ቢዘገይም ለመፍትሄ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ

74

 የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው ረቂቅ አዋጅ፣ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ካለው ችግር አኳያ ከመዘግየቱ ባለፈ ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት የሚገባ አለመሆኑን ምሑራን ይናገራሉ። በአግባቡ ከተተገበረም ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብትን እንደማይገድብም ይገልጻሉ።

አቶ በረከት ሀሰን፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ማንኛውም ሰው ሃሳቡን ያለምንም ክልከላና ቅድመ ምርመራ በጽሑፍ፣ በንግግር ወይም በስዕል በተለያዩ የሃሳብ መግለጫ አውታሮች (በጋዜጣ፣ ብሮድካስት፣ ማህበራዊ ሚዲያ ወይም በሌላ መንገድ) መግለጽ እንደሚችል የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ያስቀምጣሉ። ሆኖም አንድ ሰው ሃሳቡን በነፃነት ሲገልጽ የሌላውን ሰብዓዊ መብት መንካት፣ መጣስ ወይም ችግር ውስጥ የሚያስገባ መሆን የለበትም።

በዚህ መልኩ አንዱ የሌላውን መብት ጥሰት በሚያደርስ ሁኔታ ሃሳቡን የሚገለጽ፤ የሌላውን ማንነት የሚያኮስስና የሚሳደብ ከሆነ የሃሳብ ነፃነቱ ገደብ ይኖረዋል። ምክንያቱም ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብት እንዳለ ሁሉ ይሄን ዓይነት የሌሎችን መብት የመጣስ አዝማሚያ ሲኖርም የሃሳብ ነፃነቱ ገደብ እንደሚኖረው በዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችም ሆነ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በግልጽ ተቀምጧል።

በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና በግል ጠበቃና የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ ፀጋዬ ደመቀ፣ የአቶ በረከትን ሃሳብ ይጋራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥትም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ያለ እንደመሆኑ ማንም ሰው ሃሳቡን በነፃነት መግለጽ፤ እውነት የሆነን መረጃ ማስተላለፍም ይችላል። ይሁን እንጂ ሃሳብን የመግለጽ ሂደቱ የሌሎችን መብት ወይም የሕዝቦችን ደህንነት እስ ካለመንካት ድረስ የተገደበ እንጂ ልቅ አይደለም። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ስለሌላው ሰው አንስቶ መናገር፤ ስለ አንድ ጉዳይም አንስቶ ሂሳዊ ትችት መስጠት ይችላል።

ነገር ግን ሊሳደብ፣ ጥላቻን ሊያንጸባርቅ፣ በሰዎች ላይ የአካልም ሆነ የሞራልና ሥነልቡና ጉዳት የሚያስከትል፤ ብሔርን ወይም ሃይማኖትን የሚያንቋሸሽና የሚያንኳስስ ሃሰብ መሰንዘር እንዲሁም ያልሆነውን ሆነ ብሎ የሐሰት መረጃን ማስተላልፍ አይችልም። ያልሞተን ሰው ሞቷል፤ ያልጠፋውን ጠፍቷል፤ ያልደረሰውን ጥቃት ደርሷል፤ ወዘተ. ብሎ የሀሰት ወሬ ማዛመትም ሃሳብን በነፃ የመግለጽ ጉዳይ አይደለም። በመሆኑም ይህን ዓይነት ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በኢትዮጵያም ሆነ በዓለምአቀፍ ሕጎች የተገደበ ነው።

እንደ አቶ ፀጋዬ ገለጻ፤ በዚህ መልኩ የሚስተዋሉ የጥላቻ ንግግሮችና የሀሰት መረጃ ስርጭቶችን ለመቆጣጠር አዋጅ የወጣው በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ሳይቀር ሁሉንም የሚገዛ ዓለምአቀፍ ድንጋጌ አውጥቷል። በመሆኑም አዋጁ በኢትዮጵያ መውጣቱ ተገቢ ነው። ይልቁንም ቀድሞ ወጥቶ ቢሆን ብዙ ነገሮችን መታደግ፤ አጥፊዎችንም ተጠያቂ ማድረግ ይቻል ነበር። ምክንያቱም በዓለምአቀፍ ደረጃ እንደታዩት ዘርና መሰል ነገሮችን ማዕከል ያደረጉ ጭፍጨፋዎች ሁሉ፤ በኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ቦታዎች እየሆኑ ያሉት ሁሉ በማህበራዊ ሚዲያዎች መነሻነት በተሰራጩ የሀሰትና የጥላቻ መልዕክቶች ነው።

ይሄን ሃሳብ የሚያጠናክሩት አቶ በረከት በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የማህበራዊ ሚዲያው እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አንድ ሰው በራሱም ሆነ በሀሰት በከፈተው ገጽ ያለማንም ተጠያቂነትና ከልካይ የፈለገውን ሃሳብ በፈለገው ጊዜና መንገድ እንዲያስተላለፍ ዕድል ማግኘቱ የጥላቻ ንግግር ራስ ምታትነት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አደጉ ተብሎ በሚታሰቡ አገሮችም ነው። የጥላቻ መልዕክቶችን ለማስቀረትም ብዙ ጥረቶች ተደርገው አንዳንዶቹ ሲሳካላቸው አንዳንዶቹ እስካሁንም ዋጋ እያስከፈላቸው ነው።

