ብሔራዊ ፋይዳው ወይስ ብሔራዊ እዳው ያመዝናል?

15

ብሔራዊ ጥቅምን ከተልዕኮው አንጻር በፍትሃዊ መንገድ ማሳደግን አልሞ ይሰራል። የአገሪቱን የዋጋና የውጭ ምንዛሪ ተመን አስተካካይ ባለቤትም ነው። የፋይናንሱን እንቅስቃሴ ጤንነት በማስተካከል ለኢኮኖሚው እድገት ምቹ መደላድል የመፍጠር ኃላፊነትንም በበላይነት ይከውናል፤ ብሔራዊ ባንክ።

የውጪ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ የነፍስወከፍ ገቢን በማሳደግ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቷል። በተመሳሳይ አስከፊ ድህነትን በመቀነስ በኩል ፋይዳ ያላቸው የፖሊሲና የትግበራ እርምጃዎች መወሰዳቸውም የብሔራዊ ባንኩ የሥምንት ወራት አፈጻጸም ለአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች አይንና ጆሮ በቀረበበት ወቅት ተገልጿል።

የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንደተናገሩት ዋጋን በማረጋጋት ንረቱን በነጠላ አሃዝ እንዲወሰን ለማድረግ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል። ልዩ ልዩ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎችን በቅንጅት መጠቀም ተችሏል። የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትንም አጠናክሮ በመቀጠል በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እንዲከፋፈል ተደርጓል።

በመሆኑም በአገሪቱ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት በስምንት ወራት ውስጥ የተመዘገበው የዋጋ ንረት 10 ነጥብ 8 በመቶ ሆኗል። ይህም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው የ16 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አብራርተዋል።

ዋና ገዥው እንደገለጹት የገንዘብ ፖሊሲው አካል የሆነው የወለድ ተመንን የተረጋጋ፣ የአገሪቱን ተጨባጭ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ያገናዘበ፣ የአስቀማጮችንም ሆነ ተበዳሪዎችን ጥቅም የማይጎዳ የሥራ እድልን የሚያሰፋ እና የፋይናንስ ተደራሽነትንና አካታችነትን የሚያበረታታ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህ መሰረት ባንኩ በበጀት ዓመቱ 8 ወራት በተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፍለው ዝቅተኛ የወለድ መጠን 7 በመቶ ሆኖ ቀጥሏል። የማበደሪያ ወለድ ደግሞ በባንኮች እንዲወሰን መደረጉን ተናግረዋል።

በየካቲት ወር መጨረሻም አማካይ ተቀማጭ ወለድ ተመን 8 በመቶ እና የባንኮች አማካይ የማበደሪያ ተመን ደግሞ 13 ነጥብ 50 በመቶ ደርሷል። ከብሔራዊ ባንክ መንግስት የወሰደው ቀጥታ ብድርም 23 ቢሊዮን ብር ሲሆን ለበጀት ዓመቱ ከተያዘው 30 ቢሊዮን ጋር ሲነጻጸርም ጤናማ ነው።

ባንኩ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭን እንደ ከፊል የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያ ተጠቅሟል። በዚህም 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዋጋ ያላቸው አዳዲስ የሰነድ ሽያጮች በ8 ወራት ተከናውኗል።

 በበጀት ዓመቱ ያለፉ ወራት የባንክ ለባንክ የውጪ ምንዛሪ ገበያ አንድ የአሜሪካን ዶላር በአማካይ 27 ነጥብ 77 ብር ተመንዝሯል። በመሆኑም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት የብር ዋጋ ከአሜሪካን ዶላር አኳያ 6 ነጥብ 4 በመቶ ወርዷል። ምክንያቱ ደግሞ አምና ጥቅምት ወር የብር ዋጋ በዶላር ምንዛሪ በኩል 15 በመቶ ማስተካከያ መደረጉ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ዋና ገዥው እንዳብራሩት፤ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለውጭ ምንዛሪ ግብይት ቀርቧል፤ በመሆኑም የብር ዋጋ ያለ አግባብ እንዳይዋዥቅ ረድቷል።

ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያ እና ለመሰረተ ልማት ግንባታና ማስፋፊያ ለሚውሉ እቃዎችና መሳሪያዎች ግዥ በድምሩ 32 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በብሔራዊና በንግድ ባንኮች በኩል ቀርቧል።

ለነዳጅ ግዢ ብቻ ባለፉት 8 ወራት 1 ነጥብ 73 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሆኗል፤ 20 ነጥብ 8 በመቶ ዓመታዊ እድገት አሳይቷል፤ በመሆኑም ከጠቅላላ የገቢ ንግድ ወጪ 16 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ መያዙን ተናግረዋል።

ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የቀረበው የበጀት ዓመቱ የ8 ወራት ሪፖርት እንደሚያሳየው አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ዋናዋና ምንጮች መካከል የወጪ ንግድ፣ሐዋላ፣የውጭ ብድርና እርዳታ እንዲሁም ቀጥታ የውጪ ኢንቨስትመንት ተጠቃሾች ናቸው። በመሆኑም ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 64 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ቢገኝም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 9 ነጥብ 4 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ለዚህም የቡና፣ የቅባት እህሎች፣ የወርቅ፣ የቁም እንስሳት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቅመማ ቅመም እና የኬሚካል የግንባታ ግብዓቶች የወጪ ንግድ ገቢ መቀዛቀዝ መሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል ከግል ሐዋላ (ከግለሰቦች እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች) 3 ነጥብ 82 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተጣራ ገቢ ተሰብስቧል።

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም አንጻር ሲታይ 11 ነጥብ 9 በመቶ እድገት አሳይቷል። ምክንያቱ ደግሞ ከድርጅቶች የተገኘው የተጣራ ገቢ ከአምናው 45 ነጥብ 2 በመቶ ሲቀንስ ከግለሰቦች ሐዋላ የተገኘው ግን 22 ነጥብ 8 በመቶ እድገት በማሳየቱ ነው ተብሏል። ባለፈው አንድ ዓመት የተስተዋለው የለውጥ እንቅስቃሴ በትውልድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በአዎንታዊ እየታየ መምጣቱ ከግለሰቦች አገሪቱ የምታገኘው ሐዋላ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማበርከቱ በሪፖርቱ ተገልጿል።

ከመንግስታዊ የውጪ ሐዋላ የተጣራ 836 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ቢሆንም 11 ነጥብ 9 በመቶ ካለፈው አመት ቅናሽ አሳይቷል። ለጥሬ እቃዎች፣ ለነዳጅና በከፊል ላለቀላቸው ሸቀጦች የወጣው ወጪ ከፍ ማለቱ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

በሸቀጦች የወጪና የገቢ ንግድ መካከል የታየው የንግድ ሚዛን ጉድለት አምና ካሳየው 8 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ 8 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ሰፍቷል።

በመሆኑም የወጪ ንግድ ገቢ ሊሸፍን የቻለው 15 ነጥብ 6 በመቶ የገቢ ንግድ ወጪን ሲሆን ቀሪው ጉድለት በአገልግሎት ገቢ፣ በሐዋላ፣ በውጭ እርዳታና ብድር እንዲሁም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንደሆነ ተነግሯል።

በበጀት ኣመቱ 8 ወራት መጨረሻ በአገሪቱ 5,346 የባንክ ቅርንጫፎች (235 ንኡስ ቅርንጫፎች) ያሏቸው 18 ባንኮች ፋይናንሱን ተደራሽ በማድረግ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተገልጿል። ከእነዚህ መካከል 16ቱ የግል ሁለቱ ደግሞ የመንግስት ናቸው።በዚህም የባንኩ ዘርፍ በንኡስ ቅርንጫፍ 14 ነጥብ 04 በመቶ እድገት አሳይቷል። በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት የባንክ ቅርንጫፍና የተገልጋይ ሕዝብ ምጣኔ ከነበረበት 1ለ20 ሺህ ወደ 1ለ17 ሺህ መድረስ ችሏል።

