የበጀት ቀበኞችን ማን ይቆንጥጣቸው?

43

ድሆች ነን። ዓመታዊ በጀታችን ከዕርዳታና ብድር ድጎማ ገና አልተላቀቀም። የወጪ እና የገቢ ንግዳችን መራራቅ (የንግድ ሚዛን ጉድለት) የሰማይና የምድር ያህል ወደ መሆን ደረጃ እየተንደረደረ ነው። የብሔራዊ ባንክ ገዥው አቶ ይናገር ደሴ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት በ2011 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ብቻ አገሪቱ ያላትን ሸጣ ያገኘችው ገቢ 1 ነጥብ 64 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የተለያዩ ሸቀጦችን ለመሸመት ያወጣችው ደግሞ 10 ቢሊዮን ዶላር ነው።

 በዚህ መረጃ መሠረት የገቢ ንግድ የወጪውን መሸፈን የቻለው 16 በመቶ ገደማ ብቻ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ባለፉት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ9 ነጥብ 4 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል መባሉ ጥሩ ዜና አልነበረም። እናም መደበኛ ዓመታዊ በጀታችን ከብድርና ዕርዳታ ድጋፍ አልተላቀቀም። ይህም ሆኖ እንኳን የበጀት ጉድለት አለብን። ባለፈው ዓመት መጨረሻ የጸደቀው የፌዴራል መንግሥት የ2011 በጀት ብር 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ሲሆን (በቅርቡ የተደረገውን ማሻሻያ አይጨምርም) ይህ በጀት ከአገር ውስጥና ከውጪ አገር ባንኮች በሚገኝ ገንዘብ የሚሸፈን 59 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ነበረበት።

ከውጭ አገር ዕርዳታና ብድር በድምሩ ብር 287 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ስናይ የራስ አቅማችን የቱን ያህል አናሳ መሆኑን እንረዳለን። በዚህ ሁኔታ የሚገኝ ገንዘብ በበጀት መልክ ለመደበኛ እና ለካፒታል ወጪዎች ሲውል በቁጠባና በትክክል ሥራ ላይ ማዋል ግድ የሚለው ይህን ዝርዝር ሁኔታ ስናጤን ነው። በተግባር ግን የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ ያፈራሉ ተብለው የሚጠበቁ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የመንግሥትን የፋይናንስ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ የተመደበላቸውን በጀት እንዳሻቸው የሚመነዝሩ መሆናቸው አስገራሚነቱ እየቀረ መጥቷል። ለዚህ ችግር መንሰራፋት ትልቁ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ቆንጣጭ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ አካል መጥፋት ስለመሆኑ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው።

ልብ ሰባሪው የአምና ሪፖርት

 የፌዴራል ዋና ኦዲተር፤ ኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች የኦዲት ግኝትን ለማረም ፈቃደኛ ያልሆኑ ተቋማት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግም ዝምታ እንዳሳሰበው አፍ አውጥቶ የተናገረው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ነበር። የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የ2009 በጀት ዓመት ሂሳብና ክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም ባቀረበበት ወቅት የጎላ ችግር ያለባቸው ሆነው በመገኘታቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጠባቸው መስሪያ ቤቶች ቁጥር በየዓመቱ ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መምጣታቸውን አመልክቷል። ተቀባይነት የሚያሳጣቸው አስተያየት የተሰጠባቸው መስሪያ ቤቶች ቁጥር በ2007 ዓ.ም 37 የነበረ ሲሆን ይህ አሃዝ መቀነስ ሲገባው በ2008 እና በ2009 ቁጥሩ ወደ 53 አድጎ እንደተገኘ ነው የተገለፀው።

