«ኢትዮጵያ የተፈጠረችው አብሮ በመኖር ነው፤ የምታምረውም አብሮ በመኖር ነው»ዶክተር ፍርዲሳ ጀቤሳ

71

የተወለዱትና 1ኛደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ጃርቴ ወረዳ ገበሬ ማህበር ነው። በትምህርታቸው ጎበዝ በመሆናቸው በአምስት ዓመት ውስጥ ብቻ የአንደኛ ደረጃን ትምህርት አጠናቀው ወደ 2ኛ ደረጃ መሸጋገር ችለዋል። ይሁንና በወቅቱ በአካባቢያቸው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ወደ ሻምቦ ከተማ በመ ሄድ ለመማር ተገደዋል።

በእዛውም ትምህር ታቸውን በከፍተኛ ውጤት አጠናቀው በባህ ርዳር መምህራን ኮሌጅ ገብተው በስ- ትምህርት ሳይንስ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን አግኝተው አስመራ በመምህርነት ተመድ በው መስራት ጀመሩ። ሁለት ዓመት እንዳ ገለገሉ ግን ኤርትራ ራሷን ችላ አገር በመ ሆንዋ የመፈናቀል እጣ ገጠማቸው።

አገራቸው ከመጡ በኋላም በነቀምት መምህራን ኮሌጅ፣ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ እንዲሁም አሁን ባሉበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተለያዩ ሃላፊነቶች አገልግለዋል፤ በማገልገልም ላይ ናቸው።

በእነዚህ ጊዜያትም ማስተርሳቸውን በስርዓተ ትምህርትና ኢንስትራክሽን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰሩ ሲሆን እንዲሁም ሆላንድ በመሄድ በትምህርት ምዘናና ግምገማ ዘርፍ ሁለተኛውን የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የማስተማር ዘርፍ ማግኘት ችለ ዋል። የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ፍርዲሳ ጀቤሳ። ከእንግዳችን ጋር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉ የመመማር ማስማር ችግሮችና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል። እን ደሚከተለው እናቀርበነዋለን።

አዲስ ዘመን፡– አሁን ትንሿ ኢትዮጵያ እየተባሉ በሚጠሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። በእርሶ እምነት የግጭቶቹ ትክክለኛ ምንጭ ምንድ ነው?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- እንዳልሽው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎች በአንድ ላይ አቅፈው ይዘው የእውቀት ማዕድ የሚያቋድሱና ኢትዮጵያን በትንሹ የምናይበት ትልቅ ማዕከል ነው። ይሁንና በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተቻችሎና ተፋቅሮ የመኖር እሴት በተቋማቱ እየተሸረሸረ መጥቷል። እኔ ለግጭቶቹ ዋነኛ ምንጭ የምለው ተማሪዎቹን ከሞቀ የወላጅ ፍቅር ተረክበናቸው ስናበቃ እንደ ቤተሰብ በፍቅር ልንይዛቸው አለመቻላችን ነው።

አብዛኛው መምህርና በሃላፊነት ላይ ያለ አመራር ተማሪዎች ከየትም አካባቢ ይምጡ ከየት በፍቅርና በመተማመን ላይ እንዲኖሩ ከማድረግ ይልቅ በመከፋፈል ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖራቸው ነው የሚያደርገው።

ልጆቹ ንፁህ አዕምሮ ይዘው እንደመጡ በመዘንጋት አመለካከታቸውን የሚበርዝ አስተ ሳሰብ ስንመግባቸው ነው የቆየነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ አመራሮች እሳት ለኩሰው እሳት በማጥፋት ስራ ውስጥ ሲጠመዱ ነው የሚታዩት።

በአሁኑ ወቅት እኮ የትምህርት ጥራት የለም። ሁሉም በሚባል ደረጃ ዩኒቨር ሲቲዎቻችን ማጎሪያ እንጂ መማሪያ እየሆኑ አይደለም። አብዛኛው መምህር ከልቡ አያስ ተምርም፤ ሃላፊነቱንም እየተወጣ አይደለም።