እንደ አቶ በረከት ገለጻ፤ በኢትዮጵያም በተለይ በማህበረሰብና ማህበራዊ ሚዲያዎች በርካታ የውሸት ዜናዎች በየጊዜው ይለቀቃሉ፤ በጣም ብዙ የጥላቻ መልዕክቶችም ይተላለፋሉ። በዚህ መነሻነትም ብሔር ተለይቶ በሰዎች ላይ ድብደባ ሲከናወን፣ ጥቃት ሲደርስና ግድያ ሲፈጸም ታይቷል። በዚያው ልክ በሃይማቶች መካከልም ጥላቻን ለማስረጽ ተሰርቷል።

ይህ ደግሞ በሕግ ሊገደብ፤ የሰዎችም ሰብዓዊ መብት ሊከበርና ሰዎች በማንነታቸው ሊጠቁ የማይችሉበት መንገድ ሊፈጠር ይገባል። የመንግሥት ሥራም መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን የሰዎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር፤ በሰብእናቸው ላይ የሚሰነዘር ጥቃትንም መከላከል ነው። ከዚህ አኳያ የአዋጁ መዘጋጀት ከመዘግየቱ ባለፈ ተገቢና ትክክለኛ ነው።

በረቂቁ እንደጠቀሰው፤ የአዋጁ ዓላማ፣ ሰዎች ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደህንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማስቻል፤ በማህበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲኖርና መግባባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጎለብት ማድረግ፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና የሐሰ ተኛ መረጃ ስርጭት መስፋፋትን እና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከል እና መቀነስ ነው።

አቶ በረከት እንደሚሉት፤ በሀሰት ዜና ብዙ ነገሮች ታጥተዋል፤ በርካታ ነገሮችም ተፈጽመዋል። እናም አዋጁን እንደተባለው የሀሰት ዜናዎችን፤ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በቋናቋና በማንነት ላይ የሚሰነዘሩ የጥላቻ ንግግሮችን ለማስቀረት የሚውል ከሆነ ምንም የሚያከራክር ነገር አይኖርም፤ ተገቢና ትክክለኛ እርምጃ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ቀደም ሲል የፀረ ሽብር አዋጁ ወጥቶ ለዜጎች ሃሳብ ማፈኛነት ተግባር እንደዋለውና አሁን እንዲፈተሽ እንዳስገደደ ሁሉ፤ ይሄንንም የሰዎችን የመናገር መብትና ሃሳብ ለማፈን፤ እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያው ጫና ስለሚያደርግበት መልሶ ለማፈኛ ያወጣው ከሆነ አዋጁ መንግሥት ራሱ መልሶ የሚከስርበት አዋጅ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ ሕጉን ከማዘጋጀት በተጓዳኝ አዋጁን ሊያስፈጽምና ሊከታተል የሚችል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጠንካራ ተቋም ሊታሰብ፤ አዋጁ ሳይ ተገበር እንዳይቀር፣ ሲተገበርም ባልተገባ መልኩ ሚዲያውን ማፈኛ እንዳይሆንም በትኩረት መስ ራት፤ ተያያዥ አዋጆችን ለማስፈጸም ከተቋቋሙ ተቋማት ጋር በመቀናጀት፣ እንዲሁም የአገራት ልምድና የሕዝቦች ተሳትፎ ተፈትሾ ሊተገበር ይገባል።

አቶ ፀጋዬም በዚህ ይስማማሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንድ ሰው ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አለው። ሆኖም የሀሰትና የጥላቻ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ አካላት ላይ እርምጃ የሚወሰደውን ያክል፤ ትክክለኛ መረጃን የሚያሰራጭ ሰውም ሆነ ሚዲያ ከለላ ሊሰጠው ይገባል። ተገቢ ሂስ የሚያቀርቡትም ሊነኩ አይገባም። ነገር ግን አዋጁን ተገን አድርጎ መንግሥት የሚፈራቸውን አካላት ለመጉዳትና ለመፈረጅ የሚጠቀምበት፤ ሃሳብንም ለማፈኛ የሚያውለው ከሆነ የሃሳብ ነፃነትን ይጣረሳል፤ መንግሥትም ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል። አዋጁም ችግሩን ከማቃለል ይልቅ ጉዳቱ ይልቃል፤ በመሆኑም መንግሥት ከዚህ ተግባር ሊቆጠብ፤ በትግበራ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጉዳዮችንም ለይቶ መስራት ይጠበቅበታል። ይሄንን ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራ ተቋምም ሊኖር ይገባል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011

 ወንድወሰን ሽመልስ