በአዲስ ህይወት መፅሐፍ ላይ ውይይት ይደረጋል

37

በዳግማዊ አሰፋ ተፅፎ ለአንባቢያን የበቃው ‹‹አዲስ ህይወት›› መፅሐፍ ላይ ዛሬ ውይይት ይደረግበታል፡፡ በወር አንድ ጊዜ በጎተ (ጀርመን) ባህል ማእከል አዘጋጅነት የሚካሄደው የመፅሐፍ ውይይት ባለ ተራ በመሆንም በርካታ ደራሲያን የስነ ፅሁፍ አፍቃሪዎች እንዲሁም የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ሀሳቦች እንደሚንሸራሸሩ ታውቋል፡፡

ዛሬ በ8፡00 ሰዓት በቤተ መፃህፍት እና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይቱ የሚደረግ ይሆናል፡፡ በእለቱም በደራሲ አንዷለም አባተ (የአፀደ ልጅ) በመፅሐፉ ዙሪያ ለውይይት መነሻ ሀሳብ የሚቀርብ ይሆናል፡፡

ይህን የመፅሐፍ ውይይት (ጎተ) የጀርመን የባህል ማእከል፣ እናት ማስታወቂያ እንዲሁም ብሄራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ሁሉም የስነ ፅሑፍ አፍቃሪያን የተጋበዙ ሲሆን፤ ወደ አዳራሹ ለመግባት ምንም አይነት ክፍያ እንደማይጠይቁ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ለውጥማ አለ›› ግጥምን በጃዝ የፊታችን ሰኞ ይደረጋል

በጉዞ ሚዲያ እና ማስታወቂያ አዘጋጅነት የተሰናዳው ‹‹ለውጥማ አለ›› የግጥም በጃዝ የኪነ ጥበብ ምሽት የፊታችን ሰኞ በ11:30 በብሄራዊ ቲያትር አዳራሽ እንደሚካሄድ ከአዘጋጆቹ ሰምተናል፡፡ በመሰናዶው ወግና ዲስኩር እንዲሁም ግጥም እና መነባነብ እንደሚቀርብ ለማወቅ ችለናል፡፡

በኪነ ጥበብ ምሽቱ ላይ በርካታ ታዋቂ ወጣት እና አንጋፋ የስነ ፅሁፍ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተጋባዥነት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ ውብሸት ሙላት፣ አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ወግ እና ዲስኩር ሲያቀርቡ በግጥም ዘርፍ ደግሞ ገጣሚ ነብይ መኮንን፣ ገጣሚ ምእልቲ ኪሮስ፣ ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ሥራዎቻቸውን በተመሳሳይ የሚያቀርቡ ይሆናል፡፡ ይርጋ ታደሰም የመነባንብ ሥራውን በመድረክ ይዞ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ የክብር ተጋባዥ በመሆንም ደራሲ ይስማእከ ወርቁ በስፍራው እንደሚታደም አዘጋጆቹ እወቁልን ብለዋል፡፡

ይህ የኪነ ጥበብ ምሽት የመግቢያ ትኬት ያለው ሲሆን በጃፋር የመፅሃፍት መደብር፣በዮናስ የመፅሃፍት መደብር እንዲሁም በአይናለም የመፅሃፍት መደብር እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ አዘጋጆቹ ቀድመው ለመጡ ከሁለት መቶ ለሚበልጡ ታዳሚዎች ሚስጥራዊ ሽልማት አለን ብለዋል፡፡

‹‹ከየት ወዴት?›› አዲስ መፅሐፍ በገበያ ላይ ዋለ

በፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የተፃፈው እና ከየት ወዴት? የሚል አርስት የተሰጠው መጽሐፍ በገበያ ላይ ዋለ፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም ‹‹ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ›› የተሰኘ መጽሐፍ አሳትመው እንደነበር አይዘነጋም።

ይህ አንባቢያን እጅ እንዲደርስ ወደ ገበያ የተበተነው መጽሐፍ የሰው ዘር ዝግመተ ለውጥ እና ማህበራዊ እድገት ያለማቋረጥ መቀጠሉን የሚዳስስ እና በውስጡ በርካታ ጉዳዮችን የያዘ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡

ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ‹‹ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ›› የተባለው መፅሃፋቸው የአንድ ኢትዮጵያዊ የባዮሎጂ ሊቅ ግለታሪክ ቢሆንም፤ እግረ መንገዱን ከጣልያን ወረራ እስከዛሬ ድረስ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ በሩ የስነ ፅሁፍ ቋንቋ ይተርካል ፡፡ ከባለ ታሪኩ ሕይወት ጋር የሩቅና የቅርብ ግኑኝነት ያላቸው ዝነኛ ኢትዮጵያውያን ታሪክና ገጠመኝ ተወስቷል፡፡ ስለ ሶማ ፋኖዎች በላይ ዘለቀ ፤ እጅጉ ዘለቀና ሽፈራው ገርባ የቀረበው ታሪክ እስካሁን ያልተነገረ ነው፡፡ አዲስ የወጣው መፅሃፍፍም እንደዚህኛው በበርካታ አድናቆትን እንደሚያገኝ ተጠብቋል፡፡

«ባትፈልገኝ እፈልግሃለው» መጽሐፍ ተመረቀ

«ባትፈልገኝ እፈልግሃለው» የተሰኘው የደራሲ ሊቦኖስ ገዳሙ መጽሐፍ ትናንት የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ አዳራሽ ተመረቀ፡፡

መጽሐፉ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ነው፡፡ በፕሬዚዳንት መሐመድ ዚያድ ባሬ የምትመራው ሶማሊያ «ታላቋን ሶማሊያን» የመገንባት ህልሟን እውን ለማድረግ በ1669 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ጦሯን አዝምታ በምስራቅ እና በደቡብ ክፍል የተወሰኑ ቦታዎችን ይዛ እንደነበር እና በአጭር ጊዜ የተሰበሰበው የኢትዮጵያ ሠራዊት የሶማሊያን ወረራ እንደቀለበሰው የሚያወሳ ነው፡፡መጽሐፉ ብዙም ያልተነገረለትን የዋርደር ጦርነት ያስነብባል፡፡

ብዙ ያልተነገለትን የዋርደር ጦርነት የመሩትን ኮሎኔል ዘመድኩን ኃይሌ እና በዚያ ጦርነት ተካፋይ የነበሩ የ3ተኛ ፓራ ኮማንዶ ብርጌድ አባላትም በምርቃት ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡

«ዝክረ የኢትዮጵያ ጀግኖች» ጥበባዊ ምሽት ከነገ በስቲያ ይካሄዳል

በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር አዘጋጅነት በየወሩ የሚካሄደው ብሌን ጥበባዊ ምሽት በዚህ ወር «ዝክረ የኢትዮጵያ ጀግኖች» ጥበባዊ ምሽት ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን 2011ዓ.ም ማምሻውን ከ11፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ይካሄዳል።

በወሩ ዝግጅት የባህል ጨዋታ ፉከራና ሽለላ ይቀርባል። እንዲሁም ጀነራል ተስፋዬ ኃ/ማርያምን ጨምሮ ረ/ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ፣ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፤ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተስፋዬ ማሞ፣ አንዷለም አባተ፣ እንዳለጌታ ከበደ፤ ገጣምያን ዋስይሁን በላይ፣ ረድኤት ተረፈ እና ትዕግስት ሲሳይ ይገኛሉ ተብሏል። በዝግጅቱ ላይ መታደም ለሚፈልጉ ሁሉ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ጥሪውን አቅርቧል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011