ትምህርት ሚኒስቴርም ቢሆን ተከሽኖ የቀረበለትን ሪፖርት ከመቀበል ባለፈ የመማር ማስተማሩ ሂደት በምን መንገድ እየተካሄደ እንደሆነ፤ በተለይ ደግሞ ከፖለቲካ የፀዳ አሰራር በመዘርጋት አገሩን የሚወድ ትውልድ ለመቅረፅ ስለመቻሉ የሚያጣራበት ሁኔታ የለም። ሌላው ይቅር ተቋማቱ ባሉበት አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች እንኳ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው የሚያደርግ አሰራር የለም። በአጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱና በተቋማቱ ላይ ያሉት ውስብስብ ችግሮች የትምህርት ጥራቱ እንዲወርድ ከማድረጉም ባሻገር ተማሪዎቹ ከፈጠራ ይልቅ ራሳቸውን ለብጥብጥና ለነውጥ እንዲያዘጋጁ ምክንያት ሆኗል ባይ ነኝ።

አዲስ ዘመን፡– ስርዓተ ትምህርቱ ችግር ስላለበት መቀየር አለበት እያሉ ነው?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- እንደዛ ሳይሆን በሚፈ ለገው መልኩ እየተተገበረ አይደለም እያልኩ ነው። በሰው ላይ አልተሰራም። መምህራን የኔነት ስሜት ኖራቸው እንዲሰሩ አልተደረገም። ለነገሩ በትምህርት ሥርዓቱ ብሄራዊ አለመግባባት አለ ብዬ አላምንም። በአጠቃላይ ሥርዓቱ ላይ የነበረንን ኩርፊያ ተማሪን መጠቀሚያ አድርገነዋል።

ተማሪዎቻችን ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡት እውቀት ቀስመው፤ ተቻችሎ የመኖርን እሴት አዳብረው ሳይሆን ስለዘር፤ ፖለቲካና ሃይማኖት ሰብከናቸው በጥላቻ ተሞልተው ነው። ለዚህም ነው አብዛኛው ምሩቅ ህብረተሰቡ ጋር ሲቀላቀል ስራ ፈጣሪ ከመሆን ይልቅ ነውጥ አንቀሳቃሽ የሆነው። ደግሞም እኮ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በእኩል ጥራት ሳናስተምር እኩል ውጤት ልንጠብቅ አይገባንም። ለውጡም ቢሆን ከላይ የተንጠለጠለ እንጂ ወደ ታች አልወረደም።

አዲስ ዘመን፡- ስለለውጥ ካነሱ አይቀር ያለፈውን አንድ አመት የለውጥ ጉዞ እንዴት ይመለከቱታል?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- ባለፈው አንድ አመት የአገራችን ያለችበትን የለውጥ ጉዞ ስናይ በርካታ ጥሩ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል። ለእኔ ግን እንደ ትልቅ ምዕራፍ ሊታይ ይገባዋል የምለው እንደ ባላንጣ ስንተያይ ከነበርናቸው ጎረቤት አገሮች ጋር ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ ሰላም መፍጠራችን ሲሆን ይህም አገራችን በዓለም ላይ ያላትን ገፅታ በከፍተኛ ሁኔታ አጉልቶታል የሚል እምነት አለኝ።

የሞት ፍርድ ድረስ ተፈርዶባቸው የነበሩ ዜጎችም ነፃ መውጣታቸው፤ አገር መግባት የተከለከሉና በአሸባሪነት የተፈረጁ ሰዎች ዳግም አገራቸው መመለስ መቻላቸውና ከወገኖቻቸው ጋር መቀላቀል መቻላቸው እንደ ትልቅ እምርታ ነው የማየው። ከምንም በላይ ደግሞ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት በተጨባጭ መከበሩ የምንፈልገውንና በሌሎች አገራት እንቀናበት የነበረውን ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን አድር ጎታል የሚል እምነት አለኝ። ምንም እንኳን የተሰጠውን ነፃነት አንዳንዶች ገደብ እየጣሱና ለአገርም ስጋት እየሆኑ ቢሆንም ማለቴ ነው።

ለዓመታት በጠበንጃ ተይዞ የኖረው የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነትም ቢሆን በመተማመንና በፍቅር ላይ የተመሰረ እንዲሆን በማድረግ ረገድ በዶክተር አብይ የሚመራው መንግስት የሰራው ስራ በቀላሉ ሊታይ የሚገባው አይደለም።