እንደዚሁም ነቀፌታ የሌለባቸው ተቋማትም በ2007 ዓ.ም 36 የነበሩ ሲሆን ይህ አሃዝ መጨመር ሲገባው በ2008 ቁጥሩ ወደ 27 ዝቅ ሲል በ2009 ቁጥሩ ወደ 25 ወርዷል። ሪፖርቱ ለዚህ ምክንያቱን ሲያስቀምጥ «አንዳንዶቹ በኦዲት ግኝቱ ተምረንበታል፤ ኦዲቱ ጠቅሞናል እያሉ ወደሚታይ ተጨባጭ እርምጃ ሳይሻገሩ የተሳሳተና ያልተስተካከለ ግኝት ተስተካክሏል በማለት ጭምር ለመድረክ ፍጆታ ብቻ እያዋሉት ይገኛሉ» በማለት ነው። በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ ጥሩ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ የኦዲት ግኝቱ በህጉ መሰረት መፈፀም ሲኖርበት ለመፈፀም ፈቃደኛ ሆኖ ያልተገኘ በህግ ስለሚቀጣ ህጉ ተግባራዊ እንዲሆን ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የእምቢተኞች ዝርዝር ቢላክም መስሪያ ቤቱለኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች ተገቢውን እርምጃ ወስደው እንዲያሳውቁ ደብዳቤ ከመፃፍ ውጭ በተጨባጭ የተገኘ ውጤት የለም ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ «ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ከ2002 እስከ 2008 /ድረስ/ ያለው የኦዲት ግኝት ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተላለፈ ቢሆንም እስከ አሁን ተወስዶ የተገለፀልን እርምጃ የለም» ሲሉ ነው ዋናው ኦዲተር ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።ሪፖርቱን የተከታተሉት የምክር ቤቱ አባላት የኦዲት ግኝቱን ለማስተካከል ፈቃደኛ ያልሆኑ መስሪያ ቤቶች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየተባባሰ መሄዱ እንዳሳሰባቸው ምሬት በተቀላቀለ ሁኔታ አስተያየታቸውን ካቀረቡ በኋላ ለድክመቱ ምክር ቤቱ ራሱን ተጠያቂ አድርጓል።

በ2009 በጀት ዓመት ባለ በጀት የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ከ5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ አላወራረዱም። በጀታቸውን አላወራረዱም የተባሉት 116 የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና 15 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ነበሩ። በተጨማሪም 53 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ደግሞ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት እንደታየባቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ገልጿል። በበጀት ዓመቱም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አልተሰበሰበም።

የኦዲት ሪፖርት እንደ አንድ አብነት

 የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ2006 በጀት ዓመት ኦዲት ካደረጋቸው 135 መንግሥታዊ መስሪያ ቤቶች መካከል የዕቃና አገልግሎት ግዢ በመንግሥት ደንብና መመሪያ መሠረት የተፈፀመ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፤ በ63 መስሪያ ቤቶችና ሦስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ብር 957 ሚሊየን 510 ሺህ 040 ብር ከ14 ሳንቲም የመንግሥት የግዢ አዋጅ፤ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዢ ተፈፅሞ መገኘቱን ይፋ አደረገ። ካልተከተሏቸው የግዢ ደንብና መመሪያዎች ውስጥ የጨረታ ማስታወቂያ በማውጣት ሊፈፀሙ የሚገባቸውን ግዢዎች ያለጨረታ ማስታወቂያ በመግዛት፤ የዋጋ ማወዳደሪያ /ፕሮፎርማ/ አማካኝነት መፈፀም ያለበትን የግዢ ውድድር ሳይደረግ መፈፀሙ እና የተለያዩ ግዢዎችን ከአንድ አቅራቢ ብቻ መፈፀም የሚሉት ይገኙበታል።

 የግዢ መመሪያንና የተጨማሪ እሴት ታክስ ደንቦችን ሳይከተሉ ግዢ መፈፀም ለምዝበራና ለጥራት መጓደል እንዲሁም ለግብር አለመሰብሰብና ስወራ ጭምር የሚያጋልጥ በመሆኑ የመንግሥት ግዢ ደንብና መመሪያን አክብረው በማይሠሩ መስሪያ ቤቶች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ዋና ኢዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። ዋና ኦዲተር በ2005 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርቱ የመንግሥትን የግዢ አዋጅ፣ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ 43 መስሪያ ቤቶች የ165 ሚሊየን 892 ሺህ 637 ብር ከ56 ሳንቲም ግዢ መፈጸማቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ አሃዝ በአንድ ዓመት ልዩነት ሕገወጥ ግዢ የሚፈጽሙ መስሪያ ቤቶች ከ43 ወደ 63 ያደጉ ሲሆን ለህገወጥ ግዢ የወጣውም ገንዘብ ከካቻምና ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ791 ሚሊየን 617 ሺህ 402 ብር ከ58 ሳንቲም በ2006 በጀት ዓመት ዕድገት አሳይቷል።

