ያስተናገዱት አገራት ይመዝኑት፡፡ በአገራችን በአሁኑ ወቅት ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ፌስቡክን ይጠቀማሉ፡፡ ምንም እንኳ በጥናት የተደገፈ መረጃ ባይኖርም በርካታ የውሸት አካውንቶች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ማለት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሁሉም ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ እየተጠቀሙበት ለመሆኑ አጠያያቂ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመላ አገሪቱ ማለት ይቻላል ሰላም በሌለበትና አገር በተረበሸበት ሁኔታ ደግ ደጉን ማከናወን ቀርቶ በወጉ ውለን ማደራችን እንኳ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ወድቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ለዚህ ደግሞ የጥፋት መልዕክተኛ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋንያን ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆንም እነዚህን መታገል የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ መረጃን አጣርቶ ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢ ይሆናል፡፡

 እነዚያ በጭንቅ ያሳለፍናቸው ወቅቶች በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መረጃዎች ሁሉም ለአገር የሚበጁ እንዳልነበሩ ከደረሱት ጥፋቶች መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ፡ አማራ፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችና ክልሎች በተፈጠረው ቀውስ በህይወት፣ በመንግስትና በሕብረተሰቡ ንብረት ላይ የደረሱት ጉዳቶች የአገርን ተስፋ የሚያደበዝዙና የሕዝብን ከድህነት የመውጣት ጽኑ ፍላጎት የሚያጨልሙ ሆነው ተስተውለዋል፡፡ ይህ መቼም መደገም የለበትም፡፡

ከጥፋት አትራፊ የለምና፡፡ በአንድ በኩል በአገሪቱ የሚገኙ የተንኮል ሴራ አራማጆች፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ጎራ በመለየት ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እንዳይተማመኑ በማድረግ የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ በጠላቶቿ እጅ ላይ ለማሳረፍ ሲውተረተሩ ታይቷል። በተለይ የፌስቡኩ አፍራሽ የቃላት ዘመቻ በአገር ግንባታ፣ ልማትና ድህነትን በማጥፋት ሥራ የተጠመደን አካል በማቃቃር፣ ብሄርን ከብሄር በማጋጨት፣ የነገ ተስፋን የሰነቁ ወጣቶች በትምህርት ገበታቸው ላይ ተረጋግተው እንዳይማሩ በመቀስቅሰ ጥፋትን እያዘጋጁ ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ቀጥለዋል፡፡ ስለሆነም ለሃገራችንና ለህዝባችን ሰላም ሲባል ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ የሚያስችል ስራ መስራት አለብን፡፡

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱትና አሁንም ብቅ ጥልቅ የሚሉት የጥፋት ተልዕኮዎች የዚሁ እኩይ ተግባር መንስኤ በመሆናቸው በአፍራሽ ስብከት የተጠመደው የሕብረተሰብ ክፍል በመልካም የዕድገትና የልማት ጎዳና ላይ እየተራመደች የምትገኘውን አዳጊ አገር ነባራዊ ሁኔታ በመዘንጋት ትርምስ ውስጥ እንድትወድቅ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ተግባር ላይ ለመሰማራት በመቀስቀሳቸው የአፍራሽ ተልዕኮው ሰለባ የሆነ፣ በወገኖቹ ላይ ክንዱን ያነሳ፣ የጥፋት ተላላኪ የሆነ ሃይል እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ለዚህ ደግሞ በተለይ ስነምግባር ላይ የሚሰሩ የእምነት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች የየድርሻቸውን ባለመወጣታቸው ነው፡፡

 በእውነተኛ ሕዝባዊ ትግል በተከፈለው መስዋዕትነትና በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ በማለፍ የመጣው ለውጥ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከንቱ እንዲቀርና አገሪቱ አደጋ ላይ እንድትወድቅ የሚጋብዝ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በልዩ ልዩ መንገዶች ለማደናቀፍ በማህበራዊ ሚዲያ ጥረት የሚያደርጉ አካላት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊታገላቸው ይገባል፡ ፡ ያገኘውን መረጃ ከማግበስበስ ይልቅ አጣርቶ አቋም በመያዝ የውሸትና የጥፋት ጥሪያቸውን ማምከን አለበት፡፡

 በተቃራኒው ግን በየትኛውም ጊዜ አገሪቱን ለማጥፋትና ሕብረተሰቡን ለማበጣበጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጁ የጥፋት መልዕክተኞች ጥረት ቢያደርጉም፤ አብዛኛው ሰላም ወዳዱ ሕብረተሰብ የከፋፋዮችን ሃሳብ ሲቀበልና በተግባር ሲያውል አልታየም፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ በጥቂቱም ቢሆን በመረጃ ክፍተት ለተንኮለኞች ስውር ደባ ቢጋለጥም፤ በአገሪቱ ያለውን እውነታ በመረዳት ስህተትን በማረም ወደሚጠቅመው የሰላምና የልማት አቅጣጫ በማዘንበል የሴረኞችን ዓላማ ማክሸፍ ችሏል፡፡ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

እነዚሁ የማሕበራዊ ድረ ገፅ የጥፋት መልዕክተኞች የለውጥ ሃይሉ በሕብረተሰቡ እንዳይታመን፣ የተጣላና የተከፋፈለ በማስመሰል፣ አንዱን ብሔር በአንዱ ላይ በማነሳሳት ከክፋት ጠንሳሾቻቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማሳካት ቢውተረተሩም ከምንም ነገር ሁሉ ሰላምን የሚያስቀድመው ሕዝብ እያወገዛቸው ሰላሙን ለማስጠበቅና አንድነቱን ለማጠናከር በሚያደርገው ጥረት ከንቱ ምኞታቸው እያከሸፈ ይገኛል፡፡

በየትኛውም ወቅት የአገራት መንግሥታት የህግ የበላይነትን ለድርድር አቅርበው እንደማያውቁት ሁሉ፤ አገር የሚመራው መንግሥት ዜጎች መብትና ሰላም ለመጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል የአገሪቱን ሕዝቦች ለመረበሽ ተግተው በሚሰሩት ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል፡፡ የህግ የበላይነት ሲጣስ በአገር ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ተፅዕኖን ያስከትላል። ይህ በመሆኑም መላው ህብረተሰብና እነርሱን የሚያስተዳድረው መንግስት የህግ የበላይነትን የማክበርና የማስከበር ታላቅ አደራ እንዳለባቸው ተገንዝበው የማሕበራዊ ድረ ገፅ የጥፋት መልክተኞችን በጋራ ሊገታሏቸው ይገባል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011