የመጡ ለውጦች አልጋ በአልጋ እንዲሆኑ አይጠበቅም

12

 አዲስ አበባ፡- በሪፎርሙ የሚመጡ ለውጦች አልጋ በአልጋ እንዲሆኑ እንደማይጠበቅ እና ለውጡም ሕዝባዊ እንደመሆኑ ሕዝቡ ሊጠብቀው እንደሚገባ ተገለጸ።

የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ፓር ቲዎች፣ የአጋር ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ለውጡ ሪፎርሙ ስር-ነቀል አብዮታዊ ለውጥ ሳይሆን የሕዝብን ጥያቄ ብሎም ከውስጥና ከውጭ የተደረገውን ግፊት መሠረት አድርጎ የተከናወነ ሪፎርም ነው። ይሁን  እንጂ ሪፎርም እንደ አብዮት ቀላል አይደለም። በጣም ከባድ ነው። በመሆኑም በሪፎርሙ የመጡ ለውጦች አልጋ በአልጋ እንዲሆን መጠበቅ አይገባም።

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ባልተጠናከሩበት፤ ኅብረተሰቡም የዴሞ ክራሲ ባህሉ ባልጎለበተበት እና አንዱ የራሱን መብት ለመጠቀም የሌላውን መብት መደፍጠጥ አለብኝ ብሎ በሚያስብበት አገር ችግሩና ፈተናው ቀላል አይሆንም። ሆኖም ኅብረተሰቡ የለውጥ ፍላጎት ያለው ብቻ ሳይሆን ወሳኝ የለውጡ ባለቤትም በመሆኑ፤ አሁንም ለውጡን የሚጠብቀው ሕዝቡ ነው። ስለዚህ በለውጥ ውስጥ ጊዜያዊ ችግሮች እንደሚኖሩ በመገንዘብ ችግሮቹን በጋራ ማለፍ እንደሚቻል አውቆ የሚፈልጋትን ታላቋን አገር ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ባለበት ኃላፊነት ወስዶ የሚጠበቅበትን መወጣት ይኖርበታል።

 እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ በየቦታው መፈናቀልና ግጭቶች ሲበዙ ሕዝቡ መደናገጥና ቅር መሰኘቱ ተገቢ ነው። ሪፎርምም በባህሪው በየትኛውም ዓለም ይሄን ዓይነት ችግር ማስከተሉ አይቀሬ ነው። ሆኖም ችግሩን በመረዳት ውጥረቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት በጋራ እየሰሩ፤ ተገቢውንም እርምጃ እየወሰዱ ነው።

ነገር ግን የሕግ የበላይነት ሲባል ከማሰርና ከመግደል የዘለለ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን የማደራጀትና የማስተማር ተግባራትን እያከናወኑ ትዕግስትን ተላብሶ የተሻለ ውጤት ማምጣት ተገቢ ነው። መንግሥትም ይሄን ለማድረግ የሕግ ማስተካከያዎችን ጨምሮ ሰፊ ሥራ እያከናወነ ሲሆን፤ ኅብረተሰቡ፣ ፓርቲዎች፣ ወጣቶች፣ ሚዲያውና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች በዚሁ አግባብ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011

 ወንድወሰን ሽመልስ