በዋና ኦዲተር ሪፖርት መሠረት በ2006 በጀት ዓመት የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ አያያዝና አጠባበቅ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በ4 መስሪያ ቤቶች ብር 79 ሺህ 241 ብር ከ55 ሳንቲም የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መገኘቱን የተጠቀሰ ሲሆን ከዋና ኦዲተሩ የ2005 በጀት ዓመት ሪፖርት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል ታይቶበታል፡ በ2005 በጀት ዓመት በ5 መስሪያ ቤቶች የታየው የጥሬ ገንዘብ ጉድለት 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ያህል እንደነበር ታውቋል። የጥሬ ገንዘብና የባንክ ሂሳቦች ላይ ተገቢ ቁጥጥር አለማድረግ ለገንዘብ ብክነት፣ ጉድለትና ምዝበራ የሚያጋልጥ በመሆኑ፤ በጉድለት የታየው የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ ተገቢው እርምጃ ተወስዶ እንዲተካ፤የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ በየወቅቱ ተቆጥሮ ከመዝገብ ጋር እንዲመሳከር፤ በሂሳብ መግለጫ ሪፖርት ላይ የተመለከተው የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ በቆጠራ ከተገኘው ጋር ሊመዛዘንና ትክክለኛነቱ ሊረጋገጥ እንደሚገባ፣ በማነስ የታየው ልዩነትም ተጣርቶ እንዲተካ ወይም ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግ እና የታዩት የተለያዩ የጥሬ ገንዘብና ባንክ ሂሳብ አያያዝ ድክመቶች እንዲስተካከሉ ዋና ኦዲተር ማሳሰቡን አቶ ገመቹ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 190/2002 አንቀፅ 32 እስከ 35 በተደነገገው መሠረት በ2006 በጀት ዓመት ተሰብሳቢ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ78 መስሪያ ቤቶች ብር 2 ቢሊየን 25 ሚሊየን 166 ሺህ 722 ብር ከ68 ሳንቲም በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ መገኘቱን ዋና ኦዲተሩ አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በ2005 በጀት ዓመት በ77 መንግሥታዊ መስሪያ ቤቶች ብር 877 ሚሊየን 45 ሺህ 264 በር ከ30 ሳንቲም በደንቡ መሰረት ሳይወራረድ መገኘቱ ይፋ የተደረገ ሲሆን ይህ አሃዝ ከ2006 ጋር ሲነጻጸር የማይወራረድ ገንዘብ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እያደገና አሳሳቢ ደረጃ እየደረሰ መምጣቱን ያሳያል።

ዘንድሮስ?

በብዙዎች ዘንድ ጥርስ የሌለው አንበሳ ከሚባሉ ተቋሞች አንዱ እንደሆነ የሚገመተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሁን ሰዓት ጥርስ ስለማውጣቱ ምልክቶች እያየን ነው። በተለይ አዲሱ አመራር ወደፊት ከመጣ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በክትትልና በቁጥጥር ረገድ የተሻለ ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ በቂ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለዚህ አባባል አንድ አብነት የሚሆነው የኦዲት ግኝቶችን ያላስተካከሉ ኃላፊዎች ለህግ እንደሚቀርቡ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ሰሞኑን የማሳሰባቸው ጉዳይ ነው። የፌዴራል ኦዲተር እንደገለጸው ባለፉት ስምንት ዓመታት ብቻ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በባለበጀት መስሪያ ቤቶች ባክኗል። ከ2002 እስከ 2008 በጀት ድረስ የተሰጡ የኦዲት አስተያየቶችን ያላስተካከሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ከአዲሱ በጀት ዓመት በፊት የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ የሚያሳስብ የምክክር መድረክ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ.ም መካሄዱ በራሱ ችግሩን ለመቅረፍ እርምጃ መጀመሩን አመላካች አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

የምክክር መድረኩን የመሩት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የውይይቱ ዓላማ የኦዲት ግኝቶቹን ያላስተካከሉ የመንግሥት ኃላፊዎችን ለህግ በቀጥታ ከማቅረብ በፊት ወደ እርምት እርምጃ እንዲገቡ ለማሳሰብ መሆኑን ጠቁመዋል። ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለመንግሥት እንዲመለስ የኦዲት አስተያየት የቀረበበት የገንዘብ መጠን ብር 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን መሆኑን አስታውሰው እስከ አሁን ድረስ የተመለሰው ገንዘብ 50 ሚሊዮን ብር አካባቢ ብቻ መሆኑ የቁርጠኝነት ማነስ መኖሩን እንደሚያመላክት ጠቅሰዋል።