ያው አሁን አሁን አንዳንድ ቦታዎች ላይ ይህንን መተማመን ለማደፍረስ የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም። በኢኮኖሚ ረገድም በተለይም ስልጣንን መከታ በማድረግ ሀብት ያግበሰበሱ ባለስልጣናት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ጥረት መደረጉ የሰማይና የምድር ተራርቆ የነበረውን የህዝቡ የኑሮ ልዩነት ሚዛኑን የጠበቀ ለማድረግ ያስችላል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- የተሰጠውን ነፃነት ገደብ የጣሱ መኖራቸውንና ይህም ስጋት መሆኑን ጠቅሰዋል፤ ይህንን ሊያብራሩልን ይችላሉ?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- እውነት ነው የተፈጠ ረው ነፃነት አገሪቱን ወደአልሆነ አቅጣጫ እንዳይመራት ስጋት አለኝ። ዴሞክራሲ ማለት የራስን መብት ማስከበር እንጂ የሌላውንም ማክበር እንደሆነ የማይገባቸው በርካታ ሰዎች አሉ።

አሁን እየታያ ያለው ሁኔታ የሌሎችን መብትና ሞራል የሚነካ ተግባር በመፈፀም ሥርዓት አልበኝነት እየተስፋፋ መምጣቱን ነው። ጥቂት የማይባለው ህዝብ ለፈጠረውና በአገሪቱ ለሆነው ነገር ፈጣሪውን ከማመስገንና ይህ ሰላምና ነፃነት እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ ትንሿን ቀዳዳ እየፈለጉ መተነኳኳስን ነው የሚመርጠው።

የሚገርመው ደግሞ ሞት የተፈረደባቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ነፃ ባወጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ጦርነት ያወጁም አሉ፡ በየመስሪያ ቤቱ ይሄ መዋቅር ተዘርግቶ መንግስትን የሚነቅፉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ነው የምረዳው። በነገራችን ላይ መንግስትን ይህንን እንቅስቃሴ ለመግታት እውቀቱም ሆነ ችሎታው አለው፤ ነገር ግን ዴሞክራሲው እንዳይነካበት ሲል በሆደ ሰፊነት እንደታገሰ ነው የሚሰማኝ። በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የአዴፓ አባል የሆኑ ሰዎች ሳይቀሩ ፀረ ለውጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ህዝቡን ጥርጣሬ ውስጥ እየከተቱት ነው የሚገኙት። ስለዚህ ይህ ሁኔታ ለእኔ ስጋት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ አዲስ አበባን በሚመለከት ከኮንዶሚኒየም ቤት እጣ መውጣት ጋር ተያይዞ ቀድሞ መግለጫ ያወጣው ኦዴፓ ነው?

ዶክተር ፍርዲሳ፡– አይ ኦዴፓማ አንዳንድ የአዴፓ አመራሮች ያነሱትን ሃሳብ ተከትለው ነው መግለጫውን ያወጣው። በእኔ እምነት ይህንን ያደረገውም ህዝብን ለማረጋጋት ሲል ነው። ከአዲስ አበባ ጋር ተያይዞ ህገመንግስቱ ለኦሮሞ ህዝብ የሰጠውን ልዩ ጥቅም እስካሁን ተግባራዊ ባለመደረጉ ህዝቡ በከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ በመሆኑ ህዝቡን ማረጋጋት ተገቢ ስለሆነ ይመስለኛል መግለጫውን ያወጣው። ግን በሌላ ወገን ያሉ ፖለቲከኞች ህዝብ ከማረጋጋት ይልቅ ህዝብና ህዝብን የሚቃቅሩ ሃሳቦችን በማንሳት ወደአልሆነ አቅጣጫ እየመሩት ነው የሚል እምነት አለኝ። የሚያሳዝነው ይህንን ሲያደርጉም ተጠያቂነት የለም።

አዲስ ዘመን፡– ተጠያቂነት ሊመጣ ይገባል የሚሉት አዲስ አበባ ላይ እኛም ባለድርሻ ነን በሚሉ ወገኖች ላይ ብቻ ነው?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- አዎ፤ ምክንያቱም እስካሁን የምንመራው ላለፉት 27 ዓመታት በተመራንበት ህገ መንግስት ሆኖ ሳለ፤ ህገ መንግስቱ የሰጠውን ልዩ ጥቅም አንቀበልም ማለታቸው በህግ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። በተለይም ‹‹የአዲስ አበባ ባለ አደራ ነኝ›› የሚለው አካል በህዝቦች ላይ አለመተማመን የፈጠረ ከመሆኑንም ባሻገር ይህንን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ የሚጥስ ነው ብዬ ነው የማስበው።

አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ህገመንግስቱን የሰራው ሰው እንደመሆኑ መጠን የማፍረስ መብቱም በእጁ ነው። በህገመንግስቱም ሆነ በፌደራሊዝም ሥርዓቱ አንድራደርም በማለት የምንፈልገው ዴሞክራሲ ይመጣል ብለው ያምናሉ?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- ይህም ቢሆን እኮ ደረጃ አለው። የራሱ ጊዜና አካሄድ አለው። ግን እዛ ደረጃ አልረደስንም። አሁን ገና በውይይት ላይ ነው ያለነው። ደግሞም ጥያቄ ያለው አካል ጥያቄው የሚያቀርበበት መዋቅር መንግስት አለው። ይህንን መስመር ተከትሎ ማቅረብ የሚችልበት መንገድ አልተዘጋም።

ግን ደግሞ ማንም ግለሰብ ተነስቶ ህገመንግስቱን ልጥረብ ካለ ይህችን አገር መልሰን ወደማንጠግንበት መስመር ነው የምትገባው። እንደተሰባባረ ሸክላ ነው የምትሆነው። በህገመንግስት ያልተመራ ህዝብ ወደ ሁከት ነው የሚሄደው። ማንኛውም ግለሰብ ተነስቶ በሚፈልገው አቅጣጫ ከሄደና የሚፈልገውን ተልዕኮ ላስፈጽም ካለ ማቆሚያ የለውም። አገሪቱም ትፈርሳለች።

 አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል ህገመን ግስቱ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግስቱ መቀመጫ መሆንዋን በግልፅ አስቀምጦ እያለ በኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተማዋን የኦሮሚያ ክልል አካል ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸው በራሱ ህገመንግስታዊ ጥሰት እንደሆነ ይገልፃሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- ለእኔ አዲስ አበባ የኦሮሚያም የፌዴራል መንግስቱ መቀመጫ መሆንዋ ህገመንግስቱን የሚጥስበት መንገድ አይታየኝም። አሁንም ቢሆን አዲስ አበባ በአሮሚያ ክልል መካከል ነው ያለችው።

ፌዴራሊዝም የተዋቀረው በክልሎች ነው፤ በህገመንግስቱ ላይ እንዳውም ዘጠኝ ክልሎች ብቻ መኖራቸውን ነው የሚያስቀምጠው። ለከተማ አስተዳደር ቦታ አልሰጠም። ህገመን ግስቱ ለኦሮሚያ ክልል ህዝብ ልዩ ጥቅም እንዲከበርለት የደነገገው አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሃል የምትገኝ ስለሆነች ነው። ይህ ማለት ደግሞ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች መኖር፣ ሀብት ማፍራት አይችሉም ማለት አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኦዴፓ/ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ሆኖ እያለ፤ ለምን አዲስ አበባ ላይ ትኩረት ማድረግ ተፈለገ ሲሉ ይጠይቃሉ። ምን ምላሽ አለዎት?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- የኦሮሚያ ክልል መንግ ስት ጥያቄውን ያቀረበው የፌዴራል መንግስቱ ህገመንግስቱ ለኦሮሚያ ህዝብ የሰጠውን ልዩ ጥቅም ባለመተግበራቸው ነው። በዚህ አንድ አመት ውስጥ አንቀፅ 49 ላይ የተቀመጠውን መብት መፈፀምና ህዝቡን ማረጋጋት ነበረ ባቸው። ህዝቡም ቢሆን ያንን ጥያቄ የሚያነ ሳው በዋናነት የክልሉ ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶቹ ስላልተጠበቁለት ነው።

አዲስ አበባ ምንም እንኳ የሚያጓጓ የተፈጥሮ ሀብት ባይኖራትም መሬቱ በራሱ ያለው በኦሮሚያ እምብርት ላይ በመሆኑ ትኩረት መደረጉ ተፈጥሯዊ ነው ባይ ነኝ። በሌላ በኩል የኦሮሚያ ጨፌ ምክር ቤት የሚገኘው አዲስ አበባ በመሆኑ የክልሉ ተወላጆች ወደ እዚህ ሲመጡ በቋንቋቸው መሰረታዊ አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም።

