የጥብቅ ደኖች ልማት የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዳለበት ተገለጸ

18

 አዲስ አበባ:- እየተካሄደ የሚገኘው የደ ኖች ልማት አረንጓዴ ኢኮኖሚን ከመገንባ ትና የአየር ንብረትን ከመጠበቅ ባሻገር የሥራ ዕድል መፍጠርና የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዳለበት ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክር ስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ምክትል የልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገብረሥላሴ አፅበሀ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት 1964 ዓ.ም ጀምሮ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት አበረታች ውጤቶችን ሲያስመዘግብ የቆየ ሲሆን አሁንም በመስራት ላይ ይገኛል።

ኮሚሽኑ በምግብ ዋስትና፣ በጤና፣ በመልሶ መቋቋም፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ በስደተኞችና ስደት ተመላሾች እና በመሳሰሉ ተግባራት በመሰማራት ሲያከናውንና ማህበራዊ ኃላፊነትን ሲወጣ መቆየቱን፤ በተለይ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ-ክርስቲያን ደን ልማት እና የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ላይ በሰፊው አቅዶ በመስራት ላይ የሚገኝ መሆኑን፤ በዚህ ተግባር የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ እንዲጠበቅና ዜጎች በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ ግንዛቤ የማስጨበጥና ደኖችን የመንከባከብ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንና በዚህም ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል የሚሉት ምክትል ኃላፊው በማንኛውም ልማት ውስጥ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ማሰብ አስፈለጊ መሆኑንም አስረድተዋል።

“ድሮ ዛፍ መቁረጥ እንደ ሀጢያት ነበር የሚቆጠረው፤ ዛሬ ግን በየቦታው የተለያዩ ዛፎች ሲቆረጡ ነው የሚውሉት” የሚሉት አቶ ገብረሥላሴ አፅበሀ መንግሥትም ይህን ለመከላከል በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። “ዞሮ ዞሮ ኅብረተሰቡ ይህን ተግባር የሚፈፅመውና ደን የሚያወድመው ወዶ ሳይሆን አማራጭ በማጣቱ ነው። ይህ አማራጭ የማጣት ጉዳይም ወደሥራ አጥነት ይመራቸዋል። ይህንን ለመቋቋም ሲሉ ነው እንግዲህ ወደ እንጨት ለቅሞ መሸጥና ሌሎች ተግባራት የሚሰማሩት ሲሉም ምክንያቱን አስረድተዋል።

ለእነዚህ ወገኖች የሥራ ዕድል ካልተፈ ጠረና አማራጭ ካላገኙ በስተቀር ደን መቁረጡን አይተዉም፤ አጠቃላይ ችግሩንም በዘላቂነት ማቆም አይቻልም የሚሉት ምክትል ኃላፊ እየተሰራ ያለው ሥራ ደንን በማልማት የአየር ንብረትን መንከባከብ ቢሆንም በሌላ በኩል የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የኅብረተሰቡን ኑሮ ማሻሻል ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ኅብረተሰቡ ደኑን ሊጠብቅና ሊንከባከብ የሚችለው በማለት ኅብረተሰቡ ከልማቱ መጠቀም እንዳለበት ተናግረዋል።

ተራድኦ ኮሚሽኑ በዚህ ዙር ከጀርመን እና ኖርዌይ መሰል ተቋማት የተገኘ ብር 109 ሚሊዮን 790ሺህ 92 በጀትን በመመደብ 19 ቤተክርስቲያናትና ገዳማት የሚገኙበትን አካባቢ በደን ለማልማት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን የሚገልፁት ምክትል ኃላፊው በልማቱም 103ሺህ 363 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉም አስረድተዋል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011

 ግርማ መንግሥቴ