በባንኮቹ ቅርንጫፎች ቁጥር መጨመር እና በቁጠባ ባህል እየተሻሻለ በመምጣቱ የተጠቃሚው ቁጥር ጨምሯል።

በአገሪቱ ሁሉም ባንኮች የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 816 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሲሆን 21 ነጥብ 7 በመቶ ካለፈው ዓመት ጭማሪ አሳይቷል። 319 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር (39 ነጥብ1 በመቶ) የግል ባንኮች ድርሻ ሲሆን ቀሪው 496 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር (60 ነጥብ 9 በመቶ)በመንግስት ባንኮች የተሰበሰበ ነው።

በአጠቃላይ የፋይናንስ አመላካቾች ልማት ባንክን ሳይጨምር ባንኮች ያላቸው ጠቅላላ ካፒታል ብር 88 ነጥብ 89 ቢሊዮን ሆኗል። ከአምናው 18 ነጥብ 89 በመቶ አድጓል። አጠቃላይ ትርፋቸው ከታክስ በፊት 10 ነጥብ89 ቢሊዮን ብር ሲደርስ ካለፈው ዓመት 109 ነጥብ 14 በመቶ ጨምሯል።

አጠቃላይ ባንኮች (ልማት ባንክን ሳይጨምር) የማይመለሱና አጠራጣሪ የሆኑ ብድሮች ከአጠቃላይ ብድር አኳያ ሲታይ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው 5 በመቶ ጣሪያ በታች 3 ነጥብ 81 መሆኑ አበረታች ነው። ከእነዚህ የፋይናንስ አመላካቾች በመነሳት የባንክ ዘርፉ ትርፋማ፣ ጤናማና የተረጋጋ መሆኑን ማረጋገጥ እንደተቻለ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመላው አገሪቱ በሚገኙ 110 ቅርንጫፎች ለብድር ጠያቂዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። በበጀት ዓመቱ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ የባንኩ የብድር ክምችት 46 ነጥብ 17 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል። ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት 33 ነጥብ 94 በመቶ ብልጫ አሳይቷል። የሰጠው ብድር መጠን ብር 6 ነጥብ 23 ቢሊዮን ሲሆን ካለፈው ኣመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር 53 ነጥብ 44 በመቶ ጭማሪ አለው። በሌላ በኩል ባንኩ ብር 3 ነጥብ 25ቢሊዮን ወይም ከአምናው 12 ነጥብ 45 በመቶ ብልጫ ያለው ብድር መሰብሰብ ችሏል።

የባንኩ ጠቅላላ ሐብት ብር 84 ነጥብ 17 ቢሊዮን ሆኗል። ካፒታሉም 7 ነጥብ 67 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል። የማይመለስና አጠራጣሪ ብድር ከአጠቃላይ ብድር አኳያ ሲታይ 39 ነጥብ 45 በመቶ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው 15 በመቶ ጣሪያ በልጧል። በበጀት ዓመቱ መስከረም ወር መጨረሻም ብር 344 ሚሊዮን ኪሣራ አስመዝግቧል።

በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የተከበሩ ወይዘሮ ለምለም አድጎ በበኩላቸው፤ ባንኩ የፋይናንስ ዘርፉን የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባሩን በኃላፊነት ስሜት መወጣት አለበት። የተወሰዱ ብድሮችን ተከታትሎ ማስመለስ ይገባዋል። የሕዝብ ገንዘብ መባከን የለበትም፤ በሕግም ቢሆን ተጠያቂ እስከማድረግ ድረስ የተጠናከረ ርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። የፋይናንሱ ዘርፍ ጤንነቱ ተጠብቆ ተደራሽነቱ ሊጨምር ይገባል። የወጪ ንግዱ መጠናከር ይኖርበታል። በአጠቃላይ አሰራሩን በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል በማዘመን በዘርፉ አገሪቱ ከገባችባቸው ችግሮች ማላቀቅ የሚያስችሉ መፍትሔዎች መወሰድ አለባቸው፤ ምክርቤቱም ከጎን ሆኖ ጠንካራ ክትትል በማድረግ ሊያግዝና ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011

 ሙሐመድ ሁሴን