በተለይ ደግሞ በከተማዋ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች መሬታቸውን አግባብ ባልሆነ መንገድ መቀማታቻው ሳያንስ ውሃቸውን እየወሰድን ፍሳሻችንን እንለቅባቸዋለን። ግን ደግሞ በምትኩ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ አላደረግናቸውም።

ሌላው ቢቀር ጤና ኬላ በአቅራቢያቸው አልተሰራላቸውም፤ ርቀው ሲመጡም በቋንቋቸው አገልግሎት የማያገኙ በመሆኑ በፍጥነትና ተገቢውን ህክምና ሊያገኙ አልቻሉም። ስለዚህ ይህ ጉዳይ በእኔ እምነት ማንኛው ዜጋ በሰብአዊነት ሊረዳው የሚገባ እንጂ ጥያቄም ቅሬታም ሊያነሳበት አይገባም ነበር።

በሌላ በኩል የኦሮሞን ህዝብ በአገር አንድነት ላይ ያለውን አስተሳሰብ ለመቀየር የተሰራው ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለምሳሌ ብናነሳ እንኳ በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያ ድል ያደረገችው በኦሮሞ ጀግኖች ሆኖ ሳለ አንዲት ሃውልት የተሰራለት ጀግና የለም። ይህም በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ ቆይቷል። ደግሞም በተለያየ መንግስታት ሲበደል የቆየ ህዝብ በመሆኑ አሁንም ጥርጣሬ ውስጥ መግባቱ ምንም የሚደንቅ ነገር ሊሆን አይገባም። ከፖለቲካም አኳያ ምንም እንኳን የኦሮሞ ህዝብ ትልቁን ቁጥር ቢይዝም በፌዴራልም ሆነ በአዲስ አበባ ደረጃ ስልጣን እርከን ላይ ያለው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ህገመንግስቱ የሰጠውን ጥቅም እንዲከበርለት እንጂ ከሌሎች ወገኖቹ ተነጥቶ መኖር አይደለም። ለብቻ መኖር የሚፈልገው ኦነግም በአሁኑ ወቅት አቋሙን ቀይሯል። ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የተፈጠረችው አብሮ በመኖር ነው። የምታምረውም አብሮ በመኖር ነው። ተሸራርፈን እንኑር ብንል አናምርም። ሃይልም አይኖረንም።

አዲስ ዘመን፡- የኦሮሞ ፖለቲከኞችና ምሁራን የመስፋፋት አባዜ ህዝቡን ለትርምስ የዳረጉት ይባላል። ለዚህ ደግሞ በጌዲዮ በቤኒሻንጉል በሌሎችም አካባቢዎች ላይ ማሳያ አድርገው ይጠቀሳል። የዚህ ችግር ትክክለኛ ምንጭ ምንድን ነው ይላሉ?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- በእኔ አረዳድ ኦሮሞ መሬቱን ሲሰጥ የሌላውን ሲወስድ አላየሁም። በጌዶዮ ከተፈናቀሉት ህዝብ በላይ የኦሮሞ ህዝብ ተፈናቅሏል። ይህንን ያደረጉት የኦሮሞ ፖለቲከኞችም አይደሉም፣ መንግስትም አይደ ለም።

አክቲቪስቶችም አይደሉም ህዝብም አይደለም። መፈናቀሉን የፈፀሙት በእኔ ኮን ትሮባንዲስቶች ናቸው። በተጨማሪም ገንዘብ መድበው ህዝብና ህዝብን በማጋጨት የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ያሰቡ አካላት ለመፈናቀሉ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። ገንዘብ ከፍለው ህዝብ አሰልጥነው ግጭት የሚፈጥሩ የተደራጁ ሃይሎች አሉ።

በሌላ በኩል የፌደራሊዝም ሥርዓትን የማይፈልገውና ለውጡ እንዳይቀጥል የሚፈልግ ሃይል አለ። ቀን ቀን ኢህአዴግ ማታ ማታ ደግሞ የሴራ ፖለቲካቸውን የሚያጧጥፍ አካላት አሉ። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ስለሀገር ደንታ የሌላቸው ስለ ግል ጥቅማቸው ብቻ የሚሞቱ ሰዎች በርካታ መሆናቸውም እሙን ነው። አሁንም ሆነ ከዚህ በፊት የኦሮሞ ህዝብ የማስፋፋት እንቅስቃሴ አድርጓል የሚል እምነት የለኝም። ማድረግም ቢፈልግ ኖሮ በ1983ና 1984 ወደነበረው ድንበር ይመለስ ነበር።

