ቨርሚኮምፖስት፤ ትኩረት ያላገኘው የተፈጥሮ ማዳበሪያ

12

ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ላይ የተመሰረተውን ኢኮኖሚዋን በማዘመንና ወደ ኢንዱስትሪ በማሸጋገር መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ አቅዳ እየሠራች ትገኛለች:: ሰፊው የአገሪቱ የኅብረተሰብ ክፍል በገጠር የሚኖርና ኑሮውም በግብርና ሥራ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ለዕድገቷም የአንበሳውን ድርሻ እያበረከተ የሚገኘውን የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና ብሎም በኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ መተካት የሚያስችሉ መርሐ ግብሮችን መተግበር የመንግሥት ቀዳሚ የልማት አጀንዳ ከሆነ ቆይቷል::

አገሪቱ የሰፊው ህዝቧ ኑሮ የተመሰረተበትን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ውጤት በማሻሻል የዜጎቿን የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ልዩ ልዩ መርሐ-ግብሮችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰችም ትገኛለች:: በተለይም አገሪቱ ለዕድገቷ ዓይነተኛ መሰረት የሆነውን የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ብሎም በኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመተካት የሚያስችሉ መርሐ ግብሮችን በተለያዩ ጊዜያት ተግባራዊ እያደረገች ነው::

 በገጠር የሚገኘውን ሰፊውን የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ሥራ በማሰማራት የምግብ ዋስትናውን ያረጋገጠ ማኅበረሰብ መገንባት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን በማሳካት የአገሪቱን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ ከሁሉም ቅድሚያና ትኩረት ያገኘ ሥራ ሆኗል:: የእርሻውን ዘርፍ ምርታማነት ለመጨመር ከሚያስችሉ ነገሮች አንዱ የማዳበሪያ አጠቃቀም ነው:: በአሁኑ ወቅት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙት ሰው ሠራሽ ማዳበሪያዎች በተጨማሪ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያዎችን መጠቀም የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል::

ይሁን እንጂ፤ በምርታማነታቸው

 በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች መካከል አንዱ የሆነው ቨርሚኮምፖስት ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም:: በቨርሚኮምፖስት ምንነት፣ ፋይዳዎች፣ የትኩረት ማነስ ምክንያቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህርና የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ከሆኑትና በቨርሚኮምፖስት ላይ ምርምሮችን ካካሄዱት ከዶክተር ገዛኸኝ ደግፌ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል::

የቨርሚኮምፖስት ምንነት

ቨርሚኮምፖስት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ነው:: ከሌሎች የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች ለየት የሚያደርገው አመራረቱ ነው:: ሌሎቹ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች በመከመር፤ መሬት ውስጥ በመቅበርና በማገላበጥ የሚመረቱ ናቸው:: ቨርሚኮምፖስት ግን በትሎች አማካኝነት የሚመረት ማዳበሪያ ነው:: በቆሻሻ ላይ ትሎችን በማስቀመጥ ትሎቹ ቆሻሻውን ከተመገቡት በኋላ ከውስጣቸው የሚወጣው ፅዳጅ/ቆሻሻ የቨርሚኮምፖስቱን አብዛኛውን ክፍል ይሸፍናል::

በሂደቱ ውስጥ ትሎችና ደቂቅ ፍጥረታት (Micro-organisms) አሉ:: በሌሎች የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች የማምረት ሥራ ላይ በአብዛኛው የሚሳተፉት ደቂቅ ፍጥረታት ናቸው:: በቨርሚኮምፖስት ላይ ግን ዋነኞቹ ተሳታፊዎች ትሎች ናቸው::

 ቨርሚኮምፖስት ለአፈር በጣም ተስማሚ የሆነ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ነው:: በውስጡ የያዛቸው ንጥረ ነገሮች የአፈር ለምነትን የሚጨምሩ ናቸው:: የተክሎችን በሽታ በመከላከልም ይታወቃል:: ውሃ የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ አንድ ጊዜ መሬት ላይ ከተበተነ እስከ ሦስት ዓመታት ድረስ የመቆየት አቅም አለው:: ማዳበሪያው አንድ ጊዜ መሬት ላይ ከተደፋ በኋላ ለረጅም ጊዜ ማዕድናቱን እንደያዘ ይቆያል::

ቨርሚኮምፖስትን በመጠቀም የሚተከሉ አትክልት ከሌሎቹ ፈጥነው ያድጋሉ:: የኬሚካል ማዳበሪያዎች የሚያገለግሉት ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው:: ይህ ማዳበሪያ ውሃ የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር በደረቃማ አካባቢዎች መጠቀም ከተቻለ ለምርታማነት መጨመር ላቅ ያለ አስተዋፅዖ ይኖረዋል:: በአጠቃላይ ቨርሚኮምፖስት ተመራጭ ከሚባሉት የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች (Organic Fertilizers) መካከል ዋነኛው ነው::

