በፓርኩ የተነሳውን እሳት በሄሊኮፕተር ማጥፋት ተጀመረ -የእስራኤል የቴክኒክ ቡድንም ቦታው ላይ ደርሷል

10

 አዲስ አበባ:- በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ እየደረሰ ያለውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር በሰው ኃይል ይካሄድ የነበረውን ጥረት ለማገዝ እንዲቻል የኢትዮጵያ መንግሥት በጠየቀው ድጋፍ መሠረት የኬንያ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር በአካባቢው ደርሶ እሳቱን ማጥፋት መጀመሩ ተገለጸ፡፡

12 እስራኤላውያን ባለሙያዎችን የያዘ የቴክኒክ ቡድን በአካባቢው የተገኘ ሲሆን የእሳቱ መንስዔ በማን? በምን? እና እንዴት? እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተጠቆመ።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ለምለሙ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት በትናንትናው ዕለት በስፍራው የደረሰው የኬንያው ሄሊኮፕተር በቦታው ደርሶ እሳቱን ማጥፋት ጀምሯል፡፡

በአንድ ፓይለትና አንድ ረዳት የሚንቀሳቀሰው ይህ የእሳት ማጥፊያው ሄሊኮፕተር 1ሺህ 200 ሊትር ውሃ የሚይዝ ሲሆን፣ ውሃውን የሚያገኘው ዩኒቨርሲቲው አካባቢ ከሚገኘው ደባርቅ ወንዝ መሆኑንና ለቶሎ ቶሎ ምልልስ እየረዳው እንደሆነም አስረድተዋል።

እንደ አቶ ወርቁ ለምለሙ ገለጻ ከሄሊኮፕተሩና አብራሪ ባለሞያዎቹ በተጨማሪ አንድ እራሱን የቻለ፣ 12 እስራኤላውያን ባለሙያዎችን የያዘ የቴክኒክ ቡድን በአካባቢው የተገኘ ሲሆን የእሳቱ መንስዔ በማን? በምን? እና እንዴት? እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ከሳምንት በፊት የተቀሰቀሰውን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም የአካባቢው ነዋሪና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት፤ በተለይም የአካባቢውም ሆነ ከሌላ ቦታ በመምጣት አደጋውን ለመቆጣጠር በከፍተኛ ደረጃ

 የጸጥታ አካላት፣ ሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች በገንዘብና በጉልበት ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸው በሙሉ ሊመሰገኑ ይገባል ያሉት አቶ ወርቁ ለምለሙ፣ እሳቱ ሊጠፋ እና ደኑም ወደ ነበረበት ሊመለስ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የኅብረተሰብ እና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው በበኩላቸው፣ የፓርኩ የላይኛውን ክፍል በኅብረተሰቡ ኃይል መቆጣጠር የተቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ገደላማው አካባቢ አስቸጋሪ በመሆኑ በሄሊኮፕተር የማጥፋቱ ሥራ እየተሰራ ነው።

እስከ ትናንት 10 ሰዓት 30 ደቂቃ ድረስ አራተኛ ዙሩ እሳቱን የማጥፋት ሥራ መስራቱን አመልክተው፣ ሄሊኮፕተሩ በጥሩ ሁኔታ ሥራውን በማከናወን ላይ እንደሚገኝና ለውጥ እየታየ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ፣ የእሳት ቃጠሎው 400 ሄክታር መሬት ይሸፍናል፡፡ከ 80 እስከ 90 በመቶው ሳር፤ የቀረው ደግሞ ዛፍ የሚገኝበት ቦታ ነው። ምንም እንኳን የደረሰው አደጋ አደገኛ ቢሆንም ቃጠሎውን እዚሁ ላይ ማቆም ከተቻለ ሳሩ ሆነ ዛፎቹ ተመልሰው የማገገም አቅማቸው ፈጣን ስለሆነ በአንድ ዝናብም ሊመለሱ ይችላሉ።

በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር ኦር ዳንኤሊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተ ናገሩት፥ እስራኤል የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የባለሙያዎች ቡድኑን ልካለች።

የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ባለፈው አርብ የኢፌዴሪ ጠቅላይ

ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከእስራኤል አቻቸው ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋር በእስራኤል ድጋፍ ዙሪያ በስልክ መወያየታቸውንም ምክትል አምባሳደሩ አመልክተዋል።

12 አባላት ያሉት ይህ የባለሙያዎች ቡድን ከእስራኤል የእሳት አደጋ ብርጌድ የተውጣጣ ሲሆን፥ በሰደድ እሳት ከፍተኛ እውቀት እና ሙያ ያላቸው ባለሙያዎች መሆናቸውን ምክትል አምባሳደሩ አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በድረ ገጹ እንዳመለከተው፣ ከሳምንታት በፊት በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ የተነሣውን እሳት ለማጥፋት በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ጋር ሲተባበሩ ቆይተዋል:: ይኸውም የእሳት ማጥፋት ሥራው ከውጭ የእሳት አደጋ ሄሊኮፕተሮች የፌዴራል መንግሥት በማስመጣት ላይ በነበረት ጊዜ በሀገር ሰው ርብርብ እሳቱን ለማቆም ተችሎ ነበር::

በአሁኑ ወቅትም እስካውቶች፣ ልዩ ኃይል አባላትና በጎ ፈቃደኞች ሲረባረቡ ቆይተው ከረቡዕ ወዲህ ግን እሳቱ በሰው ለመድረስ ከማይቻልበት ረባዳ ቦታ ገብቷል:: በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመቻችነት የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት አካላት ባደረጉት ጥረትና ጥሪ ከውጭ ሀገሮች የተገኙ የእሳት አደጋ ሄሊኮፕተር እና የቴክኒክ ባለሙያዎች የእሳት ማጥፋት ሥራ መጀመር ችለዋል፡፡

መቃጠል ከጀመረ ከሳምንት በላይ ጊዜን ያስቆጠረው የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ የተመዘገበ፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ቀይ ቀበሮ፣ ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና የመሳሰሉ የዱር እንስሳት የሚገኙበት መሆኑ ይታወቃል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011

ግርማ መንግስቴ