ከኢትዮጵያ እጅ ያመለጠው ቻን በካሜሩን ቤት

13

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበትን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮን ሺፕ / ቻን/ እኤአ በ2020 ለማስተናገድ ከካፍ ኃላፊነቱን ከተረከበ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለዚህም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ ስታዲየሞች በሀገሪቱ መገንባታቸው ተቀባይነትን ለማግኘት ዋና ምክንያት ሆኖ ተመዝግቧል።

የካፍ ፕሬዚዳንት ማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ ወደ ተመረጡባት ኢትዮጵያ ብቅ ባሉበት ወቅት፤ አገሪቱ በስፖርት መሰረተ ልማት በተለይም ለእግር ኳሱ ዕድገት ከፍተኛ ወጪ መድባ የምታከናውናቸውን የተለያዩ ተግባራት አድንቀዋል። ኢትዮጵያ አህጉራዊ ውድድሮችን የማዘጋጀት ፍላጎቷንም በስኬት የማድመቅ ተስፋ እንዳላት ጭምር ምስክርነት ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ፤ ለቻን አዘጋጅነት ከመታጨቷም በላይ እያደረገች ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ መገናኛ ብዙሀን ሰፊ ዘገባዎች ሲሰራጩ ቆይተዋል።

የኋላ ኋላ ግን እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ውድድሩን ኢትዮጵያ በብቃት ስለማስተናገዷ ጥያቄን አስነስቷል። በተለይም ሀገሪቱ ለመስተንግዶ የምታደርገው ዝግጅት ሲፈተሽ በሚፈለገው ፍጥነት መጓዝ እንዳልቻለ ታይቷል። ውድድሩን ያስተናግዳሉ ተብለው የተለዩት ስታዲየሞችም አጠቃላይ ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለመሟላታቸው ከካፍ በተላኩ ባለሙያዎች ባሳለፍነው ወር መጀመሪያ ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱም የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ያደረገችው ጥረት እንዳልተሳካና መከናወን ያለባቸው በርካታ ስራዎች በአግባቡ እንዳልተከናወኑና አጥጋቢ ስራዎችም እንዳልተሰሩ በሪፖርት ቀርቧል። ኢትዮጵያ ያገኘችው የአስተናጋጅነት ዕድል ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ቢሆንም በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በኩልም ሆነ ከመንግስት ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ሳይገኝ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከሰሞኑ ግን ድብብቆሹ ማክተም እንዳለበት በማመን እውነታው ለህዝብ ይፋ ተደርጓል። በመሆኑም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፤ መንግስት ለውድድሩ ዝግጅት አስፈላጊውን ወጪ ለመሸፈን ዝግጁ አለመሆኑን በምክንያትነት ጠቅሰው ኢትዮጵያ በ2020 እንድታሰናዳ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የተሰጣትን የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) እንደማትቀበል አስታውቀዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ የኢትዮጵያ መንግስትን የዘገየ ውሳኔን መሰረት በማድረግ የ2020 የቻን ዋንጫን በአጭር ዝግጅትና ፍጥነት በተሟላበት ሁናቴ ማስተናገድ ለሚችል አገር ለማስተላለፍ በካይሮ መምከር ግድ ብሏቸዋል። በመሆኑም የአዘጋጅነት ዕድሉን ለምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ካሜሩን ተላልፏል። ካሜሩን ውድድሩን በተሻለ ሁኔታ ማስተናገድ እንደምትችል እምነታቸውን ገልፀዋል። በ2022 ለማዘጋጀት እድል የነበራት ካሜሩን አሁን ያገኘችውን እድል ተጠቅማ ለውድድሩ ዝግጅቷን አጠናክራ በመቀጠል የተሳካ መድረክ ትፈጥራለች ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የአስተናጋጅነት ዕድሉን ከኢትዮጵያ የተቀበለችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ካሜሩን በደስታ መረከቧን ቢቢሲ ጽፏል። ከኢትዮጵያ እጅ ያመለጠው የቻን አዘጋጅነት በካሜሩን ቤት እንደ መልካም አጋጣሚ የታየም መሆኑን አስፍሯል። ከኢትዮጵያ መዳፍ ውስጥ ፈለቅቃ ከወሰደችው ከካሜሩን ቤት የ2019 የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ዕድሉን አግኝታ የነበረ ቢሆንም፤ በተቀመጠው ጊዜ ዝግጅቷን የማጠናቀቅ አቅሟ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ለግብፅ መሰጠቱ አስታውሶ፤ በከፍተኛ ደስታ አጋጣሚውን ለመጠቀም የምትሰራ መሆኑን የሚያሳይ አስተያየት መሰጠቱንም አስነብቧል።

የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) በአገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቻ የሚያሳትፍ የውድድር መድረክ ሲሆን፤ በሁለት ዓመት አንዴ ይደረጋል። እኤአ 2009 የተጀመረው ቻን የመጀመሪያዋ ዋንጫ ኮትዲቯር ስታዘጋጅ፤ 2ኛውና በ2011 የተካሄደውን ደግሞ ሱዳን አዘጋጅታለች። በ2014 ደቡብ አፍሪካ ሶስተኛውን ስታስተናግድ፤ በ2016 ሩዋንዳ 4ኛውን አዘጋጅታለች። በ2018 በሞሮኮ አዘጋጅነት ለ5ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ 6ኛውና በ2020 የሚካሄደው የቻን ዋንጫ ደግሞ ወደ ምዕራብ አፍሪካ በመጓዝ ካሜሩን ቤት መግባቱ ተረጋግጧል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011