ህዝቡ ቅሬታውን በማቅረብ ያለው መሪዎቹ ዝም ስላሉ ነው። በነገራችን ላይ አርቴፊሻል ግንኙነት ፈጥረን ሀገርን ማቆም አንችልም። እንዳውም ሰውን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከተው በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ ግንኙነት ሲኖር ነው። እውነታውንና ልዩነ ታችንን አውቀን፤ ተቀብለን ስንስማማ ነው በጋራ መኖር የምንችለው።

ስለዚህ በቀጣይም ቢሆን ልዩነታችንን አክብረምን መተማመን አምጥተን መኖር የሚገባን። እውነቱን ተቀብሎ መኖር አገርን ያረጋጋል እንጂ አያፈርስም። ይህ ማለት ግን ሆነ ብለው ተነስተው ህዝብ ለህዝብ የሚያቃቅሩ ይጠፋሉ ማለት አይደለም። ወደ እውነት ካልመጣን አንድንም።

አዲስ ዘመን፡- ሁሉም የራሴ እውነት አለኝ በሚልበት አገር የትኛው እውነት ነው የሚያድነን?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- ወደ ተፈጥሮ ካልመጣን አንድንም፤ እኔ እያልኩት ያለሁት ባለፉት ዓመታት አንድ ሆነን የኖርነው በጠበንጃ ሃይል እንጂ በፍቅር አልተመሰረትንም ነው። ስለዚህ አሁንም ቢሆን የሚያዋጣው የኦሮሞ ህዝብ አለኝ የሚለውን ቅሬታ ፈትቶ መቀጠል ነው። ይህንን የህዝብ ጥያቄ አንስተው የሚሞግቱ አክቲቪስቶችም ሆነ ፖለቲከኞች ሊወገዙ አይገባም። የጠየቁት ተፈጥሮ የሰጣቸውን እውነት በመሆኑ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ሁሉም የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የሚያነሱት ሃሳብ ሁሉ እውነት ነው እያሉኝ ነው?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- እንደዛ ለማለት ፈልጌ አይደለም። ሁሉም ፍፁም ነው እያ ልኩ አይደለም። ደግሞም ማንም የበላይ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። እነዚህ አካላት የሚያቀርቡት ቅሬታ ኦሮሞ ለምን የበላይ አልሆነም አይደለም፤ እንደሌላው ህዝብ ጥቅሙ ይከበርለት እንጂ። ይህ ማለት ግንዛቤው ሳይኖራቸው የሚሰሩ የሉም ማለት አይቻልም። በኦሮሞ ስም፤ በኦሮሞ የሚነግዱ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችም አይኖሩም ማለት አይደለም። እኔ በግል የማውቀው ምሁር ሆኖ ግን ቀድሞ ያገኘው ጥቅም የቀረበት ሰው በኦሮሞ ስም እየፃፈ ህዝብና ህዝብን የሚያጋጭ ሰው አለ። መረጋጋት እንዳይኖር በርካታ ጥረቶች አሉ።

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ኦሮምኛ የስራ ቋንቋ ማድረጉ ክፋት ባይኖረውም ግን በፍቅር እንጂ ህዝቡን በግዳጅ እንዲማር ማድረጉ ቋንቋውን እንዲጠላ ያደርጋል ሲሉ ያነሳሉ?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- ቋንቋ ባለቤት የለ ውም። ቋንቋ ማወቃችን ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም። አስቀድሜ እንዳልኩት ኢትዮጵያን ከልብ ለመገንባት ከተፈለገ እውነታን መቀበል የግድ ይላል። አሁን የኔ ቋንቋ፣ የኔ ባህል ካልሆነ የሚል አስተሳሰብ ካለ ነው ጠባብ ልንለው የምንችለው። ኢትዮጵያዊ ለመሆን የግድ አማርኛ ብቻ መናገርና የኦሮቶዶክስ ክርስቲያን ተከታይ መሆን አይጠበቅብንም።