ቨርሚኮምፖስት በኢትዮጵያ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዳበሪያው ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ ረጅም ዓመታት አስቆጥሯል:: ትሎችን በመጠቀም ማዳበሪያ የማምረት ተግባር ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የነበረ ተሞክሮ ነው:: ለአብነት ያህል ግብፆች በናይል ወንዝ አካባቢ ይጠቀሙበት ነበር:: በኢትዮጵያ ግን የአጭር ጊዜ ታሪክ ያለው ማዳበሪያ ነው:: ቨርሚኮምፖስትን የማምረት ሥራ ከተጀመረ ከ15 ዓመታት አይበልጥም::

የግብርና ምርምር ማዕከላትና አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማዳበሪያውን የማምረት ሥራ ሲሞክሩ ቆይተዋል:: እንደ ሕንድ ያሉ አገራት ይህንን ማዳበሪያ አሁንም በስፋት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ:: የአምቦ ግብርና ምርምር ማዕከል ማዳበሪያውን በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ያከፋፍል ነበር:: ከዚህ በተረፈ ማዳበሪያው በኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ አልዋለም::

ትኩረት ያለማግኘቱ ምክንያቶች

ማዳበሪያው በስፋት ጥቅም ላይ ላለመዋሉ የሚጠቀሱ ምክንያቶች አሉ:: ከእነዚህ መካከል አንዱ ባለሙያዎች በዘርፉ ላይ ትኩረት አለማድረጋቸው ነው:: ማዳበሪያውን ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ትሎችን ዝርያቸውን በመለየት ረገድ ያሉ ውስንነቶችም ማዳበሪያው በስፋት አገልግሎት ላይ እንዳይውል አድርጓል:: ቨርሚኮምፖስትን በማምረት ሂደት ውስጥ ቆሻሻውን ወደ ማዳበሪያ የሚቀይሩት የትል ዝርያዎች ጥቂት ናቸው:: የእነዚህን ትሎች ዝርያ ልየታ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በብዛት ማግኘት አለመቻልም ሌላው እንቅፋት ነው::

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተግባራት

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ይምሎ ቀበሌ አስተዳደር ባከናወነው የተቀናጀ የዓሣና የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት ውስጥ ከተካተቱ ሥራዎች መካከል የቨርሚኮምፖስት ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራ አንዱ ነው:: የይምሎ ቀበሌ አርሶ አደሮችም ማዳበሪያውን መጠቀም ጀምረዋል::

ከዚህ በተጨማሪም፤ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የቡና ምርት ባለባቸው ቦታዎች በይርጋለምና በዲላ አካባቢዎች ከቡና የሚወገደውን ገለባ ወደ ማዳበሪያነት በመቀየር ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ እያከናወነ ይገኛል:: የቡናው ገለባ በአካባቢው የሚገኙ ውሃማ አካላትን በመበከል በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን በመመልከት ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ምርምሮች ተደርገው ከሦስት የቡና ማምረቻ ማዕከላት 200 ሺህ ኪሎ ግራም የቡና ገለባ በቨርሚኮምፖስትነት ከማስወገድ በተጨማሪ ማዳበሪያውን በማሰራጨት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል::

ማዳበሪያው በቡናና በአበባ እርሻዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል:: በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከግቢው ውስጥ የሚወገደውን ቆሻሻ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶች በማከፋፈል ወደማዳበሪያ ለውጠው እንዲጠቀሙበት እያደረገ ነው::

ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ሌሎች የትምህርትና ምርምር ማዕከላት፤ በተለይ ደግሞ በአካባቢያቸው ከፍተኛ የግብርና እንቅስቃሴ ያለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይህን ሥራ ቢያከናውኑ ማኅበረሰባዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው:: የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኩል ከመንግሥት ጋር በትብብር ስለሚሠራ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል::

ቀጣይ ዕቅዶች

በቀጣይ ሥራውን ለማስፋት የተያዙ እቅዶች አሉ:: ቡና በስፋት በሚመረትባቸው የደቡብ ክልል አካባቢዎች እየተሠራ ያለውን ሥራ ለማጠናከር የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ከስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር መርሐ ግብር (SIDA) ስለተገኘ ሥራውን ለማስፋት ታቅዷል:: የአካባቢው አርሶ አደሮች ማዳበሪያውን ማምረት ብቻ ሳይሆን ማዳበሪያውን በስፋት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ ጥረት እየተደረገም ይገኛል:: ለዚህም ከቡና አምራች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በትብብር እየተሠራ ነው::

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011

አንተነህ ቸሬ