የአፍሪካ እግር ኳስ የነገ ተስፋዎች መድረክ

6

የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር የአህጉሪቱን እግር ኳስ ለመረከብ ተስፋ የተጣለባቸው ታዳጊዎችን በአንድ መድረክ ያሰባስባል፡፡ በእግር ኳሱ መሰረትን የያዙ ተጫዋቾችን የሚፈሩበት ውድድሩ በታንዛኒያ አዘጋጅነት ለ13ኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ ይገኛል። የውድድሩ አላማ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለጽ ሲሆን፤በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ አፍሪካዊ ብሄራዊ ቡድኖችን ለማፍራት የሚለው ሚዛን የሚደፋ ሆኖ ይነገራል። በእግር ኳሱ ጠንካራና መሰረት ያለው ብሄራዊ ቡድን ለመገንባት ትልቅ ፋይዳን እንደያዘ ይነገርለታል።

በአህጉሪቱ የእግር ኳስ ትንሳኤ ላይ ትልቅ ድርሻን የሚሰጠው ውድድሩ እ.ኤ.አ በ1995 ነበር የተጀመረው። ውድድሩ ‹‹የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ቻምፒዮን ሺፕ›› በሚል ስያሜ መጀመሩን አበሰረ። በአፍሪካን የነገ እግር ኳስ ውጤት መሰረት የሆኑትን ታዳጊዎች የሚያሰባስበው ይህ ውድድር እ.ኤ.አ በማሊ አዘጋጅነት ለመካሄድ በቃ። በመጀመሪያው ውድድር ላይም አዘጋጇን ማሊን ጨምሮ ስምንት አገሮች በሻምፒዮናው ተሳታፊ ሆነውበታል። የጋና ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ተጠናቀቀ።

ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በቦትስዋና አዘጋጅነት ሻምፒዮናው የተዘጋጀ ሲሆን፤ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ተሳታፊ ከነበሩት አገራት አንዱ ነበር። በውድድሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመሳተፍ ባሻገር ጥሩ የሚባል ተፎካካሪ ሆኖ የታየበትም ጭምር ነው።

በውድድሩ የግብጽ ብሄራዊ ቡድን የሁለተኛው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ሻምፒዮን ሺፕ በመሆን ዋንጫውን ማንሳት ችሏል። በውድድሩ ጥሩ እንቅስቃሴ ካሳዩት አገራት አንዱ በመሆን ተጠቃሽ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አራተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ የቻለበትም ነው። ጊኒ እ.ኤ.አ በ1999 ሦስተኛውን ውድድር አስተናግዳለች። የመጀመሪያውን ውድድር አሸናፊ በመሆን ዋንጫ ያነሳችው ጋና ዳግም በተስፈኛ ልጆቿ ለሁለተኛ ጊዜ የውድድሩ ባለ ድል በመሆን ታሪክ የሰራችበት ነው።

የጋና ብሄራዊ ቡድን የፍጻሜ ተጋጣሚውን ቡርኪና ፋሶን 3 ለ 1 በመርታት ነው አሸናፊ መሆን ችሏል። በመጀመሪያው የውድድሩ መድረክም ጋና ዋንጫ ያነሳችው ናይጀሪያን 3 ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፋ ነበር፡፡

እ.አ.ኤ በ2001 በሲሺየልስ አስተናጋጅነት የተካሄደው አራተኛው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮን ሺፕ አሸናፊ ደግሞ ናይጀሪያ ነበረች፡፡ ቡድኑ የስድስተኛው ዙር ውድድር አሸናፊም ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የናይጀሪያ ቡድን ከሁለት ዓመት በኋላ በሲዋዚላንድ በተካሄደው ውድድር የአሸናፊነት ግምት ማግኘት ቢችልም የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን የሻምፒዮናነት ክብር ሲያገኝ የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ለፍጻሜ እንኳ ሳይደርስ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል። የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን የከሸፈበትን ግምት ለማደስ አራት ዓመት በመጠበቅ እ.ኤ.አ በ2007 በቶጎ አዘጋጅነት በተካሄደው ሰባተኛው ውድድር ላይ አሸናፊ መሆን ችሏል።

ከዚህ ውድድር ቀደም ብሎ በጋምቢያ አስተናጋጅነት የተካሄደውን ስድስተኛውን የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮን ሺፕ አስተናጋጇ ጋምቢያ አሸንፋለች። ጋምቢያ ውድድሩን አዘጋጅታ ዋንጫውን ያሸነፈች ቀዳሚ አገር መሆን የቻለች ሲሆን፤እ.አ.ኤ 2009 ለስምንተኛ ጊዜ በአልጄሪያ የተካሄደውን ውድድር በማሸነፍ ሌላ ታሪክ መፃፍም ችላለች።

እ.አ.አ በ2011 እና በ2013 የተካሄዱትን ውድድሮች ሩዋንዳና ሞሮኮ (እንደ ቅደምተከተላቸው) አስተናግደው ቡርኪና ፋሶ እና አይቮሪኮስት (እንደ ቅደምተከተላቸው) አሸናፊ ሆነዋል።

በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ የተሻለ ነገን ለመፍጠር የሚያስችል መሰረት የመጣል ተስፋን የያዘው ውድድሩ፣ እ.ኤ.አ በ2015 የስያሜ ለውጥ በማድረግ ‹‹ከአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ቻምፒዮን›› ወደ ‹‹የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ›› ተቀይሮ በናይጄሪያ አስተናጋጅነት ቀጠለ። የውድድሩ ድምቀትና ፉክክርም ከዓመት ወደ ዓመት እያየለ እንደመጣ ይነገርለታል፡፡

በናይጄሪያ አዘጋጅነት የተካሄደው 11ኛው ዙር ውድድርም ለዚሁ ምስክር ሆኖ ይቀርባል። ጠንካራ ፉክክርን ባሳየው በዚህ ውድድር የማሊ ብሄራዊ ቡድን አሸናፊ በመሆን ስያሜውን የቀየረውን ውድድር የመጀመሪያ ዋንጫ አንስቷል። የማሊ ቡድን ይህን ውድድር በበላይነት ማጠናቀቁ ማሊ የመጀመሪያው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ቻምፒዮን ሺፕ አዘጋጅ ከመሆኗ ጋር ሲደመር ልዩ የታሪክ አጋጣሚ ፈጥሮ አልፏል፡፡

የማሊ ብሄራዊ ቡድን በዚህ ብቻ ሳይወሰን ከሁለት ዓመት በፊት በጋቦን አስተናጋጅነት ለ12ኛ ጊዜ የተካሄደውን ውድድር ድል በማድረግ ሌላ ታሪክ መፃፍ ችሏል። የአፍሪካን ታዳጊዎች የሚያፋልመውን ውድድር ባለፉት 22 ዓመታት በነበረው ጉዞው ማሊ፣ ናይጄሪያ፣ ጋምቢያ እና ጋና እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ሲያነሱ፤ቡርኪና ፋሶ፣ አይቮሪኮስት፣ ግብጽ እና ካሜሮን እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ማንሳት የቻሉ አገራት ሆነዋል። በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ መጪውን ትውልድ ለማየት መስተዋት የሆነው ይህ ውድድር፣ ዘንድሮ (በ2019) በታንዛኒያ ለ13ኛ ጊዜ እየተካሄደ ይገኛል።

አዘጋጇ አገር ታንዛኒያ ከ23 ዓመታት በፊት ጅማሮውን ያደረገውን የዚህን ውድድር ዝግጅት የተሳካና የተዋጣለት ለማድረግ ላይ ታች ብላ ወድድሩ ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተጀምሯል።

በውድድሩ ላይም አዘጋጇ አገርን ጨምሮ ስምንት ሀገራት እየተሳተፉ ሲሆን ውድድሩም በሁለት ምድቦች ተከፍሎ እየተደረገ ይገኛል። በዚህ መሰረትም በመጀመሪያው ምድብ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ናይጄሪያ እና አንጎላ ተደልድለዋል። በሁለተኛው ምድብ ደግሞ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ ጊኒ እና ሞሮኮ ተደልድለዋል። ባሳለፍነው እሁድ ውድድሩ ሲጀመር በመጀመሪያው ምድብ የሚገኙት አዘጋጇ ሀገር ታንዛኒያ ከናይጄሪያ ጋር ጨዋታቸውን አድርገው፣ ናይጄሪያ አዘጋጇን አገር 5ለ4 በመርታት የመጀመሪያውን ድል አስመዝግባለች።

የውድድሩ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ የሚቀጥሉ ሲሆን በዛሬው እለት ናይጄሪያ ከአንጎላ ፤ ኡጋንዳ ደግሞ ከአዘጋጇ ታንዛኒያ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ያሸነፉት ናይጄሪያና አንጎላ በዚህ ጨዋታ የሚያስመዘግቡት ውጤት መርታታቸው ወደ ቀጣዩ ዙር ለሚኖራቸው ጉዞ ወሳኝ ነው። በመጀመሪያው ጨዋታ ድል ያልቀናቸው ታንዛኒያና ኡጋንዳ ሽንፈትን ካስተናገዱ ቀጣይ ጉዟቸው የሚገታ ይሆናል።

በሁለተኛው ምድብ የተደለደሉ አገራት ከነገ በስቲያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ጨዋታ ሲሆን ካሜሮን ከሞሮኮ፤ሴኔጋል ከጊኒ የሚኖራቸው ጨዋታ የሚጠበቅ ሆኗል።

በዘንድሮው ውድድር ከታዩ አስገራሚ ክስተቶች መካከል የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ አንዱ ሆኗል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ ‹‹ለድርድር የማይቀርብ›› ነው ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ስድስት ተጫዋቾች ከእድሜ ተገቢነት ጋር ተያይዞ በተነሳባቸው ጥያቄ ከውድድሩ ታግደዋል። ካሜሮን ሶስት ተጫዋቾቿን በእድሜ ተገቢነት ስታጣ፤አዘጋጇ አገር ታንዛኒያ ደግሞ ሁለት ተጫዋቾች እንዲሁም የጊኒ ብሔራዊ ቡድን አንድ ተጫዋች ታግዶባቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን ሚጣዝያ 9/2011