በተመሳሳይ ኦነግም ይህንን አመለካከት ነበር የሚያራምደው። ግን ይሄ ኢትዮጵያን አይገነባም። ኢትዮጵያ ማለት ጉራግኛ መናገር በጉራጌ ልብም ማሰብ ይጠይቃል። ትግርኛ መናገር በትግሬ ልብ ማሰብ ይጠይቃል። ኦሮምኛ መናገር በኦሮሞ ልብ ማሰብ ይጠይቃል። እነኚህ ውበቶች ናቸው ኢትዮጵያን የሚገነቡት። ስለዚህ ጠባብነት የሚሆነው የራስን ሃይማኖትና ቋንቋ በሌላው ላይ መጫን ነው። ሩቅ ሳንሄድ ደቡብ አፍሪካ እንኳ 11 የስራ ቋንቋ አላት። ታዲያ ምኑ ላይ ነው የኦሮምኛ ቋንቋ የስራ ቋንቋ ቢሆን ችግር የሚሆነው።

አማራጭ ነው የሚቀርበው እንጂ ቋንቋየን ካልተማርክ ብሎ ዜጋ ላይ የሚጭንም የለም። ሳይንሱም እንደዚያ አይልም። አሁን መጠቀም ያልቻለ ዜጋ አለ። ይጠቅመኛል ያለ መማር እንዲችል ነው። ለምሳሌ የደቡብ ተወላጆች ኦሮምኛ ይማራሉ ምክንያታቸውን ሲጠየቁ የሚመልሱት የስራ እድሎቻቸውን ለማስፋት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ስለዚህ በግዳጅ የሚደረግ ነገር የለም፤ ከሆነም ወንጀል ነው የሚሆነው። በሌላ በኩል ግን አሮምኛን ተከትሎ ጉራግኛ፣ ትግርኛም የስራ ቋንቋ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል የሚል እምነት አለኝ።

በነገራችን ላይ ዘረኝነት ተፈጥሯዊ ነው። አንቺም ብትሆኚ ከራስሽ እናት በላይ የእኔን እናት ልትወጂ አትችይም። ስለዚህ ዘረኝነት ተፈጥሯዊ ነው። ሰው ዘሩን ራሱን ይወዳል፤ ያስበልጣል። ግን ይህንን ተፈጥሮ ብንቀበል ኢትዮጵያን እንገነባለን። ግን በሰው ሰራሽ የአንድነት ፍቅር ካቆየነው ተዳፍኖ አይቀርም አንድ ቀን አፈንግጦ ይወጣል። አሁን ይህንን ሁኔታ በጥንቃቃቄ መምራት አልቻልንም። የተለወጡትን መምራት ደግሞ የአመራር ዘይቤና መሪዎችን መቀየር ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ሁሉም ቋንቋ የስራ ቋንቋ መሆን አለበት እያሉ ነው?

ዶክተር ፍርዲሳ፡– አይደለም። ከ80 በላይ ቋንቋ ባለቡት አገር ሁሉ የስራ ቋንቋ ይሁን ብንል የአገሪቱ ኢኮኖሚም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው የሚሆነው። ከሰው ብዛታችን ጋር የሚወስነው ነው የሚሆነው።

አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ከሚመራው መንግስት ምን ይቀራል ምን ሊሰራ ይገባል ብለው ያምናሉ?

ዶክተር ፍርዲሳ፡– ቃል በገቡት መሰረት የኦሮሞ ህዝብን ጥቅም ማስከበር ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡– ከኦሮሞ ውጭ ለሆነው ህዝብስ?

ዶክተር ፍርዲሳ፡- ኦሮሞን ካላረጋጋን እንደ አገር ሰላም ለመፍጠር ያዳግታል። ይህንን ለውጥ ያመጣው ህዝብ ነው። ኢህአዴግ አይደለም ያመጣው። ትክክለኛውን ስራ መስራት ማለት እኮ ለኦሮሞ መወገን ማለት አይደለም። ህገመንግስቱ ከእግዚአብሄር በታች ነው ካልን መተግበር ነው። ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለአገውም ለቅማንትም ለሲዳማም ህዝብ ጩኸት ጆሮ መስጠት ይገባል። አገውና ቅማንት አካባቢ ኢ-ፍትሀዊ ስራ ነው እየተሰራ ያለው። መንግስት ይህንን መፍታት አለበት። ማንም ዜጋ መጨነቅ መበደል የለበትም።

አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍሉ ጋር ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼ ስም አመሰ ግናለሁ።

ዶክተር ፍርዲሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2011

በማህሌት አብዱል