እንዲመለስ የተጠየቀው ገንዘብ ህግና መመሪያ ባለማክበር የወጡ፣ መክፈል ከሚገባ በላይ የተከፈሉ፣ የውል ህግ ሲጣስ ቅጣቶችን ካለማስከፈል የቀሩ፣ ታክስ ሳይቆረጥ የተፈፀሙ ክፍያዎች፣ ቅድመ ክፍያ ሳይመለስ የቀረ፣ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት የመሳሰሉ እንደሆኑ በዝርዝር አስቀምጠዋል። ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ በተደጋጋሚ የቀረበበትን ወቀሳ በማስተካከል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ 15 የፌዴራል መንግሥት ተቋማትን በብር 408 ሚሊዮን እና 20 ዩኒቨርሲቲዎችን በብር 692 ሚሊዮን ለይቶ ለምርመራ ስራ የሚያግዝ ጭብጥ መለየቱን፣ የምርመራ መዝግብ ማደራጀቱንና ለተቋማት የሚላኩ ደብዳቤዎች መዘጋጀታቸውን አብራርቷል።

የመድረኩ ተሳታፊ ባለበጀት መስሪያ ቤት ኃላፊዎች የተሰጠው ጊዜ በቂ ያለመሆኑንና በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ያሉባቸው ተጨባጭ ችግሮች እንዲታይላቸው አስተያየቶችን አቅርበዋል። የተከበሩ አፈ ጉባኤውና ዋና ኦዲቱ የድርጊት መርሐ ግብር ቀርቦ በተጨባጭ ስራ ውስጥ ተገብቶ የሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ከሚፈለግላቸው ውጭ የኦዲት ግኝቶቹ ተፈፃሚ ሳይሆኑ ከቆዩበት ጊዜ በላይ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ እንደማያስፈልግ ነው ያሳሰቡት። የፌዴራል የፀረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽንም የኦዲት ግኝቱን ለመተግበር መስሪያ ቤቶች የሚያቅማሙት ምክር ቤቱ እርምጃ የማይወስድ መሆኑን በመገመት ነው ካለ በኋላ፤ የኦዲት ግኝቱ ላይ ድርድር እንደማያስፈልግ የራሱን አቋም አራምዷል። ተሰብሳቢዎችም የድርጊት መርሐ ግብር በማዘጋጀት ከመጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግበራ እንደሚገቡ ስምምነት ተደርሷል። በዋና ኦዲተር ማቋቋሚያ አዋጅ የኦዲት ግኝቶችን የማያስተካክል ኃላፊ ከ10 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ይደነግጋል።

እንደመውጫ

የመንግሥት ዓመታዊ በጀት በዕርዳታና ብድር የሚደጎም ነው። ከሕዝብ የሚሰበሰበው ታክስ ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ሹመኞች ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር የኃላፊዎች የቆይታ ጊዜ የሚወሰነው በሥራ አፈፃፀሙ ውጤት መሰረት ነው ያሉት እዚህ ላይ ማስታወሱ አግባብነት ይኖረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ገለፃቸው እያንዳንዱን የሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ጋር የሥራ ውል ስምምነት እንደሚያደርጉና በዚህም ሚኒስትሮቹ ተቆጥሮ የተሰጣቸውን ሥራ ቆጥረው በማስረከብ አፈፃፀማቸው እየተለካ ባላቸው ውጤት መሠረት ኃላፊነት ላይ እንደሚቆዩ ገልፀዋል። ይህም ተጀምሯል።

በተጨማሪም በተለይ የአሠራር ሥርዓትንና አቅም ማነስን እንደሽፋን በመጠቀም የመንግሥት በጀት የሚመዘብሩ የሥራ መሪዎችን ለፍርድ በማቅረብ የታክስ ከፋዩ ሕዝብ ገንዘብ ባክኖ እንዳይቀር፣ አጥፊዎችም ተገቢውን አስተማሪ ቅጣት እንዲቀበሉ የተጀመሩ ሥራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው። በተግባርም ተተግብረው እንደምናያቸው ተስፋ አደርጋለሁ። (የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ለዚህ ጹሑፍ ጥንቅር የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ኢቲቪ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ.…ዜናና መረጃዎችን በግብዓትነት ተጠቅሜያለሁ)

አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011

ፍሬው አበበ